Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየሴቶች ቀን ድሮና ዘንድሮ

የሴቶች ቀን ድሮና ዘንድሮ

ቀን:

የዓለም ሴቶች ቀን በየዓመቱ በውጮቹ አቆጣጠር ማርች 8፣ በኢትዮጵያ የካቲት 29 እየተከበረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ1967 ዓ.ም. ወዲህ በየዓመቱ እያከበረችው ሲሆን፣ እንደወቅቱ ርዕዮተ ዓለም ፖስተሮች ሲዘጋጁለት ኖሯል፡፡ ከ36 ዓመት በፊት (1971 ዓ.ም.) በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ዘመን፣ በአዲስ አበባ የዓለም ሴቶች ቀንን ለማክበር የተሠራጨውን (በግራ) እና ዘንድሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በፖስተርና በፖስት ካርድ መልክ ያሳተመውንና ያሠራጨው እዚህ ላይ ይመለከቷል፡፡ (ሔኖክ መደብር)

******************

የሚሆነው ሁሉ ይሁን

እኛን ሲውጠን መከራ

አዎ እናንተማ ዝለሉ ከበሮ ምቱ ዳንኪራ

ቁረጡ ጮማና ጎድን ተራጩ ውስኪና ቢራ

    እሰይ! እናንተ ዝፈኑ ድምፃችሁ

               ያምራል ቆንጆ ነው!!

      እዬዩ ዋይታው ለእኛ ነው

      ሳቁ! ቦርቁ! ፈንድቁ!

      ከአበባና ከጨረቃ፣ ከኮከብ በላይ ድመቁ

      እሬሳችን ላይ ደንሱ አጥንታችንን አድቅቁ

እናንተ ብሉ፣ ጥገቡ፣ ተራጩ ውስኪና ቢራ

እኛ በረሃብ እንሙት ስቃይ እንግልት እናውራ

የእናንተ ሕይወት ይታደስ

የእኛ እንባ ግዴለም ይፍሰስ

የእናንተ ኑሮ ጣፈጠ

የእኛ ዓለምን ግን ኮመጠጠ

    እናንተ ወርቆች፣ አልማዞች

    እኛ ገለባ – እንክርዳዶች

    ይህ ሁሉ ይሁን እንደሻው

             ይሁን የሚሆን በሞላ

ያቺ ቀን እስክትመጣ ያቺ ጽዋ እስክትሞላ

  • ሰሎሞን ሞገስ ‹‹ከፀሐይ በታች›› (2004)

***********

የደኑ ድምፅ

በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቻይናው ንጉስ ፃኦ ልዑል ታይን ታላቁ መምህር ፓንኩ ከሚገኝበት መቅደስ ሄዶ ይማር ዘንድ ላከው። ልዑል ታይ በአባቱ እግር የሚተካ በመሆኑ ለጥሩ አመራር አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ረቦች ወይም ዕውቀቶች ታላቁ መምህር እንዲያስተምረው ሲል። ልዑል ታይ ከመቅደሱ እንደደረሰ ታላቁ መምህር ወደ ሚንግሊ ደን ላከው። ከአንድ ዓመት በኋላ ልዑሉ እንዲመለስና ደኑ ውስጥ የሰማውን ድምፅ ሁሉ እንዲያስረዳው ነግሮ።

ልዑል ታይ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲመለስ መምህር ፓንኩ እደኑ ውስጥ የሰማውን ሁሉ እንዲገልጽለት ጠየቀው። ‹‹መምህር ሆይ›› አለ ልዑል ታይ ‹‹የዋኔዎችን ኩኩታ፣ የቅጠሎችን ሻሻታ፣ የወፎችን ጫጫታ፣ የፌንጣዎችን ጭርጭርታ፣ የሳሮችን እሽታ፣ የንቦችን ጥዝጥዝታ፣ የንፋሱን ሽውታ፣ ሹክሹክታና ሁካታ ሰማሁ። ‹‹ሲል አስረዳ። ልዑሉ ገለጻውን ማብቃቱን እንደተረዳ ወደ ደኑ ተመልሶ ተጨማሪ እንዲያዳምጥ መምህር ፓንኩ አዘዘው። ልሁሉም ግራ ተጋባ። ‹‹ደኑ ውስጥ ያሉትን ድምፆች አላዳመጥኩምና ነው እንደገና የሚልኩኝ።›› ሲል ተከዘ። ሆኖም ወደ ደኑ ተመልሶ ሄደ።

