Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ አስተዳደር በሦስት ዓመታት 116.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የመከላከኛ ዘመን ወጥ ማዕቀፍ አዘጋጀ፡፡ በወጥ ማዕቀፉ የከተማው አስተዳደር በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለሚያስፈልገው ወጪ 116.8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡

በአዲሱ ዕቅድ በ2008 ዓ.ም. 34.2 ቢሊዮን ብር፣ በ2009 ዓ.ም. 39.32 ቢሊዮን ብር በ2010 ዓ.ም. ደግሞ 43.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገልጿል፡፡ ቢሮው በመካከለኛ ዘመን የወጥ ማዕቀፍ ሰነዱ ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከማዕከልና ከክፍለ ከተማ ባለሥልጣናት ጋር መክሯል፡፡ የአዲስ አበባ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፎኢኖ ፎላ እንዳሉት፣ ሰነዱ ባለፉት አምስት ወራት ጥናት ተደርጎበት የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ የከተማውን መሠረተ ልማት ደረጃ ከፍ ያደርጋል ከመባሉም ባሻገር፣ ድህነትንና ሥራ አጥነትን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሏል፡፡

አቶ ፎኢኖ እንዳሉት፣ ይህ በጀት በከተማው ውስጥ የተጀመሩ የመሠረተ ልማቶችን ማጠናቀቅ ከማስቻሉም በላይ፣ በአሁኑ ወቅት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ 28 በመቶ የከተማው ነዋሪዎችን ቁጥር ወደ 20 በመቶ ዝቅ ማድረግ ያስችላል፡፡ በተለይም በካፒታል ወጪዎች 60 በመቶ ድርሻ ይይዛሉ የተባሉት የመንገድ ግንባታ፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክቶችና የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ  ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች በተጓዳኝ አዳዲስ የትምህርትና የጤና ተቋማትና የወጣት ማዕከላት ግንባታዎች መካተታቸው ተገልጿል፡፡

ይህ ሰነድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከተመከረበትና ጠቃሚ ሐሳቦች ከተካተቱበት በኋላ ለካቢኔ ይቀርባል፡፡ አቶ ፎኢኖ እንደገለጹት፣ ይህ የመካለኛ ዘመን ገቢ ማሰባሰቢያ ማዕቀፍ ከሁለተኛው የዕድገትና ትንራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ የአምስት ዓመቱ ዕቅዱ በዋነኛነት በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራ ዓብይ ኮሚቴ ሲኖረው፣ ከዓብይ ኮሚቴው በተጨማሪ በከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚመራ  በስድስት ንዑሳን ኮሚቴዎች መደራጀቱን አቶ ፎኢኖ ገልጸዋል፡፡

ገቢን በተመለከተ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም የከተማው ገቢ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ በ2000 ዓ.ም. ሦስት ቢሊዮን ብር የነበረው በዚህ ዓመት በግማሽ ዓመት ብቻ 11.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ይሰበሰባል የተባለው በ2000 ዓ.ም. ከተሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር በአሥር እጥፍ ብልጫ አለው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች