Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበትንቅንቅ የታጀበው የእስራኤል ምርጫ

በትንቅንቅ የታጀበው የእስራኤል ምርጫ

ቀን:

እስራኤላውያን በፓርላማ ይወክሉናል የሚሏቸውን ፓርቲዎች መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. መምረጥ ጀምረዋል፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ በፍልስጤምና በኢራን ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም የሚታወቁት ሚስተር ቤንጃሚን ኔታንያሁም ሊኩድ ፓርቲን ወክለው ተወዳድረዋል፡፡

ቤንጃሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ በተደረገውና ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ምሽት ድረስ ውጤቱ ባልተገለጸው የፓርላማ ምርጫ ካሸነፉ አራተኛቸው ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ግን የኔታንያሁ ፓርቲ የማሸነፍ ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ በተለይም ከምርጫው አስቀድሞ በሰባት ዋና ዋና ፓርቲዎች የተደረጉ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች የሊኩድ ፓርቲን የፓርላማ መቀመጫ ወንበር ሊያሳንሱ እንደሚችሉ ተተንብይዋል፡፡

ብዙውን የወጣትነት ዕድሜያቸውን በአሜሪካ እንዳሳለፉ የሚነገርላቸው ናታንያሁ፣ በእስራኤል ፖለቲካ በተለይም በደኅንነት ጉዳይ እጅ የሚሰጡም፣ የሚበገሩም አይደሉም፡፡ ለኢራንና ለፍልስጤም ያላቸው አይበገሬነት፣ ተጠራጣሪነትና ግትር አቋምም ከፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ለየት ያደርጋቸዋል፡፡ በአገሪቱ የኑሮ ውድነት እየተባባሰ፣ ኢኮኖሚውም እያሽቆለቆለ ነው ቢባልም ለኔታንያሁ አገርን መምራት የሚለካው የአገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት በማስጠበቅ ነው፡፡

ሚስተር ኔታንያሁ የሊኩድ ፓርቲን እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 2005 ሁለት ጊዜ በመመረጥ የመሩ ሲሆን፣ በተለያዩ የሚኒስትርነት ሥልጣኖችም አገልግለዋል፡፡ በፓርቲው ውስጥ የነበረውን ያልተረጋጋ ፖለቲካ በማስከን ክህሎታቸው የሚታወቁት ኔታንያሁ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 ግን የፓርላማውን አብላጫ ድምፅ አስጠብቀው ለመቆየት አልቻሉም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ማብቂያ ላይ ደግሞ ከሊኩድ ፓርቲ ጋር ተጣምረው የነበሩ ፓርቲዎች ከፓርቲው በመውጣታቸው የሊኩድ ፓርቲ ጥንካሬ ተፈትኗል፡፡ ይህም አገሪቷ ማክሰኞ ባካሄደችው የፓርላማ ምርጫ ወንበር ያሳጣቸዋል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡

የኔታንያሁ ፓርቲ መላላትና የእሳቸው የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ችላ በማለት ለደኅንነት ጉዳይ ብቻ ትኩረት መስጠታቸው ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች በር መክፈቱም ይነገራል፡፡ 5.8 ሚሊዮን መራጮች በሚሳተፉበት የፓርላማ ምርጫ ወንበር ለመጋራትም የሊኩድ ፓርቲን ጨምሮ ስድስት ጠንካራ ፓርቲዎች በምርጫው ተሳትፈዋል፡፡ የምረጡኝ ዘመቻቸውም በትንቅንቅ የተሞላ እንደነበረ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የግራ ዘመም ጽዮናዊ ኅብረት የምርጫ ጥምረት (Center-left Zionist union electoral alliance) ተባባሪ መሪ የሆኑት ሚስተር አይዛክ ሄርዞግ በፓርላማው አብላጫ ወንበር ያገኛሉ ተብሎ ተተንብዮላቸዋል፡፡ የሚስተር ኔታንያሁን ፓርቲ በመተቸት የሚታወቁት ሚስተር ሔርዞግ፣ እስራኤላውያን ደረጃውን የጠበቀ ሕይወት ይኖራሉ ብለው አያምኑም፡፡ ደረጃውን ላልጠበቀ ሕይወት የዳረጋቸው ደግሞ የኔታንያሁ ፓርቲ ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ችግር አለበት ሲሉም ይተቻሉ፡፡ እስራኤል ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በቅርበት መሥራት አለባትም ይላሉ፡፡

