ሰላም! ሰላም! ‹‹የዚህ ዓለም ደስታ ደካማ ነው?›› ማን ነበር ያለው? አዎ፣ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥታችን ናቸው። ይኼውላችሁ ያ አብዮት ፍሬውንም ገለባውንም ጥሩ አድርጎ ከትውስታችን ገርስሶታል ማለት ነው። አለመታደል ሆነና ደግሞ ‘የእኛ ታሪክ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመስዝግበን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስንሠለፍ መታወስ የሚጀምር ነው’ የሚል አባዜ ይዞን፣ እንኳን ታሪካችን የባለታሪኮቹም ስም ይዘነጋን ጀመር። አደራ ደግሞ ይህንን የ‘ሚሞሪ’ ችግር በ‘ቴሌ’ እንዳታላክኩትና የታሪክ ውዝግባችንን እንዳታጦዙት። የምሬን ነው! ዘንድሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መቧቀስ የዴሞክራሲ ‘ትሬዲንግ’ መስሏልላ። እውነቴን ነው! ‹‹ቆይ ግን እኛ በስንቱ ተቧቅሰን ነው ሰው የምንሆነው?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ ባዋየው፣ ‹‹አንተማ ምኑን አይተኸው?›› አለኝ። ነገር ነገር ሲውለው እንደኔ የሚገባው የለም አይደል? ‹‹እንዴት እኔ ሳልሰማ ዘመቻ ዓድዋ በድጋሚ ታውጆ ነበር እንዴ?›› ብለው፣ ‹‹እንዲያም ልትለው ትችላለህ። ሥራ እያጣደፈህ ‘ፌስቡክ’ አላዘወትር አልክ እንጂ እኮ ሰው በኪሱ ‘ዓድዋን’ ይዞ መዞር ሆኗል ሥራው። ደግሞ የሚያሳዝንህ ይኼኛው የስድብ ፍልሚያ እርስ በእርስ መሆኑ ነው›› አለኛ። እምዬ ምኒሊክና ፈረሳቸው ያልሰሙት ጉድ አልኩ።
ይህን እያልኩ የባለሥልጣን ፈቃድና የተቋም ደብዳቤ በማያሻው ምናቤ ምንሊክን እዚህ እኛ ዘመን ላይ ሳልኳቸው። በሚወዷቸውና እንቁ የሴቶች አርዓያ በሆኑት ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ልዩ ማሳሰቢያ አዲስ ሻሽ ጠምጥመው የተነሱትን ፎቶ ገጭ አድርገው (ልጅ አዋቂው በ‘ፌስቡክ’ የግል ፎቶ ቤት ሲከፍት እሳቸውስ ለምን ይቅርባቸው?) የፌስቡክ አካውንት ሲከፍቱ። አይዟችሁ የማሰብ ነውር የለውም። የሚያስብ ሰው መፍራትና ማስፈራራት ነው ከባዱ ነውር። ተሳሳትኩ? እና እምዬ ምንሊክ ‘ላይካቸውን’ እና ‘ዲስላይካቸውን’ እየቆጠሩ እቴጌን ‹‹ወዲህ ነይማ›› ሲሏቸው። እቴጌም ‹‹ምን ሆንክ?›› በማለት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹አየሽልኝ ብርሃን የተመኘንለትን ሕዝብ›› እያሉ ‘ኮሜንት’ እያነበቡ በትካዜ ሰጥመው። እቴጌይቱ ‹‹እኔ ድሮም አንተ አለህ ብዬ እንጂ ወትሮም ለአንዲት ነፍሴ እየሩሳሌምን እንደምመኝ ታውቃለህ፤›› ሲሏቸው ለምን እንደሆነ አላውቅም ታዩኝ። ትግ ትጉ ለዳኝነት ይከብዳላ!
እንግዲህ ለዳኝነት ነገሩ ሁሉ ከብዷል ስንል ‘ምርጫ ለማቆርፈድ ነው’ የሚለን ከሳሽ አናጣም። ግን አባቶቻችን ‘ጠላት አያሳጣህ’ እያሉ ያሳደጉን ለምን ይሆን? ስል፣ ‹‹ጥበብ የሚንቁ ሰዎች በሐሰት ወይም ምርጫ በማጣት የሚወዷቸውን መሰብሰብ ይፈልጋሉ። ጥበበኞች ግን ከጭብጨባ ይልቅ በትችት አረንቋና በትግል ሰው መሆን ያውቁበታል፤›› ያሉኝ ባሻዬ ናቸው። ባሻዬ ሲላቸው ይናገሩታል እኮ። ዳሩ ዕድሜ መስታወት ሆነና ከመቆጠብ መቆጠብ (መቼስ ለእናንተ ጠበቅ አድርጉና አንብቡት አይባል፣ ሥራ እንጂ ነገር በማላላት አንታማማ) እየቀናቸው ‘አካፋን አካፋ’ የሚሉት እንደ አብዛኞቻችን ስብስባቸው ነው። ብንሸብት ባንሸብት ያው ካንድ ወንዝ መቀዳታችን ተዘነጋ? እንዲያው እኮ! አሁን ማን ይሙት ሰው ማናገር ስለምትወዱ እንጂ ከአንድ ወንዝ መቅዳትና መቀዳት ጠፋችሁ? ወንዝ ቢጠፋችሁ ባህር መሻገር ታውቁ የለ እንዴ? አይ እናንተ! አካል ባይርቅም ልብ ከራቀ ምን ቀረ ብዬ እኮ ነው።
የእውነት ለቪዛ ከሚሠለፈው ለልማት የሚሠለፈው ቢሰፈር እፍኝ አይሞላም። እንዲያማ ባይሆን ቀምቶ ሯጩና ነጥቆ በራሪው አያስመርረንም ነበር። ካወራሁ አይቀር አትሌቲክሳችን እያፈራቸው ካሉ ተተኪ ሯጮች፣ የአቋራጮች ‘ሲስተም’ ያፈራቸው አላስቀምጠን ብለዋል። ድንቆቹ አትሌቶቻችን ባንዲራችንን በዓለም አደባባይ ሲያውለበልቡ ልባችን በኩራት አብጦ ጠሽ እንዳላለ፣ እነዚህ በሙስና መም ላይ የሚፋተጉ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪዎች አንገት እያስደፉን ‘ሃይ’ ባይ አጥተናል። ኧረ እንኳን እነሱን መንገድ ላይ አይቶንም በለዘብተኞች ቅላፄ ወላ ‘ሃይ’ ወላ ‘ባይ’ የሚለንም እንደ ‘ቻፓ’ እያጠረን ነው። ለነገሩ መፈራረድ ስለምንወድ እንጂ አጥብቀው ሰላም ሲሉንም ‘ይኼ ሰው ወይ ብድር ፈልጎ ነው ወይ ጆሮ ሊጠባ ነው’ ብለን ፊታችን እንደምንከሰክስ ሴረኞች ላይ አንጨክንም። ጉድ እስከ ወዲያኛው አለ የናፈቃት የራቀችበት!
የእኛ ጨዋታ በወግ ነውና የሚዘወረው ጥቂት ገጠመኞች ጣል ላድርግባችሁ እስኪ። ሰው መቼስ ያለውን ከሰጠ ንፉግ አይባልም። ተርፎኝ ከኮሚሽኔ ባልዝቅላችሁም ወግም ስንቅ ነው ላወቀበት። አይደል እንዴ? ታዲያ ማጣፊያው አጥሯቸው ሳይወዱ የሰው ፊት የሚገርፋቸውን ትተን በግልጽም በስውርም የልመና ተግባር ላይ የተሰማሩት ወገኖቻችን ይኼ አይገባቸውም። አንዱ ባለፈው ‹‹በሁዳዴ…›› አለኝ። ‘ልመና ያበላል’ ተብሎ እንጂ ቸግሮት ጎዳና እንዳልተሰደደ ‘በሁዳዴ’ ሲለኝ ነቅቻለሁ። አይገርማችሁም? በሁዳዴ ብሎ ልመና እስኪ። ‹‹እግዜር ይስጥልኝ›› አልኩ። አላወቀም እንጂ ትህትናና ትዕግሥቴ ራሱ ጥሩ ምፅዋት ነበር።
ማንጠግቦሽ በኋላ ሳገኛት እንዲህ ብላት፣ ‹‹ትዕግሥትና ትህትና የምሕረትና የፍቅር ክፍያ መሆኑ ያልገባቸውን ግብዞች አይቶ ነዋ?›› ብላኝ ነበር። ምን ለማለት ነው ብዬ አልጠየኳትም። እንዴ! በአግቦ ፍቺ ዛልን እኮ! ‹‹እሱማ ይሰጠኛል አንተን ጠየኩ እንጂ፡፡ ደግሞ በሁዳዴ የሚመፀውት ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በፋሲካ ሲነሳ በቀኙ ይቀመጣል’ ይላል መጽሐፉ፤›› አለኝ። ‘ይብላኝ ላልተማረ’ እያልኩ በሆዴ ቶሎ ለመገላገል ኪሴ ስገባ አሥር ሳንቲም ማግኘት። አሥር ሳንቲም መኖሯን ለብዙ ጊዜ ዘንግቼ መቆየቴ ገርሞኝ የብራችን ዋጋ ማጣት አስተከዘኝ። ምሳጤዬ ውስጥ ሳለሁ እጄን ዘርግቻለሁ። (ልብ አድርጉ) ‹‹ምንድነው ይኼ?›› አለኝ እንደ አራጣ አበዳሪው ሻርሎክ ዓይኑን አፍጥጦ። ኦ ለካ ጊዜው እንኳን የሼክስፒርን ሥራዎች የራስን የሕይወት ሞራ በጥሞና እንዲያነቡ አይፈቅድም። ይቅርታ! ይቅርታ!
እኔም ከመደንፋት ‘ለማኝ ነው? ሰላይ ነው?’ ብዬ አተኩሬ ማየት። ‘አንበርብር ሚሊየነር ነው’ እያሉ በአሉታዊ መንገድ የሚያስወሩብኝ ሰዎች ስለበዙ ከእነሱ የተላከ እንደሆነ ብዬ እንጂ፣ ፀሐዩ መንግሥታችን ደህና በልማት ‘ቢዚ’ አድርጎን የማንን አንጃ ፈርቼ መሰላችሁ? አይ እናንተ! ሰላይ ከሆነ ደንፍቼ አባርሬው ሌላ የማላውቀው ሰላይ ከሚተካ ብዬ በዝግታ፣ ‹‹ያለኝ ይኼ ነው›› ስለው ሳንቲሟን በአውራጣቱ ጥፍር ወደ ላይ አንከረባብቶ በመዳፎቹ አፈነና ‹‹ጎፈር ወይስ ሰው?›› ብሎ አስመረጠኝ። ሰላይ ነው የሚለው ጥርጣሬ አየለ። አልመርጥም ብል ‘በምርጫው ፍትሐዊነት አያምንም’ ብሎ እንዳይከሰኝ ሰጋሁ። ሰው ስለጠማኝ ሰው መረጥኩ። የመረጥኩት ቢደርሰኝ ‹‹ተነቀሰው!›› ብሎ ሳንቲሟን ወርውሮልኝ ሄደ። ስንል ስንል ያለንን መመፅወት እርግማን ሆነና አረፈው እላችኋለሁ። ወይ ጊዜና ሰው!
የሰበሰቡትን ሲበትኑበት መቼስ ማንም ሰው ቢሆን ቅር ይለዋል። ያ ዓይን አውጣ ለማኝ የወረወራትን አሥር ሳንቲም ጎዳናው ላይ ሕዝብ እያየኝ አጎንብሼ አነሳኋት። ከረሜላም በአቅሙ ንቋት ምንም የማትገዛ፣ ለታሪክ ነጋሪ የቀረች በትሆንም ላብ ናት። ግን አልኩ ‘በእኔና በሕዝቤ ደካማ ጎን እስከ መቼ የሰበሰብነውን እየበተኑብን የወጠንነውን እያከሸፉብን እንገፋለን’ አልኩ። የወል ቋጠሮአችንና ቀዳዳችን ሲሰፋብኝ ወደ ራሴ ተመለስኩ። ‘ወዶ አይደለም ቅጠል ከደረቀ ያሳደገው ቅርንጫፍ በአዲስ የሚተካው’ እያልኩ በገንዘብ ሰጪና ተቀባይ ይኼን ያህል መተዛዘባችን ገረመኝ። የፈጠረ አይረሳምና ሰብስቤ ያልበተነብኝስ ምን አለኝ ስል ሳስስ ውዷ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። በሳምንቱ ማብቂያ ‘አንቨርሰሪያችንን’ (የአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጤ ሊካተቱ ጥቂት ከቀራቸው አንዱ ቃል ስለሆነ ነው እንግሊዝኛ የተናገርኩባችሁ) ለማክበር በስሱ ላዘጋጅ ያሰብኩት ድግስ ትዝ አለኝ። የልብስ እንጂ የድግስ ስስ እንደሌለው ባውቅም ለፍቅር ነውና ጉጉት ናጠኝ።
