Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተሽሮ የነበረው የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድና ተመልሶ የመጣበት ምርጫ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተመርጠው በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሻሩት አመራሮች በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡

ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በድጋሚ በተደረገ ጥሪ ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ የቻለው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሽረው የነበሩትን ፕሬዚዳንቱን አቶ ኤልያስ ገነቲን ጨምሮ እስከ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ድረስ በኃላፊነት የቆዩት ሁሉም አመራሮች ተሽሮባቸው የነበረውን ኃላፊነታቸውን መልሰው ይዘዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በምልዓተ ጉባዔ ባለመሟላት ሳይካሄድ የቀረው ጠቅላላ ጉባዔ ምልዓተ ጉባዔው በመሟላቱ ጠቅላላ ጉባዔውና የድጋሚ ምርጫው ተደርጎ አቶ ኤልያስ ገነቲ ፕሬዚዳንት፣ አቶ ታደሰ መሸሻ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሊመረጡ ችለዋል፡፡ አቶ ታደሰ መሸሻ በቀጥታ ከዘርፍ ተወክለው ያለ ውድድር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑ ናቸው፡፡ ከሁለቱ የቀድሞ አመራሮች ሌላ ከቀድሞ ቦርድ ውስጥ የነበሩና በድጋሚ ለመወዳደር ቀርበው የተመረጡት የቦርድ አባላት አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ፣ አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ አቶ ገሠሠ ተሾመ፣ አቶ ፋሲካው ሲሳይ፣ አቶ ያረጋል ገሠሠ ናቸው፡፡

ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ኤልያስ ገነቲ በሚመራው ቦርድ ውስጥ ተካትተው እንዲሠሩ ተመርጠው ከነበሩ የቦርድ አባላት ውስጥ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አቶ ኃይሌ አሰግዴ፣ አቶ ሞላ ዘገየና አቶ ፍሰሐ ሻንቆ በሐሙሱ ምርጫ ለውድድር ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ በሁለቱም ጠቅላላ ጉባሌዎች ላይም አልተገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት እነሱን ሊተኩ የሚችሉ አዲስ ተመራጮች ተካተዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት አዳዲሶቹ የቦርድ አባላት ደግሞ የዓባይ ባንክ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ፣ የሲግማ ኤሌክትሪክ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ዴሌቦና የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ጉያ ናቸው፡፡

ለፕሬዚዳንትነት በተደረገው ምርጫ አቶ ኤልያስ ገነቲ አሸናፊ የሆኑት 284 ድምፅ በማግኘት ነው፡፡ ይህ የድምፅ መጠን ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ አግኝተውት ከነበረው ድምፅ ያነሰ ነው፡፡ በወቅቱ አቶ ኤያስ አሸናፊ ያደረጋቸው ድምፅ 356 ነበር፡፡ በሐሙሱ ምርጫ ከአቶ ኤልያስ ገነቲ ጋር ለውድድር የቀረቡት ሁለት ዕጩዎች ሲሆኑ፣ አንደኛው ተወዳዳሪ የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ካሳ ናቸው፡፡ አቶ እስራኤል በዚህ ውድድር 145 ድምፅ በማግኘታቸው አሸናፊ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ እስራኤል ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ከአቶ ኤልያስ ጋር ለፕሬዚዳንትነት የተወዳዳሩ ሲሆን፣ እንደ ዘንድሮ ውጤታቸው ሁሉ ባለፈውም ዓመት አግኝተውት የነበረው ድምፅ 145 ነበር፡፡ በዕለቱ ከሁለቱ ተወዳዳሪዎች ሌላ በፕሬዚዳንትነት የተፎካከሩት አቶ ኡመር ካለ ደግሞ 71 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ካስመራጭ ኮሚቴው የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ለድጋሚ ምርጫው በፕሬዚዳንትነት ለመፎካከር የተጠቆሙትና ለቦታው የሚፈለገውን መሥፈርት አሟልተው የነበሩት ዕጩዎች አምስት ነበሩ፡፡ ሆኖም ከአምስቱ አንዱ ለቦርድ አባልነት እወዳደራለሁ በማለታቸው የተቀነሱ ሲሆን፣ ሌላኛው ተፎካካሪ ደግሞ መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ለምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴው ከውድድር መውጣታቸውን በደብዳቤ በመግለጻቸው፣ ለፕሬዚዳንትነት ለሚደረገው ውድድር ሦስቱ ብቻ ለፉክክር ሊቀርቡ ችለዋል፡፡ መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፉት ደበዳቤ ከፕሬዚዳንትነቱ ውድድር ራሳቸውን ያገለሉት አቶ ተሾመ በየነ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አቶ ተሾመ ራሳቸውን ከውድድር ያገለሉበት ምክንያት ይፋ ባይደረግም፣ አንዳንድ ወገኖች ግን በድጋሚ ምርጫው በፍርድ ቤት ታግዶ የቆየውንና በአቶ ኤልያስ የሚመራውን ቦርድ መልሶ ለማስመረጥ የተደራጀ ሥራ በንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አንዳንድ አመራሮችና በአንዳንድ የዘርፍ ምክር ቤት አባላት የተሠራ በመሆኑ ወደ ውድድር መግባቱ አስፈላጊነት ስላልታያቸው ነው የሚል አስተያየት ሲሰነዘር ተሰምቷል፡፡ ትችቱ የሚሰነዘርባቸው ወገኖች ግን ይኼንን አስተያየት ይከላከላሉ፡፡

አቶ ተሾመ ባለፈውም ዓመት ከአቶ እስራኤልና ከአቶ ኤልያስ ጋር ለመወዳደር የተጠቆሙ ቢሆንም፣ አስመራጭ ኮሚቴው ለውድድር ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡ ይህም በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ ውዝግብ የፈጠረ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የአቶ ተሾመ ጉዳይ አወዛጋቢ እንዲሆን አድርጎ የነበረው አቶ ተሾመ የሚወክሉት ኩባንያ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በመቅረባቸው የመወዳደሪያ መሥፈርቱን አያሟሉም በሚል ነው፡፡ ይህ አካሄድ ግን ተገቢ እንዳልነበር በመገለጽ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ሰፊ ክርክር ተደርጎበታል፡፡

የዘንድሮ የምርጫ አስተባባሪ ኮሜቴ አቶ ተሾመ ግን መስፈርቱን ያማሏሉ ተብሎ የድጋሚ ምርጫው ለውድድር መቅረብ የሚችሉ መሆኑን ቢያረጋግጥም፣ ምርጫው ሦስት ቀን ሲቀረው ከውድድሩ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ተሾመ ምልአተ ጉባዔው ሳይሟላ በተበተነው የመጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በተጠራው ጠቅላላው ጉባዔ ግን ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

በሐሙሱ ምርጫ ለቦርድ አባልነት በተደረገው ውድድር 15 ዕጩዎች ተፎካካሪ ሆነው ቀርበው ነበር፡፡ የምርጫው ውጤት ሲታወቅም የዓባይ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ያሉት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ የቦርድ አባል ሆነዋል፡፡ ተሽሮ በቆየው ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተመርጠው ከነበሩ የቦርድ አባላት መካከል ከፍተኛ ድምፅ አግኝቶ የነበረው ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከወ/ሮ መሰንበት ሌላ ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባላት እንዲያገለግሉ የተመረጡት ቀሪዎቹ የቦርድ አባላት አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ፣ አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ አቶ ተመስገን ዴሌቦ፣ አቶ አሰፋ ጉያ፣ ዶ/ር አይናለም ዓባይነህ፣ አቶ ገሠሠ ተሾመ፣ አቶ ፋሲካው ሲሳይና አቶ ያረጋል ገሠሠ ናቸው፡፡ ከነዚህ ተመራጮች ውስጥ ከወ/ሮ መሰንበት፣ አቶ አሰፋ ጉያና ዶ/ር አይናለም ውጪ ያሉት በሙሉ በተሻረው ቦርድ ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡

ድጋሚ የተራው ጉባዔ

ከ15 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት ንግድ ምክር ቤት 500 አባላት መገኘት ባለመቻላቸው ኮረም አልሞላም ተብሎ መበተኑ ይታወሳል፡፡ ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ ድጋሚ ጥሪ ተደርጎ ጠቅላላ ጉባዔው በሳምንቱ ሐሙስ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲካሄድ ሲወሰን፣ በዚህም ስብሰባ ኮረም አይሞላ ይሆናል የሚል ሥጋት የነበራቸው ጥቂት አልነበሩም፡፡ ነገር ግን እንደተፈራው ሳይሆን ቀርቶ በሐሙሱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ  548 በመጀመርያ አባላት በመገኘታቸው ጠቅላው ጉባዔው ሊካሄድ ችሏል፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው መጀመር በኋላ ዘግይተው ወደ ጉባዔው የገቡ አባላት ስለነበሩ በዕለቱ የተገኙ አባላት ቁጥር ከ606 በላይ መሆን ችሏል፡፡ በስብሰባው ባለፈው ሳምንት ተገኝተው ከነበሩት በተሻለ ተሰብሳቢ የተገኘበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ባለፈው ዓመት ተገኝቶ ከነበረው 780 አባላት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ በሐሙሱ ጠቅላላ መጋቢት 3 ቀን ከተገኙት አባላት ቁጥር በላይ መገኘት የተቻለው ግን የተለያዩ ጥረቶች ተደርጎ ነው፡፡ ባለአደራ ቦርዱ አባላት እንዲሳተፉ ግፊት ያደረገ በመሆኑ ጭምር የተሻለ ተሳታፊ ሊገኝ ችሏል፡፡ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርትም በድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ኮረም ያለመሟላት እንዳይስተጓጉል ከአንድ ሺሕ በላይ አባላት በቀጥታ የስልክ ጥሪ አድርጓል፡፡ ሌሎች የጥሪ መንገዶችን ተጠቅሞ በርካታ አባላት እንዲገኙ ለማድረግ ጥሯል፡፡ የባለአደራ ቦርዱ አባል አቶ አየነው ፈረደ፣ በትክክል ጥሪው እየተደረገ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን፤ ጥሪ ሲተላለፍም በግንባር መከታተላቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ለንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ላሉ ነጋዴዎች መልዕክቱ እንዲደርስ በመደረጉ ካለፈው የተሻለ ተሳታፊ ሊገኝ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን እንደተደረገው የቀጥታ ጥሪ ጥረት የተፈለገውን ያህል አባል ተገኝቷል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ የንግድና የአገልግሎት ዘርፍ አባላት ቁጥር አንሷል፡፡ በሐሙሱ ስብሰባ ጉባዔውን ለማስጀመር የሚያስችለው ኮረም ሲሞላ ከተገኙት ውስጥ 60 በመቶዎቹ የዘርፍ አባላት ናቸው፡፡ ከንግድና ከአገልግሎት ዘርፍ የተገኙት አባላት ቁጥር 40 በመቶ ነው፡፡ ይህም አሁንም ከጠቅላላ ተሳታፊዎች ውስጥ በዘርፍ ማኅበራት የተደራጁት አባላት ብልጫውን ወስደዋል፡፡ በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይም የንግድ ምክር ቤቱን ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ እንዲጠራ በፍርድ ቤት ማስወሰን የቻሉት የኅብረት ኢንሹራንስ ተወካይ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አልተገኙም፡፡

እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ኮርፖሬት የሚባሉ ኩባንያ መሪዎች ብዙዎቹ አልተገኙም፡፡ ከዚህም ሌላ ንግድ ምክር ቤቱን ሲመሩ የነበሩ የቀድሞ አመራሮች ውስጥ ብዙዎቹ የተገኙበት አልነበረም፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ በተፈጠረ ያለመግባባት መንስዔ የሆነውንና አቶ ኢየሱስ ወረቅ ዛፉ በአምናው ጉባዔ ላይ እንዳይገኙ ያስወሰኑት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ዘገየም አልተገኙም፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ያልተገኙት አሁንም ጠቅላላ ጉባዔው እየተካሄደ ያለው በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የሚፈለገውን ምልዓተ ጉባዔ ይዞ አይደለም የሚል አቋም ስላላቸው ነው፡፡ ጉዳዩም በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ልገኝ አልችልም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ከምርጫ ውጤቱ በኋላ

