Saturday, April 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰማዕታት ሐውልት ግንባታ መለኪያው ምንድነው?

በመንግሥቱ መስፍን

በዚህ ርዕስ ላይ እንደ ተቆርቋሪ ዜጋ ሐሳብ መሰንዘር የፈለግኩት ጉዳዩ በአገራችን ተደጋግሞ ሲነገርና ሲተገበር በማስተዋሌ ነው፡፡ ጉዳዩን አጀንዳ አድርገን ሐሳብ ብንለዋወጥበትም የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ በታሪክም ሆነ በፖለቲካ ውዝግባችን ውስጥ እየጐላ የመጣ አጀንዳም ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ሐውልት ይቀረፃል፣ በሁነኛ ቦታም ለመታሰቢያነት ይቀመጣል፡፡ በየጊዜው በሚዘከር በዓልም እንዲታወስ ከትውልድ ትውልድ በሐውልቱ ላይ የተቀረፀው ምሳሌ (Symbol) ይታወሳል፡፡ ሐውልት የሚቀረፅላቸው ሰዎች የአገር፣ የሃይማኖት ወይም የጦር መሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በአንዳንድ የታደሉ ማኅበረሰቦች በሳል ምሁራንና የፈጠራ ሰዎች ሐውልት ይቆምላቸዋል፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ከጥንት ጀምሮ ለአገርና መሪዎችና ለባለውለታዎች ሐውልት ማስቀረፅና ማቆም ያለና የነበረ ቢሆንም፣ በአብዛኛው በሕይወት ካሉት ይልቅ ለሙታን የሚቆሙ ሐውልቶች ይበዛሉ፡፡ በአደባባይ ሐውልት የቆመላቸው መሪዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሐውልት ማቆም በቋሚ ሕግና ሥርዓት የሚመራ፣ በሕዝብ አስተያየት የሚዳብር፣ በምሁራን ትችትና ውይይት የሚፀድቅ አልመስል እያለ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ የቅርስ ጥበቃ መሥሪያ ቤቶች፣ የባህልና ቱሪዝም አካላት አልያም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መሰል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚመክሩበትም አልሆነም፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚናገሩት በሕዝብ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች እንኳን መክረው ሳይግባቡበት፣ በፖለቲካ ፍላጐት ብቻ በጥቂት የገዥው ፓርቲ (የየብሔራዊ ድርጅቶቹ) መሪዎች የሚወሰንና ከፍተኛ የአገር ሀብት እየፈሰሰበት የሚቆም ሆኗል፡፡

የውሳኔውና የበጀቱ ጉዳይ ብዙም ላያስጨንቅ ቢችል እንኳን፣ የሐውልቶቹ መቆም ለአገር ምን ፋይዳ አለው? ለቀጣዩ ትውልድ የሚቆይለትስ ምንድነው? ብሎ ማመዛዘን ላይ በጥልቅት እየተፈተሸም አይደለም፡፡

በአገራችን ታሪክ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ በእርስ በርስ ግጭትም ሆነ በፖለቲካ አለመግባባት በርካታ ዜጐች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ እነዚህን ወገኖች በመዘከር ደግሞ መቻቻል የሌለበት ፖለቲካ እንዳይከሰት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት እንዳይሰፍን፣ መከባበርና መፋቀር እንዲሰፍን ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡ ምንም ያህል አንዱ ወጊ ሌላው ተወጊ፣ አንዱ አጥቂ ሌላኛው ተጠቂ ወይም እርስ በርስ ተቃዋሚ መሆኑ ቢታወቅም ሁሉንም ያማከለ ታሪክ ገላጭ ሐውልት መቀመጡ ቢያንስ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመ ሁነት በመሆኑ ‹‹ይሁን!›› ሊባል ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር ይህም ቢሆን በነጭ ሽብርም እንበለው በቀይ ሽብር ወገንም ሳይወዱ በግድ ወይም ፈቅደው ገብተውም መስዋዕት የሆኑ የዚህች አገር ዜጐችንም ታሳቢ የሚያደርግ ካልሆነ የተሟላ ነው ሊባል አይችልም፡፡

አንዳንዶች በእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸመን መተላለቅ ለማሰብ ሐውልት የመቆሙን ተገቢነት ቢያምኑም፣ መብዛትና መጋጋል የለበትም ባይ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ በብዙ አገሮች ከውጭ ጠላትና ከወረራ ጋር በተደረገ ተጋድሎ መስዋዕት ለሆኑ ዜጐች (መሪዎች) ማቆም ትክክል ነው ይላሉ፡፡ ለአብነትም በአገራችን የጣሊያን ፋሽስት ወራሪ ኃይል በንፁኃን ላይ የፈጸመውን ግፍ ለማሰብ እንደቆሙ ሐውልቶች ማለት ነው፡፡ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ ለሶማሊያ ወረራ መካች ሠራዊት አባላት፣ ወዘተ እንደተተከሉት የድልና የሰማዕታት ሐውልቶች፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየሆነ ያለው ግን ከዘመናዊ ኢትዮጵያ (ከ1950 እስካሁን) ታሪክ በፊት የነበሩ ክስተቶችን መምዘዝ እየታየ ነው፡፡ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን እየሰማን እንዳለው የአፄ ምንሊክ ጦር ባደረገው የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎች (ሰማዕታት) የሐውልት ግንባታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ግንባታው ተጠናክሮ እየቀጠለ መስሏል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ወሬው ወደ አደባባይ የወጣው የአርሲው አኖሌ ግዙፍ ሐውልት አወዛጋቢነት ገና ሳይቋጭ፣ 34 ሚሊዮን ብር የወጣበት የሐረር ጨለንቆ የሰማዕታት ሐውልት እንደሚመረቅ ሰምተናል፡፡ በሐረር ከተማና በጅግጅጋ እየተገነቡ ያሉ ሐውልቶችም አሉ ይባላል፡፡

እዚህ ላይ ግልጽ እንዲሆን የምሻው ንፁኃን የወላይታ፣ የሲዳማ፣ የከፋ፣ ብሔረሰቦች አባላት አልሞቱም የሚል መነሻ እንደሌለኝ ነው፡፡ ነገር ግን ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ሥልጣኔ ሳይኖር የተፈጸመ የእርስ በርስ ጦርነት እንደነበር መዘንጋት የለበትም፡፡ እውነቱ የጦርነት ታሪክ ሆኖ ሳለ ከአስገባሪው ወገን የተሰው ዜጐች (ወታደሮች) በኩልም ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው እንደረገፉ በየታሪክ ድርሳናቱ ሠፍሮ ይገኛል፡፡

ከሁሉም በላይ እነዚያ ለሺሕ ዓመታት የዘለቁ የእርስ በርስ ጦርነቶች በገዥዎች ጋሻ ጃግሬነት ሲፈጸሙ፣ በሌላው ዓለምም ተመሳሳይ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሠለጠነ በሚባለው አውሮፓ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ እነ ቻይና፣ አሜሪካና የላቲን ሕዝቦችም በዚሁ ታሪክ ውስጥ አልፈዋል፡፡ ሁሉም ነገር ታልፎ ግን ዛሬ ዓለም ላይ ወደ 200 የሚጠጉ የየራሳቸው ሉዓላዊ ግዛት ያላቸው አገሮች መፈጠራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በታላቋ አገራችን ውስጥ ከጥንት እስከዛሬ ለተፈጸመው ግፍና በደል ሐውልት እንሥራ ብለን ብንነሳሳ መቆሚያው የት ሊሆን ይችላል? አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ ‹‹ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፋቸው ገጽ 33 ላይ እንዲህ አቅርበዋል፡፡

‹‹አፄ ቴዎድሮስ የጐጃም ገዥ ደጃች ተድላ ጓሉ ከመሞታቸው በፊት ሸፍተው ስለነበር ከእሳቸው ጦር የተማረከውንና እሳቸውን ተቀብሎ አስተናግዷል የተባለውን አገር ሕዝቡን ሰብስበው እጅና እግሩን እየቆረጡ ፈጁት፡፡ ከመቅደላ የምንሊክን ማምለጥ እንደሰሙ የታሰሩትን የወሎ መኳንንቶችና የወ/ሮ ወርቂትን ልጅ አምጡልኝ ብለው እግርና እጃቸውን እየቆረጡ ገደል ያስጥሏቸው ጀመር፡፡ ወደ ዘጌም በሄዱ ጊዜ የባላገሩን ቤት እየበረበሩ ዕቃው ተዘርፎ ሲያልቅ፣ በጓሮ ያለውን አትክልት እየጨፈጨፉ እንዳይበቅል ከሥሩ አስነቀሉ፡፡ ቁሙንም ከብት ከበጌምድር ባላገር ዘርፈው ደብረ ታቦር አምጥተው ለወታደሮቻቸው አከፋፈሉት፡፡ ደግሞ የሜጫና የአገው መኳንንት የክህደት ነገር ተገኝቶባቸው አራት መቶ የሚሆኑ ተይዘው እህልና ውኃ ሳያገኙ እንዲያልቁ አደረጉ፡፡››

