Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም 400 ሺሕ የ‹‹4G›› ሞባይል ኔትወርክ አስመረቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም በ1.6 ቢሊዮን ዶላር እያስገነባ ከሚገኘው የቴሌኮም ማስፋፊያ አካል የሆነውንና ዓለም የደረሰበትን ‹‹4G›› የሞባይል ቴክኖሎጂ መጋቢት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡

የፕሮጀክት ግንባታውን ያከናወነው ሁዋዌ የተባለው የቻይና ቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ፕሮጀክት አጋማሹን፣ በተለይም የአዲስ አበባ ኔትወርክ ማስፋፊያና አዲስ የ‹‹4G›› ኔትወርክ ተከላን ያካተተውን የከተማውን ፕሮጀክት አጠናቋል፡፡

ሁዋዌ የያዘው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ የነበረውን የ‹‹2G›› ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ወደ ‹‹3G›› የማሸጋገርና 400 ሺሕ ደንበኞችን የሚያስተናግድ የ‹‹4G›› ኔትወርክ መዘርጋት ያካትታል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የ‹‹2G›› እና ‹‹የ3G›› ኔትወርኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲዛይን የሚደረጉት የስልክ የድምፅ ግንኙነት በተሳካ ሁኔታ ለማድረግ ነው፡፡ ‹‹4G›› የኔትወርክ ዓይነት ግን የድምፅ ግንኙነትን የሚደግፍ ቢሆንም በአብዛኛው ዲዛይን የሚደረገው ፈጣን የዳታ (የመረጃ) ልውውጥን ለመደገፍ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የሞባይል ኔትወርክ ከ‹‹2G›› ወደ ‹‹3G›› እየተዘዋወረ ቢሆንም፣ በርካቶች ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጠው የ‹‹3G›› ኔትወርክ የፍጥነት ደረጃ ደስተኞች አለመሆናቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ተጠቃሚዎችን በሚገባ ያላረካው የ‹‹3G›› አገልግሎት ለተጠቃሚዎች እየተዳረሰ ባለበት ወቅት፣ ኢትዮ ቴሌኮም የ‹‹4G›› ኔትወርኩን አስመርቆ ወደ አገልግሎት በመግባት ላይ መሆኑን ማሳወቁ በርካቶችን አስገርሟል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራሂም አህመድ ግን የ‹‹4G›› ኔትወርክ አገልግሎት እጅግ ፈጣን እንደሚሆን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን አገልግሎት ላይ ከዋለው የ3G ኔትወርክ በ10 እጥፍ ይበልጣል፤›› ብለዋል፡፡

የተመረቀው የ‹‹4G›› ኔትወርክ ራሱን የቻለና 400 ሺሕ ደንበኞችን ብቻ የሚያስተናግድ በመሆኑ፣ የተባለውን አገልግሎት በሚገባ ለመስጠት ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ለሚፈልጉ ነዋሪዎች ያላቸውን ነባር ሲም ካርድ መቀየር ሳያስፈልጋቸው፣ የ‹‹4G›› አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ወይም ደግሞ አዲስ ሲም ካርድ በማውጣት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች