Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሉሲና ቡና ኢንሹራንስ ከፍተኛ የጉዳት ካሳ ክፍያ ማስተናዳቸውን አስታወቁ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመድን ኢንዱስትሪውን ዘግይተው ከተቀላቀሉት ድርጅቶች መካከል ሉሲና የቡና ኢንሹራንስ አክሲዮን ኩባንያዎች 2009 ዓ.ም. ፈተና የበዛበትና ከፍተኛ የካሳ ክፍያ ጥያቄ ያስተናገዱበት ዓመት እንደነበር ገለጹ፡፡ የሞተር ኢንሹራንስ የካሳ ክፍያ ከዕቅዳቸው በላይ ወጪ እንደጠየቃቸውም አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ይህንን የገለጹት፣ ኅዳር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረጓቸው ጠቅላላ ጉባዔዎች ወቅት ነበር፡፡ ሁለቱም የመድን ድርጅቶች ዓምና ካቀዱት በላይ የካሳ ክፍያ በመፈጸማቸው ዓመታዊ የትርፍ መጠናቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን በዓመታዊ ሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

የሉሲ ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በ2009 ዓ.ም. ተከታታይ የካሳ ጥያቄ ቀርቦለት ለማስተናገድ በመገደዱ ዓመቱ በፈተና የታጀበ ነበር ብሏል፡፡ ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስና በመሥራት ፈተናውን በመቋቋም አትራፊ መሆን እንደቻለም ኩባንያው ጠቅሷል፡፡  

ሉሲ ኢንሹራንስ በ2009 ዓ.ም. 114.6 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ የተጣራ ዓረቦን ገቢው ደግሞ 76.74 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውቋል፡፡ የተጣራ ገቢው በ28.4 ሚሊዮን ብር ቢጨምርም፣ የ48.1 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ ጥያቄ ቀርቦለት የ40.6 ሚሊዮን ብር ካሳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ይህም ለዓምና እንዲከፈል ታቅዶ ከነበረው አንፃር የአራት ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱ ታውቋል፡፡ በመሆኑም ዓምና የቀረበለት የጉዳት ካሳ ጥያቄ ከእጥፍ በላይ እንደጨመረ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለሉሲ ኢንሹራንስ ካቻምና ቀርቦለት የነበረው የጉዳት ካሳ ጥያቄ 23.37 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የዓምናው የጉዳት ካሳ ጥያቄ በ24.8 ሚሊዮን ብር እንደጨመረም አመላክቷል፡፡ የጉዳት ካሳ ጥያቄ የጨመረበት ምክንያትም በአገሪቱ በ2009 ዓ.ም. የደረሰው  የተሽከርካሪ አደጋ ቁጥር መጨመር፣ የተከፈለው ካሳ መጠን ከፍ እንዲል ማደረጉን የሉሲ ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ተፈራ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ሉሲ ኢንሹራንስ ለጉዳት ካሳ ካዋለው የ40.6 ሚሊዮን ብር ክፍያ ውስጥ 32 ሚሊዮን ብር ለተሽከርካሪዎች አደጋ የዋለ ነው፡፡ ኩባንያው ለዓምና ይዞት የነበረው የሞተር ኢንሹራንስ የካሳ ክፍያ መጠን 27.5 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ይታሰብ ነበር፡፡ የአደጋው መብዛት ግን ከ4.3 ሚሊዮን ብር በላይ ከዕቅዱ ብልጫ ያለውን ክፍያ ለማስተናገድ አስገድዶታል፡፡ ሉሲ ኢንሹራንስ በ2009 ዓ.ም. ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ላላቸው ንብረቶች የመድን ሽፋን ሰጥቷል፡፡

ቡና ኢንሹራንስ በበኩሉ በ2009 ዓ.ም. ሥራዎቹን ሲያከናውን የቆየው ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በመቋቋም እንደነበር አስታውቋል፡፡ ዓምና በአገሪቱ የመድን ኢንዱስትሪ ውስጥ አጋጥመው ነበር በማለት ቡና ኢንሹራንስ በዝርዝር ካቀረባቸው ችግሮች ውስጥ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የደመወዝ ክፍያና ውድድር ምክንያት የሠለጠነ የሰው ኃይል ከገበያው ማግኘት አዳጋች መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ይህም በዓረቦን ዋጋ ላይ ብቻ የመሠረተውን የመድን ኩባንያዎች ከፍተኛ ፉክክር፣ አዲስ ለተቋቋመ ድርጅት ፈታኝ ያደርግበታል፡፡ ዓምና የተመዘገበው የተሽከርካሪ አደጋም ከፍተኛ በመሆኑ በኩባንያው ትርፋማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ፣ የተከፈለ ካፒታሉን ለማሳደግ ባለአክሲዮኖች ቃል የገቡትን መጠን አለመክፈላቸው ቡና ኢንሹራንስ ከጠቀሳቸው ፈተናዎች ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ኩባንያው አዲስ በመሆኑ አንዳንድ የኢንሹራንስ ደላሎችና ትላልቅ ድርጅቶች ከኩባንያው ጋር ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት አነስተኛ ሆኖ መገኘቱ በኩንያው ሪፖርት ውስጥ ተካተዋል፡፡

በአገሪቱ በተከሰቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ምክንያት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸውና ከተሽከርካሪ መድን ውጭ ያሉ ሌሎች የኢንሹራንስ ዓይነቶች በተለይም የባህርና የየብስ ጉዞ ዋስትና፣ የቦንድና ከባንክ ጋር በተያያዘ በብድር ዋስትና ለተያዙ ንብረቶች የሚሰጡ የመድን ሽፋኖች በከፍተኛ ደረጃ መቀዛቀዛቸው በ2009 ዓ.ም. በኢንዱስትሪው ውስጥ ጎልተው የወጡ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ በተለይም ከውጭ ምንዛሪ እጥረት አኳያ በባህርና በአየር ለሚመጡ ዕቃዎች የሚሰጠው የማሪን ኢንሹራንስ ሥራ እጅግ የተቀዛቀዘበት ጊዜ ቢኖር የ2009 ዓ.ም. እንደነበር  የቡና ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት አሳይቷል፡፡

እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችን ማሳለፉን የጠቀሰው ቡና ኢንሹራንስ ዓምና የ134.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ገቢ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ጠቅላላ የዓረቦን ገቢው በ2009 ዓ.ም. ለማግኘት ካቀደው ጋር ሲመሳከር ውጤቱ 96 በመቶ እንደተሳካ አስታውቋል፡፡ ከካቻምናው ገቢ ጋር ሲነፃፀርም በ28.34 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ግን በ2009 ዓ.ም. 63.8 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ወጭ ከማድረጉ ባሻገር፣ በእንጥልጥል ላይ የሚገኝ የካሳ ክፍያ ጥያቄ መጠን 47.6 ሚሊዮን ብር እንደሚጠበቅበት ገልጿል፡፡  

የኩባንያው የውል ሥራ አፈጻጸሙ የተጠበቀውን ያህል እንዳልነበር ከሚያመላክቱ ነጥቦች መካከል በ2009 ዓ.ም. ከውል ሥራ ውጤት አፈጻጸም ያገኘው 9.8 ሚሊዮን ብር መሆኑ አንዱ ነው፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ ይህ አፈጻጸም ካቀደው የ23.7 ሚሊዮን ብር አንፃር ሲታይ የ59 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በዕቅዱ ልክ መፈጸም ያልቻለውም በተሽከርካሪ መድን ዓመታዊ የውል ትርፍ ላይ የተመዘገበው ኪሳራ የተነሳ እንደሆነ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ አስታውቆ፣ ለዚህም በ2009 ዓ.ም. የተመዘገበው ከፍተኛ የተሽከርካሪዎች አደጋ ዓብይ ምክንያት እንደነበር አስታውቋል፡፡ በሞተር ኢንሹራንስ የተመዘገበው የ8.5 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ምክንያት ሆኗል፡፡

የቡና ኢንሹራንስ ጠቅላላ ሀብት በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረው 170.1 ሚሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም. ወደ 224.9 ሚሊዮን ብር ማደጉን የሚጠቅሰው የኩባንያው ሪፖርት፣ በአንፃሩ የኩባንያው ዕዳ 150.6 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ አመላክቷል፡፡

ቡና ኢንሹራንስ እስከ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያስመዘገበው የዕዳ መጠን 150.6 ሚሊዮን ብር የደረሰበት ዋና ምክንያት በእንጥልጥል ላይ የሚገኙ የካሳ ጥያቄዎች፣ ለጠለፋ ዋስትና የሚከፈሉና ጊዜያቸው ላበቃ የዋስትና ሽፋኖች የተያዙ መጠባበቂያዎች ክምችት በመኖሩ ሳቢያ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የኩባንያው የተጣራ ሀብት 74.2 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኩባንያው ኢንቨስትመንቶችን በተመለከተ በሪፖርቱ እንደተካተተው በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ያለውን የአክሲዮን ድርሻ ወደ 37.5 ሚሊዮን ብር ከፍ ማድረጉ አንዱ ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. የ16.5 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ከባንኩ ገዝቷል፡፡ ከእህት ኩባንያው ከገዛቸው አክሲዮኖች በተጨማሪ አሥር ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ከዓባይ ኢንዱስትሪ አክሲዮኖች ማኅበር አክሲዮኖችን ለመግዛት የተስማማ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 25 በመቶውን ወይም የ2.5 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙንም አስታውቋል፡፡

እንዲህ ያሉ ክንውኖችን ያሳለፈው ቡና ኢንሹራንስ፣ በ2009 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 7.1 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ይህ ትርፍ በ2008 ዓ.ም. ከነበረው የ1.1 ሚሊዮን ብር አንፃር የተሻለ እንደነበር አሳይቷል፡፡

ሉሲ ኢንሹራንስ በበኩሉ በ2009 ዓ.ም. 13.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዘገቡን ገልጿል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2008 ዓ.ም. አኳያ በ676 ሺሕ ብር ብቻ ብልጫ አለው፡፡

ቡና ኢንሹራንስ ግንቦት 2005 ዓ.ም. በ237 ባለአክሲዮኖች በ6.7 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሕይወት ነክ ያልሆኑ የዋስትና ዓይነቶችን በመስጠት ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በአሁን ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን 78.8 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የተፈቀደ ካፒታሉ 100 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ የሉሲ ኢንሹራንስ ኩባንያ የተከፈለ ካፒታል 99 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች