Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቫይታሚኖች የበለፀጉ የመኮረኒና ፓስታ ምርቶች ወደ ገበያ ሊገቡ ነው

በቫይታሚኖች የበለፀጉ የመኮረኒና ፓስታ ምርቶች ወደ ገበያ ሊገቡ ነው

ቀን:

በማዕድናት የበለፀገ የስንዴ ዱቄት መመረት ጀመረ

በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ኢትዮጵያውያን እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ ለመቀነስ ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የሆነውን የሥነ ምግብ ፕሮግራም ተከትሎ፣ አስትኮ ፉድ ኮምፕሌክስ በማዕድናትና በቫይታሚኖች የበለፀጉ የመኮረኒና ፓስታ ምርቶች ወደ ገበያ ሊያስገባ ነው፡፡

የአስትኮ የንግድ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ዋቅቶላ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቫይታሚንና በማዕድናት የበለፀገ የስንዴ ዱቄት መመረት የጀመረ ሲሆን በቅርቡ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ በቀጣይ በማዕድናትና ቫይታሚን የበለፀጉ የመኮረኒና የፓስታ ምርቶች ለገበያ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡

አቶ ፀጋዬ እንደሚሉት፣ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲና በፓርትነርስ ኢን ፉድ ሶሉሽን ቴክኖሰርቭ ትብብር የተመረተው የበለፀገ የስንዴ ዱቄት፣ በአከፋፋዮች በኩል ለኅብረተሰቡ እንዲዳረስ የሚደረግ ሲሆን፣ በሒደት ኅብረተሰቡ በቀጥታ መግዛት የሚጀምርበት ሥርዓት ይዘረጋል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ይፋ የሆነውና ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ኢትዮጵያ በማኅበራዊውና በኢኮኖሚያዊው ዘርፍ እየተጋፈጠች ያለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ የተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፣ የተመጣጠነ ምግብ ሳያገኝ ያደገ ሕፃን በትምህርትና በሥራ ዘመኑ ውጤታማ ስለማይሆን በአገሪቱ ላይ የሚፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከባድ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ከአምስት ሕፃናት ሁለቱ የቀነጨሩ (Stunted) ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ቁመታቸው ከዕድሜያቸው ጋር ሲነፃፀር ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ካስቀመጠው መጠን በታች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ 28 በመቶ የሚሆነው የሕፃናት ሞት የሚከሰተውም ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ በሚከሰት ሕመም ነው፡፡ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ በሕፃናት ላይ የሚከሰተው ሞትም የኢትዮጵያን አምራች ዜጋ 8 በመቶ ቀንሶታል፡፡ 

ሕፃናት አንድ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በሚያጋጥማቸው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ሕመሞችን ለማከም፣ አገሪቷ ለጤና ከምትመድበው 44 በመቶ ያህሉን ታወጣለች፡፡ 

ከትምህርት ጋር በተያያዘም 16 በመቶ የሚሆነው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን መድገም የሚከሰተው ከመቀንጨር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የቀነጨሩ ተማሪዎች ጤናማ አስተዳደግ ካላቸው ጋር በትምህርት ሲነፃፀሩ 1.1 ዓመት ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡   

ኢትዮጵያ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉታዊ ተፅእኖዎችን ለመጋፈጥ በዓመት 55.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የምታወጣ መሆኑንም ዳሰሳው አሳይቷል፡፡

ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ እየከፈሉ ያለውን ዋጋ ለመቀነስ በ2005 ዓ.ም. በአገር ደረጃ ብሔራዊ የሥነ ምግብ ፕሮግራም ይፋ ሆኗል፡፡ ፕሮግራሙ ካካተታቸው ነጥቦች ውስጥም ሕዝቡ በብዛት የሚጠቀማቸውን ምግቦች በንጥረ ነገር ማበልፀግ (fortification) ይገኝበታል፡፡ ስንዴና ዘይት ደግሞ በንጥረ ነገር ወይም በቫይታሚኖችና በማዕድናት እንዲበለፅጉ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

በማዕድናትና ቫይታሚኖች የበለፀገው የስንዴ ዱቄት ይፋ የተደረገው ማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በዮድ አቢሲኒያ በተደረገ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሆን፣ ይህም የሥነ ምግብ ፕሮግራሙን ለማሳካት አንድ ዕርምጃ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ ተናግረዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...