Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለእኛ ባህልና ተፈጥሮ አንድ ናቸው››

ዶ/ር ሚሊዮን በላይ፣ የመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር

መልካ ኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. የተመሠረተ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ባህልን አስተሳስሮ የሚሠራ ድርጅት ሲሆን፣ በተለያዩ ክልሎች ቅርንጫፎች ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ትኩረቱን በወጣቶችና ሴቶች ላይ አድርጎ የሥራ ፈጠራ ሥልጠና በመስጠትና የቁሳቁስ ድጎማ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችን በመጠበቅና አደጋ ሲያጋጥማቸው እንዲያገግሙም በማድረግ ላይ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት አሥረኛ ዓመቱን ያከበረው ድርጅቱ፣ ጥብቅ ብዝኃ ሕይወቶችን በዩኔስኮ የማስመዝገብና የተቀደሱ የተፈጥሮ አካባቢዎችን የመከለል ሥራም ይሠራል፡፡ በድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከመልካ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ጋር ምሕረተሥላሴ መኰንን ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት ወደ ተፈጥሮ ጥበቃ ሥራ እንደገቡና ስለ መልካ ኢትዮጵያ አመሠራረት  ያብራሩልን?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- የተወለድኩት መርካቶ ነው፡፡ መርካቶ ውስጥ ደን የለም፡፡ ክረምት ግን ከወላጆቼ ጋር ወደ አዲስ ዓለም ሄጄ እቆይ ነበር፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ያለኝ ግንኙነት የተጀመረው ያኔ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂ ነው የተማርኩት፡፡ ብዙ ጊዜ ለትምህርት ወደ ፓርኮች እንሄድ ስለነበር ስለፓርኮች ግንዛቤ ኖረኝ፡፡ በመምህርነት የሠራሁበት ግንደ በረት ተፈጥሮአዊ ቦታ ነው፡፡ እዛ ከዲማ የሚባል የሚያምር ደን ነበረ፡፡ እንዳለመታደል አሁን እዛ ቦታ ተመልሰን ስንሄድ ደኑ የለም፡፡ ከ20 ዓመት በፊት  ወሊሶ በመምህርነት ስሄድ የአካባቢ እንክብካቤ ትምህርት ክለብ አቋቋምኩ፡፡ ያኔ ኢትዮጵያን ዋይልድ ላይፍ ኤንድ ናቹራል ሒስትሪ ሶሳይቲና ለምን የመሰሉ ጥሩ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ በነዛ ሥር ስሠራ የበለጠ ከተፈጥሮ ጋር ተቆራኘሁ፡፡ ክለባችን በየዓመቱ ተፈጥሮአዊ ዘመቻ ስለሚያዘጋጅ ታዋቂ ሆነ፡፡ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጋዜጠኞችን እንጠራ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ መጥተው ነበር፡፡ ከዛ ኢትዮጵያን ሔሪቴጅ ትረስት ሲቋቋም ተቀላቀልኩ፡፡ የኔ ኃላፊነት ወጣቶችን መመልመል ነበር፡፡ በሦስት ዓመት ውስጥ ወደ 130,000 አገር በቀል ችግኞች ተክለናል፡፡ ተከላው አስደሳች ቢሆንም ፈታኝ ነበር፡፡ ተማሪዎቹን ጠዋት በብርድ ወደ እንጦጦ ይዤ ወጥቼ ከተከላው በኋላ ትምህርት ሰጥቼ ወደየትምህርት ቤታቸው እመልሳቸዋለሁ፡፡ ሐሳባችን ችግኙን መሬት ላይ መትከል ብቻ ሳይሆን ሐሳቡን ሰው ልብ ላይ መትከል ነበር፡፡ ከ15 ዓመት