የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት 11 ልዑላኖችን ጨምሮ 200 ባለሀብቶችን ከሙስና ጋር በተያያዘ ነው በማለት በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት ነግሷል፡፡ የኢኮኖሚው መዋዠቅና በሳዑዲ የአክሲዮን ገበያ ማሽቆልቆል ለአገሪቱም ሆነ ለአካባቢው አገሮች የኢኮኖሚ ቀወስ አመላካች መሆኑም ይነገራል፡፡
ጉዳዩ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውና ከአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢል ሳልማን የሥልጣን ፍላጎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢገለጽም፣ ሳዑዲ ‹‹በሙሰኞች ላይ የጀመርኩት ዘመቻ ይቀጥላል›› ብላለች፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም ‹‹የሳዑዲ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ ያውቃል›› ሲሉ ድጋፋቸውን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በሳዑዲ ከሙስና ጋር የተያያዘው የባለሀብቶችና የልዑላን እስር ጉዳይ ቀጣናውን እያነጋገረ ባለበት ወቅት፣ ዜጎቿ ከሊባኖስ እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፏ ቀጣናውን ከኢኮኖሚም አልፎ የጦርነት ቀውስ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚል ሥጋት አጭሯል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ እንደሚለው፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ዜጎቿ ከሊባኖስ እንዲወጡ ትዕዛዝ ማስተላለፏ፣ በሁለቱ የዓረብ አገሮች መካከል የኢኮኖሚ ቀውስ ከማስከተሉም ባለፈ ለዓመታት በቃላት ጦርነት ውስጥ ያሉት ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ምድረ ሊባኖስን የጦርነት ዓውድማ ሊያደርጓት ይችላሉ የሚል ሥጋት አስከትሏል፡፡
ቀድሞውንም በኢራን የሚደገፈውና በሊባኖስ የፖለቲካና የመከላከያ ኃይል ውስጥ ተሰሚነት አለው የሚባለው ሒዝቦላሀ በሳዑዲ ዓረቢያ ላይ ጦርነት አውጇል ባለችበት ማግሥት፣ ዜጎቿ ከግዛቲቱ እንዲወጡ ማድረጓም ቀጥሎ ጦር ያማዝዛል አስብሏል፡፡
የሳዑዲ ዓረቢያ ያልተጠበቀ ዕርምጃ በሊባኖሳውያኑ ዘንድ መደናገጥን የፈጠረ ሲሆን፣ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ወላጆች ቀጥሎ ምን ይከሰታል? በማለት ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ተንታኞች ጦርነቱን እስራኤልም አትፈልገውም ሳዑዲም ብቻዋን አትወጣውም ብለው፣ ሳዑዲ በሰከነ መንፈስ እንድትጓዝ አሳስበዋል፡፡
በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዘመን በዋይት ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ዳይሬክተር የነበሩትና አሁን የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ሮበርት ማሌይ፣ ‹‹በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ አቀጣጣዮች አሉ፡፡ ያለው መግባባት አነስተኛ በመሆኑ ብዙ ጉዳዮች በመፈንዳት አደጋ ላይ ናቸው፡፡ በቀጣናው ጉዳዮች በተሳሳተ አቅጣጫ የማይሄዱበት አጋጣሚ ጥቂት በመሆኑ መረጋጋትን ለመፍጠር በሰከነ መንፈስ መጓዝ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ ሰሞኑን እንደ አዲስ ከቀጣናው ተቀናቃኟ ኢራን ጋር የጀመረችው ፍጥጫና 11 ሉዑላንን ጨምሮ በድንገት በቁጥጥር ሥር ያዋለቻቸው 200 የሳዑዲ ዜጎች፣ የሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ሥልጣን ለመቆጣጠር የጀመራቸው ዘመቻዎች አካል ናቸው ቢባልም፣ ይህ በሊባኖስ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል፡፡
ሰሞኑን ከየመን ወደ ሳዑዲዋ ሪያድ ለተተኮሰው ሮኬትም የሒዝቦላህና የኢራን እጅ አለበት ብለው የሳዑዲ ባለሥልጣናት መደምደማቸውና ሊባኖስ በሳዑዲ ላይ ጦርነት አውጃለች ማለታቸው ለሊባኖስ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዓድ ሐሪሪ ድንገት ወደ ሪያድ አቅንተው ሥራ መልቀቃውን ማሳወቃቸው ደግሞ ጥርጣሬን ፈጥሯል፡፡
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሪሪ ወደ አገሬ እመለሳለሁ ቢሉም የሰውየው በድንገት ከሥልጣን ለቅቄያለሁ ማለት ኢራን፣ ሒዝቦላህና ሊባኖስ የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸው ያሳያል አስብሏል፡፡ በሌላ በኩልም ሳዑዲ ዓረቢያ ሐሪሪ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የራሷን ሚና ተጫውታለች ሲሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ሳዑዲ በኢራንና በሊባኖስ ላይ ጣት መቀሰሯ በሊባኖስ ላይ የጎላ አደጋ አለው፡፡ የሊባኖስ ፖለቲከኞችና የባንክ ባለሀብቶች እንደሚሉት፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በኳታር ላይ እንደጣለችው ማዕቀብ በሊባኖስ ላይ ልትጥል ተችላለች፡፡
