Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየተጋነነው የመልካም አስተዳደር ዲስኩር

የተጋነነው የመልካም አስተዳደር ዲስኩር

ቀን:

በኢዮብ አሰለፈች ባልቻ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚዲያዎቻችን ላይና በተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች አንደበት ላይ የማይጠፋ የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ የሚወሰድ ፍቱን መድኃኒት አለ። እርሱም “መልካም አስተዳደር” ይባላል። ከፖለቲከኛው እስከ ነጋዴው፤ ከገዥው ፓርቲ ካድሬ እስከ ቀንደኛ ተቃዋሚው ድረስ አብዛኞቹ ሊባል በሚያስችል መልኩ የተግዳሮታችን ሁሉ ማጠንጠኛ ብለው የሚገልጹት “የመልካም አስተዳደ እጦት”ን ሲሆን፤ መፍትሔ ብለው የሚያስቀምጡት ደግሞ “የመልካም አስተዳደር መስፈን”ን ነው። በነገራችን ላይ የቤተ እምነቶችንም ችግር በመልካም አስተዳደር እጦት መግለጽ ከተጀመረም ውሎ አድሯል።

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ይህ ለሁሉም ነገር ፍቱን መድኃኒት ተደርጎ የተወሰደውን መልካም አስተዳደር የሚባለውን ነገር ከጽንሰ ሐሳብና ከተግባራዊ ሁኔታ አንፃር ለማየት መሞከር ነው። በእኔ አተያይ ስለ መልካም አስተዳደር ያለው ገዥ አመለካከትና የተሰጠው ዋጋ የተጋነነ ነው። በተጨማሪም ይህ የተጋነነ አመለካከት ደግሞ ሌሎች የዕለት ከዕለት ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚወስኑ ነገሮችን ችላ እንድንላቸውና አትኩሮት እንዳንሰጣቸው እያደረገን ነው የሚል መከራከሪያ ሐሳብ አለኝ። ይህንን ሐሳቤን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመግለጽ እንዲረዳኝ መልካም አስተዳደር ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ከታሪካዊ መነሻው ጀምሮ በአጭሩ ለመዳሰስና ለመተንተን እሞክራለው።

የመልካም አስተዳደር ዲስኩር መነሻ

እ.ኤ.አ. በ1989 የዓለም ባንክ የአፍሪካ ችግር የአስተዳደር ቀውስ (Crisis of Governance) ነው ሲል አወጀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መልካም አስተዳደር የሚለው ጉዳይ በአስተሳሰብ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ኃይልና ትርጉም ያለው ጉዳይ መሆን ጀመረ። የዓለም ባንክና መሰል ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መልካም አስተዳደር የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የሚገልጹት በመንግሥትና በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በተጠቃሚ ዜጎች ወይም በደንበኞች መካከል ሊኖር በሚገባው ወጥ የሆነ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ አሠራር ነው። ይህም አሠራር ገላጭ የሆኑ ምናልባትም በአብዛኛው ዘንድ እንደ መፈክር በሚታወቁ ሕጎች፣ መርሆዎችና ደንቦች ይታገዛል። ይህ አስተሳሰብ የበለጠ ገኖ መውጣት የጀመረበት ጊዜ በተለይ የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም የሚባለው የዓለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት በኢኮኖሚ ደከም ያሉ አገሮች ላይ ጫና በሚያሳድሩበት ወቅት ነበር። ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ የሕግ የበላይነትና የመሳሰሉት መርሆዎች እስካሁን ድረስ መልካም አስተዳደር ለሚባለው ዲስኩር መገለጫዎች ሆነው ያገለግላሉ። እዚህ ጋ አንድ አትኩሮት መስጠት ያለብን ነገር ቢኖር “መልካም” የሚለው አገላለጽ አንድን ነገር ልቦናዊ ተቀባይነት ያለው (Normatively Accepted)፣ በራሱ ጥሩ የሆነ ነገር እንደሆነ አድርገን እንድንወስደው ተፅዕኖ ማሳደር የሚችል መሆኑን ነው።