ለብዙ መዓልትና ሌሊት በደኑ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ማዳመጡን ቀጠለ። ነገር ግን ከዚህ በፊት ከሰማው ሌላ የሚሰማው አልነበረም። አንድ ቀን ጧት አንድ ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ ከዚያን ዕለት በፊት ከሰማው ለየት ያለ ርቅቀ፡ ድቅቅ ያለ ድምፅ ተሰማው። ጆሮውንም፡ አእምሮውንም አቅንቶ ሲያዳምጥ ድምፁ ጉልህ እየሆነ መጣ። አንድ ነገር የተገለጠለት መሆኑን ተረዳ። ‹‹መምህር ወደዚህ የላኩኝ ይህንን የመሰለ ድምፅ እንዳዳምጥ ሳይሆን አይቀርም።›› ሲል ገመተ።

ልዑል ታይ ወደ መቅደሱ እንደተመለሰ ታላቁ መምህር በተጨማሪ ምን እንደሰማ እንዲነግረው ጠየቀው። ‹‹መምህር ሆይ›› አለ በትህትና እራሱን ዝቅ አድርጎ ‹‹አእምሮዬን ከፍቼ፣ ጆሮዬን አቅንቼ ሳዳምጥ የማይሰማውን ሰማሁ። የሰማሁትም አበቦች ሲፈኩ፣ ጸሐይ ምድርን ስታሞቅ፣ ሣሮች የጠዋቱን ጤዛ ውኃ ሲጠጡ ነበር። ‹‹አለው። መምህሩም ራሱን በእርካታ ነቀነቀና” ጥሩ ተገንዝበሀል። ‹‹አለው።›› የማይሰማውን መስማት ጥሩ መሪ ለመሆን አስፈላጊ ረብ ወይም ሥርዓት ነው።

አንድ መሪ የሕዝቦቹን ልቦና ሲያዳምጥ፣ ያልተገለጸ ስሜታቸውን ሲረዳ፣ ይፋ ያልወጣ ጭንቀታቸውንና ቅሬታቸውን ተገነዝቦ መፍትሔ ሲፈልግ፣ አንድ ነገር መጓደሉን ሲገነዘብና ለዜጎቹ እውነተኛ ፍላጎት መሟላት ሲጥር ብቻ ነው የሕዝቦቹን አመኔታ ሊያገኝ የሚችለው። የአንድ አገር ውድቀት የሚመጣው መሪዎች ቃላትን ብቻ ሲያዳምጡና የዜጎቻቸውን ሐሳብ፣ ስሜትና ፍላጎት ጠልቀው መገንዘብ ሲሳናቸው ነው።›› ሲል አብራራለት።

  • ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው ‹‹ቡክስ ፎር ኦል›› (2007)

 

*******

90 ዓመታት የፈጀ መዝገበ ቃላት

አንድ ጣሊያናዊ አሳሽ እ.ኤ.አ. በ1621 ፐርሴፖሊስ በምትባል በጥንቷ ፋርስ የምትገኝ ከተማ ፍርስራሽ ውስጥ በማይታወቁ ፊደላት የተጻፈ ጽሑፍ አገኘ። በ1800ዎቹ ዓመታት ደግሞ በኢራቅ የመሬት ቁፋሮ ያካሄዱ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ በሸክላ ጽላቶችና በቤተ መንግሥት ግድግዳዎች ላይ የተቀረጹ በርካታ ጽሑፎች አገኙ፤ እነዚህ ጽሑፎች ጣሊያናዊው አሳሽ ካገኘው ጋር በሚመሳሰሉ ፊደላት የተጻፉ ነበሩ። ጽሑፎቹ የተዘጋጁት እንደ ዳግማዊ ሳርጎን፣ ሃሙራቢና ዳግማዊ ናቡከደነፆር ያሉ ገዥዎች ይጠቀሙባቸው በነበሩ የሜሶጶጣሚያ ቋንቋዎች ነው። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉት ፊደላት ኪዩኒፎርም የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

የጥንቷን ሜሶጶጣሚያ ታላላቅ ሥልጣኔዎች ለማወቅ እነዚህን ጽሑፎች መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህም ምክንያት የእነዚህን ሰነዶች ትርጉም ለማወቅ የሚጥሩት ምሁራን፣ የአካድ ቋንቋ አጠቃላይ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘቡ፤ ይህ ቋንቋ ከአሦርና ከባቢሎን ቋንቋዎች ጋር በጣም ይቀራረባል።

ጄ ደብሊው ዶት ኦርግ በድረ ገጹ እንደዘገው፣ ይህንን ተፈታታኝ ሥራ ያከናወነው በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የምሥራቃዊ አገሮች ጥናት ተቋም ነው፤ ሥራው የተጀመረው በ1921 ሲሆን ከ90 ዓመታት በኋላ ማለትም በ2011 ተጠናቅቋል።

በ26 ጥራዞች የተዘጋጀውና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ የአሦር ቋንቋ መዝገበ ቃላት 9,700 ገጾች አሉት። መዝገበ ቃላቱ ከ2500 ዓ.ዓ. ጀምሮ እስከ 100 ዓ.ም. በሶርያ፣ በቱርክ፣ በኢራቅና በኢራን ይነገሩ የነበሩትን ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ያካትታል።

******

ጠጅ ስትጠጅ

ጠጅ ስትጠጅ ውኃውን በማር አጣፈጠችው ማሩንም በጌሾ አመረረችው በሌላም ሥርና ቅጠል አስቈጣችው፡፡ ጠጅ ተቈጣ የማን ራስ ሊከሰክስ ይሆን? ጠጁ የመላበትም የብርሌው መልክ ቅርፊት የሌለው የሚዋጥና የሚገመጥ ብርቱካን መስሎ ተደረደረ፡፡ የማን ልብ ሊማርክ ይሆን? ጠጅ ያማረው ጐበዝ መንገዱን ሰብሮ ጉዳዩን ትቶ ገብቶ ሲጠጣ ንግግሯን እንደ ውኃው ማር ስታልሰው ባለጠጂቱን ሰማት፡፡ በጠጅ ቁጣ ዓይኖቹን ለጋ ደመና እንደፈነጠቀበት እንደ ማታ ሰማይ ያቅላላው ጐበዝ ገንዘብንና ጤንነትን በፍጹም ናቀ፡፡ የጠጁ ስሜት ልግስናን አስተማረው፡፡ በፍጻሜው ከሬት የሚመረውን ማር ለመቁረጥ ወደ ቀፎው ሲመለከት ንብ ነደፈችው፡፡

*************

የራበው ዓይን የለውም

የፍየል ዓይን ወደ ቅጠል ሲመለከት የነብር ዓይን ወደ ፍየል እንደሚመለከት ፍየል አላየም፡፡ ተርቦ ሳለ የሚዋጥ ፍሬ ከወጥመድ ውስጥ ሲያይ ወጥመዱን አልተመለከተም፡፡ ያ የራበው ጐበዝ አገኘሁ ብሎ ፍሬውን ሊያነሳ እጁን ቢያገባ ወጥመዱ እጁን አጣብቆ መንትፎ አስቀረው፡፡ ወይ እጅ ላንድ ቀን መብል የዘላለም መብሊያውን አጣ፡፡ ለመብል ባይንሰፈሰፍ እጁን በወጥመድ ባልተመነተፈመ ነበር፡፡