በፊት ካልቸራል ኤንድ ስፒሪችዋል ቫልዩ ኦፍ ባዩዳይቨርሲቲ የሚል መጽሐፍ ላይ በላቲን አሜሪካ ስላለ ማኅበረሰብ የተጻፈ ጽሑፍ አገኘሁ፡፡ በአካባቢው ያሉ ሴቶች በባህላቸው መሠረት ተሰብስበው ቅርጫት ይሠራሉ፡፡ በነሱ ምልከታ ቅርጫቱ የሴቶችን ማሕፀን ይወክላል፡፡ ጽሑፉን ሳነበው የተፈጥሮና ባህል ቁርኝት ብልጭ አለልኝ፡፡ ቅርጫቱ የሚሠራባቸው የተለያዩ ሳሮች የተፈጥሮ ውጤት ናቸው፡፡ እኛ አገርስ እንደዚህ ዓይነት ባህል የለም ወይ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ፡፡ ንጽፈ ሐሳቡን ጽፌ ለድርጅቱ ዳይሬክተር ካቀረብኩ በኋላ ገንዘቡ ተገኘ፡፡ ሆለታ የባህልና ብዝኃ ሕይወት ሥልጠና ለመምህራን ከሰጠን በኋላ በየማኅበረሰቡ ቤት እየተዘዋወሩ ቁሳቁሶች ከምን እንደተሠሩና በአካባቢው ከባህል ጋር ያላቸውን ቁርኝት እንዲያጠኑ ተደረገ፡፡ ያገኘነው ምላሽ የሚያስገርም ነበር፡፡ ሆለታን በሚያክል አነስተኛ ከተማ በባህልና ብዝኃ ሕይወት መሀከል ጥብቅ ቁርኝት ካለ በሌሎች አካባቢዎች ምን ያህል ሊሰፋ እንደሚችል አሳየን፡፡ በኔ ተሞክሮ ሰው መሥራት ስለሚፈልገው ነገር ግልጽ ሐሳብ ካለው ገንዘቡ ከየትም ይመጣል፡፡ እኛም ገንዘብ አገኘንና ወሊሶ ውስጥ ከእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክልል የመጡ ባህሎችን ያሳተፈ ትልቅ የባህልና ብዝኃ ሕይወት ዝግጅት ለሦስት ቀን አካሄድን፡፡ ከዛ ፒኤችዲ ለመሥራት ወደ ፈረንሳይ ሄጄ እንደተመለስኩ መልካን ጀመርኩኝ፡፡ መልካ በጠቀስኩት ተሞክሮዎች የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መልካ ሲጀመር የተነሳባቸው ዓላማዎች ምን ነበሩ?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- የሸካ ደንን በዩኔስኮ የማስመዝገብ ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ የአገራችን የዘር መሸርሸር ትልቅ አጀንዳ እየሆነ ስለመጣ የአገራችንን ነባር ዝርያዎች መጠበቅ ሌላው ፕሮግራም ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዊልደርነስ ፋውንዴሽን የሚባል ድርጅት አለ፡፡ እነሱ ሰዎች ወደ ፓርካቸው ሲሄዱ በቡድን አድርገው ከአንድ መሪ ጋር ጫካ ውስጥ ይለቋቸዋል፡፡ እኔም ደርባን ያለ ፓርክ ውስጥ ተመሳሳይ ተሞክሮ ነበረኝ፡፡ ፓርኩ ውስጥ አንበሳ፣ ዝሆን፣ ከርከሮና ሌሎችም የሚያስፈሩ እንስሳት አሉ፡፡ ለቀናት ከነሱ መሃከል ብንኖርም ምንም አላደረጉንም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ጥቁሮች መሬታቸው እየተወሰደ ፓርክ ይሆን ነበር፡፡ ይህንን ለማመላከት ወጣቶችን ፓርኩን ከሚጠብቁ ሽማግሌዎች ጋ ፓርኩ ውስጥ ያስገቧቸዋል፡፡ ሸማግሌዎቹ ለወጣቶቹ ስለ ባህላቸው እየነገሯቸው ወጣቶቹ ከተፈጥሮ ጋር ይገናኛሉ፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተዘዋውሬ ተሞክሮ ስላገኘሁ ልምዶቹን አዋሕጄ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ሰኚ›› በሚል ተጀመረ፡፡ ሰኚ ወጣት ተማሪዎች ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን ስለ ማኅበረሰባቸው ባህልና ተፈጥሮ የሚማሩበት ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰኚ የተካሄደው ባሌ ነው፡፡ መልካ ሲመሠረት የመጀመሪያው ፕሮግራምም ሰኚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰኚ ወጣቶች ከሽማግሌዎች ጋር በመሆን ስለተፈጥሮና ባህል የሚያጠኑበት አሠራር ነው፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ካርታ እንዲሠሩ ማድረግም ሥራችሁን ከምታከናውኑበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ መሰል መንገዶች በማኅበረሰቡ ምን ዓይነት አስተዋፅኦ አላቸው?