ሰሞኑን በሹክሹክታ ወሬ ደርቶ ነው የሰነበተው፡፡ የሐበሻ ልጆች በተለመደው ‹‹ሽፍንፍን›› ወሬያቸው ሲባባሉት የነበረው ባይገባኝም፣ አንዱ ደፋር ገለጥለጥ ያደረገው ቡሉኮ የለበሰ ወሬ ‹‹ወቸ ጉድ›› ሲያሰኘኝ ሰነበተ፡፡ እኔም የታዘብኩትንና የሰማሁትን በሙሉ መናገር ባልችልም በአጭሩ ግን እንዲህ ከትቤዋለሁ፡፡ ‹‹በቃል የያዙት ይረሳል፣ በጽሑፍ የያዙት ይወራረሳል›› ይሉ ዘንድ ገጠመኜን እንዲህ ልንገራችሁ፡፡
ነገሩ ይህ ነው፡፡ ወሬ እንደ ቋያ እሳት በሚግለበለብበት ፌስቡክ ላይ የቢጤዎቼን እንቶ ፈንቶ ስቃርም፣ አንዱ ፖለቲካው ሠፈር ውስጥ ያለ ወጣት ‹‹እህ እህ…›› ዓይነት እጅ እግር የሌለው መልዕክት ትንሽ ሰዎች ይቀባበሉታል፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የከረመበትን ሰቆቃ በደምሳሳው የገለጸበት አኳኋን ጥያቄ ያጫረባቸው ሌሎች ‹‹ተንፍሰው›› ማለት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መሀል አንዱ ‹‹…ቤት የሚሸት ነገር አለ›› ብሎ አጭር አስተያየት ጣል ያደርጋል፡፡ በዚህ መሀል ግራ መጋባት የተጫጫናቸው አስተያየቶች ይሰነዘራሉ፡፡
‹‹የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ…›› በሚል ዕድሜ ጠገብ ተረትና ምሳሌ በመጠቀም አንድ የኢሕአዴግ ወጣት ፖለቲከኛ ‹‹በሚስጥር የተያዘ›› ነገር ያፈነዳል፡፡ ሰዎችን ግራ አጋብቶ የነበረው ጉዳይ በጨረፍታ ታወቀ፡፡ ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ ታዋቂ አባላት ከጽንፈኛው ዳያስፖራ ፖለቲከኛ ቡድን የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኤርትራ ሲያመሩ መያዛቸውን የገዛ ጓደኞቻቸው መናገራቸውን ያትታል፡፡ በፌስቡክ በሚታወቁ የፓርቲው አባላት ዘንድም መደነጋገር የተፈጠረ የሚያስመስሉ ምልልሶች ይታያሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ‹‹እባካችሁ ስለጉዳዩ የምታውቁ እውነቱን ተናገሩ!›› የሚል ጥሪ ይተላለፋል፡፡ እኔ ይህንን ጽሑፍ እስከምጽፍ ድረስ ግን ስለጉዳዩ ያውቃሉ የተባሉ ምንም አልተናገሩም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖችም ትንፍሽ አላሉም ነበር፡፡ ይልቁንም የፓርቲው አንዳንድ አባላት የፌስቡክ ፕሮፋይል ፎቶአቸውን በሙሉ ወደ ጥቁር ቀይረውት ነበር፡፡ ተረጋግተው ይሁን በሌላ አላውቅም በነጋታው ጥቁሩ ጠፍቶ ነበር፡፡
ይህንን በዚህ እንተወውና እስኪ ወደኋላና ወደፊት እየሄድን የአገራችንን የፖለቲካ ጉዞ እንቃኘው፡፡ እንደኔ ዓይነቱ በ40ዎቹ አጋማሽ ያለ ሰው የዚህን ዘመን የፖለቲካ ሒደት ሲገመግመው ችግር አለ ብሎ ቢደመድም አይፈረድበትም፡፡ በበኩሌ የአገራችን የዘመኑ ፖለቲካ በመርህ መመራት አቅቶት በደመነፍስ የሚጓዝ ከመሆኑም በላይ፣ ከዴሞክራሲያዊነትና ከሰብዓዊነት መንፈስ እያፈነገጠ ነው፡፡ ዓላማ የሚባል ክቡር ነገር መርህ የለሽ በሆኑ ሰዎች እየተደፈጠጠ፣ አጋጣሚዎች በሚፈጥሩዋቸው ድንገተኛ ጉዳዮች ላይ መንጠላጠል የተጣባን በሽታ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡
ከዚህ ቀደም ስለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከሚገባው በላይ የሰበኩንና አልፈው ተርፈውም በትልቅ ጥራዝ በምሁራዊ ትንታኔ ያጠገቡን ምሁር፣ ድንገት ሳይታሰብ ሰላማዊ ትግሉ አብቅቶለታል ብለው ነፍጥ እንደሚያነግቡ አረዱን፡፡ በወጣትነታቸው ዘመን ለጥቂት ጊዜ የተንጐማለሉበት በረሃ ገቡ ብለን ስንጠብቅ ኒውዮርክ ጫካ (Concrete Jungle) ውስጥ ሆነው በኢንተርኔት ‹‹ትግሉን ሲያጧጡፉት›› አየናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በገዛ ቴሌቪዥን ጣቢያቸው ሳይቀር ስንት የተናገሩለት ትግል ‹‹ጓደኛቸውን›› አስበልተውበት አደፈጡ፡፡ ከመነሻው የተሳሳተው የዜሮ ብዜት ሥሌታቸው የትም እንደማያደርሳቸው ሲታወቅ፣ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው በፎቶ ሞንታዥ የሚሠሩትን ‹‹ሽምቅ ኃይል›› በሺዎች እያባዙ ይነግሩናል፡፡ ውስጥ አዋቂዎች ግን ‹‹አቤት ውሸት›› እያሉ ይዘባበቱባቸዋል፡፡ እንኳን የሠለጠነ ተዋጊ መንገድ መሪ የላቸውም ይላሉ፡፡
አንድን ሥርዓት አልተስማማኝም ብሎ መቃወም ይቻላል፡፡ መርህ ኖሮ ምክንያት ኖሮ ወደ ዳር የሚገፋ ችግር ካለ የቻለ ወጣ ብሎ መሞከር መብቱ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዘመን ለዚህ ዓይነቱ ጊዜ ያለፈበት ውስብስብ ጉዳይ ይመቻል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ በበኩሌ አይሞከርም እላለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው በየትኛው አደረጃጀትና የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ? ሁለተኛ ለዚህ ዓይነቱ ትግል የተዘጋጀና መስዋዕትነት የሚከፍል የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው? ሦስተኛ በምን ዓይነት መልክዓ ምድር ጠንካራ አስጠጊና ድጋፍ የሚሰጥ ኃይል? የሚባሉት መልስ ይሻሉ፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ‹‹ፋኖ ተሰማራ›› ለማለት በሩ ሁሉ ተዘጋግቷል፡፡ ለምን? ዘመኑ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ ትግል ስለሚፈልግ፡፡ ከዚህ ውጪ እንጓዛለን ያሉት በረሃ ሳይሆን አውሮፓ አሜሪካ ነው ያሉት፡፡ በቃ!
ይህንን ጉዳይ አንስተን ጓደኛሞች ስናወራ የተባባልነው በዚህ ዘመን ችግር አለ፡፡ ገዥው ፓርቲ በተለይ የመብት ጉዳዮችን ችላ በማለቱ ችግሮች መፈጠራቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ የትግል ሒደት ትዕግሥትና መፈተንን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ ባይሳካ ነገ ሰላማዊው ትግል ፍሬ ያፈራል፡፡ ቢቻል ሥርዓቱ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ማበብ ከልቡ እንዲሠራ የሚያስገድደው ጠንካራ ሰላማዊ በሕዝብ የሚደገፍ የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠር የግድ ነው፡፡ አሁን ያሉት አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች መርህ አልባ ብቻ ሳይሆኑ ከኮሙዩኒስት አስተሳሰብ ያልተላቀቁ፣ በጭፍን ጥላቻና ድጋፍ አባላቶቻቸውን የቃኙ፣ ከብሔራዊ ጥቅም ይልቅ ለቡድን ፍላጐት የሚተጉ፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ንድፈ ሐሳብ በቅጡ ያልተላበሱ፣ አባላትንና ደጋፊዎችን በፅኑ መሠረት ላይ ለማታገል የሚችል ጠብሰቅ ያለ ማኒፌስቶ የሌላቸው፣ በአጠቃላይ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ምን ዓይነት መጠይቆችን ማሟላት ይገባዋል የሚለው ሁለንተናዊ የደረጃ መሥፈርት የማይወጣላቸው ናቸው፡፡ ይህንንም ብዙዎች በአደባባይ ባይናገሩም በሹክሹክታ ይስማሙበታል፡፡ የአንድ ፓርቲ አባላት ከአንዱ ወደ አንዱ በፈለጋቸው ጊዜ ዘው የሚሉትም በዚህ ዓይነቱ መርህ አልባነት ነው፡፡
ለብዙ ጊዜ የሰማሁት ዊንስተን ቸርችል ተናግሮታል የሚባል አንድ አስገራሚ አባባል አለ፡፡ ‹‹አንድ ሰው በሃያ ዓመቱ ሶሻሊስት ካልሆነ ልቡ ርህሩህ አይደለም፡፡ ነገር ግን ያ ሰው በአርባ ዓመቱ ኮሙዩኒስት ሆኖ ከተገኘ አዕምሮ የለውም፤›› ነው አለ የሚባለው ቸርችል፡፡ የእኛ አገር ፖለቲከኞችም ከወጣትነት የግራ የፖለቲካ አባዜ አሁንም መላቀቅ ባለመቻላቸው በትግሉ ጉዞ ላይ ደንቃራ ሆነዋል፡፡ ለሰላማዊ ትግል መከፈል የሚገባውን ዋጋ ሳይከፍሉ ‹‹ጫካ ግቡ›› እያሉ ወጣቶችን ችግር ውስጥ መክተት ደግሞ አደጋ ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ሆኖ ቀረርቶ ማሰማት ደግሞ ከነውርም በላይ ውርደት ነው፡፡ የከንቱ ከንቱ መሆን ነው፡፡ አንድ የማከብረው ጓደኛዬ፣ ‹‹ከኮምፒዩተር ጀርባ የመሸጉ ስመ አርበኞች በቅዠት ውስጥ እየኖሩ ማርጀታቸውን እንኳ ረስተውታል፤›› ያለኝ መቼም አይረሳኝም፡፡
(አያሌው፣ ከሰሜን ማዘጋጃ)