Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አብዮት እንደበረከት›› - አገራዊ አንድነት በቸርነት ሥዕሎች

‹‹አብዮት እንደበረከት›› – አገራዊ አንድነት በቸርነት ሥዕሎች

ቀን:

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ዕይታ በሚስብ፣ አረንጓዴያማና የተንጣለለ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገኛል፡፡ ቀድሞ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ መኖሪያ የነበረውን ቤት ዛሬ አካዴሚው ይገለገልበታል፡፡ ቀደምት ታሪካዊ ሕንፃዎች በተለያየ ግንባታ ሳቢያ የመፍረስ አደጋ ባንዣበበባቸው በዚህ ወቅት፣ ቤቱ አገልግሎት እየሰጠ መዝለቁ መልካም ተሞክሮ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የጥንት ይዘቱን ሳይለቅ በዚህ ዘመን በተመቸ ሁኔታ ጥቅም እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፡፡

‹‹ወዳጄ ልቤ››፣ ‹‹አዲስ ዓለም››፣ ‹‹ማህደረ ብርሃን ሀገረ ጃፓን›› እና ሌሎችም መጻሕፍትን በማሳተም ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የድርሻቸውን ያበረከቱት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ በዲፕሎማሲውና በትምህርቱም ዘርፍ ጉልህ ሚና ተጫውተው አልፈዋል፡፡ መኖሪያቸውም በሳይንሱ ዘርፍ የላቁ ግኝቶችን ለማስተዋወቅ፣ ጥናትና ምርምር ለማካሄድና የውይይት መድረክ ለመፍጠር እየዋለ ነው፡፡

በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበብ ማዕከል ጥበባዊ ሥራዎችን ያማከሉ ክንውኖች ይካሄዳሉ፡፡ ከአራት ወር በፊት ሠዓሊና ገጣሚ ቸርነት ወልደገብርኤል በማዕከሉ ውስጥ እየኖረ እንዲሠራ መንበር (ሬዚደንሲ) ተሰጠው፡፡ ግቢውን ከመጠቀሙ ባሻገር ሥራውን ለመደገፍ የሸራና ቀለም ወጪውንም ማዕከሉ ሸፈነ፡፡ ቸርነት አራቱን ወራት አጠናቆ፣ ‹‹አብዮት እንደ በረከት›› (ሬቮሉሽን አስ ብለሲንግ) የተሰኘ የሥዕል ዐውደ ርዕይ አዘጋጅቶም ኅዳር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በማዕከሉ ለዕይታ በቅቷል፡፡

እስከ ጥር 2 ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆየው ዐውደ ርዕዩ፣ 27 ሥዕሎች ተካተውበታል፡፡ የዐውደ ርዕዩ መጠሪያ በሆነው ‹‹አብዮት እንደ በረከት›› ስያሜ የተካተቱትን አራት ሥዕሎች ጨምሮ፣ አብዛኞቹ የቸርነት ሥራዎች ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ይዳስሳሉ፡፡

ማኅበራዊ ሁነትን ከተመረኮዙ ሥራዎች መካከል ‹‹እንጀራ›› እና ‹‹ለምለም›› የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚገፉ ሰዎች፣ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚያዩትን ውጣ ውረድ ያመለከታል፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብሎ በመቃኘት፣ አገሪቱ ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ በርካቶች ሕይወታቸውን መሰዋታቸውን የሚያስተጋቡ ሥዕሎችም ተካተዋል፡፡ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ እንዲሁም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ረገድም ብዙዎች መስዋዕትነት መክፈላቸውን ሥዕሎቹ ያንፀባርቃሉ፡፡ ‹‹የተከፈለበት››፣ ‹‹ተራኪው››፣ ‹‹ክፍያ›› እና ሌሎችም ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ጠቢባን የሚኖሩበትን ዘመን በመግለጽ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመተቸት ወይም በማወደስ ታሪክን ወደ ቀጣዩ ዘመን ያሸጋግራሉ፡፡ የአንድን ማኅበረሰብ ማንነትና ነባራዊ ገጽታ በማመላከት ረገድ ጥበብ ከፍተኛ ሚና አላት፡፡ የቸርነት ሥዕሎችም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በማሳየት የወደፊቱ ምን መምሰል አለበት? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በነባራዊው ፖለቲካ የብሔር ልዩነት አንድን ማኅበረሰብ ከሌላው በጎራ ለይቶ ለፀብ ሲጋብዝ ይስተዋላል፡፡ ከአንድነትና ኅብረት ይልቅ የብሔር ልዩነት እየተተኮረበት መምጣቱ የግጭት መንስኤ ሆኖ የሰዎች ሕይወት መቀጠፉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ የቸርነት ሥዕሎች ይኼንን አገራዊ ሁኔታ ያጠይቃሉ፡፡ እሱ እንደሚገልጸውም፣  ሥራዎቹ ፍቅርና አንድነትን በመስበክ፣ ጤናማ የሆነ አብዮት ለአገሪቱ እንደሚበጅም ያሳስባሉ፡፡