የማይራብ የለም፡፡ ቢሆንም የራብ ተከታይ ሞት እንዳይሆን ፍሬው ከምን ውስጥ እንደሆነ መመልከት ነው፡፡

  • ሰንደቅ ዓላማችን መጋቢት 24 ቀን 1935 ዓመተ ምሕረት

******************

ሲበሉ የላኩት

ምሳውን ሲበላ አሽከሩን ላከው የተላከ አፉን ላከከ እንደሚባለው ቢያጐርሰው እኮ በተሻለው ነበር፡፡ አሽከሩ ሲላክ ያይ የነበረው ከጌታው ፊት የቀረበውን መብል እንጂ የጌታውን መልዕክት አልነበረም፡፡ የሆድ ነገር ሆድ ይበላልና የምግቡን ጉምጃን ብቻ በሆዱ ሲያጢያጢን መንገድ ቢጀምር ምን እንደተላከና ወዴት እንደተላከ መልዕክቱንም የተላከበትንም አንዱንም አጣው፡፡

መመለስ አይቀርምና የማታ ማታ ወደጌታው ተመለሰና ጌታው እህ ቢለው ምን እህ አለ አጉርሰው ልከውኝ ቢሆን የእኔም ልብ ባልጠፋም የእርስዎም መልዕክት ባልተጓጐለም ነበር ብሎ ሲበላ የላከውን መልዕክት አደረሰ፡፡

  • ሰንደቅ ዓላማችን መጋቢት 24 ቀን 1935 ዓመተ ምሕረት

******************

የአዲስ አበባ 6ኛ ቀበሌ ሹም ከ72 ዓመት በፊት ያቀረበው የወንጀል ሪፖርት

መጋቢት 3 ቀን ከሌሊቱ በ4 ሰዓት እደጃች ነሲቡ ሰፈር ያልታወቁ ወስላቶች 1 ቦምብ ወርውረው መተኮሱን አስታወቀ፡፡

መጋቢት 3 ቀን መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ አቅራቢያ በቀበሌው ሹም መርማሪዎች ለጊዜው ምን እንደሆኑ ያልታወቁ ሰዎች ጥለውት የተገኘ 1 የጅ ቦምብ መገኘቱን አስታውቆ ለአዲስ አበባና ለአውራጃዋ ገዥ መሥሪያ ቤት አስረከበ፡፡

መጋቢት 5 ቀን ከሌሊቱ በ6 ሰዓት አብዱል ሐጂ ሰይድ 2 ክፍል የሣር ክዳን ቤት ከእኩሌታው ዕቃ ጋር መቃጠሉን አስታወቀ፡፡

መጋቢት 5 ቀን ከሌሊቱ በ8 ሰዓት ቶላ ያደቴ ከሚባለው ቤት ያልታወቁ ሰዎች በሩን ለመክፈት ሲሞክሩ ስለነቁባቸው ሁለት ጥይት ተኩሰው አመለጡ ሲል አስታወቀ፡፡

መጋቢት 10 ቀን ማሞ አባተ፣ ሊሚ ጉዮ፣ ከበደ ወልደ ገብርኤል፣ ሙለታ ዳዲ፣ ጐፈር አየለ፣ አባይነህ ታፈሰ፣ ቦንብ ተክሌ እነዚህ 7ቱ ሰዎች ከ2 ወር በፊት ጀምረን ከ1 ጊዜ እስከ 6 ጊዜ የስርቆት ሥራ እየሠራንና ከየሌቦቹም ጋር እየተስማማን ሥራችን ስርቆት ነው ሲሉ በ1 ቃል ስላመኑ 7ቱም ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ መላካቸውን አስታወቀ፡፡

መጋቢት 10 ቀን ከሌሊቱ 5 ሰዓት ተክለ ሃይማኖት አቅራቢያ ሐጅ አብዶ አሩሲ ቤት ሌላ ገብቶ ከበረንዳ ላይ ሊሰርቅ ሲሞክር አብዱላሒ የሚባለው አሽከሩ በጥይት ገደለው፡፡ የሞተው ከወዴት እንደመጣ መልኩን የሚያውቀው ሰው አልተገኘም፡፡

  • ሰንደቅ ዓላማችን መጋቢት 24 ቀን 1935 ዓመተ ምሕረት

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...