Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሴናተር ቴድ ክሩዝ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ቆርጠው ተነስተዋል

ሴናተር ቴድ ክሩዝ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን ቆርጠው ተነስተዋል

ቀን:

አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ ላይ ለምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን እያዘጋጁ ቢሆንም፣ የቴክሳሱን ሴናተር ቴድ ክሩዝን ቀድሞ ዕጩ የመሆን ፍላጐቱን የገለጸ የለም፡፡

ሪፐብሊካኑና በወግ አጥባቂነታቸው የሚታወቁት ሴናተር ክሩዝ፣ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ፍላጐት እንዳላቸው በትዊተር ገጻቸው አሳውቀዋል፡፡ በአሜሪካ ቨርጂንያ በሚገኘውና ከ13 ሺሕ በላይ መደበኛ እንዲሁም ከ100 ሺሕ በላይ የርቀት ተማሪዎችን ለሚያስተምረው ክርስቲያናዊው ሊበሪቲ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ዕቅዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው በመገኘት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን የገለጹት የ44 ዓመቱ ሴናተር ክሩዝ፣ ‹‹አሜሪካ ተመልሳ ኃያል እንድትሆን አዲስ ጠንካራና ወግ አጥባቂ ትውልድ ያስፈልጋታል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሴናተር ክሩዝ ሪፐብሊካኖች ለ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚያቀርቡትን ተወዳዳሪ በቅድመ ምርጫ ለመለየት ከሚያሳትፏቸው ፖለቲከኞች አንዱ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁም ናቸው፡፡ የሪፐብሊካን ፓርቲ ከአሥር ወራት በኋላ በጠቅላላው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደረውን የሪፐብሊካን ዕጩ ለመምረጥ የውስጥ ምርጫ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ፍላጐቱ ያላቸው የፓርቲው ፖለቲከኞች ለተቋቋመው የፓርቲው ኮሚቴ የሕይወት ታሪክ መግለጫቸውን እያሳወቁ ነው፡፡ የሪፐብሊካኑን የውስጥ ምርጫ ያሸንፉ አያሸንፉ ያላወቁት ሴናተር ክሩዝ ደግሞ ለፓርቲያቸው ከማሳወቅም ባለፈ፣ ‹‹ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እሳተፋለሁ፡፡ አሜሪካንም መልሼ አጠነክራታለሁ፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ይረዳኛል፤›› ብለዋል፡፡

በአሜሪካ የፖለቲካ ምኅዳር የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ‹‹ሄልዝኬር›› ፖሊሲ በመንቀፍና እ.ኤ.አ. በ2013 በአሜሪካ በከፊል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለተወሰኑ ቀናት እንዲዘጉ በማድረግ ዝናን ያተረፉት የኢቫንጀሊካን እምነት ተከታዩ ሴናተር ክሩዝ፣ ‹‹ጊዜው የእውነት ነው፡፡ አሜሪካኖች ሁሌም ሲያደርጉ እንደከረሙት ፈተናን የምንጋፈጥበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአሪዞናው ሴናተር ጆን ማክኬይን ባለፈው እሑድ ሴናተር ክሩዝ ወሳኝ ዕጩ መሆን ይችላሉ ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊትም ሥራቸውን በብቃት መወጣት የሚችሉ ብለዋቸው ነበር፡፡

በአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከያዟቸው ዘጠኝ ክርክሮች አምስቱን የረቱት ሴናተር ክሩዝ፣ ከሐርቫርድ የሕግ ትምህርት ቤት እንደተመረቁ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

እ.ኤ.አ በ1970 በካናዳ አልበርታ ግዛት ካልጋሪ ከተማ የተወለዱት ሴናተር ክሩዝ አባታቸው ኩባዊ ሲሆኑ፣ እናታቸው ደግሞ አሜሪካዊት ናቸው፡፡

አሜሪካ ባላት የውጭ ፖሊሲ፣ ቤተሰባዊ እሴት፣ ኢኮኖሚና ሕገ መንግሥት ላይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች አሉ የሚሉትና ‹‹ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ጥላ ሥር›› የሚለው ቃል ሊከበር ይገባል በሚለው አባባላቸው የሚታወቁት ሴናተር ክሩዝ፣ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2016 በምታደርገው ጠቅላላ ምርጫ ቢያሸንፉ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ሒስፓኒክ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡

ይህ ግን በአሁኑ ጊዜ ለብዙዎች ጥያቄዎችን አጭሯል፡፡ የቴክሳሱ ሴናተር ቴድ ክሩዝ ካናዳ መወለዳቸው ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ አያስችላቸውም የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱም ነው፡፡   

በካናዳ የተወለዱት ቴድ ክሩዝ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት መወዳደር ይችላሉ ወይስ አይችሉም? በሚል ቮክስ ድረ ገጽ እንዳሰፈረው፣ እሳቸው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መወዳደር ይችላሉ፡፡

ሴናተር ክሩዝ ካናዳ ውስጥ ቢወለዱም ከትውልድ ቀናቸው ጀምሮ አሜሪካዊ ናቸው፡፡ እናታቸው ኢሊያኖር ዳራጋ አሜሪካዊት ሲሆኑ፣ አባታቸው ራፋኤል ክሩዝ ደግሞ ኩባዊ ሆነው አሜሪካ ተሰደው የአሜሪካ መኖሪያ ፈቃድ በማግኘት ረዥሙን ዕድሜያቸውን ያሳለፉ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2005 ወዲህ ደግሞ የአሜሪካ ዜግነትን አግኝተዋል፡፡

ሴናተር ክሩዝ አሜሪካዊነታቸው በእናታቸው ብቻ ነው፡፡ በአሜሪካ ሕግ ደግሞ ከወላጆች አንዱ አሜሪካዊ ከሆነ ወይም በአሜሪካ አሥር ዓመት ቆይቶ ዜግነት ካገኘ፣ ከቆየበት አሥር ዓመት አምስቱን ዓመት አሥራ አምስት ዓመት ሞልቶት የኖረው ከሆነ፣ የሚወልደው ልጅ ከአሜሪካ ውጪም ቢሆን የአሜሪካ ዜግነት ያገኛል፡፡ በመሆኑም ይህ ሕግ አዋቂውን ሴናተር ክሩዝ አያሰጋቸውም፡፡

ክሩዝ ካናዳ በመወለዳቸው ማንኛውም ሰው አሜሪካ ሲወለድ በውልደቱ ዜግነት እንደሚያገኝ ሁሉ፣ የካናዳ ዜግነት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም የቴክሳስ ሴናተር ከሆኑ በኋላ በውልደት ያገኙትን የካናዳ ዜግነት ሽረዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ናቹራል ቦርን ሲትዝን›› በሚለው የአሜሪካ ‹‹ናቹራላይዜሽን አክት ኦፍ 1970›› ከአሜሪካ ውጪ የተወለዱም ቢሆኑ አሜሪካዊ ዜግነት ካለው ከተወለዱ አሜሪካዊ እንደሚሆኑ ያስረዳል፡፡

የአሜሪካ ኮንግረስ እ.አ.አ. በ1790 ሽሮ በ1795 በተካው ድንጋጌ ደግሞ ከአሜሪካ ውጪ የአሜሪካ ዜግነት ካላቸው የተወለዱ ‹‹ዜጋ›› ናቸው ብሎ ያስቀምጥና ‹‹ናቹራል ቦርን ሲትዝን›› የሚለውን ግን ሳይገልጸው ያልፋል፡፡

ይህ ምናልባት በሴናተር ክሩዝ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ መወዳደር ላይ ጥያቄ  ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ለዚህም ኮንግረሱ ሊያፀድቀው የሚገባ ውሳኔ መኖር አለበት የሚሉ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እየሰጡም ነው፡፡

በጄኔራል ኒኤል ካታያልና በፓል ክሊሜንት ተጽፎ በሐርቫርድ ሕግ ትምህርት ቤት የታተመው ጽሑፍ፣ ዜግነትን አስመልክቶ በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ አሻሚ አንቀጾች ቢኖሩትም፣ ወሳኝ የሆኑ ሕጐች የሚያሳዩት ሴናተር ክሩዝ አሜሪካዊ ወይም ‹‹ናቹራል ቦርን›› መሆናቸውን ነው ይላል፡፡

ሴናተር ክሩዝ እ.ኤ.አ. ለ2016 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ ፍላጐት በማሳየታቸው ምክንያት የውልደታቸው ጉዳይ በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በዜና አውታሮች እንደ ጥያቄ ቢነሳም፣ በእሳቸው ዕይታ ሥፍራ አላገኘም፡፡ ካናዳ መወለዳቸውንም እንደ እክል ሲያነሱት አልተሰማም፡፡

በሊበርቲ ዩኒቨርሲቲ ለታደሙ ተማሪዎች ንግግር ሲያደርጉም፣ ‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ ሕክምና የሚገኝበት መዋቅር የሚዘረጋ፣ የአገር ውስጥ ገቢ ክፍያን የሚያስቆም፣ ውጣ ውረድ የበዛበትን ኑሮ የሚያሻሽልና ጋብቻ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲመሠረት የሚያበረታታ ዓላማ ያለው ፕሬዚዳንት በዓይነ ህሊናችሁ ሳሉ፤›› በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...