ወዲያው እጄ ላይ ያሉ ሁለት ቪላዎችን ለማሻሻጥ ወደቀጠርኳቸው ሰዎች ደወልኩ። አካባቢውን ስጠቁማቸው ወጣት የመሰሉኝ ደንበኛዬ ሳገኛቸው ዕድሜያቸው ወደ ሰባ ይጠጋል። ‹‹መሬት ቢከሽፍበትም ሰው ቤት ላይ ያለው አቋም አይሏል፤›› ያለኝ አንድ ደላላ ወዳጄ ትዝ እያለኝ አንድ አንድ ስንባባል፣ ከልጆቻቸው ጋር ስቴት 30 ዓመታት ኖረው መምጣታቸውን አጫወቱኝ። ‹‹ቤቱ ለልጆችዎ ነው ማለት ነዋ?›› ስላቸው፣ ‹‹ኧረ ለራሴ ነው። እዚያ እንግዲህ ምንም የጎደለብኝ ነገር አልነበረም። ግን በሰው አገር በትንሽ ትልቁ የማያበራ ‘ቢል’ ለመክፈል የሥርዓቱ ባሪያ ሆነው የሚኖሩ ልጆቼን እያየሁ ከምሞት፣ በአገሬ የመብራትና የውኃ ‘ቢል’ እየከፈልኩ ኖሬ በቃሽ ስባል ወገኔ ቢቀብረኝ ይሻለኛል።›› አሉኝ። ጥቂት ዘወር ዘወር ብለው ቤቱን አዩና ለመግዛት መወሰናቸውን ሳያወላውሉ ሲነግሩኝ ማንጠግቦሽና እኔ የምንቆርሰው ሰማይ ጠቀስ ‘ቶርታ’ ፊቴ ላይ ድቅን። እኛ እኛ ሕንፃማ እንዴት ይታየናል?
እንሰነባበት በሉ። ምቀኛና ጠላት በአሉባልታ ከሚያሰቃየኝ አይቶ ይውጣለት ብዬ በአጀብ ቶርታዬን ታቅፌ ቤቴ ገባሁ። ማንጠግቦሽ ቶርታውን ስታይ በድንጋጤ ወከክ ብላ ቀረች። ምነው ስላት፣ ‹‹ሰው ዳቦ መግዣ ዳገት ሆኖባታል ጭራሽ ኬክ ይዘህልኝ መጣህ? ምን አደረግኩህ አንበርብር?›› ብላ ራሷን ያዘች። ‹‹የፈረንሳይ አብዮት እኛ ቤት የሚደገመው እኔና አንቺ ማን ስለሆንን ነው? ይኼን ራስሽን በእቴጌ እኔን በአፄ ሒሳብ ማስላት አቁሚ። ዛሬ የደስታችን ቀን ነው አደብ ግዥ…›› እያልኩ የአባወራነት ሚናዬን በአግባቡ ተወጣሁ። በሐሳብ ነው ታዲያ በጉልበት አላልኩም። የዘንድሮ ጆሮ እኮ አይታመንም። ወዲያ ደግሞ ባሻዬ ተነስተው፣ ‹‹ዕድሜያችሁ ይርዘም ሐሳባችሁ ይስመር…›› እያሉ መመረቅ ያዙ። ምርቃታቸው ትንሽ ተንዛዛ መሰል የደስታዬ ተካፋይ ሁኑ ብዬ የጋበዝኳቸው የቅርብ ወዳጆቼና ጎረቤቶቼ፣ ‹‹ምነው የባሻዬ ምርቃት የምረጡኝ ቅስቀሳ መሰለ?›› ብለው ሲያንሾካሹኩ ሰማሁ። ዋናው ሐሳቤ ግን የሰበሰብኩትን ፍቅር እንደ አሥር ሳንቲሜ የሚበትንብኝ አጋጣሚ እንዳይፈጠር ሁሉንም በሳቅ በጨዋታ ማስተናገድ ላይ ነበር። መስተንግዶዬ ሰመረ። ኬኩም ተቆረሰ። ስለ ፍቅር አወራን ሳቅን። ምሽቱ ሲገፋ ሁሉንም ወደ ቤቱ ተነስቶ ሄደ። እንግዶቻችን ከመሸኘታችን ማንጠግቦሽ ቀድማኝ አልጋ ውስጥ ገብታ ፊቷን አዙራ ተኛች። የኬኩና የዳቦው ፖለቲካ መሆኑ ነው። እኔም ገብቶኝ እኔም ጀርባዋን አቅፌ ሳባብል አደርኩ። በዚህ መሀል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ አንዱ ሲቆጣ ሌላው ካላባበለ፣ አንዱ ሆድ ሲብሰው ሌላው አይዞህ ካላለው፣ አንደኛው መረረኝ ሲል አንዱ ጣዕም ካልፈጠረ ጎራ ለይቶ ማቅራራት ምን ይፈይዳል? ከማቅራራት ፍቅር መዝራት አይበጅም ትላላችሁ? መልካም ሰንበት!