Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከተፈጥሮ ጋር እርቅ

ከተፈጥሮ ጋር እርቅ

ቀን:

ከሰፊው ሜዳ ባሻገር የባሌ ሰንሰለታማ ተራራ በጉም ተሸፍኖ ይታያል፡፡ ሜዳው ተጠናቆ ከተራራው በታች በኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኘው ኮረብታ ሲወጡ ቀዝቃዛው አየር ሰድሮ ይይዛል፡፡ የምንጐበኘው አካባቢ በእንጨትና ሽቦ የታጠረ ክልል ነው፡፡ አጥሩን አልፈው ወደ ክልሉ ሲዘልቁ ግዙፍ ዛፎች ይታያሉ፡፡ ወደ ኮረብታው መጨረሻ ያሉት ዛፎች በርዝማኔም በቁጥርም ይበልጣሉ፡፡ አስጐብኚያችን በዓይናችን ኒያላዎችን  እንድናፈላልግ ነገረን፡፡ በተለይ ሴት ኒያላዎች በቡድን በቡድን ሆነው ከጥቅጥቁ ደን ወደገላጣው ቦታ ስለሚወጡ በቀላሉ እንደሚገኙ አስታወቀ፡፡ ገለጻውን ሳይጨርስ ከዛፎቹ መሀከል ጥቂት ኒያላዎች ብቅ ብቅ አሉ፡፡

ቦታው ባሌ ዞን ዲንሾ ወረዳ የምትገኘው ሚዎ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ በአካባቢው ከሚገኙ የማኅበረሰቡ የተቀደሱ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች (ሳከርድ ናቹራል ሳይትስ) አንዱ ገደብ ገዳላ ይባላል፡፡ የአካባቢው አዛውንት አቶ ቱርኬ አዶኬ እንደሚሉት፣ ጥብቅ ቦታው የተለያዩ የእምነትና ባህላዊ ክንዋኔዎች የሚካሄዱበት ነው፡፡ ቦታው የተለያዩ የዱር እንስሳት መኖሪያም ሲሆን፣ ሰፋሪ ሰዎች ወይም የቤት እንስሳት እንዳይገቡበት ታጥሯል፡፡ ገደብ ገደላ የዱር እንስሳት ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሀገር በቀል ዕፅዋትም መገኛ ነው፡፡ በውስጡ ካሉ የዱር እንስሳት የምኒሊክ ድኩላና ኒያላ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ገደብ ገዳላ ከጥቂት ዓመታት በፊት አጥር እንዳልነበረው በአካባቢው የጥበቃ ሥራ የሚያከናውኑ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ወደ ውስጡ ሰዎችና የቤት እንስሳት ይገቡ ስለነበረም በውስጡ የነበሩ የዱር እንሰሳት አካባቢውን ለቀው ለመሸሽ ተገደው ነበር፡፡ በእርግጥ ከረዥም ዓመታት በፊት አካባቢው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ የዱር እንስሳት መኖሪያ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ የአካባቢው ማኅበረሰብ ገደቡን ጥሶ ወደ ክልሉ መግባት ጀመረ፤ የዱር እንሰሳቱም ሸሹ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ ገደብ ገዳላ ዳግም ከተከለለ በኋላ የቀድሞ ይዞታው ቀስ በቀስ እየተመለሰ ነው፡፡ አሁን ሰው ስለማይገባ የዱር እንስሳቱ ክልሉን እንደገና ለመኖሪያነት እየተጠቀሙበት ነው፡፡

በዲንሾ ወረዳ ውስጥ በተመሳሳይ የተከለሉ 11 የተቀደሱ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች አሉ፡፡ ቦታዎቹ ከ4 እስከ 10 ሔክታር ስፋት ያላቸው ሲሆኑ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለያየ የሥራ መስክ ቢሰማሩም ባላቸው ጊዜ ጥብቅ ቦታዎቹን ይንከባከባሉ፡፡ ከተከለሉት ቦታዎች ጥቂቱ ፀበል እንዳላቸውና ሌሎቹም የተለያየ ሥርዓት እንደሚከናወንባቸው ነዋሪዎቹ ያስረዳሉ፡፡   

