Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተያዙ 6.1 ሜትሪክ ቶን የዝሆን ጥርሶች ተቃጠሉ

ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተያዙ 6.1 ሜትሪክ ቶን የዝሆን ጥርሶች ተቃጠሉ

ቀን:

168 ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በፍርድ ቤት ቅጣት ተጥሎባቸዋል

ባለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ተለያዩ 19 የአፍሪካና የዓለም አገሮች ለማለፍ ሲሞክሩ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገ ፍተሻ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ 6.1 ሜትሪክ ቶን የዝሆን ጥርሶችና ከጥርሶቹ የተሠሩ የተለያዩ ጌጣጌጦች መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ተቃጠሉ፡፡

ከ168 በላይ ሕገወጥ የዝሆን ጥርስ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለውና ፍርድ ቤት ቀርበው የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው በኋላ፣ በሕገወጥ መንገድ ይዘዋቸው የተገኙት የዝሆን ጥርሶች እንዲወረሱ ተደርጐ፣ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ላለፉት 30 ዓመታት ሲከማቹ መክረማቸውን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 30 ዓመታት ልዩ ጥበቃ ሲደረግላቸው የከረሙት የዝሆን ጥርሶችና ከጥርሶቹ የተሠሩ ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች፣ በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ለኳሽነት እንዲቃጠሉ ተደርጓል፡፡

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃጠሉትን የዝሆን ጥርሶችና ጌጣጌጦች በሚመለከት የተናገሩት አቶ ዳውድ ከሕገወጥ ሰዎች ዝውውር፣ ከአደንዛዥ ፅዕና ከሽብርተኝነት ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ከማመልከታቸው አኳያ፣ ኢትዮጵያ የወሰደችው ዕርምጃ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዝርያቸው ለአደጋ ለተጋለጡ የዱር እንስሳት፣ ለዓለም አቀፍ እንስሳትና ለዕፅዋት ስምምነት የተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኢትዮጵያም ከ1981 ዓ.ም. ጀምሮ ስምምነቱን ተቀብላ ማፅደቋን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ መነሻ ያደረገችው ሕገ መንግሥቱን እንደሆነ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ኮንቬንሽኖች የሕገ መንግሥቱ አካል ናቸው፤›› እንደሚልም አስታውሰዋል፡፡

ኢንተርፖል ባወጣው መረጃ መሠረት ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል፣ ደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ አውሮፕላን ማረፊያና ኬንያ በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል፣ ሕገወጥ የዝሆን ጥርስ ኮንትሮባንድ ዝውውር የሚካሄድባቸው ዋናዎቹ ቦታዎች መሆናቸው መገለጹን አስረድተዋል፡፡ ከዚያ በመነሳት ማሳሰቢያም ማስተላለፉን አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማሳሰቢያው መሠረት ከአንድ ተቋም ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረምና ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ ሰባት ዓለም አቀፍ ተቋማት በተገኙበት፣ የሳይተስ ሴክሬታሪያት ታዛቢዎች በተገኙበት ዓለም አቀፍ ቆጠራ፣ እ.ኤ.አ. ከዲሴምበር 16 እስከ 22 ቀን 2013 መደረጉንና እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2014 ለሳይተስ ሴክሬታሪያት እንዲደርስ መደረጉን አቶ ዳውድ አብራርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ስለሕገወጥ የዱር እንስሳት እ.ኤ.አ. በ2014 በለንደን በተደረገ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ተገኝታ በሠራችው ሥራ የምሥራቅ አፍሪካ ሞዴል ሆና መወሰዷን አክለዋል፡፡

ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተገኘ የዝሆን ጥርስና ውጤቶቹ እ.ኤ.አ. ከ1989 ጀምሮ በተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ መሠረት፣ ማንኛውም አገር የዝሆን ጥርስን ለገበያና ለንግድ ማዋል እንደማይቻል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በተደረሰው ስምምነት መሠረትም ኢትዮጵያም ያከማቸችውን ሕገወጥ የዝሆን ጥርሶችና ውጤቶች ለማቃጠል መወሰኗን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ አከማችቶ ማስቀመጥ የፀጥታ ችግርም እንደሚኖረው አክለዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ታኅሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ አማካይነት፣ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲቃጠሉ መደረጉንም አቶ ዳውድ ገልጸዋል፡፡

በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ከሚቃጠሉት የዝሆን ጥርሶች፣ ከእንጨትና ከኬሮሲን፣ እንዲሁም ከሚቃጠለው አመድ የሚወጣው ካርቦን ዳይኦክሳይድ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከል፣ በ30 ሔክታር ቦታ ላይ 90 ሺሕ ችግኞች እንደሚተከሉም ገልጸዋል፡፡

ችግኞቹ የሚተከሉበት ደን ያለበት ቦታ ‹‹በሕገወጥ አዳኞች የተገደሉ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ዝሆኖች መታሰቢያ ደን›› ተብሎ እንደሚጠራም አክለዋል፡፡ ለዝሆኖቹ መታሰቢያ ሐውልት እንደሚገነባም ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዘጠኝ ሬንጆች በሳር የተሸፈኑ ቦታዎች ከ1,900 በላይ ዝሆኖች፣ ከ900 እስከ 1,100 የሚሆኑ ዋልያዎችና 900 ቆርኬዎች እንደሚገኙና የቀይ ቀበሮም ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አቶ ዳውድ ገልጸዋል፡፡

ቃጠሎው ሲካሄድ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልማት ፕሮግራም ተወካዮች፣ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ አምባሳደር ግሬግ ዶሪና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...