‹‹አብዮት እንደ በረከት›› በተሰኙ ሥራዎቹ፣ የሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ሳይሆን ጽንሰ ሐሳብን የተመረኮዘ አብዮት እንደሚበጅ ይገልጻል፡፡ ‹‹አብዮት አሉታዊ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እውነታው ግን ሰውን የሚበላ ሳይሆን የሐሳብ አብዮት አዎንታዊ ነው፡፡ አገራችንን በዘር የማይከፋፍል፣ ፍቅርና ሰላም የሚያመጣ አብዮት ከመቼውም በላይ አሁን ያስፈልገናል፤›› ይላል፡፡

አብዮት አገርን የሚያዋህድና ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ በእኩልነት የሚኖሩበት ዓለም የሚፈጥር መሆን እንደሚገባው ያምናል፡፡ ሰዎች ብሔራቸው፣ ሃይማኖታቸው አልያም የመጡበት አካባቢ ከመታየቱ በፊት ሰው መሆናቸው መቅደም አለበት፡፡ ‹‹ሰውን በሰውነት ከማክበር፣ ከመቀበልና ከመውደድ ይጀምራል፡፡ ሰው ‹ይህ ቦታ የአንተም የአባትህም ሳይሆን የኛ ነው› ተብሎ የሚባረርበት አገር ማየት አልፈልግም፤›› ሲል ቸርነት ያስረዳል፡፡

‹‹ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግና በፍቅር የሚማርክ መሆን አለበት፤›› ሲል የወደፊቱ አቅጣጫ ምን መምሰል እንደሚገባው ይናገራሉ፡፡ በአሁን ወቅት የሚስተዋለውን ብሔር ተኮር ግጭት በመንቀፍም፣ አገራዊ አንድነት እንዲቀድም ያሳስባል፡፡ ችግሩ የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ በአፋጣኝ ካልተፈታ የሁሉንም ዜጋ በር እንደሚያንኳኳ ገልጾ፣ አገሪቱ ከጥላቻ እንድትጸዳ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

ከአገር ባሻገር በመላው ዓለም በቀለምና በዘር ያለውን ክፍፍልም ማጣቀስ ይቻላል፡፡ ሠዓሊው እንደ ጥቁር ሰው በምዕራባውያኑ ዓለም ከነበረው አሉታዊ ተሞክሮ በመነሳትም እኩልነትም መስፈን እንዳለበት በሥዕሎቹ ይናገራል፡፡ ‹‹የምንኖረውን አጭር ዕድሜ በፍቅር ማጣጣም ይበልጣል፤›› የሚለው ቸርነት፣ በሥራዎቹ የሚያስተላልፈው ሐሳብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ዓለም መሆኑን ያስረግጣል፡፡

የሰው ልጆች የሚወለዱበትን የዘር ግንድ የመምረጥ አቅም እንደሌላቸው በማስታወስ፣ ‹‹በምርጫው ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ አማራ የሆነ የለም፡፡ ፈልጎ ነጭ፣ ጥቁር የሆነ የለም፡፡ ስለዚህ ወደ ፍቅር እንሂድ! በማስተዋል እንራመድ!›› ይላል፡፡

‹‹ተራኪው›› የአንድ ወታደር ጫማን ያሳያል፡፡ በሥዕሉ አንድ ሕይወቱ ያለፈ ሰው ምላስም ይስተዋላል፡፡ በ‹‹ክፍያ›› ሥዕል በቀይ ቀለም መንገድ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ይታያል፡፡ ቸርነት እንደሚለው፣ እነዚህ ሥዕሎች በቀደሙት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ለአገሪቱ የተከፈለ መስዋዕትነት ማሳያ ናቸው፡፡ የቅርብ ጊዜውን የባድመ ታሪክ ጨምሮ ከዛ በፊት በነበሩት ዓመታትም፣ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ሲደፈር፣ ሕዝቡ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ ተብሎ ሳይከፋፈል በአንድነት መነሳቱን ያስታውሳል፡፡ ወደ አሁኑ ትውልድ ሲመጣም፣ ቀደምት አባቶችና እናቶች ያለ ብሔር ክፍፍል በአንድነት የቆሙላት አገር ዛሬም የአንድነት ምድር እንድትሆን መልዕክት ያስተላልፋል፡፡

አብዮት እንደበረከት አገራዊ አንድነት በቸርነት ሥዕሎች

 

እንደ ሠዓሊና ገጣሚነቱ የሚኖርበትን ዘመን ከማንፀባረቅ ጎን ለጎን፣ ‹‹‹አገሬን በጣም ስለምወዳት ያገባኛል፤›› ሲል በጉዳዩ ያለውን ድርሻ ይገልጻል፡፡ ‹‹መስዋዕትነቱ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ነጻነትና ለአገር አንድነት ነው፤›› ይላል፡፡

ጥበባዊ ሥራዎች እንደ ታሪክ ሰነዶች ዘመንን ያንፀባርቃሉ፡፡ ጠቢባን በሥዕሎቻቸው፣ በግጥሞቻቸው፣ በዘፈኖቻቸው አልያም በሌሎችም የጥበብ ውጤቶች ነባራዊ ሁነቱን ማንፀባረቅ እንዳለባቸውም ያምናል፡፡

በእርግጥ በሥነ ጥበቡ ዘርፍ ሠዓሊያንና ቀራፂያንም ከሚገጥሟቸው መሰናክሎት መካከል በቂ ቦታ አለማግኘት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ረገድ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሥነ ጥበባት ማዕከል የመንበር (ሬዚደንሲ) መርሐ ግብር መልካም አማራጭ ይዞ መጥቷል፡፡

መሥሪያ ቦታ ማጣት ሠዓሊያንን እንደሚፈታተን የሚገልጸው ቸርነት፣ ማዕከሉ በሱ የጀመረው የመንበር መርሐ ግብር በሌሎች ሠዓሊያን እንደሚቀጥልም ተስፋ ያደርጋል፡፡ ‹‹የማዕከሉ ኃላፊዎች ትልቅ ልብ አላቸው፡፡ ቦታው በጣም ሰፊ በመሆኑም ለሥራ ይመቻል፡፡ አሁን የጎደለው ቀጥሎ በሚመጣው ሠዓሊ እየተሞላ መርሐ ግብሩ እያደገ ይሄዳል፤›› ይላል፡፡

ሠዓሊያን ቤተሰብ ሲያፈሩ የቦታ ጉዳይ የበለጠ አሳሳቢ እንደሚሆን ከተሞክሮው ይገልጻል፡፡ በወራት ልዩነት ሥዕል እየተሸጠ፣ ገቢውም ለሸራና ቀለም መግዣ እየዋለ መሥራት እንደሚከብድም ያክላል፡፡ ከዚህ አንፃር ማዕከሉ፣ ሠዓሊያን የሚያስቡበትና የሚሠሩበት ቦታ በመስጠትና የግብዓት ወጪያቸውን በመሸፈን የጀመረው መዝለቅ አለበት ይላል፡፡ ‹‹በማዕከሉ የነበረኝ ጊዜ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ደስተኛም ነበርኩ፤›› ሲል ወቅቱን ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ ካለው ሰፊ ቦታ አንፃር የመንበር መርሐ ግብሩ በሌሎች ባለሙያዎች ቢቀጥልም ውጤታማ ይሆናል፡፡ ከሥነ ጥበቡ በተጨማሪ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃና ሌሎችም ዘርፎችም ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ በቀጣይ በማዕከሉ በቸርነት ሥዕሎች ላይ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፣ ግጥሞቹን የሚያቀርብበት መድረክም ይዘጋጃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...