ገደብ ገዳላን ከሚጠብቁት አንዱ አቶ ቱርኬ አዶኬ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ደኑ ሲመናመን በውስጡ የነበሩ እንስሳት ስለተጋለጡ በአቅራቢያው ወደነበረ እርሻ እየገቡ ሰብል ያጠፉባቸው ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ዛፎችን መትከል ከጀመረ በኋላ እንስሳቱ ቀስ በቀስ እንደተመለሱና የሚመገቡት ስለሚያገኙም ከክልሉ እንደማይወጡ ይገልጻሉ፡፡

ወደ ጥብቅ ቦታው እርሻቸውን አስፋፍተው የነበሩ ግለሰቦች ከአካባቢው መልቀቃቸውን ይናገራሉ፡፡ አካባቢው ከቀደመ ይዞታው በተቃራኒ ለመጐሳቆል የበቃው በሰው እጅ ስለሆነ ክስተቱ እንዳይደገም ጥበቃቸውን ማጠናከራቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ሰኢድ አሊ ሌላው የክልሉ ጠባቂ ሲሆኑ፣ በተከለለው አካባቢ ውስጥ የዘመናት ዕድሜ ያላቸው ዕፅዋት እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እነዚህ አገር በቀል ዕፅዋት እንዳይቆረጡ ቦታው መከለሉ መፍትሔ ሆኖታል፤›› ይላሉ፡፡ የተከለለው አካባቢ የተቀደሰ በመሆኑ ቀጣዩ ትውልድም ተረክቦ ሊንከባከበው እንደሚገባ ያክላሉ፡፡

የተጨፈጨፈውን ዛፍ ለመተካት የተተከሉ ዕፀዋት እያደጉ ሲሆን፣ እንዳይጠፉ መጠበቅ የአካባቢው ወጣቶች ኃላፊነት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ጐብኝዎች ወደ ባሌ ሔደው የተቀደሱ ቦታዎችን ለመመልከት የሚችሉት ተጠብቀው ሲቆዩ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ቦታዎቹ ሲጠበቁ ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ትርጉም ላይ ያተኩራሉ አቶ ሰኢድ፡፡

የባሌ የተፈጥሮ ሀብት በሰዎች ሰፈራና ደን ጭፍጨፋ አደጋ ቢያንዣብብበትም አቶ ሰኢድና አቶ ቱርኬ የቀበሌያቸውን ጥብቅ የእምነት ቦታና ብዝሀ ሕይወት ለመታደግ የሚጣጣሩ ይመስላሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ዘወትር ወደ አካባቢያቸው ለሚመጡ ጐብኝዎች ወደ ደኑ የተመለሱ እንስሳትን ለማስጐብኘት ይጠባበቃሉ፡፡ በቦታው ያገኘናቸው የዲንሾ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጌታሁን ለገሠ፣ ‹‹አብዛኛው የተፈጥሮ ሀብት በሰው እጅ ቢጠፋም፤ ሕዝቡ የተፈጥሮ ሀብቱን የመመለስ ፍላጐት ይታይበታል፤›› ይላሉ፡፡

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ፣ የደን ክልሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች የተጣላን ለማስታረቅና ለተለያየ አገልግሎትም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ደኑ ጥቅጥቅ ባለበት ዘመን እንደነበሩት በርካታ ኒያላዎች ሁሉ በአሁንም ጊዜ የተራቆተው ደን ማገገም በመጀመሩ ኒያላዎቹ ወደ ቦታው ተመልሰው እየተራቡ ናቸው፡፡ የእነርሱ መበርከትም የቱሪስት ፍሰትን ስለሚጨምር ለአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ያምናሉ፡፡

