Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  በተቋማት አድሏዊነት ላይ ያነጣጠረው የመድረክ ማኒፌስቶ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  የምርጫ ማኒፌስቶ በተለይ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲዘጋጅ የገዢው ፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂን ይዘት፣ እንዲሁም አፈጻጸም በመገምገም የሚቀየሩ፣ የሚቀጥሉና ክለሳ የሚደረግባቸውን ጉዳዮች በመለየት የፓርቲውን አቋም ለመራጮች ለንፅፅር ለማቅረብ ሲያገለግል ነው የሚታወቀው፡፡ መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. መድረክ በጽሕፈት ቤቱ ይፋ ያደገው ማኒፌስቶ ግን ከዚህ ለየት ይላል፡፡

  መድረክ የገዢው ፓርቲን ፖሊሲና ስትራቴጂ በጥልቀት በመመርመር ትንታኔ አቅርቦ አማራጮችን ከማቅረብ ይልቅ፣ የኢሕአዴግ የአፈጻጸም ድክመትን በማረም ‹ሀቀኛ› ሥርዓት መፍጠርን እንደ አማራጭ ቆጥሯል፡፡ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የተቆጣጠረው የሕዝብ ተቀባይነት አግኝቶ ሳይሆን፣ በኃይል እንደሆነ መድረክ ያምናል፡፡ ‹‹ሌሎች አማራጭ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የተደራጁ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለሕዝቡ አስተዋውቀው ድጋፍ በማግኘት በምርጫዎች ተወዳድረው በማሸነፍ ለሥልጣን እንዳይበቁ የፖለቲካ ምኅዳሩን ዘግቶት ይገኛል፤›› በማለት ማኒፌስቶው ያትታል፡፡ የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየጠበበ መጥቶ አሁን እየተዘጋ ነው፡፡ ምኅዳሩ ተዘግቶም ጭምር በምርጫ የምንሳተፈው ብቸኛ የትግል ሥልታችን ምርጫ ስለሆነ ነው፡፡ ሌላ አማራጭ የለንም፤›› ብለዋል፡፡

  ኢሕአዴግ የመሠረተውን ጨቋኝ አገዛዝ ለማስቀጠል ባለው ምኞት በአገሪቱ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት ሊገነቡ አለመቻላቸውንም በአፅንኦት ይገልጻል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ ሚዲያው፣ ሕዝባዊ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግድ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፓርላማ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ክልሎች፣ ኤምባሲዎች፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ ኃይል፣ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ ባለሥልጣን፣ የትምህርት ተቋማትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመድረክ ግምገማ እነዚህ ተቋማት ገዢው ፓርቲን እያገለገሉ እንደሆነ ያሳያል፡፡ አማራጩ ደግሞ ተቋማቱን ከገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው እንዲሠሩ ማስቻል ነው፡፡

  ኢሕአዴግ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን እዋጋለሁ እያለ በተቃዋሚነት ሽፋን ላሰለፋቸውና ማንንም ለማይወክሉ ነገር ግን በኪራይ ሰብሳቢነት የሚተዳደሩ ስብስቦችና ግለሰቦችን›› እንደሚያደራጅም መድረክ ይከሳል፡፡ የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የትኞቹ ናቸው በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ሌሎቹ በደንብ ስለሚታወቁ መጥቀስ አያስፈልግም፡፡ ለምሳሌ ግን የቀድሞው የእኛ ፓርቲ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በኢሕአዴግ እንደሚረዳ ማስረጃ አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

  በነፃነት ለመንቀሳቀስ ጥረት የሚያደርጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንፃሩ ከአባሎቻቸው መዋጮና ከደጋፊዎቻቸው በሚያገኙት አነስተኛ ገንዘብ በየአካባቢው የተለያዩ ድርጅታዊ እንቅስቃሴዎችና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያካሂዱ ገደብ የለሽ ጫና እንደሚደረግባቸው መድረክ አመልክቷል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ለእስራት፣ ለስደት፣ ለሥራ አጥነትና ለመሳሰሉት እንግልቶች እየዳረገ ፓርቲዎቹን የማዳከምና የማቀጨጭ ዘመቻውን አጠናክሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል፤›› ሲልም ማኒፌስቶው ያስቀምጣል፡፡

  የመድረክን ማኒፌስቶ አንብቦ ከኢሕአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂ ለመለየት የሚቸገሩ ሰዎች ቢኖሩም፣ ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን መፍጠርን በራሱ እንደ አማራጭ ፖሊሲ መውሰዱን ግን መገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ‹‹አማራጭ አቅርበናል፡፡ ለምሳሌ ኢሕአዴግ ሥልጣን ለብቻው ጨምድዶ ሰላምና መረጋጋት በአገሪቱ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ እኛ ሥልጣን ብንይዝ ሁሉን አቀፍ የሆነ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንፈጥራለን፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ መድረክ ከኢሕአዴግ በተቃራኒ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንደሚያደርግ፣ ሰብዓዊ መብትን እንደሚያከብር፣ ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት እንደሚያቋቁም፣ ነፃ ተቋማትን እንደሚመሠርትና ፍትሐዊ ንግድን እንደሚያሰፍን ገልጸዋል፡፡ መድረክ እፈጥራቸዋለሁ ብሎ እንደ አማራጭ የዘረዘራቸውን ጉዳዮች ገዢው ፓርቲ እንዳሟላ የሚያምን ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ምርምር ያደረጉ ምሁራን እርምት ተደርጎባቸውና አፈጻጸሙ ተጠናክሮ ሊስተካከሉ የሚችሉ ጉዳዮች እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ መድረክ በአብዛኛው ጉዳይ ላይ ያለው አቅራረብ ይህን ይምሰል እንጂ እንደ አማራጭ የሚወሰዱ አጀንዳዎችንም አቅርቧል፡፡

  የሕግ የበላይነት ወይስ የኢሕአዴግ የበላይነት?

  መድረክ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና ሌሎች ሕጎች ለዜጎች የተለያዩ መብቶችን ቢያጎናፅፉም፣ ሕጎቹ በወረቀት ላይ እንዲቀሩና ተግባር ላይ እንዳይውሉ በመደረጉ ‹‹የሕግ የበላይነት ሳይሆን የገዢው ፓርቲ መሪዎች የበላይነት›› በአገሪቱ መረጋገጡን አመልክቷል፡፡

  ይህም በዋነኛነት በኢትዮጵያ የፓርቲና የመንግሥት ሚና በመቀላቀሉ እንደሚገለጽ መድረክ ያስረዳል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ለፓርቲው ሥራና ጥቅም እያዋለው ነው፤›› ሲልም ይከሳል፡፡ ዶ/ር መረራ ይህን ችግር ገዢው ፓርቲ ከሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ጋር ያገናኙታል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን እከተላለሁ ቢልም፣ እንደ ኮሙዩኒስት ፓርቲ ውሳኔ አሰጣጡ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ መንግሥት ሀብት ሲቆጣጠር ትንሽም ቢሆን ሁላችንም ድርሻ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው ሀብቱን ከተቆጣጠረ ተጠቃሚው የፓርቲ አባል ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ማኒፌስቶው ‹‹ለዘመናት ሳይፈታ የኖረው የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄም ዛሬም በአግባቡ መፍትሔ ሳያገኝ በመቅረቱ አገራችንን የባሰ ውስብስብ ችግር ውስጥ እንዳይከታት የሚያሳስብ ደረጃ ላይ ተደርሷል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ መድረክ ከዚህ ቀደም አፈጻጸሙ ላይ የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ቢያመለክትም፣ በሕገ መንግሥቱ ለተቀመጡ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ድጋፍ ይሰጥ ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ መድረክ የአቋም ለውጥ ያመጣው ኢሕአዴግ በሁሉም ነገር በተለይ በፌዴራል ሥርዓቱ አፈጻጸም ላይ ወደኋላ እየተንሸራተተ በመምጣቱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

  የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና ተመራማሪው አቶ አበራ ደገፋ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸውና ጥበቃ የሚደረግላቸው መብቶች የሚመሰገኑ ቢሆንም፣ በይዘት ደረጃ በተወሰነ ሁኔታ፣ በአፈጻጸም ደረጃ ደግሞ በብዛት ችግሮች እንደሚታዩ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ በይዘት ደረጃ በሀብት ክፍፍልና በገቢ ምንጭ ላይ ክፍተት አለበት፡፡ የመሬት ባለቤትነት ላይም እንዲሁ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያላቸው ሚና ግልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሕግ ማዕቀፉ ክፍተት ይልቅ አተገባበሩ ላይ የሚታዩ ችግሮች ሕገ መንግሥቱን ትርጉም አልባ እንዲያደርጉት ሥጋት አለኝ፡፡ የኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ መሆንና በክልሎች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር መጥበቁም ሌላ ችግር ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚከተለው የልማታዊ መንግሥት በክልሎች ነፃነት ላይ የራሱ ጫና አለው፡፡ እርግጥ ነው በክልሎች መብትና በብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መብት መካከል ልዩነት አለ፤›› ብለዋል፡፡ አቶ አበራ በአጠቃላይ የፌዴራሊዝሙ አፈጻጸም ኢትዮጵያን አሀዳዊ መንግሥት እንደሚያስመስላት ጠቁመዋል፡፡

  የመድረክ የቋንቋ ፖሊሲ

  የመድረክ ማኒፌስቶ ‹‹ከአማርኛ በተጨማሪ ሰፊ ብዛት ያለው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ማኒፌስቶው ተጨማሪ ቋንቋዎች የትኞቹ እንደሆኑ የማይጠቅስ ሲሆን፣ በምን መሥፈርት እንደሚመረጡም በግልጽ አያስቀምጥም፡፡ ዶ/ር መረራ ምርጫው እንደ አገሪቱ አቅም የሚወሰን ቢሆንም ኦሮምኛ፣ ከዚያ ቀጥሎ ትግርኛ፣ ከዚያ ቀጥሎ ሶማሊኛ በተጨማሪ የሥራ ቋንቋነት ሊመረጡ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ግን ኦሮሚኛ ከአማርኛ ጋር መምጣቱ ለአገሪቱ ሰላም፣ አንድነት፣ መረጋጋት እንዲሁም አንድ የጋራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጠቃሚ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ለዚህ አንዱ የጠቀሱት አብነት የአማርኛና የኦሮሚኛ ቋንቋዎችን የሚናገረው የሕዝብ ብዛት ከ70 በመቶ በታች አለመሆኑን ነው፡፡

  ዶ/ር ዮናታን ፍስሐ “A tale of two Federations: Comparing Language Rights in South Africa and Ethiopia” በሚለው የምርምር ሥራቸው፣ ደቡብ አፍሪካ ለ11 ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋነት ዕውቅና ብትሰጥም በተግባር ግን አንድ ቋንቋ በሥራ ላይ መዋሉን፣ ሌላ አንድ ቋንቋ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ጥቅም ላይ ቢውልም ሌሎቹ ቋንቋዎች ግን ለይስሙላ የሥራ ቋንቋ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሁሉም ቋንቋዎች እኩል እንደሆኑ ሕገ መንግሥቱ ቢገልጽም፣ አማርኛ ብቸኛው የሥራ ቋንቋ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ለሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች አማርኛ የሥራ ቋንቋ ሆኖ የተመረጠው ውጤታማ ተግባቦት የሚፈጥር በመሆኑ እንጂ፣ የተናጋሪዎቹን የበላይነት ለመጠበቅ እንዳልሆነ ማሳመን ከፍተኛ ፈተና እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ቋንቋ ማኅበራዊ መስተጋብር ለመፍጠር ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች አጥኚዎች ደግሞ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋዎችን ማምጣት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ኢኮኖሚዎች አስቸጋሪ እንደሚሆን ያስገነዝባሉ፡፡