እንግዲህ በአንድ አካባቢ የወረደን መዓትና የተፈጸመን አረመኔነት እንመልከት፡፡ ግን ያለፈ ዘግናኝ ታሪክ ነውና ከታሪክ ድርሳንነት ባለፈ ሐውልት እያቆምን ‹‹ሰማዕታቱን›› እንዘክር ቢባል እንዴት ሊሆን ይችላል? ተወላጅነታቸው ከጐንደር የሆኑት አፄ ቴዎድሮስ ጐንደሬውን፣ ጎጃሜውን፣ አገውን፣ ወለዬውን፣ ትግሬውን፣ ሸዋውን ምን ያህል እንደጨፈጨፉት አይዘነጋም፡፡ ስንት ቦታ ሐውልት ሊቆምስ ይችላል!?

በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ዘመነ መሳፍንት ያለ እርስ በርስ የተባላንበት የታሪክ ሁነት የለም፡፡ ያ አያት ቅድመ አያቶቻችን ባልሠለጠነ ዘመን የከፈሉት መስዋዕትነት ዘር ሳይለይ በአገዛዞች ጭካኔና ጭፍንነት የከፈሉት ዋጋ ነው፡፡ አፄ ዮሐንስ በትግራይ፣ በወሎ፣ በሸዋ፣ በጐጃምና በጐንደር ዘምተዋል፡፡ በጦርነት ውስጥ በየአካባቢው ሰዎች ረግፈዋል፡፡ ሀብት ንብረት ወድሟል፡፡ የጐንደር ነገሥታት የዛሬዎቹ ደቡብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ አካባቢዎች አይውረዱ እንጂ ስንት የእርስ በርስ ፍጅት አድርሰዋል፡፡ በደቡብም የጊቤ ነገሥታት፣ የወላይታ፣ የሊሙ፣ የኢናሪያ፣ ወዘተ ገዥዎች እንዴት ያለ ጦርነትና የሕዝብ ዕልቂት በሥልጣን ሽሚያና ግዛት ማስፋፋት ስም ይፈጽሙ እንደነበር አይታወቅምን!?

ከዚህ ሁሉ አስጸያፊ ድርጊት በኋላ ግን በዓለም በነበረው የኃይል አማራጭም ተጉዘን ቢሆን የዛሬዋ ኢትዮጵያ ‹‹አገር›› መሆን ከቻለች፣ ቢያንስ አንድ ምዕተ ዓመት አሳልፈናል፡፡ ወደኋላ ተመልሰን ያንን አስጸያፊና አሳፋሪ ታሪክ በመምዘዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ሐውልት መቅረፁስ ምን ሊፈይድና ሊረባ ይችላል?

በነገራችን ላይ ከደቡብና ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ወደ መሀልና ሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄዱ ዘመቻዎች ያደረሱት የሕዝብ ዕልቂትም የታሪካችን አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ አንዱን አብነት ብንጠቅስ ከአዳልና ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የተነሳው ግራኝ መሐመድን ማስታወስ ይቻላል፡፡ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከላይ በጠቆምኳቸው ቦታዎች ጦር ደግነው የተከላከሉትን ወታደሮችና ገዥዎች ብቻ ደምስሶ አላቆመም፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በተለይ የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስትና አማኞችን እያረደና እየጨፈጨፈ ኢትዮጵያን ለስምንት ዓመታት ቀጥቅጦ አልገዛም እንዴ? ገዳማት፣ መነኮሳትና አድባራት እንዳይሆኑ ተደርገው የጠፉት መቼ ነው? ለዚህስ የትኛው አካባቢ ሐውልት ቆመ? ሙታኑስ መቼ ‹‹ሰማዕታት›› ተብለው ታወሱ?

የኢትዮጵያን አዳፋ ታሪክ መዝዤ ልዘርዝረው ብል የጋዜጣ ገጽም ሊበቃኝ አይችልም፡፡ እውነቱን ለማንሳት ያህል ግን በቂ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ከምንሊክ ጋር በተያያዘ እየወጣ ያለው አዲስ የሚመስል ታሪክና የሰማዕታት ሐውልት ቀረፃ ሥራው እንደምን ሊስፋፋና ሊጠናከር ቻለ? በተለይ ዛሬ በአገራችን ያሉት ብሔረሰቦች ተከባብረውና እኩል ሆነው መኖር በጀመሩበት ጊዜ፣ ዜጐች በቋንቋቸው መማርም ሆነ መዳኘት እንዲሁም በራሳቸው አብራክ ክፋዮች በሚተዳደሩበት አዲስ ምዕራፍ፣ ቁስል ማከክና ንትርክ መምዘዝ ለምን ተፈለገ ብሎ መጠየቅ ጤና ማጣት አይመስለኝም፡፡