የመልካም አስተዳደር ዲስኩር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለኢካዊ ችግሮችን ለመፍታት በመሠረታዊ ደረጃ የሚያስቀምጠው መፍትሔዎች አስተዳደራዊ በሆኑና በተለይ በባለሙያዎች የሚፈጸም፣ ሥራን በአግባቡ የመከወን ሒደቶችን ነው። ስለዚህም ዋነኛ አትኩሮቱ ተቋማትን ማጠናከር፣ የአሠራር ደንብና መመርያዎችን ማውጣት ላይ ነው። መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው ቴክኒካዊ በሆኑ ክህሎቶች መኖር ነው ብሎ ስለሚያስብ፣ እነዚህን ክህሎቶች በባለሙያዎች ዘንድ እንዲኖሩ የሚደረገው በጥቅሉ “አቅም ግንባታ” (Capacity Building) ተብሎ በሚጠራው ተግባር ነው። አቅም ግንባታ ሰዎችንም ሆነ ተቋማትን ታሳቢ ተደርጎ ሲከወን በተያያዥ የሚደረገው ሌላ ተግባር ደግሞ ምርጥ ተሞክሮ ወይም ልምድ (Best Practice) የሚባለው ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ ምርጥ የተባለ ከሌላ ቦታና ሁኔታ የተቀዳ ተሞክሮ ከነባራዊው ዓውድና ዕውነታ ጋር የመጣጣም ዕድሉ ከፍተኛ ክፍተትን ሲፈጥር ይታያል። ወጥ የሆኑ ሕግና ሥርዓትን፣ የአፈጻጸም ሒደቶችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጎላው የመልካም አስተዳደር ዲስኩር በተለይ በአገራችን የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ውስጥ ስንት ዓይነት አሠራሮችን ያለ በቂ ጥናትና መረዳት በዘመቻ መልክ ሊተገብር እንደሞከረ ብዙ ማሳያዎች አሉ። ለምሳሌ ውጤት ተኮርና ቢፒአር የተባሉትን አንድ ሰሞን ለሁሉ ነገር መፍትሔ ተደርገው ይወሰዱ የነበሩ፣ ነገር ግን አሁን ከነጭራሹ የማንሰማቸው ብዙ ሚሊዮኖች ብር የወጣባቸውን ፕሮግራሞችን ማንሳት ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ ይህን መሰል የመልካም አስተዳደር መፍትሔዎች ለውድቀታቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ትልቁ ተግዳሮት “የፖለቲካ ቁርጠኝነት” (Political Will/Commitment) አለመኖርን ነው። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ለየትኛውም ጉዳይ ስኬት አስፈላጊ መሆኑ በስብሰባዎች፣ በመፈክሮችና በተለያዩ መድረኮች ቢገለጽም የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚቆሰቁሱ ቁልፍ ጉዳዮች በአግባቡ ስለማይነኩ አገራዊ የቁራ ጩኸት ከመሆን አያልፍም።

ከተግባር አንፃር የመልካም አስተዳደር ዲስኩርን ውሱንነት በሁለት መንገድ ልናየው እንችላለን። የመጀመርያው የመልካም አስተዳደር ዕይታ በይበልጥ የሚስተጋባው በዓለም ዓቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ሲሆን፣ ዋና ዋና ጉዳዮቻቸው የሚያያዙት የሕዝባዊ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ከማሻሻል፣ የኢኮኖሚ ተቋማትን ብቃትና የገንዘብ አጠቃቀም ብክነትን መቀነስ፣ የግሉ የክፍለ ኢኮኖሚን ሚና ማሳደግ፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እንዲሁም በባለሙያና በመረጃ የተደገፈ የተደገፈ የፖሊሲ ሥርዓትን ከማስፈን አንፃር ነው። ሁለተኛው የመልካም አስተዳደር ዕይታ በይበልጥ የሚንፀባረቀው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአብዛኛው የምዕራብ አገሮች ሲሆን መሠረታዊ ጉዳዮቻቸው ፖለቲካዊ ሒደቶችና ክንውኖች ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህም የሚገለጹት የምርጫ ተቋማትን በማገዝ፣ ያልተማከለ ሥርዓትን በማበረታታት፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት በማበረታታ፣ የዜጎች የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶችን፣ ማስከበር፣ ሙስናን በመከላከልና የመንግሥትን ምላሽ የመስጠት አቅም በማጠናከር ላይ ነው።

ዋና ማስረጃዎች

በአሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገባቸው ከፍተኛ ዕውቅናና ሙገሳ እየቀረበላቸው ያሉትን ኢትዮጵያንና ሩዋንዳን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ መልካም አስተዳደር የሚባለው ዲስኩር ምን ያህል ውሱንነት እንዳለበት ለማየት እንችላለን። ሁለቱም መንግሥታት በአኅጉራዊና በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ያላቸው ዕውቅና ተከታታይና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ደሃ ተኮር የሆኑት የልማት ስኬቶቻቸው ናቸው። በተመሳሳይ ሁለቱም መንግሥታት  የዜጎችን የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ባለማክበር፣ መሠረታዊ በሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ፖለቲካዊ ቅኝት ባላቸው አፋኝ ሕጎቻቸውና የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በመገደብ ተመሳሳይ የሆነ ወቀሳና ትችት ይደርስባቸዋል። የእነዚህን ሁለት መንግሥታት ወቅታዊ  ሁኔታ ከመልካም አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ስንቃኘው የሚኖረን ምልከታ ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይከብዳል። ለምሳሌ የእናቶችንና የሕፃናትን የሞት መጠን በመቀነስ ደረጃ ሁለቱም መንግሥታት ያስመዘገቡትን ስኬት በዜጎች ላይ በሚያደርሱት ፖለቲካዊ የመብት ጥሰት ስንል በዜሮ ልናባዛው (ይቻለን ይሆን) እንቸላለን?

የሰብዓዊ መብት ጉዳይን በተመለከተ እነዚህ አገሮች ጣት ሊቀሰርባቸው የሚገባውን ያህል፣ በሌላው አቅጣጫ ደግሞ የልማት አጋር የሚባሉት ተቋማት የአፍሪካ የዕድገት ተምሳሌት አድርገው እንዲስወድዋቸው በቂና ተጨባጭ መረጃም አለ። ከዚህ አንፃር የመልካም አስተዳደር መነጽር ሊነግረን የሚችለው ነገር ቢኖር በእነዚህ መንግሥታት ምን ዓይነት ተግባራት በትክክለኛው የአፈጻጸም ቀመር እየተከወኑ እንዳሉና እንደሌሉ እንጂ፣ ለምን በዚህ ወይም በሌላ መንገድ እንደተከወኑ አልያም እንዳልተከውኑ አይደለም። በእኔ አስተያየት የማኅበረሰብ ዕድገትንና ለውጥን ቀጥተኛ በሆነ የክንውን ሒደትና ቀመር ለመግለጽ መሞከር ለሌሎች የጎንዮሽና  ኢመደበኛ ለሆኑ ግንኙነቶች የምንሰጠውን አትኩሮት ሊጋርድብን አይገባም። መልካም አስተዳደር የሚሰብከው ፍፁም መደበኛ የሆነ የሕግና የሥርዓት ሒደት ልቦናዊ ተቀባይነት ቢኖረውም፣ የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴያችንን ግን በብቸኝነት አይመራውም፣ ሊመራውም አይችልም። ስለዚህም ኢመደበኛ የሆኑ ግንኙነቶች በማኅበረሰብ ዕድገትና የለውጥ ሒደት ውስጥ ያላቸውን ሚና ማየት ተገቢ ይመስለኛል።

መደበኛ ያልሆኑ (ኢመደበኛ) ግንኝነቶች አቅም

መደበኛ ያልሆኑ የግንኙነት መንገዶች በሕግ ደረጃ ከተቀመጡ የአስተዳደር መመርያዎች ወይም መርሆዎች በበለጠ የሰዎችን ጉዳይ በተቀላጠፈ መልኩ እንዲፈጸም የሚያደርጉበት ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ መደበኛ ያልሆኑ የግንኙነት መንገዶች የምላቸው ሰዎች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያሚ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያደርጓቸውን የሐሳብ ልውውጦችና ድርድሮች፣ የሻይ ቡና ወጎችና አንዳንድ ጊዜም ጥቅምን መሠረት ያደረጉ ግንኙነቶችን ነው። በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ጉዳይ የሚፈጸመው በየቢሮው ግድግዳ ላይ በተለጠፉ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችና ሥርዓቶች ሳይሆን፣ ጉዳዩን በመከወን ሒደት ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ሰዎች መካከል ባለው መደበኛ ያልሆነ የትውውቅና አለፍ ሲልም የጥቅም ትስስር ምክንያት ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ወደ አንድ የመንግሥት ወይም የግል ተቋም ለጉዳይ ከመሄዳቸው በፊት የሚጠይቁት ጥያቄ፣ ‘እዚያ የሚሠራ ሰው ማንን አውቃለሁ?’ ወይም እዚያ የሚሠራ ሰው የሚያውቅ ወዳጅ እንዳላቸው ነው። ይህ ዓይነት መደበኛ ያልሆነውን የግንኙነት መስመር ለታለመው ስኬት እንደ ወሳኝ ግብዓት የመጠቀም ነገር ከታችኛው የቀበሌ ወይም የእድር ጉዳይ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ዓለም አቀፋዊና ሉዓላዊ አገሮችን በሚያሳትፈው የድርድር መድረኮች ላይም የሚንፀባረቅ ነው። ለምሳሌ በተለምዶ የ”ኮሪደር ዲፕሎማሲ” ተብሎ የሚጠራው መደበኛ ያልሆነ ተፅዕኖ የማሳረፊያና ስኬትን የመቀመሪያ መንገድ ከመደበኛ የስብሰባ መደረኮችና ሥርዓቶች ውጪ በሻይ ሰዓትና  በመሰል የግብዣ ሰዓቶች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች የሚከወን ነው። እነዚህን መሰል መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች ምናልባትም በሕግና በሥርዓት ወይም በተጻፉ ሕጎች ብቻ ለመሳካት ረዘም ያለ ጊዜና ሒደት የሚጠይቁ፣ ጉዳዮችን ባነሰ ጊዜና በብቃት ለመከወን የሚያግዙ መንገዶች ናቸው።

