Thursday, February 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማፈንገጥ አይቻልም!

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደምትነት ለአሥር ዓመታት ከፍተኛ ውጣ ውረድ የተደረገበት የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በስድስት አገሮች ተፈርሞ ይፋ የተደረገው፣ የዓባይ ውኃን በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም፣ ለመንከባከብና ለማልማት ነው፡፡ ስምምነቱ እያንዳንዱ የተፋሰስ አገር በግዛቱ ውስጥ የመጠቀም መብትን ሲያጐናጽፍ፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ መርህን በመከተል ለውኃው ልማት አስተዋጽኦ ማድረግን ያካትታል፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. በ2010 በኡጋንዳ ዋና ከተማ ኢንተቤ የፀደቀው ስምምነት ከዚህ በፊት በግብፅና በቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ፣ ከዚያም በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረጉ ኢፍትሐዊ የሆኑ ስምምነቶችን ውድቅ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ስምምነቱን የፈረሙና በፓርላማቸው ያፀደቁ ወይም በማፅደቅ ሒደት ላይ ያሉ አገሮች ይገዙበታል፡፡ ከዚህ ስምምነት ማፈንገጥ አይቻልም፡፡ አራት ነጥብ፡፡

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረትም ሆነ መነሻ ይህ ስምምነት ነው፡፡ የታችኞቹ የተፋሰስ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) ከዚህ ስምምነት በተቃራኒ ቢቆሙም፣ ሱዳን የስምምነቱ አካል ሳትሆን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ብትደግፍም፣ ግብፅ ግድቡ በውኃ ድርሻዬ ላይ ጉዳት ያመጣል ብላ እላይ ታች ብትልም፣ ኢትዮጵያ አሁንም በፅናት መቆም ያለባት ከዓባይ ተፋሰስ ስምምነት ፈራሚ አገሮች ጋር ነው፡፡ ግብፅ ባመቻት መንገድ ሁሉ ለግድቡ ግንባታ መሰናክል የሚሆኑ አማራጮችን ብታቀርብም፣ የኢትዮጵያ ኃላፊነት ግብፅ በግድቡ ምክንያት ጉዳት እንደማይደርስባት በፅናት ማስረዳት፣ ይልቁንም ግብፅ ለፍትሐዊ የዓባይ ወንዝ ውኃ አጠቃቀም ተባባሪ እንድትሆን ማግባባት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ በግልጽ በሰፈረው መሠረት፣ በሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደምትወስድ ቃል መግባት ይጠበቅባታል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ተገልጿል፡፡ በትብብር ማዕቀፉ ስምምነት ውስጥ ጉልህ የሆነ ጉዳት ማድረስ እንደሚያስጠይቅ በግልጽ በመቀመጡ፣ ኢትዮጵያም ይህንኑ ገዥ ሕግ ታከብራለች፡፡ ከዚህ ውጪ የቀድሞ ኢፍትሐዊ ስምምነቶችን በዚህ ዘመን እየጐተቱ ችግር ለመፍጠር የሚያውኩ ካሉ በቃችሁ ነው መባል ያለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻዋን አይደለችም፡፡ የተፋሰሱ አገሮች አብረዋት አሉ፡፡ ይልቁንም የትብብር ማዕቀፉን የሚፃረር ሌላ ስምምነት ቢደረግ ነው አደጋ የሚፈጠረው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ስምምነት ማፈንገጥ አይቻልም፡፡

የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የሆነ የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ችግሮች ሲፈጠሩ እንኳ፣ እንዴት መፈታት እንዳለባቸው በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ይህ ስምምነት በፍትሐዊነትና በትብብር ለመበልፀግ የሚያስችሉ ታሪካዊ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ የተፋሰሱን አገሮች ሕዝቦች በእኩልነት የሚያስተናግድና ለበለጠ ትብብር የሚያነሳሳ ነው፡፡ ከዚህ ስምምነት ማፈንገጥ ማለት ደግሞ ለኢፍትሐዊነትና ላልተገባ ድርጊት የሚያጋልጥ ነው፡፡ ወደ ቀድሞዎቹ አድሎአዊና አሳፋሪ ስምምነቶች የሚመልስ ነው፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ተቀባይነት የማይኖረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያም ሆነ የሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦች የማይቀበሉት ነው፡፡ ከትብብር ይልቅ ጠላትነትን፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን፣ ከብልፅግና ይልቅ ድህነትን፣ ከዘመናዊነት ይልቅ ኋላቀርነትን የሚያበረታቱት የቀድሞዎቹ ስምምነቶች ዳግም ለድርድር ሊቀርቡ አይገባም፡፡ ተቀባይነት የላቸውም፡፡

