ከሚያዚያ 10 እስከ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው የጣና ከፍተኛ እርከን የውይይት መድረክ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአፍሪካ እየተስፋፉ የመጡት ሃይማኖት ነክ የደኅንነት ሥጋቶች ላይ እንደሚመክር ታወቀ፡፡
የጣና ፎረም ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኤልሻዳይ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ የዘንድሮው የጣና ከፍተኛ እርከን የውይይት መድረክ ሰፊ መሠረት ይዞ የሚካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሚካሄደው መድረክ ተሳታፊዎቹ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አፍሪካውያንና ከምሥራቅ አፍሪካ በተለይም ከኢጋድ አባል አገሮች የሚመጡ ነበሩ፡፡ ይሁንና ይህን በመቀየር ዘንድሮ ከፈረንሣይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮችና ከተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች በተለይም ከምዕራብ አፍሪካ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
ካለፉት የጣና የውይይት መድረኮች በተለየ ዘንድሮ ከፎረሙ በፊት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ስለውይይት መድረኩ አስፈላጊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በራዲሰን ብሉ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፣ በዕለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና የመድረኩ መሥራችና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ ለተለያዩ የኤምባሲ ኃላፊዎች ስለመድረኩ ገለጻ መስጠታቸውንም አቶ ኤልሻዳይ ጠቁመዋል፡፡ መድረኩ ለሁለት ቀናት ከመምከሩ በፊት የ25 ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በፀጥታ ጉዳይ ላይ ክርክር እንደሚያደርጉም አቶ ኤልሻዳይ ገልጸዋል፡፡ የቅድመ መድረኩ እንቅስቃሴ በጋና አክራ በተደረገው የውይይት መድረክ መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ኤልሻዳይ፣ ውይይቱ የመድረኩን መሠረት ለማስፋት ወሳኝ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል፡፡
መድረኩ የሚመክርበት የሃይማኖት ነክ የደኅንነት ሥጋት እንደ አጀንዳ የተመረጠው በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. በኋላ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ በቦኮ ሐራም የደረሰው ጥቃትና በፈረንሣይ በቻርሊ ሄብዶ ጋዜጣ አዘጋጆች ላይ የደረሰው ጥቃት የአጀንዳውን ወቅታዊነት በማጠናከሩ ለተሳታፊዎች ተጨማሪ ፍላጎት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ አቶ ኤልሻዳይ ከዚህ በፊት በነበሩ የጣና መድረኮች እስከ አምስት የሚደርሱ የአገር መሪዎች ተሳታፊ ቢሆኑም፣ የውይይት መድረኩ አንድ ወር እየቀረው ዘንድሮ መድረኩን ለመታደም ከወዲሁ ሰባት የአገር መሪዎች እንደሚመጡ ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡ ለደኅንነት ሲባል ግን የመሪዎቹን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
በባህር ዳር በሚካሄደው የጣና የደኅንነት መድረክ የአፍሪካ የአገር መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የእምነት ተቋማት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የሚዲያ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ይታደሙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጣና ከፍተኛ እርከን የውይይት መድረክ በሰላምና በደኅንነት ላይ ያተኮረ ነፃ የውይይት መድረክ ሲሆን፣ ተቋሙን ለመመሥረት ተነሳሽነቱን የወሰዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋምና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጣና የውይይት መድረክ ቦርድ ሰብሳቢ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሲሆኑ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታሞ ምቤኪ፣ የቀድሞው የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒየር ቡዮያና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከመድረኩ አባላት መካከል ይገኛሉ፡፡