ከኢራን ጋር ግንኙነት አለው የሚባለውን ሒዝቦላህ ሊባኖስ ማሽመድመድ ካልቻለችም ሳዑዲ ለሊባኖስ የምትተኛ አትሆንም፡፡ ሳዑዲ በሊባኖስ ላይ የምትጥለው ሁለገብ ማዕቀብ ደግሞ ሦስት መቶ ሺሕ ሕዝብ ላላትና አራት መቶ ሺሕ ሕዝቦቿ በባህረ ሰላጤው አገሮች እየሠሩ በዓመት ከሰባት እስከ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለሚልኩላት ሊባኖስ ውድቀት ነው፡:፡ ቀድሞውንም የተዳከመውና በብድር የተመታው ኢኮኖሚዋ የሚላሽቅ ይሆናል ተብሏል፡፡
ይህ የሚያሳስባቸው የሊባኖስ ባለሥልጣናት ሥጋታቸውን እየገለጹ ቢሆንም፣ በእምነት ድንበር ተገድበውና ለዓመታት የባህረ ሰላጤው ኃያልነትን ለመቆናጠጥ አልመው የቃላት ጦርነት ውስጥ የከረሙት ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በሊባኖስ የውክልና ጦርነታቸውን ሊከፍቱ እንደሚችሉ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ከአምስት ዓመታት በላይ በዘለቀው የሶሪያ እርስ በርስ ጦርነት ኢራንና ሒዝቦላህ ከሩሲያ በማበር ፕሬዚዳንቱን በሽር አል አሳድ፣ ሳዑዲ ደግሞ ከአሜሪካ አብራ ተቃዋሚዎችን በመውጋት ሶሪያን የውክልና ጦርነት አውድማ አድርገዋታል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶሪያውያን ለስደት፣ እንዲሁም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
በአገሮች ላይ የውክልና ጦርነት በማድረግ ጽንፍ ለጽንፍ ሆነው የሚታዩት አሜሪካና ሩሲያ ቢሆኑም፣ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው ውጥረት ተቀናቃኞቹና የአንድ ቀጣና አገሮቹ ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ሁሌም በህቡዕና በገሃድ እንደተፋለሙ ነው፡፡ በአገራቸው ምድር የቃላት ጦርነቱን፣ በሰው አገር ደግሞ ጦር መማዘዙን ከያዙትም ዓመታትን አስቆጠረዋል፡፡ ሳዑዲ ከአሜሪካ፣ ኢራን ከሩሲያ መወገናቸውም ይታወቃል፡፡
ከኢራቅ አይኤስን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ኢራቅ ከኢራንም ሆነ ከአሜሪካና ከሳዑዲ ጋር አብራ የምትሠራ ቢሆንም፣ ኢራን ከሳዑዲም ሆነ ከአሜሪካ ጋር መሳ ለመሳ ሆና አታውቅም፡፡ በየመን ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በማስቆሙ ሒደትም ሳዑዲና ኢራን ፊትና ጀርባ ናቸው፡፡
በየመን ሳዑዲ መራሹ ጦር የአገሪቱን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላህ ደጋፊዎች የሆኑትን የሺሃ ሁቲ አማፅያንን ሲወጋ፣ ኢራንና ሒዝቦላህ ደግሞ የአማፅያኑ ደጋፊዎች ናቸው፡፡
በቀጣናው የሚዛን ማማውን መቆናጠጥ የሚፈልጉት ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በሶሪያ፣ በኢራቅና በየመን የውክልና ጦርነታቸውን በግልጽና በህቡዕ እያካሄዱ ቢሆንም፣ ለባህረ ሰላጤው ይበልጡን ሥጋት የሆነው የሳዑዲና የሊባኖሰ ግንኙነት መሻከር ነው፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ብቻ አራት ጊዜ ያህል ዜጎቿ ከሊባኖስ እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፈችው ሳዑዲ፣ አሁን ንግግሯ ሁሉ ጦርነት ጦርነት የሚሸት ሆኗል፡፡ በሒዝቦላህና በኢራን ላይም ውንጀላዋን እያበዛች ትገኛለች፡፡
የሳዑዲና የኢራን ፍጥጫም መካከለኛው ምሥራቅን እንዳይጠራርጋት ሥጋት አለ፡፡: በተለይ ሳዑዲ በሊባኖስ ላይ ጦርነት ካነሳች የሱኒውና የክርስቲያን ማኅበረሰቡ ስለሚዳከም ሺሃው ሒዝቦላህ በሊባኖስ የበላይነቱን ይቆጣጠራል፡፡ ይህ ደግሞ የሳዑዲ ጨዋታ ማክተሚያ ይሆናል ሲሉ በኦክላሆማ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ምርምር ማዕከል መሪ ጆሽዋ ላንዲስ ይናገራሉ፡፡
ሆኖም ከሊባኖሰ ባለሀብቶችንና መልቀቂያ ያቀረቡትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሪሪን ጨምሮ ከፖለቲከኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ በሊባኖስ ላይ ፊቷን በማዞር ሒዝቦላህን በምትረዳው ኢራን ላይ አዲስ ጫና ለመፍጠር ሽር ጉድ ይዛለች፡፡
የፖለቲካ ተንታኞች ግን ይህ ለሳዑዲ አያዋጣም፣ ሽንፈት ያጎናፅፋታል እያሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በየመን፣ በኢራቅና በሶሪያ የነበራት ጣልቃ ገብነት ሳይቋጭ ወደ ሊባኖስ ማማተሯም መካከለኛው ምሥራቅን እንዳልነበረ ያደርጋል ተብሏል፡፡