አሁን ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የዓባይ ውኃ አጠቃቀምንና ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ‹‹ፖለቲካዊ ስምምነት›› በካርቱም ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንትም በኢትዮጵያ ለሦስት ቀናት ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ በፓርላማ ተገኝተውም ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ከግብፅ አካባቢ ሰሞኑን የተለመደው የፕሮፓጋንዳ ንፋስ በስሱ ሽው ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ አማካይነት ተዘጋጅቷል የተባለው ይህ ‹‹ፖለቲካዊ ስምምነት›› ካይሮ ደርሶ እንደተነበበና ግብፅ ፍላጎቶቿን እንዳካተተችበትም እንዲሁ በስሱ ተወርቷል፡፡ የመጀመሪያው የግብፅ ዓመታዊ የውኃ ፍጆታ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ፈጽሞ እንዳይቀንስ፣ ይህም በቂ ባለመሆኑ እንዲጨምር የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚሞላው 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንዲቀንስ የሚለው ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ ከግብፅ የመጣ ተባራሪ መረጃ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል እንዲህ የሚባል ነገር የለም ተብሏል፡፡ ጥሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ባለሥልጣናት በዓባይ ጉዳይም ሆነ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ መነጋገራቸው ተገቢ ነው፡፡ ይደገፋል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት አለመፍጠሩ እንዲጠና መደረጉም እንዲሁ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አሁን የተለየ ‹‹ስምምነት›› ሊደረስ ነው ሲባል ግን፣ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ፈራሚ አገሮች ሁሌም መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ስምምነቱ ደግሞ ገዥ ሕግ መሆኑ መቼም ቢሆን መረሳት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የዚህ ስምምነት የጀርባ አጥንት ስለሆነች በማንም ተፅዕኖ መንበርከክ የለባትም፡፡ ሰሞኑን ይደረጋል በተባለው የሦስቱ አገሮች ‹‹የፖለቲካ ስምምነት›› ይህ በቁርጠኝነት መንፀባረቅ አለበት፡፡ በአደባባይ መነገርም አለበት፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ሕዝብን ወክሎ አስፈጻሚ ነው፡፡ ገንዘቡንና ጉልበቱን አስተባብሮ የሚገነባውን ይህን ግድብ ሕዝቡ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚያየው ሲሆን፣ ከዚህም በላይ ደግሞ የታሪኩ አሻራ ነው፡፡ ሕዝባችን ደግሞ ወንድምና እህት የሆኑት የግብፅና የሱዳን ሕዝቦችን በድግቡ ግንባታ ምክንያት እንደማይጎዳ ደጋግሞ በመንግሥት አማካይነት ቃል ገብቷል፡፡ ይህም ቃል ይከበራል፡፡ በተለይ ግብፆች የኢትዮጵያ ሕዝብን ቃል መቀበል አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የመተማመንና የመከባበር መገለጫ የሆነ የአደራ ቃል ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የሌለ ሥጋት በመፍጠር የግድቡ ውኃ የመያዝ አቅም መቀነስ አለበት፣ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይልም እንዲሁ ማነስ አለበት የሚለው ፍላጎታቸው እንዲገታ መደረግ አለበት፡፡ ኢፍትሐዊ አቀራረብ ስለሆነ በግልጽ ይነገራቸው፡፡

ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ የግብፅ መንግሥት ለትብብር ፍላጐት ማሳየቱ ጥሩ ነው፡፡ ይደገፋል፡፡ ይበረታታል፡፡ ነገር ግን ከጥንት ጀምሮ ውስጥ ለውስጥ እንደ ሳር ውስጥ እባብ የሚስለከለከው የግብፅ ፖለቲከኞች ሴራ ግን የለም ብሎ መዘናጋት ሞኝነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ግብፆች በጦር ከማስፈራራት እስከ የፋይናንስ ማዕቀብ ድረስ በርካታ አሻጥሮችን ፈጽመዋል፡፡ ይህንን እኩይ ተግባራቸውን እያሰቡና አንድ ዕርምጃ ወደፊት እየቀደሙ፣ በብልጠትና በብልኃት የታጀበ ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ማከናወን ጠቃሚ ነው፡፡ ግብፆች ወደኋላ ለመመለስ ሲያሴሩ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ እነሱን ወደ ትብብር ማዕቀፉ መጐተት አለባት፡፡ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የዓባይ ወንዝ አጠቃቀም መርህ ያለው እዚህ ታሪካዊ ስምምነት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

የግብፅ መንግሥት የራሱን የመጫወቻ ካርድ እየሳበ ሚዛን ለማሳት ጥረት ሲያደርግ፣ በጨዋና በዲፕሎማሲ ቋንቋ ፈሩን እንዲይዝ መደረግ አለበት፡፡ ያልተገባ ‹‹ጨዋታ›› ውስጥ እየተገባ ፀብ ከመቆስቆስ ይልቅ፣ ትብብር ይበልጣል መባል አለበት፡፡ በካርቱም ቆይታም ሆነ በአዲስ አበባው የአልሲሲ ጉብኝት ወቅት ከፍጥጫ ይልቅ መቀራረብና መተባበር እንደሚበጅ፣ ይህም ትብብር ዘላቂ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ደግሞ በሚገባ የሰፈረው የተፋሰሱ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ውስጥ እንጂ፣ ያረጁትና ያፈጁት ስምምነቶች ውስጥ አይደለም፡፡ ይህም በግልጽ ሊነገር የግድ ይላል፡፡

የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መከበር አለበት የሚባለው ለተፋሰሱ አገሮች መድኅን ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ስምምነቱ ለፍትሐዊነትና ለምክንያታዊነት የቆመ ነው፡፡ ሁሉንም አገሮች በእኩልነት የሚያይ ነው፡፡ እኩል ተጠቃሚነትን መርህ የሚያሰፍን ነው፡፡ ጠላትነትን አስወግዶ ትብብርን የሚያጠናክር ነው፡፡ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦች በፍትሐዊና በምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ እንዲተሳሰሩና እንዲበለፅጉ ይረዳል፡፡ ለዚህም ነው ከዚህ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ማፈንገጥ የማይቻለው!         

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...

ቢሮአቸውን ዘግተው በተገልጋዮች ላይ የቅርብ ሩቅ የሆኑ ሹማምንት ጉዳይ ያሳስባል

በንጉሥ ወዳጅነው  በአሁኑ ወቅት ብቻ ሳይሆን ትናንትም ቢሆን የተመረጡም ሆኑ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...