አንዳንድ ተቃዋሚዎችና ምሁራን ‹‹በኢትዮጵያ ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት መፈጠር አለበት፤›› ሲሉ እምብዛም ትኩረት አልሰጠውም ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ግን እጅግ አስፈላጊና ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን የዛሬው ትውልድ ሊያጤነው ይገባል፡፡ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የመሰሉ አገራዊ ፕሮጀክቶች መላው ኢትዮጵያውያን ተረባርበውና ተረዳድተው እየገነቡ ነው፡፡ በመንገድ፣ በውኃ፣ በኤሌክትሪክ፣ በስልክ፣ ከአንድ ቋት የሚጠቀሙና የተሳሰሩም ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ወደኋላ ተመልሶ ለመነጣጠልና ለመቃቃር በር የሚከፍት ድርጊት ውስጥ መግባት በየትኛውም መንገድ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

‹‹በሰማዕታት ሐውልት›› ግንባታ ላይ ከአንዳንድ የኢሕአዴግ ሰዎችና መለስተኛ ባለሥልጣናት ጋር የመወያየት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በእውነቱ ብዙዎች እንደማያምኑበትና በጉዳዩ ላይም ግልጽ ዕውቀት እንደሌላቸው ነው ያረጋገጥኩት፡፡ ተገቢነት የሌለውና ለመጭው ጊዜ ሥጋት የሚያጭር ተግባር መሆኑንም የሚያስረዱ አሉ፡፡

ለምሳሌ ደርግ ጨፍጫፊ ነው፡፡ በርካታ ንፁኃንን ፈጅቷል፡፡ በዚያ የታሪክ አጋጣሚ የተሰው ዜጐችን ለማሰብ ሐውልት ቢገነባ ቢያንስ ደርግ የሚባል አጥፊ ቡድን ጣት ይቀስርበታል፡፡ ይህም ቢሆን በብሔራዊ ዕርቅ መታገዝ ያለበት ቢሆንም ቢያንስ በደርግ ውስጥ በማወቅም ባለማወቅም የነበሩ በዳዮች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ በመሆናቸው፣ መገለሉ በብሔርና በሠፈር ሊሆን አይችልም፡፡ ደርግና የደርግ ሥርዓት ጋሻ ጃግሬዎች የታሪክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በቀድሞዎቹ የአፄዎቹ ሁኔታ ግን ወታደሮችና ተዋጊዎች የሚመለመሉት ከወጡበት ማኅበረሰብ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ጐንደሬ ዘማች፣ የአፄ ዮሐንስ የትግራይ ታጣቂ፣ የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጐጃሜ ገበሬ፣ የአፄ ምንሊክም ይበልጥ የሸዋው አርሶ አደር ዘማች የበዛበት ነው፡፡ ንጉሥ ጦና፣ አባ ጅፋርም ሆኑ ጎበና ዳጨው ከወላይታ፣ ከጅማና ከወለጋ (በቅደም ተከተላቸው) ወታደር መልምለው አስታጠቀው ነው የዘመቱት፡፡

ይህ በመሆኑ ደግሞ በየዘመኑ ለነበሩት ጭፍጭፋዎች ገዥዎቹንና ሥርዓቶቹን ብቻ ኮንነን ልንቆም አንችልም፡፡ ይልቁንም በታሪክ አጋጣሚ ለዘመናት ተዋህዶና ተወልዶ የነበረውን ሕዝብ አንተ የእገሌ ወገን፣ የዚያኛው ወታደር (ነፍጠኛ) የልጅ ልጅ ወደሚል ቅያሜና መቃቃር ይሄዳል፡፡ እየተሻሻለ በመጣው አብሮነት ውስጥ የልዩነት በር ሊከፍት አይችልም ብሎ ማሰብም ያስቸግራል፡፡

መከራከሪያ ነጥቤን ለማጠናከር ባለፈው ዓመት የአኖሌ ሐውልት ጉዳት ሲነሳ በየአካባቢው የታየውን ሁኔታ ላስታውስ፡፡ ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ…›› እንዲሉ ወትሮም የፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠረውን ሁኔታ ተጠቅመው መነጠልና ሌሎችን ‹‹ውጡልን›› ማለት የሚቀናቸው ጠባቦች በየአካባቢው ፀብ ጭረዋል፡፡ ዜጐችን አፈናቅለው የሕይወት ሕልፈትም አጋጥሟል፡፡

