Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአውሮፕላን በመጥለፍ የተከሰሰው ረዳት አብራሪ በሌለበት በጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ

አውሮፕላን በመጥለፍ የተከሰሰው ረዳት አብራሪ በሌለበት በጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ

ቀን:

ከሁለተኛው ክስ ነፃ ወጥቷል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውንና የበረራ ቁጥሩ ET-702 ቦይንግ 767 አውሮፕላን በመጥለፍ፣ ከመዳረሻው ውጪ እንዲያርፍ በማድረግና ተሳፋሪዎችን ለአደጋ በማጋለጥ ወንጀል ክስ የተመሠረተበት ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ፣ በሌለበት በ19 ዓመታት ከስድስት ወራት በጽኑ እስራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ወሰነ፡፡

ዳኛ ዮሴፍ ኪሮስ፣ ዳኛ ማጫሽወርቅ ነገደና ዳኛ ኃይሉ ኤራጎ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን ላይ ባስተላለፉት ቅጣት እንዳብራሩት፣ ረዳት አብራሪው ዋና አብራሪ ፓትሪዚዮ ባርቤሪ መፀዳጃ ቤት ሲገቡ፣ የመፀዳጃ በሩን በመቆለፍ በሱዳን አድርጎ ወደ ጣሊያን ሮም ይበር የነበረውን አውሮፕላን አቅጣጫውን ያላግባብ ቀይሯል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈቃድ ውጪ ወደ ስዊዘርላንድ አየር ክልል ውስጥ በማስገባት ተሳፋሪዎቹንና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ በመጨረሻ በስዊዘርላንድ (ያለ መዳረሻው) ጄኔቭ ከተማ እንዲያርፍ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ረዳት አብራሪው በአገር ውስጥ ባይኖርም፣ ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት ወንጀል በመሆኑ ተሳፋሪዎችን ለአደጋ በማጋለጥና በሕገወጥ መንገድ በጉዞ ላይ የነበረን አውሮፕላን የመያዝ ወይም የማገት ወንጀል መፈጸሙን በመግለጽ ክስ መቅረቡን በዝርዝር አስፍረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን የወንጀል ሕግ 507(1)፣ ማለትም ማንም ሰው በኃይል፣ በዛቻ ወይም  በማናቸውም ሌላ ማስፈራሪያ ዘዴ፣ በተንኮል ወይም በሌላ ሕገወጥ መንገድ በአገልግሎት ወይም በበረራ ያለ ወይም በማረፊያው የቆመ አውሮፕላንን አስቦ የያዘ ወይም በቁጥጥር ሥር ያዋለ፣ ከ15 እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ የሚደነግገውን መተላለፉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

ተከሳሹ አውሮፕላኑን በሕገወጥ ሁኔታ እንዲያርፍ ባደረገበት ስዊዘርላንድ እጁን ለመንግሥት ሰጥቶ በእስር ላይ መሆኑ የተሰማ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በደረሰው ክስ መሠረት ተከሳሹን ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ አዞ ነበር፡፡ ፖሊስ ፈልጎ ሊያገኘው እንዳልቻለ ለፍርድ ቤቱ ሲናገር፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ 73ኛ ዓመት በቁጥር 253 በዕለተ ረቡዕ ዕትም ጥሪ እንዲደረግለት አስደርጎ ሊቀርብ ባለመቻሉ፣ ክሱ በሌለበት እንዲታይ ብይን ከሰጠ በኋላ ክሱ ረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን በሌለበት ቀጥሏል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በቀጥታ ያለምንም ተከራካሪና ተቃዋሚ ተከሳሹ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ በወቅቱ ዋና አብራሪ የነበሩትን ጣሊያናዊውን አብራሪ ሚስተር ፓትሪዚዮ ባርቤሪን፣ በዕለቱ የበረራ አስተናጋጆች ኃላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ሜሮን ሙሉጌታንና የአውሮፕላኑ የበረራ አስተናጋጆች የነበሩትን ህሊና ሶሪ፣ ሜሮን ዳምጠውና ኤፍሬም ማሞ የተባሉ ምስክሮቹን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ከአየር መንገዱ ስለበረራ ቁጥር ET-702 በዕለቱ ስለነበረው የተከሳሹን የጤንነት ሁኔታ የሚያስረዳ ሰነድና ተከሳሹን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የጻፈውን ደብዳቤም አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ምስክሮችና ሰነዶች ሲመረምር፣ ተከሳሽ ረዳት አብራሪ ሆኖ መመደቡን፣ ጉዞው ከአዲስ አበባ ወደ ሮም መሆኑን፣ 193 መንገደኞችንና ዘጠኝ የአውሮፕላኑ ሠራተኞችን አሳፍሮ እንደነበር መገንዘብ መቻሉን ገልጿል፡፡ ሱዳን አየር ክልል ውስጥ እንዳለ አቅጣጫውን እንዲቀይር በመደረጉ፣ 223,336.46 ዩሮ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ካቀረበው የሰነድ ማስረጃ መረዳቱን ፍርድ ቤቱ በስፋት ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹን መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ጥፋተኛ ብሎታል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በረዳት አብራሪ ኃይለ መድኅን አበራ ላይ ያቀረበበት ሁለተኛ ክስ ተከሳሹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 508(1) የተደነገገውን በመተላለፍ፣ የጠለፈውን አውሮፕላን በድንገትና በፍጥነት ሁለት ጊዜ “ከፍና ዝቅ” በማድረግ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ የምግብ ማቅረቢያ ቁሳቁሶች በመንገደኞቹ ላይ እንዲገለባበጡ በማድረግና አውሮፕላኑን አስጊ ሁኔታ ላይ መጣል ወንጀል መሆኑ በውሳኔው ላይ ሰፍሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ፣ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች በረዳት አብራሪው የተፈጠረውን ነገር ያወቁት አውሮፕላኑ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ካረፈ በኋላ መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የተከሳሹ ድርጊት በማንኛውም በረራ ላይ ሊያጋጥም የሚችል ከሚባል ውጪ፣ በሕጉ እንደተጠቀሰው በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት ያላደረሰና በአውሮፕላኑም ላይ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ባለመሆኑና ዓቃቤ ሕግም እንደ ክሱ ያላስረዳ መሆኑን ገልጾ፣ ተከሳሹ ከሁለተኛው ክስ በነፃ እንዲሰናበት ወስኗል፡፡

ፍርድ ቤቱ መጋቢት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው የ19 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት ፍርድ ላይ እንዳብራራው፣ የአውሮፕላኑ መንገደኞች ከቦታ ቦታ ሲጓጓዙ ወደ አውሮፕላኑ ከገቡበት ሰዓት ጀምሮ የሚፈልጉበት ቦታ እስከሚደርሱ ድረስ፣ ለሕይወታቸውና ለደኅንነታቸው የሚተማመኑት አውሮፕላኑን የሚያበሩትን ሰዎች ነው፡፡ በመሆኑም አብራሪዎችም በተጠበቁበት ኃላፊነት ልክ መገኘት ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ ተከሳሹ ለማንም የማይሰጥ ከባድ ኃላፊነት በአየር መንገዱ የተሰጠው ቢሆንም፣ የራሱን ፍላጎት ለማሟላት አስቦ ከእሱ የተሻሉትን ዋና አብራሪ ወደ አውሮፕላን መቆጣጠሪያ ክፍል እንዳይገቡ አድርጓል፡፡ አውሮፕላኑንም በሕገወጥ መንገድ ተቆጣጥሮ ከአምስት ሰዓት በላይ አብርሯል፡፡ ከመዳረሻው ቦታ ውጪ እንዲያርፍም አድርጓል፡፡ በምስክሮቹ እንደተገለጸው አውሮፕላኑ ጄኔቭ ካረፈበት ሁለትና ሦስት ደቂቃ ቢቆይ ኖሮ ነዳጅ በመጨረሱ በመንገደኞቹ ላይ ይደርስ የነበረው ከፍተኛ ጉዳት ከግምት ውስጥ ሲገባ፣ የወንጀል አፈጻጸሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚመደብ ሆኖ እንዳገኘው አብራርቷል፡፡ የወንጀል ደረጃው ከፍተኛ ስለተባለ ሊወሰንበት የሚገባውን መነሻ ቅጣት በቅጣት አወሳሰን መመርያው መሠረት ሲሰላ፣ 19 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እስከ 21 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት የሚደርስ ቅጣት ሊጣልበት የሚችል መሆኑን ገልጿል፡፡

የተከሳሹን የወንጀል አፈጻጸምና የነበረውን ከፍተኛ ኃላፊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በ19 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት መነሻ ቅጣት ይዟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ቅጣቱ እንዲከብድ የቅጣት ማክበጃ ቢያቀርብም፣ ቀድሞ የፈጸመው የወንጀል ሪከርድ የሌለበትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 53612 ላይ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም፣ አንድ የቅጣት ማቅለያ መያዙንም ፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

በተከሳሹ ላይ አንድ የቅጣት ማክበጃና አንድ የቅጣት ማቅለያ ምክንያቶች ቢቀርቡም፣ በመነሻነት ከተያዘው ቅጣት በላይ ከብዶም ይሁን ቀሎ የሚወስንበት ምክንያት ባለመኖሩ፣ በመነሻ ቅጣቱ በ19 ዓመታት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሙሉ ድምጽ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ፍርዱን ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...