Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትአሁንም ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ትግልና ግብግብ አልተሸጋገርንም

አሁንም ወደ ሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ትግልና ግብግብ አልተሸጋገርንም

ቀን:

በቶላ ሊካሳ

ተደጋግሞ እንደተገለጸው በምርጫ ዓመት ቅድመ ምርጫ ወቅት ውስጥ እንገኛለን፡፡ በመካከሉ ጣልቃ የገባ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ተካትቶ ያላየነው፣ ከመጋቢት 6 ቀን ጀምሮ ለ14 ቀናት የሚቆየው ልዩ የመራጮች ምዝገባ ሥራ አለ ቢባልም፣ አሁንም ‹‹የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ›› ፕሮግራም ውስጥ ነን፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ገና ዕጩዎቹን በነቂስና በየምርጫ ክልሉ ለይተን አላወቅንም፣ አልተዋወቅንም፡፡

በዚህ መካከልና ይህ በእዚህ እንዳለ በፓርቲዎች መካከል የሚካሄዱ ክርክሮችንም እየሰማን ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ሁለት ክርክሮች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ምርጫዎች እንዳስመዘገቡትና እንደመሰከሩት፣ የ2007 የምርጫ ሒደትና የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ክርክሮች ጭምር ደግመው እንደሚያረጋግጡት አሁንም ገና በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አየር ጠርቶ ወደሰከነ የፖለቲካ ኃይሎች ሰላማዊ ትግልና ግብግብ አለመሸጋገራችን ዛሬም ግልጽ ነው፡፡

- Advertisement -

ኢሕአዴግ በጦር መሣሪያ መንግሥት ከያዘ በኋላ ሰላማዊ የሐሳብ ትግልን ከተቀናቃኞች ጋር ማካሄድ ነበረበት፡፡ ይህንን አላደረገም፡፡ ኢሕአዴግ በታወቀ ምክንያት መሣሪያ ያነሳበትን ትግል ካሸነፈና ደርግን ከደመሰሰ በኋላ በፖለቲካ በኩል ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ጫካ ውስጥ ከተለመደው የጦርነት ሥልት መውጣት ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር ይዞ መገኘት አልቻለም፡፡

ብዙ ጊዜ፣ ምናልባትም ሁልጊዜ የሰላማዊ ትግል ጉዳይ ሲነሳ የሚወቀሱትና የሚከሰሱት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ በእርግጥ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ፋይዳ ቢስ የሚያደርጉ፣ አድርገውና አውጀውም የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ ከእነዚህ ከለየላቸው ተቃዋሚዎችና አማፂያን ይልቅ ይበልጥ በየጎራው (እዚህም እዚያም) ፋይዳ ቢስና ምሥጋና ቢስ የሆኑት በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው፣ አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ናቸው፡፡ ዛሬ በታወቀና እንደ አዝማችና እንደ ዜማ በየመድረኩ በሚፈከር አባባል፣ በሕጋዊነት መቀጠል ወይም ወደ ሕገወጥነት መዞር እየተባሉ የጫካን መንገድ በሚያመለክት ፕሮፓጋንዳ ወይም ክስ ይነዘነዛሉ፣ ይወገዛሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በዚህ ምክንያት ተመርረው ወይም ተደናግጠው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገሏቸው መቁጠርም አለ፡፡ ከሕገወጡ ይበልጥ ሕጋዊውን መንገድ ተመራጭና ቀላል የሚያደርግ የፖለቲካና የባህል አሠራር ማልማት አለመቻልም ችግር ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የማይነገረው ችግር ከተቃዋሚዎች ይልቅ መንግሥትን፣ ገዢውን ፓርቲ የሚመለከተው የሥር የመሠረት ችግር ነው፡፡ የደርግን መንግሥት ለመዋጋት መሣሪያ ማንሳት፣ የትጥቅ ትግልን መምረጥ ያስፈለገበት ምክንያት የታወቀ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት በገዛ ራሱ ሞት በነበረበት አገር ከጥራኝ ዱሩ የተሻለ አማራጭ አልነበረም፡፡ የትጥቅ ትግሉን ከጀመሩት መካከል ከረዥም ጊዜ ትግልና ተጋድሎ በኋላ አማፂያኑ በኢሕአዴግ አምሳል ደርግን ደምስሰው አዲስ አበባን ተቆጣጥረው ጊዜያዊ መንግሥት አቋቋሙ፡፡ ኢሕአዴግ አሸንፎ መላውን አገሪቷን ሲቆጣጠርና ጦርነቱ ሲቆም ግን ትግሉም አብሮ አቆመ አልተባለም፡፡

ጨዋታውም አልፈረሰም፡፡ ፖለቲካውና ፖለቲካዊ ትግሉም አላከተመም፡፡ ይልቁንም ‹‹አሉታ ኮንቲኒዋ›› ተባለ፡፡ ትግሉ ቀጠለ፡፡ ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ተለውጦ ቀጠለ ተባለ፡፡ ተራማጁ ኢሕአዴግ አድኃሪውን ደርግ በትጥቅ ትግል ደመሰሰ እንጂ የደርግን ጨምሮ አመለካከቶች አልተደመሰሱም፡፡ አይደመሰሱም፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ዋነኛ ኃይል የሆነው ኢሕአዴግ በጦርነት ደርግን አሸነፊ ማለት የኢሕአዴግ ሐሳቦች ከሌሎች ጋር በነፃና በሰላም ተወዳድረው አሸነፉ ማለት አይደለም፡፡ አልነበረም፡፡

ኢሕአዴግ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ ባለመለወጡ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና አሠራር ባለማሳየቱ ለዚህ የተባለውና የተመደበው የሽግግር ወቅት አላግባብ ባከነ፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ሲያሸንፍም ሆነ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ደግሞ ባለቤት አላቸው፡፡ የእነዚህ ነባርና አዲስ የተፈጠሩት አስተሳሰቦች ባለቤቶች ደግሞ ተቃዋሚዎች ሆኑ፡፡ ገና መንግሥት ሥራውን ሲጀምር ያለተቃዋሚ የሚመራው ሥራ አለመኖሩን ሲያውቅ ጫካ የገባበት የጥንት የሥር ምክንያት ተረስቶ ልዩ ሴራና ተንኮል እንደተጋረጠበት አድርጎ ቆጠረ፡፡ በሐሳብ መለየትን፣ የተለየ ሐሳብ ባለቤት መሆንን ተቃወመ፡፡ የሚቃወመውን ውለታ ቢስ አድርጎ ፈረጀ፡፡

በመሆኑም የተቃዋሚዎች አቋም ትክክለኛ ሆነም አልሆነም፣ ይርባም አይርባም በፖለቲካው ሒደት ውስጥ ልክ እንደ እሱ የተነሱበት ምክንያትና ሥፍራ እንዳላቸው በበጎ አይን ማየት አልሆንልህ አለው፡፡ እምቢ አለው፡፡ ኢሕአዴግን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተፎካካሪነት እንዳይለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር እንዳይይዝ ካደረጉት ምክንያቶችና ጉዳዮች መካከል አንዳንዶቹ ዛሬም ከ24 ዓመታት በኋላ ተደጋግመው የሚሰሙት ናቸው፡፡ በፖለቲካው መድረክ ላይ ያኔ ጫካ እያለ የእሱ ተከታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በልጦ የመገኘቱ ምክንያት ትክክለኛ መመርያ ትክክለኛ አቋም በመያዙ መሆኑን ያምናል፡፡ ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላም በፖለቲካው ሒደት ውስጥ የትክክለኛው ወይም የስህተተኛው መለያው መንገድ በትጥቅ ትግሉ ድል አድርጎ የበላይነቱን የጨበጠው ነው ማለቱን እንሰማለን፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች በተለይም ምርጫ በመጣ ቁጥር፣ ትግሉ የሚይዛቸውና የሚያራሩጣቸው፣ የፖለቲካ መስመሮቻቸውን በየቅል ሳያጠሩ፣ በጋራም ሳያቀራርቡ፣ ኢዴሞክራሲያዊነትን ሳያራግፉ፣ ከተጠራጣሪነትና ከመሠሪ ሥሌት፣ ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት ሳይላቀቁ፣ የአገሪቱ መላ ብሔር ወይም ብሔረሰቦች የተያያዙበትን ጠንካራ ትብብር ሳያበጁና ሳይዘጋጁ፣ ኢሕአዴግን እንደምንም ብሎ ከመጣል ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ከመድረስ ማዕዘን የወቅቱን አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ዓላማና ግብ፣ የትግል ሥልትና ስትራቴጂ ይዘው ለመንቀሳቀስ ብዙ ችግር አለባቸው፡፡

ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ፊቺ መፍትሔ አምጪ የዴሞክራሲ ኃይል መሆን የሚችሉት በዱሮ ሥርዓት ናፋቂነት የማያሳማ የፖለቲካ ጥራት ብልጫ ሲያመጡ ነው፡፡ ለምሳሌ በ97 ምርጫ ሰፊ ድጋፍ የነበራቸው ተቃዋሚዎች የዱሮውን ሥርዓት ሊመልሱ፣ የብሔር ብጥብጥ ሊያመጡ ነው የሚለውን ፍርኃትና ወሬ ማስወገድ አልቻሉም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ስለሚያካሂድብን ነው የሚል መከራከሪያ ካለም፣ ቢያንስ ቢያንስ ለማሳሳት የሚመች ችግር እንደነበረባቸውና እንዳለባቸው ማየትም ይገባቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኢሕአዴግነትንና ተቃዋሚነትን የማይደራረሱ ሁለት የጠላትነት ጎራዎች አድርጎ በሁለቱም በኩል የተያዘ አቋም አለ፡፡ እነዚህ የጠላትነት ጎራዎች እያሉ የተሰነገው የዴሞክራሲ ሒደት ይራመዳል፣ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ይካሄዳል ማለት ያስቸግራል፡፡ በዚህ ‹‹አንደራረስም›› ላይ የተመሠረቱ በውስጥና በውጭ ያሉ ኩርፊያዎች መፍረስ አለባቸው፡፡ ኢሕአዴግን መደገፍም ሆነ መቃወም እንኳን ወንጀል ነውር መሆን የለበትም፡፡ አንድን ወይም ሌላ ተቃዋሚ ድርጅትን ከመደገፍና ከመቃወም ጋር ፀብ ሊኖር አይገባም፡፡ ፀባችን ከጭፍን አቋም ከጭፍን ጥላቻና ድጋፍ ጋር መሆን አለበት፡፡ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ሁለቱም መታወር ናቸው፡፡ የአንዱ ጭፍን ተቃውም የሌላውን ጭፍን ድጋፍ ይጠቅማል፡፡ ሁለቱም ለጥላቻዎች ያጋልጣሉ፡፡ ሁለቱም ለኢሕአዴግ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት መራዘም ጠቅመዋል፡፡

በኢሕአዴግና በተቃዋሚዎች ዘንድ በአመለካከትና በአቋም አንደራረስም ወይም ተቃራኒ ነን የሚባለው በአብዛኛው በስሜት ከመማረርና ለሥልጣን ትግል ይበጀኛል ከማለት ጋር የተያያዘ እንጂ፣ አብሮ ከመሥራት የሚያግድ ግንብ በመካከላቸው የለም፡፡

ኢሕአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ሲል፣ እኛ ወይም እነሱ ‹‹ሊበራል ዴሞክራሲ›› እንላለን የሚል ልዩነት ቆዳዊ ነው፡፡ ‹‹አብዮታዊ›› የሕወሓት/ኢሕአዴግ ያለፈ አመለካከት ቅሪት ነው፡፡ በተሀድሶው ጊዜም አሸናፊው ቡድን ሊጥለው ሞክሮ የነበረ፣ የካድሬውን ድጋፍ አጥቶ ላለመውደቅ ሲል ያቆየው ቅጽል ነው፡፡ በተረፈ ዛሬ የሚወራለት ዴሞክራሲ የሊበራል ዴሞክራሲ አንድ ምንዛሪ ነው፡፡ የዴሞክራሲው የይምሰል መሆንና አለመሆን፣ አብዮታዊ የመባልና ያለመባል ሳይሆን ሕዝብ ቢፈቅድም ባይፈቅድም በሥልጣን ለመቆየት የመፈለግና ለዚህ እንዲመች አድርጎ የማኮላሸት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ከየትኛውም አቅጣጫ ሊመጣ የሚችል ነው፡፡

የብሔሮችን ጉዳይ ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› አንዱ ማስረጃ ሊያደርጉ የሚሹ ካሉ ፖለቲካ ደህና ሰንብት ይበሉ፡፡ የብሔሮችን ጥያቄ አውቆና አክብሮ የመያዙ ነገር ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች ሊያመልጡት የማይችሉት የኢትዮጵያ እውነታ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር ከማደራጀትና ጥሪትን ቆጥቦ ለፈጣን ዕድገት ከማዋል አኳያ ሁሉንም ጉዳይ መመዘን ከተቻለ፣ እንዲሁም የትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ጥያቄ በሰላማዊ፣ በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚለው አመለካከት መሠረት ከያዘና ሕዝብን ማዳመጥ ከመጣ ሌላው ነገር ሁሉ ቀላል ይሆናል፡፡

በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ አንደራረስም ተባብለው ነገር ግን በምርጫው መድረክ ላይ አነሰም በዛም የሚገናኙትን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሌላው ዋነኛ መገለጫ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና ልማትን ከብቻ ከሥልጣን ጋር አጣብቆ እኔን ብቻ ምረጡ የሚለው በመንገብገብ ብቻ የማይብራራ አሠራር ነው፡፡

አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲን፣ ፍትሕን፣ ልማትንና ነፃነትን ብቻ ከሥልጣን ጋር ማጣበቅ የመንግሥትን ለውጥ ከአገር ህልውና፣ ከብሔር/ብሔረሰቦች መብት፣ ከሃይማኖቶች ነፃነት ጋር ማዛመድ የሌላው ወገን መለያና መታወቂያ ሆኗል፡፡ ይህ ግን በጭራሽ ልክ አይደለም፡፡ ይህንን የምንለው ከ‹‹ምርጫ ቅስቀሳ›› አኳያ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግሮች በአንድ ወይም በሌላ ቡድን ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ችግሮች ሰፊና ውስብስብ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቡድኖቹም ሰንካላነትና “ጥበት” ስላለባቸው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ችግሮች የተሟላ ማብራሪያና መፍቻ ያለው ማነው? የኢትዮጵያን ሕዝቦች በፖለቲካ ትባቱና በድርጅታዊ ትስስሩ አሰባስቦ ሌሎችን ቡድኖችን ማኮሰስ የቻለስ ማን አለና? ይህ ይቅር የሁሉንም የየፊና የሥልጣን ሩጫ እያጋለጠ የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ በወንበር በልጦ ሥልጣንን የመጠቅለል ጉዳይ እንዳልሆነ በምርጫው ማንም ቀናው ማ፣ ፓርላማ ተገባም አልተገባ ዋናው ጉዳይ ተባብሮ የኢትዮጵያና ሕዝቦች ከውድቀት በማንሳት መረባረብ መሆኑን ለማስገንዘብ የጣረ ነበር?

‹‹ብሔራዊ እርቅ›› እየተባለ እስከዛሬ ሲጮህ የነበረው አነሰም በዛም ይህንኑ የአገሪቱን እውነት ከመረዳት የመጣ ይመስል ነበር፡፡ ወደ ምርጫ ዘመቻ ሲኬድና ደጋፊ እየበረከተ ሲመጣ (በምርጫ 97) ዋናው ጉዳይ ሥልጣን መሆኑ ወለል ብሎ መጣ፡፡ ፖለቲካዊ ጫና ሊያሳርፉ ከሚችሉ ቡድኖች/ወገኖች ጋር ሰፊ ቅርበት ከመፍጠርና ውድና ምርጥ የሕዝብ ልጆችን ከማሰባሰብ ይልቅ፣ የኢሕአዴግ ፖለቲካ ቁስለኛና ተቃራኒ የሆነውን ሁሉ በዙሪያ አጋብሶ ለ97 ምርጫ የመድረስና ብዙ ዕጩ አቅርቦ አሸናፊ የመሆን ፍላጎት አይሎ ታየ፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት ያኔ በክርክሮች ሒደት እንደታየው በሁለቱም ዋና ተቃዋሚ ቡድኖች ዘንድ መሪዎቹ እንኳ የማይዘበራረቁ የጋራ አቋሞች ማበጀት ይቀራቸው ነበር፡፡

ዋነኞቹ ተቃዋሚዎች በሁኔታ አስገዳጅነት በተባበሩ ጊዜ የብቻ ሥልጣን ጉዳይ በጭራሽ አልተረሳም ነበር፡፡ ልብ አድርጉ የምንነጋገረው በምሳሌነት አንስተን ስለምርጫ 97 ነው፡፡ የምናሳየውና ለማስረዳት የፈለግነው ደግሞ የዚች አገር ችግር በአንድ ወይም በሌላ የፖለቲካ ድርጅት ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን ነው፡፡ እናም ሙሉ የሥልጣን አሸናፊነትን በኢሕአዴግ ‹‹ማጭበርበር›› ከማጣታቸው በቀር፣ በእነሱ ቤት ፖለቲካቸውን የተሳካ አድርገው ማሰባቸው አልቀረም ነበር፡፡ በእርግጥ ኢሕአዴግ በገዛ እጁ ሕዝብን እንደ ማስመረሩ ሥልጣን የመጠቅለል ሰፊ ዕድል ነበራቸው፡፡ ያን ዕድል ያመከነው ግን ከኢሕአዴግ ‹‹እንከን›› ይልቅ የራሳቸው ያልጠራ ድሪቶ አቋምና የየብቻ ሩጫ ነበር፡፡ በዚህ በኩል የነበረባቸውን ችግር መወጣት ችለው ቢሆን ኖሮ ለኢሕአዴግ (ድምፅን ማጭበርበር) እጅግ በጣም አስቸጋሪ በሆነበት ነበር፡፡ ያገኙት ድምፅና ድጋፍም የአቋማቸውን አንጀት አርስነት ሳይሆን የኢሕአዴግን ምክነትና የሕዝቡን ክፉኛ መማረር የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡

ጥያቄው ቅንጅትና ኅብረት ኢሕአዴግን በልጠው ጥምር መንግሥት ፈጥረው ቢሆን ኖሮ የዚች አገር ዕጣ ምን ይሆን ነበር? ከአንቀጽ 39 ጋር ትግል ሊገጥሙ? ኢሕአዴግ ዝም ብሎ ሥልጣን ሊያስረክባቸው? በጋምቤላ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል ገዢ ሸሪኮቹ (አጋሮቹ) በኩል የመገንጠል ማስገደጃንና ውዝግብን ተጠቅሞ ሥልጣኑን ለማስመለስ አይሞክር ይሆን? መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ቢከሰቱም እንዲሟሸሹ የሚያደርጉት በየትኛው የፖለቲካ ጥበባቸውና እርዝማኔያቸው?