በባህር ዳር የስፖርት ፌስቲቫል ወቅት አንዳንድ ባለጌዎችና ፍርፋሪ የፖለቲካ ትርፍ ለመለቃቀም የተመኙ ሰዎች በፈጠሩት ፀብ በርካታ ኢትዮጵያውያን አዝነዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች (ሱሉልታ፣ አምቦ፣ መቱና ደንቢዶሎ) የታየው ነገር ግን 25 ዓመታትም አልፎ መቆራቆሱ አለመቅረቱን ነው፡፡ በደቡብ፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልሎች በአብሮነት ለዓመታት ተከባብረውና ተዋልደው የኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች (በተለይ አማራ፣ ትግሬና ኦሮሞ) እንደ ባዕድና ወራሪ ታይተው የተፈጸመባቸው ያልተገባ ድርጊትም ውስጥ ውስጡን እያደገ በመጣ የታሪክ መፋለስ ምክንያትና መዘዝ መሆኑን መካድ ያስቸግራል፡፡

እዚህ ላይ መንግሥት ችግሩን ተገንዝቦ በራሱ መዋቅር ውስጥ ያሉ የጠባብነትም ሆነ የትምክህት አቀንቃኞችን እየለየ የእርምት ዕርምጃ መውሰዱን አይተናል፡፡ ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤት ሊያስቀጣ የሚችል ወንጀል እንደሆነና የመንግሥት ድጋፍ የሌለው ደባ መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ በትውልዱ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት፣ መቻቻልና መከባበር ሊገነባ ይገባል፡፡ ያለፈው ታሪክ ሁሉ ይረሳ፣ ይዘንጋ ባይባልም ያንን የታሪክ አተላ በድል ተሻግረን ወደ ሌላ ምዕራፍ በብቃት እየተጓዝን ያለን ሕዝቦች መሆኑ ላይ በስፋት መሥራት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እዚህ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ገለጻን ለምን መዘንጋት ተፈለገ ማለት እሻለሁ፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ውጣ ውረድና የገዥዎች ጭቆና አልፈዋል፡፡ አንዱ ማኅበረሰብ በስሙ እየተነገደ ከጭቆናና ከስቃይ ሳይወጣ፣ ሌሎችን ድርብ ጭቆና ውስጥ ለማስገባት መሣሪያ ሲደረግ ነበር፡፡ አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ በሚል ሽፋን የብዙዎች መብት ተገፏል፡፡ ያ የታሪክ ዕድል ግን በታላቅ የሕዝብ አብዮት ላይመለስ ተቀብሯል፡፡ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም የጋራ ፕሮጀክታቸው የሆነውን የህዳሴ ጉዞ በዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊነት መንፈስ ጀምረዋል፡፡ ይህንን ነባራዊ ሀቅ በመዘንጋት የኖረውን ቁስል በማከክ እንዲመረቅዝ የሚፈልጉ ወገኖች ከትምክህትና ከጥበት ያልተላቀቁ ኃይሎች ናቸው፡፡ በአቋራጭ ሥልጣንና ኪራይ ሰብሳቢነትን ማንገሥ የሚሹ መሆናቸውም ታውቆ በውስጥም በውጭም ትግል ማድረግ አለብን፤›› (ቃል በቃል ላይሆን ይችላል) በማለት በአንድ ልሳን ላይ ከትበውት ይገኛል፡፡

ይህ ሆኖ ሲያበቃ እየዋለ እያደር የሚመጣው ነገር እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ወደኋላ የሚመልስና የሚያነታርክም ተግባር ነው፡፡ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የታሪክና የቅርስ አብሮነታችንን ማሳየት ለምን እንፈራለን? የየማንነታችን ብሩህ መገለጫዎችን ማጉላትና ማድመቁስ ለምን ችላ ይባላል? ለ24 ዓመታት የተጻፉ አዳዲስ ታሪኮችን ትተን ያን አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ስናነበንብ የምንኖረውስ እስከመቼ ይሆን!? በእርግጥ ከብዙ መቅደቅ መነሳት በኋላ በዚህ ጊዜ የቆምንባት ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ያለፈው ውጣ ውረድ የጋራ ታሪክ ውጤት መሆኑን ቸል ለማለት ይቻላልን!? በማለት ጩኸቴን ላሰማ እወዳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

                      

     

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles