Saturday, September 24, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ጤንነት ይመርመር!

  የአንድ አገር ኢኮኖሚ አንፃራዊ ጤንነት ከሚለካባቸው በጣም ጠቃሚ ከሆኑ መለኪያዎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ የክምችት መጠንና አያያዝ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህንን ክምችት በሚፈለገው መጠን በውጤታማ መንገድ መጠቀምም ለኢኮኖሚው አንፃራዊ ጤንነት ይበጃል፡፡ የአገራችን የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ለኢኮኖሚው መረጋጋት አመላካች በመሆኑ፣ ጠንካራ ቁጥጥርና ግምገማ ካልተካሄደበት ለብክነትና ለምዝበራ ይጋለጣል፡፡ በተለይ ከአገሪቱ ወደ ውጭ የሚወጣና ወደ አገሪቱ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ አጥብቆ ጠያቂና ተመልካች ከሌለው ጥፋቱ የከፋ ይሆናል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ጠቃሚ የሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡

  1. የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት አልተጣጣሙም

  በአሁኑ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፡፡ አስመጪዎች ወረፋ እየጠበቁ የውጭ ምንዛሪ ከማግኘታቸው በተጨማሪ፣ በቆይታቸው ወቅት በሚያስገቡዋቸው ዕቃዎች ዋጋ ላይ በሚታይ ጭማሪ ምክንያት በገበያው ውስጥ ንረት ይፈጠራል፡፡ ለዚህም በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ኩባንያዎች በመከፈታቸውና የተለያዩ ቢዝነሶች በመድራታቸው ምክንያት፣ አቅርቦትና ፍላጎት እየተጣጣሙ አይደለም፡፡ በመሆኑም ቅድሚያ በጣም መሠረታዊ ለሚባሉ ገቢ ዕቃዎች ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከፍላጎት በማነሱ ሳቢያ ወደ ውጭ ለተለያዩ ጉዳዮች በሚጓዙ ግለሰቦች ላይ ሳይቀር ጫናው ይስተዋላል፡፡ በአስመጪነት የተሰማሩ ኩባንያዎችና ጥሬ ዕቃ የሚፈልጉ አምራቾችም ተቸግረዋል፡፡ አቅርቦትና ፍላጎቶችን ለማጣጣም የሚረዳ የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሔ የግድ ይላል፡፡

  1. የውጭ ምንዛሪ ገቢ መመናመን

  በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ገበያዎች ውስጥ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ከኤክስፖርት የሚገኙ የውጭ ምንዛሪ ገቢዎች እየቀነሱ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ከመንግሥት በሚወጡ ሪፖርቶች ዕቅድና አፈጻጸም አለመጣጣማቸው ታይቷል፡፡ አገሪቱ በተለይ ከግብርና ምርት የምታገኛቸው የውጭ ምንዛሪ ገቢዎች ሲያሽቆለቁሉና እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎችና የመሳሰሉት በተገኙበት ዋጋ እንዲሸጡ ማሳሰቢያ ሲሰጥ፣ ጎን ለጎን ችግሩ የት ድረስ እንደሚጓዝ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በዓለም ገበያ ውስጥ በሚታዩ ችግሮች ምክንያት ላኪዎች ለኪሳራ ለሚዳርጉዋቸው የኤክስፖርት ምርቶች ድጎማ ማድረግ ጭምር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በአገሪቱ የገቢ ንግድ መግዘፍ ምክንያት የሚገኘው ውስን የውጭ ምንዛሪ አላወላዳ ሲል ችግሮች ተባብሰው እንዳይቀጥሉ መላ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ የኤክስፖርት ምርቶችን ብዛትና መዳረሻዎችን በተመለከተ በወቅታዊ መረጃ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ማድረግ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡     

  1. ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ፍልሰት

  ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ፍልሰት በተለያዩ መንገዶች የሚከሰት ሲሆን፣ በአገራችንም ይኼው ችግር ጎልቶ ይታያል፡፡ አገሪቱ በዓመት አሥር ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ከምታጣባቸው መንገዶች መካከል አንዱ፣ በውጭ ዜጎችና ኩባንያዎች አማካይነት የሚካሄደው ዝርፊያ ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ጥቁር ገበያ እያስፋፉ ነው፡፡ የተለያዩ ሬስቶራንቶችን፣ ሆቴሎችንና የንግድ ተቋማትን የከፈቱ የውጭ ዜጎች በገፍ የሚያወጡት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከማሻቀቡም በላይ ጥቁር ገበያውን እያደሩት ነው፡፡ እንዲሁም የገቢ ዕቃዎችን ከዋጋቸው በላይ እንደተገዙ በማስመሰል (Over Invoicing) አገር ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ለምሳሌ 100 ዶላር የወጣበትን ምርት 500 ዶላር እንደወጣበት አድርገው የውጭ ምንዛሪ ያጋብሳሉ፡፡ ይህንን ዓይነቱን የውጭ ምንዛሪ ዝርፊያ በተለያዩ ዘዴዎች ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ብርቱ ቁጥጥር ሊደረግበት የሚያስፈልገው ሕገወጥ ተግባር ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ጤንነትም ያናጋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ተግባር ውስጥ ዜጎችም ተሳታፊ ናቸው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡   

  1. የሐዋላ ኩባንያዎችና የጥቁር ገበያ መድራት

  በአሁኑ ጊዜ በርካታ የገንዘብ አስተላላፊ (ሐዋላ) ኩባንያዎች በአገሪቱ ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኩባንያዎች የሚያስከፍሉት የአገልግሎት ኮሚሽን እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት፣ በርካቶች ወደ ጥቁር ገበያው እንዲሳቡ ተደርገዋል፡፡ በተለይ በውጭ የሚገኙ ዜጎች የውጭ ምንዛሪውን በመደበኛው መንገድ ከመላክ ይልቅ፣ በግለሰቦች እጅ በመላክ ጥቁር ገበያውን አማራጭ አድርገውታል፡፡ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን እያጣች ነው፡፡ እንደ አማራጭ የሚታዩት የሐዋላ ኩባንያዎች አሠራር እንዲሻሻል ካልተደረገ በስተቀር የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የበለጠ ችግር ይገጥመዋል፡፡ ጥቁር ገበያው በተስፋፋ ቁጥር ደግሞ ሕገወጥነት የበለጠ ይስፋፋል፡፡ መፍትሔ ይፈለግ፡፡

  1. ጠንካራ ቁጥጥር ካልኖረ ችግሩ ይቀጥላል

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከበርካታ ተግባራቱ መካከል የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ጤንነትን መጠበቅ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የአበዳሪ አገሮችንና የባንኮችን ቀልብ የሚስብ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማፈለገው ሁኔታ እንዲራመድ የማድረግ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ክምችቱ ጤነኛ የሚሆነው አጠቃቀሙ ሕጋዊ መንገድን ሲከተል ብቻ ነው፡፡ የንግድ ባንኮች የውስጥ አሠራሮችን ጤናማነት ከመፈተሽና የዕርምት ዕርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ የአጭርና የረጂም ጊዜ መፍትሔዎችን ጭምር ማየት ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ንግድ ባንኮች ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆኑ የማኑፋክቸሪንግና መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጭ ለሚያስገቡ አስመጪዎች በአግባቡ የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጡ ማገዝ አለበት፡፡ አገሪቱ ካላት ክምችት ላይ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ባንኮቹ እንዲሰጡ በማድረግና በባንኮቹ መካከል የሚከናወነው ግብይት ጤናማነት ተጠብቆ እንዲካሄድ ማድረግ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው፡፡ በተጨማሪም ላኪዎች በዓለም ገበያ ውስጥ የሚያጋጥማቸው የዋጋ ማሽቆልቆል ለኪሳራ እንዳይዳርጋቸው አለሁ ማለት አለበት፡፡ ሁሉም አሠራሮች ጤናማ ሆነው እንዲቀጥሉ በከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል መታገዝ ይገባዋል፡፡

  በሌላ በኩል የረዥም ጊዜ ተግባሩ መሆን ያለበት የአገሪቱን ኤክስፖርት በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እዚሁ ማምረት ማስጀመር ነው፡፡ ይህ አገሪቱ የያዘችው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ቢሆንም፣ በጠንካራ አፈጻጸም ተግባራዊ ሊሆን ይገባል፡፡ ኤክስፖርት ተስፋፍቶ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተገኘ እንዲሄድ ሲፈለግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ሸቀጦች እዚሁ ሲመረቱ የውጭ ምንዛሪው ከብክነት ይድናል፡፡ ከሕገወጦችም ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ በተለይ በገቢና በወጪ ንግድ መካከል የሚታዩ ክፍተቶች ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መመናመንና ዝርፊያ ዋነኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅዱ ተግባራዊነት ይጠበቃል፡፡

  በአጠቃላይ በውጭ ምንዛሪ ክምችትና አጠቃቀም ላይ ተገቢው ጥበቃና ቁጥጥር ካልተደረገ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ጤንነት ችግር ነው የሚሆነው፡፡ ኢኮኖሚው ጤና ካጣ ስለዕድገቱ ማሰብ አይቻልም፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጠንካራ ቁጥጥር ካልተደረገበት ኢኮኖሚውን ጤና አሳጥቶ መናጋት ያመጣል፡፡ ለዚህም ነው የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ጤንነት ይመርመር የሚባለው፡፡ በጥብቅ ይታሰብበት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

  ለቻይናው ፖሊጂሲኤል ኩባንያ የተሰጠው ውል ተቋረጠ

  የማዕድንና ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ አልምቶ ኤክስፖርት...

  የሕግ ክልከላዎችና የሚያስነሱት ቅሬታ

  በኢትዮጵያ የአገርና የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ተብለው የሚወጡ አንዳንድ ሕጎች፣...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...

  ሴረኝነት የሰላም ጠንቅ ነው!

  በአዲሱ ዓመት የመላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በወታደራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የሕዝባችንን ፍላጎት...