የግብፅ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው በፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ
የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር ሆሳም አልሞጋሃዚ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች የመግባቢያ ሰነድ፣ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ውኃ የመያዝ አቅም እንድትቀንስ ያደርጋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ አቻቸው አጣጣሉት፡፡
በቅርቡ የሚቀጠር አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በግብፅና በሱዳን ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ካረጋገጠ፣ ሦስቱ አገሮች ሰሞኑን በደረሱበት የፖለቲካ መግባባት መሠረት ኢትዮጵያ የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም እንድትቀንስ ትገደዳለች ሲሉ የግብፅ ሚኒስትር ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን መናገራቸው ተሰምቶ ነበር፡፡
የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር እየጠቀሱ የነበረው ስምምነት ሰሞኑን የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮች በካርቱም ተገናኝተው የመግባቢያ ስምምነት ያዳረጉበትን የፖለቲካ ሰነድ ነው፡፡
ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረቀቀ መሆኑን ለማወቅ ቢቻልም፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወሰን ተሻጋሪ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አምባሳደር ኢብራሒም ኢድሪስ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትርም ስምምነቱ ኢትዮጵያ የግድቡን መጠን እንድትቀንስ ሊያስገድዳት የሚችል ነው ካሉ በኋላ፣ የግድቡን የግንባታ ሒደት ሦስቱ አገሮች በጋራ እንዲቆጣጠሩት ያስችላልም ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዝርዝር የፖለቲካ ስምምነቱ በሦስቱም መንግሥታት እስካሁን ይፋ አልሆነም፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ አገልግሎት ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የግብፅ አቻቸውን መግለጫ አጣጥለውታል፡፡
‹‹መስማማት የምንችለው በተወያየንበት ጉዳይ ነው፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በሱዳን በተወያዩበት ወቅት በግድቡ ውኃ የመያዝ መጠን ላይ እንዳልተነጋገሩና ሰነዱም ላይ አለመካተቱን አስታውቀዋል፡፡
ይህንን የግድቡ መጠን ይቀንስ የሚል መከራከሪያ ግብፆች በተደጋጋሚ አንስተው የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም በግልጽ ተነግሯቸዋል ብለዋል፡፡ የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ ጉልህ ጉዳት አለማድረስንና የመሳሰሉ አጠቃላይ መርሆዎችን የሚመለከቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በንዑስ ተፋሰስ ሥር ያሉ አገሮች የራሳቸውን ስምምነት ማድረግ እንደሚችሉና በምሥራቅ የተፋሰሱ አገሮች መካከል የተደረሰው ስምምነትም ይህንን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
በተያዘው ፕሮግራም መሠረት ሦስቱ አገሮች በዚህ ሳምንት የፖለቲካ ስምምነቱን በሱዳን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ሳምንትም የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በኢትዮጵያ ከመጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፓርላማ በመገኘትም ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስና ከኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