መልካም አስተዳደር በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ የእነዚህን ወሳኝ የግንኙነት ሒደቶች ሚና ማየት ይከብዳል። ሁሉም ነገር ፍፁም መደበኛ በሆነ መንገድ፣ በሠለጠኑ ባለሙያዎች፣ የአፈጻጸምና የውሳኔ መመርያዎችንና ተዋረዶችን በጠበቀ ሁኔታ እንዲከናወኑ እንጂ፣ ውስብስብ የሆኑትን በግለሰቦች መካከል የሚደረጉትን ድርድሮችና መስተጋብሮች ዋጋ አይሰጥም። ፖለቲካዊ ትብብሮች፣ የጥቅምና የግንኙነት መረቦች፣ የቡድኖች መመሥረትና መፍረስ ለአንድ ሥርዓት ተግባራዊ እንቅስቃሴና ዘላቂነት ከፍተኛ የሆነ ሚና አላቸው። እነዚህን መሰል ትብብሮችና የግንኙነት መረቦች ናቸው ሙስናን መሰል ትልቅ ነቀርሳ ተቋማዊ ልባስ ሰጥተውት ከአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ዕይታ የተሰወረና ብዙም አሳሳቢ ያልሆነ ችግር ተደርጎ እንዲቀርብ የሚያደርጉት። በየቢሮው ያሉን ጉዳዮቻችን ይሳኩ ዘንድ የሒደቱን አቅጣጫ የሚወስኑት በየመገናኛ ብዙኃኑና በየስብሰባ አዳራሹ የንግግር ማሳመሪያ የሆኑት ከትንንሽ የግርግዳ ፖስተሮች እስከ የመንገድ ዳር ትላልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ያጣበቡት የሥነ ምግባር መርሆዎችና ፉከራዎች ሳይሆኑ፣ ከአንድ ግለሰብ እስከ ከፍተኛ ፈጻሚዎችና ባለሥልጣናት የተዘረጉት የጥቅማ ጥቅም መረቦችና መደበኛ ያልሆኑ ትስስሮች ናቸው።

 የመልካም አስተዳደር እሳቤ ጉዳዮች የሚፈጸሙባቸውን የመጫወቻ ሕጎችና ሥርዓቶችን ስለማውጣትና ስለማስጠበቅ ስንጨነቅ፣ መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶችን አቅም መረዳት ግን ይህን መሰል ሕጎችና ሥርዓቶች በማውጣት ሒደት ውስጥ ስላሉት ቀዳሚ ሕጎችና ሥርዓቶች አትኩሮት ይሰጣል። ለምሳሌ በሺሕ ብሮች የሚቆጠር ገንዘብ በሙስና ያገኘ ሰው ወንጀለኛነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተወራና አግባብ ያለው ቅጣት የሚፈጸምበት ሒደት ባለበት አገር ውስጥ፣ ብዙ ሚሊዮን ብሮችን የዘረፈና በሙስና ሀብት ያካበተን ሰው ምንም ሕጋዊ ዕርምጃ እንዳይወሰድበት ከሚያደርገው አንዱ ምክንያት በዚህ የሙስና ሒደት ውስጥ ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልሂቃን መኖራቸው ነው።  ተጠያቂነትና ግልጽነት እያሉ በመጮህ ብቻ ይህንን ማኅበረሰባዊ ሰንኮፍ ማስወገድ መቻላችንን እጠራጠራለሁ። ይልቁንም መደበኛ ባልሆኑ ግንኙነቶች ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የጥቅም ትስስርን በአግባቡ መረዳትና ማወቅ የመጀመርያው  ዕርምጃችን ሊሆን ይገባል። ይህንን ስል ግን እንደ አለማዳላት፣ ታማኝነትና ተጠያቂነትን የመሳሰሉ ለልቦናችን ዋጋ የምንሰጣቸው የመልካም አስተዳደር መርሆዎች አያስፈልጉም እያልኩኝ አይደለም። ነገር ግን በቂ አለመሆናቸውን ለማሳየት እንጂ። ሙስናን፣ አድርባይነትንና ጥቅምን ብቻ መሠረት ያደረገ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበረሰባዊ መስተጋብር በመፈክር ልናስቀረው ፍፁም አንችልም። መሬት ላይ ያለው ሀቅ የሚያስረዳን የተጻፉ ሕጎችን የቱንም ያህል እንደ መፈክር  ይዘናቸው ስንጮህ ውለን ብናድር፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልሂቃኑ ፍላጎቶች ከተጻፉ ሕግና ሥርዓታት በላይ ዋጋና ተሰሚነት እንዳላቸው ነው።