እነዚህና መሰል ጥያቄዎች በወቅቱ የብዙ አገር ወዳጆችና የዴሞክራሲ ናፋቂዎች ጭንቀቶች ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል እብሪትና ከመሰሪነት መገላገልን መናፈቅና በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የተቃዋሚ ቡድን ጠቅልሎ እንዳያሸንፍ መመኘት አብረው ሊጎዳኙ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ጉዳዩን ለማስረገጥና ሰፋ አድርጎ ለማሳየት ልክ የዛሬ 20 ዓመት በ1987 ዓ.ም. ደረጀ መርሻ የተባሉ ጸሐፊ፣ ገና በትኩሱ ያኔ አዲስ በተፈጠረው በድኅረ ቀዝቃዛው ጦርነትና በመዋቀር ላይ በነበረው አዲስ የኃይል ሚዛን ውስጥ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሊኖረው የሚገባውን መልክ እንዴት እንዳሳዩ እንመልከት፡፡

አንደኛ፡- ማንም የፖለቲካ ድርጅት የፈለገውን ያህል ቢያብጥ በአገሪቱ ላይ ሰፍረው የቆዩትን ችግሮች ዛሬ ከሚገለጹት ጋር ጨምሮ ብቻውን ለመፍታት አይችልም፡፡ በአገር ውስጥ የሚነሱበትን ተቃውሞዎች እየተከላከለ፣ የውጭ ተፅዕኖ እንዳይሰረስረው እየታገለ፣ ለሕዝቡ የሚበጅ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕቅዶችን በተግባር ለማዋል አቅሙም ጊዜውም አይኖረውም፡፡ ያሻውን መርሐ ግብር አውጥቶ በቂ የመሰለውን ሥራ እየሠራ ብቻዬን እየገዛሁ እቀመጣለሁ ቢል የአገሪቱ ችግሮች ብዛትና ምስቅልቅልነት በተለያዩ መልኮች እየተቋጠሩ ሊፈትኑትና ከሥልጣን ሊያስፈነጥሩት መምዘግዘጋቸው አይቀሬ ነው፡፡ ብሎ ብሎም ዕቅዶቹን በሥራ ከመተርጎም ይልቅ ከባላጋራዎቹ ጋር በመተናነቅ የአገሪቱን ጥሪትና የራሱን ኃይል ወደ መከስከስ መዞሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ሁለተኛ፡- በዛሬው የዓለም ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ደሃና የውጭ ኃያላን ጥገኛ አገር ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት የሌለበት የግብግብ ወይም የትንቅንቅ ፖለቲካ ማካሄድ አይቻልም፡፡ የአሪቱን መንግሥት የጨበጠ ወገን ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በሐሳበ ሰፊነትና በታጋሽነት፣ በመሐሪነትና በአርቆ አስተዋይነት ለማስጠጋትና ለማቀፍ ካልቻለ በየሰበቡ እየተነሱ የሚነቃነቁ ፖለቲከኞች በውጭ እገዛ የአገር ግንባታውን ጥረት እንዲያናጉ በር ይከፍትላቸዋል፡፡ የአገሪቱን ችግሮች በሙሉ አጣርቶ የሚያውቅና የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት የሚያዳምጥ ሰፊ የፖለቲካ ግንባር ተቋቁሞ የተቻለውን ያህል የፖለቲካ ኃይሎችን ለማቀፍ ከተቻለ ግን፣ ተነጣይ ንቅናቄዎች ቢነሱም ያንን ያህልም ተቀባይነት አይኖራቸውና ለእነሱ ሲባል የማያልቅ ድርድር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡

እነዚህን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ለመቀበል የማይችል በዚህች ምድር ላይ የሌለ ኋላቀርና ደንቆሮ ነው፡፡ በእውነት ለአገርና ለወገን ፍቅር ያለው ድህነታችንና ኋላቀርነታችን ተወግዶ ብልፅግና ከምኞት አልፎ ሕያው እንዲሆን የሚሻ ዜጋ ሁሉ ይህን እንደ መሠረታዊ መነሻ መቀበል አለበት፡፡ በዛሬው የዓለም ሁኔታ በፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ልክ ዱሮ ይባል እንደነበረው ሌላውን በሙሉ ጨፍልቄና ፈንግዬ ሥልጣን ይዤ ሕዝቡ ተስማማ አልተስማማ ለብቻዬ እገዛለሁ የሚል ሁሉ ጤናውን መመርመር አለበት፡፡

