አሰለፈች መርጊያ ለአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷታል
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በወርቅ ደረጃ ከሚመድባቸው ዓመታዊ የሩጫ ውድድሮች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን ከወር በኋላ ይካሄዳል፡፡ ከመምና አገር አቋራጭ ውድድሮች ፊቱን ወደ ማራቶን ያዞረው ቀነኒሳ በቀለ በለንደን ከሚጠበቁ ተወዳዳሪዎች አንዱ የነበረ ቢሆንም፣ እንደማይወዳደር ታውቋል፡፡ በሴቶች የዱባይ ማራቶን አሸናፊዋ አሰለፈች መርጊያ ከወዲሁ የአሸናፊነቱ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ቀዳሚ ሆናለች፡፡
ባለፈው ጥር በተደረገው የዱባይ ማራቶን ከወሊድ በኋላ ተሳትፋ አሸናፊ የሆነችው አሰለፈች ርቀቱን 2 ሰዓት፣ 19 ደቂቃ፣ 31 ሰከንድ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ምንም እንኳ አንድ ማራቶን የሮጠ አትሌት ሁለተኛውን ማራቶን ለመወዳደር በቂ የማገገሚያ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቢመክሩም፣ በዱባይ ማራቶን ያስመዘገበችው ሰዓት በለንደን ከሚጠበቁ ፈጣን ሰዓቶች ሦስተኛ መሆኑ ለአትሌቷ መነሳሳትን ከመፍጠሩም በላይ ለውሳኔዋ ትክክለኛነት መነሻ ሳይሆናት እንዳልቀረም ይናገራሉ፡፡
በሚያዝያ ወር በሚደረገው በዚሁ የለንደን ማራቶን ከሚወዳደሩት አራት ምርጥ አትሌቶች አንዷ ሆና ስለመቅረቧም የአይኤኤኤፍን ድረ ገጽ ጨምሮ ዘገባዎች እየገለጹ ይገኛል፡፡ ከነዚህ አትሌቶች ኬንያውያቱ ኤድና ኪፕላጋት፣ ሜሪ ኪታኒ፣ ፕሪስካህ ጂፕቶና ራሷ አሰለፈች መርጊያ ይጠቀሳሉ፡፡
የለንደን ማራቶንና ሌሎችንም ታላላቅ ማራቶኖች የአዘጋጆችን ቀልብ በእጅጉ እየሳቡ ከሚገኙ አትሌቶች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን በግንባር ቀደምትነት መጠቀስ ከጀመሩ ሰነባብቷል፡፡ በዚሁ መነሻነት ለለንደን ተፎካካሪዎቿ ኬንያውያን ከወዲሁ ሥጋት እንደምትሆን ከምትጠበቀው አሰለፈች በተጨማሪ ያለፈው ዓመት የቶኪዮና የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ትርፊ ፀጋዬም ተመሳሳይ ግምት አግኝታለች፡፡ የአትሌቷ ምርጥ ሰዓትም 2 ሰዓት፣ 20 ደቂቃ፣ 18 ሰከንድ የበርሊን ውጤቷ ሲሆን፣ በለንደን ስትሮጥ የመጀመርያዋ እንደሆነም ታውቋል፡፡
ከምንጊዜም በላይ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀው የለንደን ማራቶን በጠንካራ ተፎካካሪነት ከተጠቀሱት አራቱ አትሌቶች በተጨማሪ በርቀቱ 2 ሰዓት፣ 21 ደቂቃ ማጠናቀቅ የቻሉ ሌሎችም ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉም እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከነዚህ አትሌቶች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ቱርካዊት የሆነችው ኤልቫን ዓብይ ለገሰ ትጠቀሳለች፡፡
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል ለሚጠበቀው የለንደን ማራቶን በረዥም ርቀት በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮናዎች ተደራራቢ ድሎች በማስመዝገብ ስሙን በወርቅ መዝገብ ያስቀመጠው ቀነኒሳ በቀለ አንዱ ነበር፡፡ አትሌቱ ባለፈው ጥር ተደርጎ በነበረው የዱባይ ማራቶን ተወዳድሮ ባይሳካለትም፣ ግን ደግሞ ከወር በኋላ በሚደረገው የለንደን ማራቶን እንደሚወዳደር ማስታወቁን ተከትሎ በውድድሩ ትልቅ ግምት ተሰጥቶዋቸው ከቆዩ አትሌቶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ አትሌቱ በለንደን ማራቶን እንዳይሳተፍ ምክንያት ተደርጎ የቀረበው ደግሞ በዱባይ ማራቶን ያጋጠመው ጉዳት እንደሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ቀነኒሳ ከረዥም ርቀት ወደ ማራቶን ፊቱን ካዞረ በኋላ ባለፈው ሚያዝያ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የፓሪስ ማራቶን የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር በማሸነፍ ነበር 42 ኪሎ ሜትር 195 ሜትር የሚሸፍነውን የማራቶን ሕይወቱን አንድ ብሎ የጀመረው፡፡