‹‹አመፅ በማነሳሳት ወንጀል አቤቱታ የቀረበባቸው የናይጄሪያ ቀዳማዊት እመቤት በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ምርመራ ይደረግባቸዋል››
የዓለም የወንጀል ፍርድ ቤት በናይጄሪያ ቀዳማዊት እመቤት ፔሸንስ ጆናታን ላይ በቀረበለት አቤቱታ መሠረት፣ አመፅ በማነሳሳት ድርጊት ምርመራ እንደሚያካሂድባቸው ከተናገረው የተወሰደ፡፡ የናይጄሪያ ጋዜጦች ባወጡት ዘገባ መሠረት፣ ቀዳማዊት አመቤት ጆናታን ደጋፊዎቻቸው የኦል ፕሮግሬሲቭ ኮንግረስ ፓርቲ አባላትን በድንጋይ እንዲደበድቡ አዘዋል፡፡ ይህንንም ድርጊት ፓርቲው ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቤቱታ በማቅረቡ፣ ፍርድ ቤቱ የሴትየዋ ድርጊት መመርመር አለበት ብሏል፡፡ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ፣ ፍርድ ቤቱ ቀዳማዊት እመቤት ጆናታንን መርምሮ ከመክሰስ አያመነታም ብለዋል፡፡ ‹‹ማንም ሰው ከምርጫ በፊት፣ ወቅትና በኋላ አመፅ የሚቀሰቅስ ከሆነ ይከሰሳል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ዘገባዎች እንደሚያስረዱት የገዥው ፒፕልስ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተቀናቃኝ ኦል ፕሮግሬሲቭ ኮንግረስ ፓርቲ አባላትን ‹‹ጊዜ ያለፈበት መድኃኒት›› ናቸው ከማለታቸው በተጨማሪ፣ በደጋፊዎቻቸው ድብደባ እንዲፈጸምባቸው ማዘዛቸው ቀዳማዊት እመቤት ጆናታንን እያስወቀሰ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ቀዳማዊት እመቤት ፔሸንስ ጆናታን ናቸው፡፡