በአካባቢው ያገኘናቸው የአራት ልጆች እናቷ አርሶ አደር ወ/ሮ ሹጴ ሁሴን ዛፎች በብዛት ስለተተከሉ ዝናብ እናጣለን ብለን አንሠጋም ይላሉ፡፡ የተከለለው አካባቢ ብዙ ታሪክ ያለውና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ማንነት የቀረበ ስለሆነ ደኑ በተመናመነመነበት ወቅት ፈጣሪያቸውን እንደተለማመኑ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ቦታው አባቶቻችን ተሰባስበው የሚመክሩበትና እርቅ የሚወርድበት ነበር፡፡ ሰዎች ይዞታቸውን አስፍተው ክልሉ ሲጣስ ይጠፋል ብለን ሠግተን ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ ሹጴ፣ አሁንም አካባቢው የተለየ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ቀድሞ እንስሳትን ለመመገብ ወደ አካባቢው የሚገቡ ሰዎች አሁን እነሱም እንስሶቻቸውም ቢታቀቡም በጥብቅ ክፍሉ አቅራቢያ አሁንም የቤት እንስሳት ይገኛሉ፡፡ ከቦታው ስፋት አንፃር ጥቂት ጠባቂዎች የቤት እንስሳቱ ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ሊያግዷቸው የሚችሉ አይመስልም፡፡ ወ/ሮ ሹጴ አንዳንድ የቤት እንስሳት ወደ ውስጥ ገብተው ይመገባሉ፡፡ ቢሆንም ጠባቂዎቹ ለመቆጣጠር የተቻላቸውን እየሞከሩ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ገደብ ገዳላ ያሉ የተቀደሱ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ የየአካባቢው ሥርዓቶች የሚካሄዱባቸው እነዚህ ቦታዎች ጥበቃ ተደርጐላቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉም ይጠበቃል፡፡ በባሌ የሚገኙ መሰል ቦታዎች እንክብካቤ እንዲደረግላቸው መልካ ኢትዮጵያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ድርጅቱ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ በተለያዩ ክልሎች ይንቀሳቀሳል፡፡ በዲንሾ ወረዳ የተመለከትናቸው የተቀደሱ የተፈጥሮ ቦታዎች ተከልለው ጥበቃ እንዲደረግላቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር፣ በማሠልጠን እንዲሁም የቁሳቁስ ዕርዳታ በማድረግ ይሳተፋል፡፡

ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት የተመሠረተበትን 10ኛ ዓመት ባሌ ውስጥ ባከበረበት ወቅት የተቀደሱ ጥብቅ የተፈጥሮ ቦታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ ተከልለው እንክብካቤ የሚደረግላቸው የተቀደሱ ቦታዎች ለማኅበረሰቡ የሚሰጡትን ጠቀሜታ የጠቆሙ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካና አውሮፓ አገሮች የተውጣጡ የውይይቱ ተካፋዮች በየአገራቸው ካለው ተሞክሮ በመነሳት፣ የየማኅበረሰቡን እምነትና ባህል ጠብቆ ለማቆየት ቦታዎቹ እንደሚጠቅሙ ተናግረዋል፡፡

የየማኅበረሰቡ እሴቶችና ልዩ ልዩ የእምነት ሥርዓቶች ቀጣይነት የሚኖራቸው አካባቢዎቹ ሲጠበቁ ብቻ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች በማንኛውም አጋጣሚ ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን  ማጣት ሲጀምሩ የማኅበረሰቡ እሴቶችም አብረው ይሸረሸራሉ በማለት የአካባቢዎቹን ጥበቃ አስፈላጊነትን ያንፀባረቀ አስተያየት የሰጡ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከየአካባቢው ተወላጆች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው እነዚህ አካባቢዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በባህልና ብዝሀ ሕይወት መሀከል ጥብቅ ቁርኝት አለ፡፡ የየማኅበረሰቡ ባህል ከሚገለጽባቸው መንገዶች ተቀዳሚ የሆኑት የተፈጥሮ ሀብቶች ጥበቃ አፅንኦት ያሻዋል፡፡

ወ/ሮ ሹጴን የመሰሉ የዲንሾ ወረዳ ነዋሪዎች ባህላቸውና ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚያከናውኑባቸው አካባቢዎች መጠበቅ የሁሉም ሰው ኃላፊነት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በገደብ ገዳላ አቅራቢያ ካሉ ሌሎች ጥብቅ አካባቢዎች መሀከል ጀልዲና ቤርዴፎን ይጠቅሳሉ፡፡ ብዙዎች በተለይ ወደ ጀልዲ ፀበል ለመጠመቅ ይሔዳሉ፡፡ የአካባቢው ተፈጥሮአዊ ሀብት ባይጠበቅ ይህንን ለማካሔድ አስቸጋሪ እንደሚሆን ወ/ሮ ሹጴ ይገልጻሉ፡፡ ገደብ ገዳላን የመሰሉ ቦታዎች መጠበቃቸው የአካባቢውን ሥርዓት ጠብቆ እንደሚያቆይ በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...