በዛሬይቱ አገራችን ገዥው ፓርቲም፣ ዜጎችም፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሁሉም የሚስማሙበት ጉዳይ ቢኖር የመልካም አስተዳደር እጦት ስለሚባለው ችግራችን ነው። ለአብዛኛው የኅብረሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ኑሮው ላይ የሚደርስበት ጫና ስለሆነ በቅርበት ያውቀዋል። የበለጠ መደበኛ ያልሆነ የግንኙነት ትስስር ያላቸው ሰዎች ይህንን ጫና በቀላሉ ለማለፍ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥልቶችን ሲጠቀሙ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የግንኙነት መረብ የሌላቸው ግን ወይ ከማያልፉት ነገር ጋር ሲላተሙ፣ ወይ በምሬት ሲበሳጩ ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ገዥው ፓርቲ አካባቢ ላሉ ተዋንያን መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶቻቸው ባለተጻፈ ሕግ በመመራት የፖለቲካ ድጋፍን የሚያሰባሰቡበትና ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ድርድሮችን ያካትታሉ። በተለይ በአሁኑ ጊዜ አገራችን ካለችበት የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ አንፃርና ስኬት ላይ ለመድረስ የተሻሉና የተመቻቹ ዕድሎች በአንፃራዊነት በበዙበት ሁኔታ ውስጥ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥቅሞች በከፍተኛ ሁኔታ እርስ በእርስ የተያያዙ ናቸው። በዚህን መሰል ድባብ ውስጥ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት መርሆዎች በላይ የሰዎችን ተግባር የሚቃኘው “የማን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተነካ?” የሚልና “ማን ምን ያገኛል?” የሚለው ነው።

ከዚህ አንፃር በአገራችን ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚጥሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገዥውን ፓርቲ “መልካም አስተዳደርን አላሰፈንክም” ብለው ሲከሱት ይገርመኛል። በእኔ ዕይታ መልካም አስተዳደርን ላለማስፈኑና ከዚህ አንፃር ስለመውደቁ ራሱ ገዥው ፓርቲ ከማንም በላይ መናገር የሚችል ይመስለኛል፣ ይናገራልም። ሁልጊዜ የምንሰማውን ከገዥው ፓርቲ የሚቀርበውን “በአፈጻጸም ላይ ያሉ ችግሮች” የሚለውን ጥቅል ምክንያት ማንሳት እንችላለን። ይልቁንም በተሻለ ሁኔታ ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት መነሻ ልናደርገው የሚገባው መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች ያላቸውን አቅም መረዳትና ማወቅ፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ከማነሳሳትም ሆነ ከማሳጣት አንፃር ያላቸውን ሚና መገንዘብና ማወቅ፣ ከዚያም በምናስበው ሁለንተናዊ የማኅበረሰብ ልማት ውስጥ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ መገምገም ነው። እንደዚህ ያሉ መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች ከማኅበረሰብ ተቋማትና ከግለሰቦች ባህሪ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝትና መተሳሰር ስላላቸው የትኛውም የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የልማትና የዕድገት ዕቅድ ውስጥ ተገቢው አትኩሮት ሊሰጣቸው ይገባል። ይህ በጎ ጎናቸውን ለመጠቀም አሉታዊ ተፅዕኗቸውንም ለመቀነስ ይረዳል።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ማንችስተር በልማት ፖሊሲና አስተዳደር የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ ሲሆኑ፣ ጹሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን። ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...