ሁለቱን መሠረታዊ ነገሮች ስንደረድር የማይረሳውን ሦስተኛ ጉዳይ ሁሉም እንደሚያውቀው አንጠራጠርም፡፡ ይኸውም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ግንባር ለመመሥረት የግድ ዴሞክራሲን በአገሪቱ የማስፈን ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሁሉም ኃይሎች ሊሰባሰቡ የሚችሉበት የመነጋገሪያ፣ የመከራከሪያ ካስፈለገም የመታገያ መሣሪያ ነውና ዴሞክራሲ ሳይኖር ምንም ማከናወን አይቻልም፡፡ እርስ በርስ በለበጣ እየተመሰጋገኑ፣ አንዱ ሌላውን ስለሥራውና ስለአስተሳሰቡ የማይጠይቅበት፣ የእያንዳንዱ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እስከምን ድረስ መሆኑ የማይታወቅበት እንደ ኢሕአዴግ ዓይነት የጌታና የአሽከር ግንኙነት የሰፈነበት ስብስብ ሳይሆን፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ፍጭት የሚታይበት ሰፊ ‹‹የጃንጥላ ድርጅት›› የማቆም ዴሞክራሲ የግድ መኖር አለበት፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን በሥራ ላይ ያለው የ1999 ዓ.ም. የአሠራር ደንብ ፓርላማ ውስጥ የመንግሥት ተጠሪ፣ የፓርቲ ተጠሪ፣ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ሁለተኛ ተቃዋሚ ፓርቲ አሉ ማለትን የአገር የፖለቲካው ጤናማ የአየር ሁኔታ ነው ብሎ ያምናል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ማለት በምክር ቤቱ ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ የፖለቲካ ድርጅቶች በምክር ቤቱ ውስጥ የፓርቲውን ወይም የፓርቲያቸውን ሥራዎች እንዲያስተባብሩ የሚወከላቸው (የሚወክላቸው) የምክር ቤቱ አባል የሆኑ አባላቱ (አባሎቻቸው) ናቸው፡፡

ከገዥው ፓርቲ (ወይም ፓርቲዎች) ውጪ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በምክር ቤቱ ውስጥ የፓርቲያቸውን ሥራዎች እንዲያስተባብሩ የሚወክሏቸው የምክር ቤት አባል የሆኑ አባሎቻቸው ደግሞ የፓርቲ ተጠሪዎች  ይባላሉ፡፡

ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ  ማለት ደግሞ በፓርላማው ውስጥ ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ መቀመጫዎችን ያገኘ ፓርቲ ነው፡፡ ከዚህኛው ከዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ቀጥሎ በምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫዎችን ያገኘው ፓርቲ ደግሞ ሁለተኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ይባላል፡፡ ይኸው ደንብ ስለ “የተቃዋሚዎች ቀን” (Opposition Day) ይናገራል፡፡ ይደነግጋል፡፡ የፓርላማ ቡድን የሚባል ተቋምም አለው፡፡  

ፓርላማው 547 መቀመጫዎች አሉት፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ “እንደገና አበራ” እየተዘመረለት የመጣው፣ እንደገና እያበራ ነው የሚባለው የኢትዮጵያ ምርጫ የ2002 ውጤት ከሁለት መቀመጫዎች በቀር ሁሉንም (የአጋሮችን ጨምሮ) በኢሕአዴግ ያስያዘ ነው፡፡

በዚህ መካከል አንድነት ከመድረክ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ከአንድነት አንዳች ነገር ሆነው ተስፈንጥረው ተወርውረዋል፡፡ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ጋዩ የከፋ ዞን የጊምቦ የምርጫ ክልልን ውክልና ኢሕአዴግ ምን ቸገረኝ ብሎ፣ ሥራ ፈትቶ፣ ጊዜ አጥፍቶ ሊቀናቀናቸው እንደሚችል እንዳልገባቸው ከወዲሁ ምርጫ 2007 ውስጥ ገልጸዋል፡፡

መጠነ ሰፊውንና ግትልትሉን የኢትዮጵያ ችግር ለማስወገድ የመረጥነው አቅጣጫ ይህን የመሰለ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...