  ዶ/ር መረራና አቶ አበራ ግን የኢኮኖሚ ተፅዕኖው ቢኖርም ችግሩን አለመቅረፍ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከኢኮኖሚው ተፅዕኖ ይበልጣል ይላሉ፡፡ አቶ አበራ በየትኛውም የፌዴራል ሥርዓት አንድ ቋንቋ በሥራ ቋንቋነት ሲመረጥ የተናጋሪው ሕዝብ ብዛትና የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅም ከግምት ውስጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ በእነዚህ መሥፈርቶች ኦሮሚኛ ከአማርኛ ጋር ተወዳዳሪ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ኦሮሚኛ በሥራ ቋንቋነት የማይመረጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ከኦሮሚኛ ቀጥሎ ግን እንደ ሲዳሚኛ፣ ትግርኛና ሶማሊኛ ተቀራራቢ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡ የትኛው ይቅደም የሚለውን ለመወሰን መሥፈርቶቹን በአግባቡ ማጥናት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

  ሕዝብን ተጠቃሚ ያላደረገ የኢኮኖሚ ዕድገት

  መድረክ በማኒፌስቶው ላይ የኢሕአዴግ የተሳሳቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና አተገባበራቸው በእርሱ ጥላ ሥር የተሰባሰቡ አዲስ የገዢ መደቦችንና አቀባባይ የከበርቴ ክፍሎችን በሚጠቅም መንገድ በማዋቀሩ፣ ጥቂቶችን አበልፅጎ ብዙኃኑን ማጎሳቆሉን አትቷል፡፡ ‹‹በተለይ በወጣቱ ላይ በአስከፊ ሁኔታ እየተንፀባረቀ በመጣው የኑሮ ውድነት፣ ድህነትና ሥራ አጥነት ተተኪውን ትውልድ ለከፍተኛ ተስፋ መቁረጥና ስደት እየዳረገው ይገኛል፤›› ሲልም ያክላል፡፡ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ከመፍታት ፈንታ በተጨባጭ የሕዝብ ኑሮን ሲያሻሽል ያልታየውን የፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ዲስኩር በማስተጋባት ተጠምዶ እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡

  ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደሃ ተኮር መሆኑንና የበርካታ ሚሊዮኖችን ሕይወት እየቀየረ ስለመሆኑ ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ ዶ/ር መረራና አቶ ጥላሁን ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥቂቶቹን በማበልፀግ ብዙኃኑን ያገለለ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ዶ/ር መረራ የተቋማቱ ሪፖርት የሚጠቀመው ዳታ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚዘጋጅ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ነፃ በሆነ አካል የተረጋገጠና ታምኖበት የተዘጋጀ ዳታ አይጠቀሙም፡፡ ሰፊ ጥናት አድርገው ሳይሆን ጥቂት ናሙና ወስደው ነው ዳታ የሚጋግሩት፤›› ብለዋል፡፡ በደሃውና በሀብታሙ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት አደገኛ በሆነ መልኩ እየሰፋ እንደሆነ የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፣ ‹የሚበላው ያጣ ሕዝብ አንድ ቀን መሪዎቹን ይበላል› የሚለውን አባባላቸውን ኢሕአዴግ እንዳይረሳው አሳስበዋል፡፡

  መድረክ በማኒፌስቶው ላይ የገለጻቸው ሌሎቹ አማራጭ ሐሳቦች በተለይም በግብርናው ላይ ኢሕአዴግ ከሚያራምዳቸው ሐሳቦች ጋር ተቀራራቢ ናቸው፡፡

  (ለዚህ ዘገባ ነአምን አሸናፊ አስተዋጽኦ አድርጓል)

  - Advertisement -