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- በካርታ ሥራ አንድ አካባቢ ከ50 ዓመት በፊት ምን እንደሚመስል ሽማግሌው ሲያብራራ አዲሱ ትውልድ ታሪኩን ያውቃል፡፡ ኅብረተሰቡ አንድ ላይ ሆኖ ካርታውን ስለሚሠራ የየግል እውቀታቸውን አንድ ላይ ያመጣዋል፡፡ የጋራ መግባባት ፈጥሮ ለተግባር ያነሳሳቸዋል፡፡ ካርታው አካባቢው ያለውን ነገር በሞላ ያሳያል፡፡ አዲሱና የቀደመው ትውልድ አንድ አጀንዳ እንዲኖሯቸው ያደርጋቸዋል፡፡ ሳከርድ ናቹራል ሳይትስ (የተቀደሱ የተፈጥሮ ቦታዎች) ጥበቃ ኅብረተሰቡ በአንድነት በአንድ አካባቢውን እንዲጠብቅና የዱር እንስሳትም መኖሪያ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ባህላዊ እምነት ያላቸው ሰዎች በቦታው ሲያካሂዱ በሰኚ ደግሞ ሰው ከራሱ፣ ከተፈጥሮና ከባህሉ ጋር ይገናኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በምትሠሩባቸው አካባቢዎች ለኅብረተሰቡ ምን ዓይነት አገልግሎቶች ትሰጣላችሁ?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- የምንሠራው በአማራ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች ነው፡፡ በጋምቤላ በማዣንግ ወረዳ እንሠራለን፡፡ አማራ ክልል በወረኢሉ ወረዳ የምንሠራ ሲሆን፣ ኦሮምያ ውስጥ ግንደበረት፣ ተለጮ ቀበሌ፣ ወልመራ ወረዳ እንዲሁም ሰበታና ሆለታ እንሠራለን፡፡ ሸካ ዞን ውስጥ በማሻ፣ በአንደራቸና በየኪም እንሠራለን፡፡ አንደኛው ኅብረተሰቡ ሕይወቱ እንዲሻሻል ማድረግ ነው፡፡ ለሰው ልጅ የገንዘብ ዕርዳታ መስጠትና ሥልጠና መስጠት በጣም ይለያያል፡፡ በጣም ችግረኛ የሆኑ ሴቶችን ሰብስበን የሥራ ፈጠራ ሥልጠና እንዲሰጣቸው እናደርጋለን፡፡ የድህነት መጥፎነቱ ሰው በራሱ ላይ ያለውን እምነት ሸርሽሮ ምንም ማድረግ እንደማይቻል እንዲያስብ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እችላሁ የሚል መንፈስ እንዲኖራቸውና ያሏቸውን አማራጮች እንዲመለከቱ እናደርጋለን፡፡ ብዙዎች ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ ድፍረት ስለሚያገኙ ዓይናችን ተገለጠ ነው የሚሉት፡፡ ማድረግ የሚፈልጉትን ለይተው ካወቁ በኋላ እንረዳቸዋለን፡፡ በተመሳሳይ ለወጣቶችም የሥራ ፈጠራ ሥልጠናው ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የምታከናውኗቸው ሥራዎችስ ምንን ያካትታሉ?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- አንዱ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት በአፈርና ውኃ ጥበቃ የሚሠራውን መርዳት ነው፡፡ መጀመሪያ ከመንግሥት ጋር ሆነን በጣም የተጎዱ አካባቢዎችን እንለያለን፡፡ ለምሳሌ የተቦረቦሩ ቦታዎች  ሲኖሩ ቦረቦሩ ቀስ በቀስ ይሰፋና ገደል ስለሚሆን የእርሻ መሬት ያጠፋል፡፡ ስለዚህ በአፈርና ውኃ ጥበቃ በቦረቦር የተጎዳ አካባቢን እናድናለን፡፡ ሌላው ችግኝ ተከላ ነው፡፡ ለምሳሌ ባሌ ውስጥ ትልቅ የችግኝ ተከላ ጣቢያ አለን፡፡ ችግኞች አፍልተን ለማኅበረሰቡና መንግሥትም መትከል ሲፈልግ እንሰጣለን፡፡ በኛ ችግኝ ጣቢያ አገር በቀል ችግኞች ይገኛሉ፡፡ ትልቁ ሥራችን ኅብረተሰቡ የተወሰነ ሔክታር መሬት ከልሎ እንዲጠብቅ ማድረግ ነው፡፡ አካባቢን ከልሎ እንዲጠበቅ ማድረግ አካባቢውን ከንክኪ ውጪ ስለሚያደርገው ቶሎ እንዲያገግም ይረዳዋል፡፡ መጀመሪያ የተሠራው በትግራይ ድንጋያማ አካባቢ ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት ወደአካባቢው ሔጄ ካየሁት አንፃር አሁን ያለውን ሁኔታ ስመለከት ለማመን ከብዶኝ ነበር፡፡ ነዋሪዎቹ የተለያዩ ቦታዎችን ከልለው አካባቢው እንዲያገግም አድርገዋል፡፡ የሌላ አካባቢ ገበሬዎችን ስኬታማ ወደሆኑ አካባቢዎች ወስደን የተሠራውን ስናሳያቸው ለምን እኛስ አካባቢያችንን አንጠብቅም የሚል ስሜት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል፡፡ ወደአካባቢያቸው ሲመለሱ እነሱም ቦታዎችን ከልለው ይጠብቃሉ፡፡ ሌላው ባዮስፌር ሪዘርቨ (ጥብቅ የብዝኃ ሕይወት ቦታ) ነው፡፡ ለዚህ አንድ ዞን በአጠቃላይ ይከለላል፡፡ በዞኑ የልማት ቦታ ስለሚተው ልማትን አይከለክልም፡፡ ለልማት በሚውል አካባቢና መጠበቅ ባለበት አካባቢ መሀከል ክፍተት ይኖራል፡፡ ሰው የልማት ሥራውን እያስፋፋ ሲመጣ የተጠበቀው አካባቢ እንዳይነካ ይደረጋል፡፡ ልማት ሲባልም ሁሉም ነገር አይፈቀድም፡፡ አካባቢን የሚያጠፋ እንቅስቃሴ አይፈቀድም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ጥብቅ ብዝኃ ሕይወት ቦታ በመከለል ማኅበረሰቡም የመንግሥት አካላትም ደስተኛ ናቸው፡፡ መንግሥት ከዩኔስኮ ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነት ስለገባ የተመዘገቡ ቦታዎች እየተጠበቁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት በጥብቅ ብዝኃ ሕይወት ሸካ ዩኔስኮ ላይ እንዲመዘገብ አድርጋችኋል አሁን ደግሞ ማዣንግን ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ ነው፤ ከምን ደረሰ?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- ሸካ በዓለም ላይ በፍጥነት ከተመዘገቡት ጥብቅ ብዝኃ ሕይወት ቦታዎች አንዱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሔ የሆነው እጃችን ላይ ብዙ መረጃ ስለነበር ነው፡፡ ማዣንግ የሔድነው የአካባቢው ነዋሪዎች እርስ በእርስ ተስማምተው አስመዝግቡልን ብለው ጠርተውን ነው፡፡ ሸካ ሥራ ከጀመርን ከአምስት ዓመት በኋላ ያዩና ከፋ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የሸካ ሕዝብ ለምን የኛ አይመዘገብም የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ አንድ ቦታ ከመመዝገቡ በፊት መሟላት ካለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ካርታዎች፣ የአካባቢው ባህልና ታሪክ ጥቂቱ ናቸው፡፡ ሸካ በሠራንባቸው ዓመታት ኅብረተሰቡ ስለሚያውቀንና ፍላጎቱን እንደምናሳካለት ስለተረዳ አምኖን ነበር፡፡ ጥናት እንዲሠራ የቀጠርነው ሰው ያዩን ያስመዘገበና ብዙ ጥናት የሠራ ነበር፡፡ ሸካ በአጭር ጊዜ ስኬታማ የሆነው ለዚህ ነው የማዣንግ እንቅስቃሴ ከተጀመረ በኋላ ኅብረተሰቡ በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጥብቅ ብዝኃ ሕይወት ቦታዎች እንዲስፋፉ ይፈልጋል፡፡ የጋምቤላ ክልልም በጉዳዩ ተስማምቷል፡፡ አሁን ቅድመ ሁኔታዎቹ ባጠቃላይ ተሟልተዋል፡፡ ሸካና ማዣንግ ዙሪያ ሲሊኖኖ የሚባል ደን  አለ፡፡ ደኑ ከሁለቱም ሊበልጥ ይችላል፡፡ ያንንም አካተን ማስመዝገብ ከቻልን በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አሥር ዓመታት ባደረጋችሁት እንቅስቃሴ ምን ዓይነት ፈተና ገጥሟችኋል?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- የኅብረተሰቡ ፍላጎት በየጊዜው ስለሚለዋወጥ አብሮ ለመሥራት ያስቸግራል፡፡ ዛሬ አንዱ ሲሟላ ነገ ሌላውም ይጠብቃል፡፡ ሰዎችን አደራጅተን ስንሠራም በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል፡፡ በመንግሥት በኩል ያለው ችግር የሠራተኞች ቋሚ ሥልጣን አለመኖር ነው፡፡ ከአንዱ ሥራ ወደ ሌላው በፍጥነት በሚዘዋወሩበት ወቅት እንደኛ ላለ ድርጅት ሥራውን ለማስፈጸም ያስቸግራል፡፡ በርካታ ስብሰባዎች ስለሚካሄዱ ሠራተኞችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻላችን ሌላው ችግር ነው፡፡ ሌላው እንደምንፈልገው ለመሥራት በቂ ገንዘብ አለመኖሩ ነው፡፡ የሸካ ሠራተኞቻችን መኪና ያገኙት ከሰባት ዓመት በኋላ ነው፡፡ ለዓመታት ረዥም ርቀት በእግራቸው እየተጓዙ ነበር የሚሠሩት፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ማነቆ የሆነብን ለሲቪል ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የወጣ አዋጅ ላይ የሰፈረው 70/30 ፕሮግራም ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ አድቮኬሲ ድርጅት፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሕግ አጥንተን፣ ድክመቱን አውጥተንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ አድርገን አዲስ የወጣውን ሕግ አስተችተን አቅርበናል፡፡ አሁን በ70/30 መሠረት ያንን ማድረግ አንችልም፡፡ እኛ 30 በመቶ ለአስተዳደራዊ ሥራ አውለን አናውቅም፡፡ ችግሩ አስተዳደራዊ ወጪ የሚባለው የቱ ነው? የሚለው ነው፡፡ መንግሥት ከምንሠራው ሥራ ጋር አብሮ እንዲሄድ ታስቦ የሠራተኞች ውይይት ቢከፈት ወይም ሥልጠና ቢሰጥ እንደ አስተዳደራዊ ሥራ አይቆጠርም፡፡ መንግሥት ገበሬው ጋ ካልደረስክ ምን አግብቶህ ነው የምታሠለጥነው ሊል ይችላል፡፡ ገበሬው ብቻ መሥራት ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው፡፡ ገበሬውና የመንግሥት አካላት በአንድ ቋንቋ መናገር አለባቸው፡፡ እኛ የምንሠራውን ሥራ መንግሥት ማወቅ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ የሕግ ማስፈጸም ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ፍርድ ቤት ያለ ዳኛ የአገሪቱን የአካባቢ ሕግ (ኢንቫሮመንታል ሎው) ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር በጥልቀት ላያውቀው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤት የሚሠለጥኑት በሌላ ነው፡፡ አብዛኞቹ በአካባቢ ሕግ ስፔሻላይዝ አድርገው አይሠለጥኑም፡፡ እኛ ደግሞ በ70/30 ምክንያት ሥልጠናውን መስጠት አንችልም፡፡ አሁን የጀነቲክ ኢንጂነሪንግ (የዘረመል ምሕንድስና) ሕጋችን ሊሻሻል ነው፡፡ የጥናትና ምርምር ተቋሞች ብዙ ስብሰባ እያደረጉ ነው፡፡ የኛን ምልከታ ግን በ70/30 ምክንያት መንግሥትም ሌላው ሕዝብም እንዲሰማው ማድረግ አልቻልንም፡፡ የጥብቅ ብዝኃ ሕይወት ቦታዎች መመዝገብ የመንግሥትም የሕዝብም ፍላጎት ነው፡፡ ሥራው አማካሪ ካልተቀጠረ ሊሠራ አይችልም፡፡ አንድ ቦታ የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ አሟልቶ ለማስመዝገብ አቅም አይኖርም፡፡ ደርባን ኮፕ ሰቨንቲን የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ እያለሁ አንድ የማውቀው ሰው ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ ጂአይኤስ ላይ ትልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባ አናዘጋጅም ብሎ ሲጠይቀኝ ደስተኛ ነን አልኩት፡፡ ስብሰባው ግን በአስተዳደራዊ ወጪ የሚሸፍን ስለሆነ ማሳካት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጂአይኤስ እንደ ስካይ ሮኬት ከረቀቁ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ሁሉም ጂአይኤስ እያለ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ምን ያህሉ ናቸው ከጂአይኤስ ጀርባ ያለውን ሳይንስና ፅንሰ ሐሳብ የሚገነዘቡት የሚለው ነው፡፡ በጂአይኤስ ላይ ለጥቂት ቀናት ለዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎችና አማካሪዎች ዓለም አቀፍ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡ ያ ግን የአስተዳደር ሥራ ስለሆነ አይቻልም፡፡ ቢሆንም ሥራ የሚያስተው ችግር የለብንም፡፡  

ሪፖርተር፡- የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ባህልንን አጣምሮ ስለሚያስኬደው ፕሮግራማችሁ አብራሩልን? በሁለቱ መሀከል የምትፈጥሩት ትስስር በምን ይገለጻል?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- ብዝኃ ሕይወትና ባህል ተጣምረው ይሄዳሉ፡፡ ከሚያገናኟቸው አራት ነገሮች አንዱ እምነት ነው፡፡ ባሌ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ቦታ አለ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በእምነታቸው ምክንያት ያንን ቦታ ይጠብቁታል፡፡ አካባቢውን ሲከልሉትም ሲጠብቁትም ደስተኞች ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች በመላው ኢትዮጵያና በዓለምም ይገኛሉ፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ያመጣው የኅብረተሰቡ ካፒታሊስቲክ የሆነ አመለካከት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰቡ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት የእኛ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በኦሮሞ ባህል አንድ ሰው ልጅ ከሌለው ዛፉን በራሱ ይሰይመዋል፡፡ ሰውየው ሲጠራ ‹‹አባ እከሌ›› ተብሎ በዛፍ ስም ይጠራል፡፡ ጋምቤላ ቶተም አኒማልስ (የአካባቢው መገለጫ የሆኑ እንስሳት) አሉ፡፡ ለኑዌሮች ነብሮች ዘመዶቻቸው