አሜሪካ ኤምባሲ ‹‹የሴቶች ታሪክ ወር››ን ምክንያት በማድረግ ለሴት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ውድድር ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ውድድሩ የሚያካትተው በሙያው ያሉ ፕሮፌሽናሎችንና እውቅና ባለው የሥነ ጥብብ ትምህርት ቤት በመማር ላይ የሚገኙ ሴቶችን ነው፡፡ የሴቶችን ሕይወት ለሚያንፀባርቁ ማንኛውም ዓይነት የሥነ ጥበብ ውጤት ክፍት ነው፡፡
በፕሮፌሽናል ሠዓልያን ዘርፍ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የሚወጡ የ40,000፣ የ20,000 እና የ10,000 ብር ሽልማት ያገኛሉ፡፡ ተማሪዎች እንደየደረጃቸው 10,000፣ 7,000ና 5,000 ብር ይሸለማሉ፡፡ ከፍተኛ ደረጃ አግኝተው የሚያጠናቅቁ ሥራዎች በአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም የአሜሪካ ማዕከል በሚገኝባቸው ባህርዳር፣ ድሬዳዋ፣ ሐረርና ጅማ ለእይታ ይቀርባሉ፡፡
የዘንድሮው የሴቶች ታሪክ ወር እየተከበረ ያለው ‹‹ሜክ ኢት ሀፕን›› በሚል መሪ ቃል ሲሆን፣ ወሩን ታሳቢ በማድረግ የሴቶች የሥነ ጥበብ ውድድር ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪሺያ ሀስላክ መጋቢት 8፣ 2007 ዓ.ም. በኤምባሲው ስለ ውድድሩ ባሳወቁበት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ውድድሩ ኢትዮጵያውያት በሥነ ጥበብ ዘርፍ ያላቸውን ስፍራ ለማሳደግና ለማበረታታት ያለመ ነው፡፡ መሰል ውድድሮች ከሚኖራቸው ጠቀሜታ አንፃር በየዓመቱ የሚሰናዳበትን መንገድ እንደሚያመቻቹም አክለዋል፡፡
አምባሳደሯ የአሸናፊዎችን ሥራዎች የሚያሳየው ዐውደ ርዕይ (ሚያዝያ 15 በኤምባሲው የሚከፈት) የሴቶች ታሪክ ወር ክብረ በዓል አንዱ መገለጫ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ከሥነ ጥበብ በተጓዳኝ ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚጫወቱት ሚና ጎልቶ እንዲታይ፣ እንዲማሩ፣ በተለያየ የሥራ መስክ እንዲሰማሩና መብታቸውን እንዲያስከብሩ ኤምባሲው የድርሻውን ይወጣል ብለዋል፡፡
የውድድሩ አስተባባሪና አርት ኪውሬተር ዶ/ር ደስታ መጐ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሥነ ጥበቡ ዘርፍ ሴቶች በተገቢ መልኩ ቦታ ተሰጥቷቸው ተሳታፊ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ በመሆኑም ውድድሩ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ያሉ ሴት ባለሙያዎችን በማሳተፍ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ‹‹ውድድሩ ሴቶችን ከመደገፍ ባሻገር ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት መድረክ ይከፍትላቸዋል፡፡ በሴት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች መሀከል ትስስርም ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡
ውድድሩ ሥዕል፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ኢንስታሌሽን፣ ቪዲዮ አርትና ሌሎችም ቪዥዋል አርት የሆኑትን ያካትታል፡፡ ውድድሩ ይፋ ከሆነበት ዕለት ጀምሮ ተወዳዳሪዎች አንድ ወይም ሁለት ሥራ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ውድድሩ የሚያካትተው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩና ኢትዮጵያዊያት ሠዓልያንን ብቻ ሲሆን፣ ሥራዎቻቸው የሚዳኙት በኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ይሆናል፡፡
ሌላዋ የውድድሩ አስተባባሪ ማርጋሬት ናጋዋ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎች በብዛት አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ጋለሪዎች በመቅረብ የተወሰኑ በመሆኑ፣ ዐውደ ርዕዩ በተለያዩ ከተሞች እየዞረ ባለሙያዎቹን የሚያስተዋውቅ ይሆናል፡፡ ዐውድ ርዕዩን ‹‹በተለይም ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ የወደፊት ተስፋ ለሆኑ ወጣት ባለሙያዎች ትልቅ ዕድል ነው፤›› በማለትም አመልክተዋል፡፡
ማርጋሬት እንደምትለው፣ በሴቶች ወር በሚደረገው እንቅስቃሴ ለሴቶች ትኩረት እንዲሰጥ መገፋፋቱ ከሥነ ጥብብ ባለፈ በሌሎችም ዘርፎች የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡ ሴቶች ለሥራዎቻቸው እውቅና እንዲሰጣቸውም ያግዛል፡፡ ሠዓሊት ደስታ ሐጎስም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥታለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴት የሥነ ጥብበ ባለሙያዎች እንደማይበረታቱና ችሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክም ጠባብ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ ውድድሩ የአንጋፋዎቹንም ሆነ አማተሮችን ጥበባዊ ውጤት አሳይቶ ‹‹ሴቶች መሥራት ይችላሉ፤›› የሚል መልዕክት ያለው ነው ብላለች፡፡
‹‹የሴቶች ታሪክ ወር›› ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሚከበርበት ማርች ወር (የካቲት 22 እስከ መጋቢት 22) የሚከበር ነው፡፡ በየዓመቱ ሴቶችን ማብቃትና በማኅበረሰቡ ያላቸውን ሚና ማንፀባረቅ ዓላማቸው ያደረጉ ክንውኖችን ያስተናግዳል፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ ኤምባሲ አሜሪካዊቷን አርቲስት ማያ ቴሬስ ከኢትዮጵያውያት የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር አገናኝቶ ነበር፡፡ ማያ ‹‹ሁ ዳዝ ሺ ቲንክ ሺ ኢዝ›› የተሰኘና አሜሪካውያት ባለሙያዎች የሚገጥማቸውን ውጣ ወረድ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም አሳይታለች፡፡
ከኢትዮጵያ ሴት ሠዓልያን ማኅበር አባላትና ሌሎችም ባለሙያዎች ጋር ኢትዮጵያውያን በዘርፉ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ተወያይተው ነበር፡፡ ከሳምንታት በፊት የጥቁር ታሪክ ወርን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ጋለሪ የአሜሪካውያት ሥራዎች ለዕይታ መብቃታቸው ይታወሳል፡፡