የጽዮናዊ ኅብረት (Zionist union) ፓርቲ ተባባሪ መሪ ዚፒ ሊቪን ሌላዋ የእስራኤልን የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት የሚፋለሙ ናቸው፡፡ ሚስ ሊቪን በኢራንና በፍልስጤም ባለሥልጣናት ላይ ያላቸው አቋም ከኔታንያሁ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡

በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት እንደ ዋና አጀንዳ ያነሱትም፣ እስራኤል ከፍልስጤምና ከኢራን ጋር ያላትን ልዩነት ነው፡፡ እሳቸው ልዩነቶችን በማጥበብና አብረው በመሥራት በቀጣናው ያለውን ውጥረት ለማርገብ እንደሚጥሩ አሳውቀዋል፡፡

የቀኝ ዘመም ካላኑ ፓርቲ ሚስተር ሞሼ ካህሎን እንደ ምርጫ አጫዋች የሚቆጠሩ ግን ወሳኝ ሰው ናቸው፡፡ ፓርቲያቸው በፓርላማው ሊያገኝ የሚችለው መቀመጫ ከሚስተር ኔታንያሁ ወይም ከሚስተር ሔርዞግ ፓርቲዎች ጋር ጥምር ለመፍጠር ካልሆነ አብላጫ የሚይዝ አይደለም፡፡ በመሆኑም የኔታንያሁም ሆነ የሔርዞግ ፓርቲዎች ከሚስተር ካህሎን ፓርቲ ጋር ጥምረት ለመፍጠር ይፈልጋሉ፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው ሚስተር ካህሎን፣ የሊኩድ ፓርቲ የቀድሞ የዌልፌርና የኮሙዩኒኬሽንስ ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ሌላው የኔታንያሁ ተቀናቃኝ አይማን ኦዴ ናቸው፡፡ ሚስተር ኦዴ በእስራኤል የፖለቲካ ታሪክም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ለእስራኤላውያን ታዋቂ አልነበሩም፡፡ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ ግን በእስራኤል የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ብቅ በማለት ብዙዎችን አስደምመዋል፡፡ በእስራኤል የኮሙዩኒስት ፓርቲ ሓዳሽ ዋና ጸሐፊ ወጣቱ ኦዴ፣ አምስት የዓረብ ፓርቲዎች በጥምረት እንዲወዳደሩ ያመቻቹ ናቸው፡፡

ከፍልስጤማውያን የማንነት ጥያቄ ይልቅ ሰብዓዊ መብትና እኩልነትን አጀንዳቸው ያደረጉት ሚስተር ኦዴ፣ በእስራኤል የዓረብ ፖለቲካ አዲስ ገጽታ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡

በእስራኤል ፓርቲዎች በተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት የሚመረጡ በመሆናቸው፣ በብዙ ልዩነት ወይም ሙሉ ለሙሉ አንዱ ፓርቲ አሸንፏል አይባልም፡፡ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች እንደሚያሳዩት፣ የጽዮናዊው ኅብረት አብላጫ መቀመጫ እንደሚያገኝ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሚስተር ኔታንያሁ አብላጫ ድምፅ ቢያጡ እንኳን ከኅብረቱ ጋር ለመጣመር ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡

በእስራኤል የፓርላማ መቀመጫ ለመቆናጠጥ ከሊኩድ ፓርቲ ጥምረትነታቸው የወጡና ሌሎችንም ጨምሮ 13 ፓርቲዎች በቅስቀሳ ወቅት የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በምርጫ የማይሳተፉም አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እ.ኤ.አ. በ2015 ምርጫ ብዙ ወንበር ያጣሉ የሚሉ አስተያየቶች ቢሰጡም የማሸነፍ ዕድላቸው 50፣ 50 ነው ያሉም አሉ፡፡ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች በኔታንያሁ ላይ ከባድ ዘመቻ ማካሄዳቸው ለፓርቲያቸው መጥፎ አጋጣሚም ነበር፡፡ ኔታንያሁ አሸነፉም አላሸነፉም ያለፉት አራት ወራት በፓርቲያቸው ላይ የገነቡትን ተዓማኒነት አሽመድምዶታል፡፡ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ፓርቲውን ይመርጣሉ ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ ለኔታንያሁ ያላቸው አመለካከት መቀየሩን በእስራኤል፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአይሁዶች ላይ ያጠነጠኑ ዜናዎችን የሚዘግበው ሃርቴዝ ዘግቧል፡፡

በእስራኤል የፓርላማ ምርጫ ውጤት ከታወቀ በኋላ አሸናፊ ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ይመሠርታሉ፡፡ ይህ በተከናወነ በሰባት ቀናት ውስጥ ደግሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሪዩቪን ሪቭሊን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማሉ፡፡

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...