ስለሆኑ በምንም ዓይነት አይገድሏቸውም፡፡ ሁለተኛው የእህልና የከብት ዝርያዎች ዓይነት ነው፡፡ በየአካባቢው ስላሉ ዝርያዎች የየአካባቢውን ባህል ከሚያውቀው ሰው ውጭ ሌላ ሰው አይረዳም፡፡ ከአንድ ሽማግሌ ጋር ባሌ ተራሮች ላይ ቢወጣ ለተለያዩ በሽታዎች ባህላዊ መድኃኒት የሆኑ ቅጠላ ቅጠሎች ያሳያሉ፡፡ እነሱን ተፈጥሮን እንዲያነቡ ያደረጋቸው ባህሉ ነው፡፡ ባህልን ስናስተዋውቅ ተፈጥሮን የምናስተዋውቅበት አንዱ ምክንያት ይኼ ነው፡፡ የኦሮሞ ምርቃት በአብዛኛው ስለ ተፈጥሮ ነው፡፡ ስለተፈጥሮ ሲወራ ስለባህል የሚነሳውም ለዚህ ነው፡፡ ለእኛ ባህልና ተፈጥሮ አንድ ናቸው፡፡ ደን ተጨፈጨፈ ደን ተቃጠለ ሲባል የኅብረተሰቡ ዕውቀትም አብሮ ተቃጠለ ነው የምንለው፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ በፊት በእጁ ላይ ወደ መቶ ዓይነት ዝርያ ነበር አሁን ግን ጥቂት ቀረ ሲባል ከስንዴው ዝርያ ጋር ተያይዞ የኅብረተሰቡም ዕውቀትም አብሮ ጠፋ ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሥረኛ ዓመታችሁን ያከበራችሁበት ባሌ ከተማ የሚገኘው የባሌ ተራሮች ፓርክ አደጋ የተጋረጠበት ነው፡፡ በሰዎች ሰፈራ ምክንያት በአካባቢው ላይ ችግር እየደረሰ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎችም መሰል ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ዋነኛ መንስኤው ምንድነው?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- የግንዛቤ እጥረት ነው ሊባል አይችልም፡፡ የደን ጥቅምን በሚገርም ጥልቀትና ታሪካዊ ዳራ የሚያስረዱ ሽማግሌዎች አሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ስለ ደን ጥቅም ሲነገር ይሰማል እንጂ አይተገብረውም፡፡ ይህን የምለው ከመሬት ተነስቼ ሳይሆን ማፒንግ ስለሠራሁ ነው፡፡ ከሌላ ማኅበረሰብ በተለየ መልኩ ከባሌ ማኅበረሰብ ጋር አውርቻለሁ፡፡ እኔ የሚመስለኝ ችግሩ የሚከሰተው በግለሰቦች ግላዊ ፍላጎት ሳቢያ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የደኑን ጥቅም ቢያውቅም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ እንዲያጠፉት ይገፋፋቸዋል፡፡ ፓርኩ ውስጥ ከብታቸውን ሲያስገቡ ይቀጣሉ፡፡ ቢሆንም አካባቢው ስለደረቀ ከብቶቻቸውን የሚመገቡት ሲያጡ ፓርኩ ውስጥ ከማስገባት ወደኋላ አይሉም፡፡ የፓርኩ ሕዝብ ግንኙነት ኅብረተሰቡን በማማከር ረገድ ደካማ ነው፡፡ በየጊዜው ቅራኔ ስለሚፈጠር ሕዝቡ ለፓርኩ ፍቅር የለውም፡፡ ሰውና ፓርኩ መሀከል የመንፈስ ትስስር መፈጠር አለበት፡፡ እኛ ወጣቶችን ጫካ ውስጥ ስለምንወስዳቸው ከፓርኩ ጋር የመንፈስ ትስስር እንዲፈጥር ለማድረግ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተመሠረተ በኋላ ምን ዓይነት አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- አዲሱ ትውልድ ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝት እንዲኖረው እየሠራን ነው፡፡ አሁን ባለን አቅም ተወስነን እንጂ አቅም ቢኖረን ወጣቱን በሙሉ ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ በትልቅ አቅም አሁን የምንሠራውን ብንቀጥል ችግሩን እንቀርፈዋለን፡፡ እጀግ የተወሳሰበ ችግር በመሆኑ እንፈታዋለን አልልም፡፡ የተጋጋጡ አካባቢዎች እንዲመለሱ ችግኝ አከፋፍለናል፡፡ በተወሰነ መልኩ ለሴቶች የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ በማከፋፈል ሕይወታቸው እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ ሥነ ሕዝብ፣ ጤናና አካባቢን ባካተተ ፕሮግራማችን የሃይማኖት አባቶች ሳይቀሩ የሚሳተፉበት ውይይት  እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ በሚሠራባቸው አካባቢዎች ከተተገበሩ ፕሮጀክቶች የበለጠ ስኬታማ የምትሉት የቱን ነው?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- ዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያገኘም ስለሆነ ሰኚ ስኬታማ ነው፡፡ ወጣት የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችን አፍርተንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የገንዘብ ዕርዳታ የሚያደርጉላችሁ ተቋሞች እነማን ናቸው?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- ከስዊድን ስዊድሺ ሶሳይቲ ፎር ኔቸር ኮንሰርቬሽንና ሲዳ ናቸው፡፡ ከኖርዌይ ኖርዌይጂያን ፒፕልስ ኤይድና ዘ ዴቨሎፕመንት ፈንድ አለ፡፡ አሁን ፉድ ፎር ዘ ወርልድ የተባለ የጀርመን ድርጅት የአማራውን ፕሮግራም ይሸፍንልናል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ ላይ የሚያስተዳድሩት ሲቪል ሶሳይቱ ፈንድ የሰጠንን ሸካ ላይ እየተሠራበት ነው፡ ሴንት ልዊስ ዙ የተባለ የአሜሪካ ድርጅት የደጋ አጋዘን እንዲጠበቅ በየዓመቱ ይረዳናል፡፡ የምንሠራው ነገር ጠንካራ ስለሆነ በውስጤ ገንዘብ ይጠፋል የሚል ሥጋት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት እቅዳችሁ ምንድነው?

ዶ/ር ሚሊዮን፡- ዓላማችን ሥራዎቻችንን ማላቅ ነው፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሆነን ስትራቴጂያችንን እያጣራን ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ፕሮግራሙን ወስዶ በአገሪቱ እንዲያስፋፋው እንፈልጋለን፡፡ እኛ እንደ ማሠልጠኛ ቦታ እንሆናለን፡፡ ከኢትዮጵያ ዋይልድ ላይፍ ኮንሰርቬሽን ኤጀንሲ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ፓርኮች እየበዙ ስለሆነ በየፓርኩ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ማሠልጠን እንፈልጋለን፡፡ የጥብቅ የተፈጥሮ ቦታ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች ደግሞ እርስ በእርስ እንዲተሳሰሩ እንፈልጋለን፡፡ የተቀደሱ የተፈጥሮ አካባቢዎች ክለላና ጥበቃ እንዲስፋፋም እንፈልጋለን፡፡ ሌላው የዘር ጥበቃ ነው፡፡ በኛ ዘር ላይ የተመሠረተ እርሻን ለማስፋፋት ከሚመለከታቸው አከላት ጋር ተነጋግረንና ፕርግራሙም የአገር ሆኖ መሥራት እንፈልጋለን፡፡ በተወሰኑ ቦታዎች ባለው ፕሮግራም መሠረት በተሻሻለ ዝርያና ማዳበሪያ ሊሠራ ይችላል፡፡ ዓላማችን በየቦታው ያለውን ፕሮግራም አድስን ለመንግሥት በሚመች መልኩ ካዘጋጀነው በኋላ መንግሥት የራሱ አካል አድርጎ እንዲያስፋፋውና ሌሎችም መንግሥታዊ ድርጅቶች እንዲያስፋፉት ማድረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...