በሐሙሱ ጠቅላላ ጉባዔ የተደረገው ምርጫ ከቀድሞዎቹ አመራሮች ውስጥ አብዛኛዎቹን ማስመረጥ ተችሏል፡፡ ይህም በአንዳንድ ወገኖች እነዚህን አመራሮች መልሰን እናስመርጣለን የሚለውን ፍላጎታቸውን አሳክቶላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ በድጋሚ ለመመረጥ በዕጩነት የተደረገው ምርጫ ያልቀረቡት በተለይ እንደ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴና አቶ ኃይሌ አሰግዴ ከቀድሞው ቦርድ ጋር በጋራ የሠሩት ለጥቂት ወራት ሲሆን፣ በአንድ ሳምንት ሁለት ጊዜ በተጠራው ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ሳይገኙ የቀሩበት ምክንያት ግን አልታወቀም፡፡ ከቀድሞ የቦርድ አባላት ውስጥ በዕጩነት ያልቀረቡት አቶ ሞላ ዘገየ ግን ፍርድ ቤት የቀድሞውን ቦርድ እስካገደ ድረስ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በወቅቱ በተፈረጠው ያለመግባባትም ተመልሶ ለመመረጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአብዛኛው በምክር ቤቱ ውስጥ በተፈጠረው ውዝግብና አሠራር ቅር ተሰኝተው ራሳቸውን ያገለሉና በድጋሚ ለመመረጥ ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ ሳይሳተፉ እንደቀሩ ይታመናል፡፡

አዲሶቹ ተመራጮችና የአገልግሎት ዘመን

አዲሶቹ ተመራጮች የሚያገለግሉት ለአንድ ዓመት ብቻ ነው፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባል ግን መተዳደሪያ ደንቡ አንድ ተመራጭ የሚመረጠው ለሁለት ዓመት ነው ስለሚል በዚሁ መሠረት መተግበር አለበት የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡  የሐሙሱ ተመራጮች የአገልግሎት ዘመን አንድ  ዓመት እንዲሆን የተፈለገው በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጉባዔ ላይ አዲስ አበባን ወክሎ የሚገኝ ተመራጭ ስለሚያስፈልግ አንድ ዓመት መሆኑ ተገቢ ነው የሚል መከራከሪያ በመቅረቡ ነው፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ ውይይት ተደርጎ ተመራጮቹ የሥራ ዘመን አንድ ዓመት ይሁን በሚለው ጉዳይ ስምምነት ላይ ተደርሶበታል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ 10ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በተፈጠረው ችግር በመስተጓሎሉ 10ኛውና 11ኛውን ጠቅላላ ጉባዔ በአንድ ላይ አጣምሮ እንዲካሄድ ጠቅላላ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የሐሙሱ ጠቅላላ ጉባዔ ሒደት

በድጋሚ የተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባለፈው ሳምንት በክብር እንግድነት ተገኝተው ምልዓተ ጉባዔው ባለመሙላቱ ተመልሰው የነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ጉባዔውን በይፋ ከፍተዋል፡፡  በዕለቱም ባደረጉት ንግግር መንግሥት ለንግድ ኅብረተሰብ ድጋፋ እያደረገ መሆኑንና ይኼንንም ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑን ነው፡፡ በተለይ የግል ዘርፉ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረውም ነው ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ከመንግሥት ጋር በመወያየት ለመፍታት ከአዲስ አበባ አስተዳዳር ጋር መፈራረሙን ያስተዋሉት ምክትል ከንቲባው ‹‹ይህንም የሕዝብ ክንፍ  በከተማችን የልማትና የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ የሚያሳድግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ከከተማው አስተዳደር ጋር ለመገንባት የታቀደው የኤግዚቢሽን ማዕከል ግንባታ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረጋቸውንና ይኼንንም ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ስኬት አስተዳደሩ ከፍተኛ አክሲዮን መግዛቱ ለንግድ ኅብረተሰቡ ያለውን አጋርነት ያሳያልም በማለት ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸው ማብቂያም በአሠራር ሒደት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን በሰከነ መልኩ በውይይት የመፍታት ልምድና ባህል ማዳበር፤ ምክር ቤቱ ለተቋቋመለት ዓላማ ሲያካሂድ ለዴሞክራሲያዊ አሠራር መጎልበት የሚኖረው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን በመገንዘብ አዲሱ አመራር ሥራውን ማካሄድ ይገባዋል በማለትም አሳስበዋል፡፡

የክብር እንግዳው ከተሸኙ በኋላም መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው በተለያዩ አጀንዳዎችን ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ጠቅላላ ጉባዔው በድጋሚ እንዲካሄድ የሚል በመሆኑ የንግድ ምክር ቤቱ 2005 በጀት ዓመት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት በድጋሚ ቀርቧል፡፡ ይህንንም ሪፖርት እንደ አንድ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ያቀረቡት የንግድ ሚኒስቴር ዴኤታውና የንግድ ምክር ቤቱ ጊዜያዊ ባላደራ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሊ ሲራጅ ናቸው፡፡ በተመሳሳይም አምና የቀረበው የኦዲት ሪፖርት በድጋሚ ቀርቧል፡፡

በሁለቱም ሪፖርቶች ላይ መጠነኛ ውይይት ተደርጎ በሙሉ ድምፅ ሊፀድቅ ችሏል፡፡ ከዕለቱ አጀንዳ ጋር የተያያዘ ባይሆንም በንግድ ምክር ቤቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ አስተያየቶች ከአባላት ተሰንዝረዋል፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እየታየበት ያለውን ፋክቻ ይመለከታል፡፡ አስተያየት ሰጪው በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ተፈረጠ የተባለውን ውዝግብ በሽምግልና መጨረስ ይችል ነበር ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱ አንቱ የተባሉ አባላት እያሉት እነሱ ማስማማት ሲችሉ ይህ አለመሆኑ የንግድ ምክር ቤቱን መልካም ስም እየነካ መሆኑ ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ምርጫ ከመገባቱ ቀደም ብሎም ሊያነጋግሩ ይችላሉ የተባሉ አንዳንድ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ አንዱ ‹‹በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ከተገኙት ውስጥ አብዛኞቹ የዘርፍ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ምርጫውን ማካሄድ ይችላል?›› የሚል ይገኝበታል፡፡

ወደ ምርጫ ሒደቱ ከተገባ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ዕጩዎች ያልተገባ የምረጡኝ ዘመቻ በስብሰባው አዳራሽ በር ላይ ሲያደርጉ ነበር የሚልም አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ በዕለቱ የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን የተመረጡት ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ይኼንን አስተያየት ተቀብለው ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩትን አስቁመናል በማለት አልፈውታል፡፡

ባለአደራ ቦርዱ

በምልዓተ ጉባዔ ሳይሟላ ሳይካሄድ የቀረውን ጠቅላላ ጉባዔ አስመልክቶ ያደረገው ምክክር እንዲሁም በድጋሚ በተጠራው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ አባላት በነፃ ሐሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ይህንን በማድረጉ ከተሰብሳቢዎች ጭምር ምስጋና የተለገሰው ሲሆን፣ የድጋሚ ጠቅላላ ጉባዔ ጥሪው ላይ ግን ያልፈተሸው ነገር እንደነበረበት የሚጠቅሱ አሉ፡፡

አንዱ በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ የጠቅላላ ጉባዔ ጥሪ መደረግ ያለበት ከ15 ቀናት ቀደም ብሎ ነው፡፡ ድጋሚ ጉባዔው የተጠራው ግን በአንድ ሳምንት ልዩነት ነው የሚለው አስተያየት እንደ ክፍተት ታይቷል፡፡ ከዚህ ውጪ ባለአደራ ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለማስፈጸም አስፈላጊውን ሥራ መሥራቱን ብዙዎች የሚስማሙበት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለአደራ ቦርዱ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጽሕፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የተዋቀረ ሲሆን፣ በሁለቱም ጠቅላላ ጉባዔዎች ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ተወካይ አልተገኙም፡፡ ተወካዩ ያልተገኙት ከኢትዮጵያ ውጭ ለሥራ በመሄዳቸው ነው፡፡

የባለአደራ ቦርዱ ሥራውን በጥቂቱ ሲያካሄድ የነበረ በመሆኑ የሚናገሩት አቶ ዓሊ ሲራጅ፣ ክፍተት እንዳይፈጠር ብዙ ጥረት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴውን በጥንቃቄ መምረጥ ተችሏል ተብሏል፡፡ የምርጫ አስተባባሪውን የኖክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ጥላሁን በሰብሳቢነት፣ አምባሳደር ብሩክ ደበበ ደግሞ በጸሐፊነት እንዲመሩት ተደርጎ ነበር፡፡ አዲሶቹ ተመራጮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች