Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርተጠያቂነት የጠፋበት የጉዞ ዕገዳ ሕገወጥነትን እያስፋፋ ነው

ተጠያቂነት የጠፋበት የጉዞ ዕገዳ ሕገወጥነትን እያስፋፋ ነው

ቀን:

በያብስራ ዮፍታዬ

ሰሞኑን ከአንድ ጋደኛዬ ጋር ስለሥራ ስንጨዋወት የሚከተለውን ቀልድ አዘል ሽሙጥ አወጋኝ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በለንደን አንድ ጎዳና አንድ ሰው በአጋጣሚ ከሌላው ሰው ጋር በመንገድ ላይ ከሌላው ሰው ጋር ይገኛንና በጋራ የእግር መንገድ ይጀምራሉ፡፡ አንደኛው አንድ ከመንገድ ዳር ያለ መጠጥ ቤት እያሳየው፣ ‹‹ይገርምሃል እዚያ መጠጥ ቤት ከዊሊያም ሼክስፒር ጋር አንድ ሁለት እንልበት ነበር፤›› ይለዋል፡፡ አብሮት ያለው ሰው ደንገጥ ብሎ፣ ‹‹ወዳጄ ምን ነካህ ሼክስፒር እኮ ከሞተ ከ400 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፤›› ቢለው፣ ‹‹ወቸው ጉድ አቤት የጊዜ መብረር?›› አለው አሉ፡፡  የጊዜን ዋጋ  አለማወቅ ይሏል እንዲህ ዓይነቱን ነው፡፡

ተጠያቂነትና ኃላፊነት የጎደላቸው 18 ወራት

- Advertisement -

      የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቅምት 14 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት በወጣ ድንገተኛ መግለጫ ከጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ  ለስድስት ወራት ለሥራ ወደ ውጭ በተለይም መካከለኛው ምሥራቅ መጓዝ አስቁሟል፡፡ በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ረገድ የሚታዩ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች ተፈትሸው ተገቢውን ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው ድረስ ለስድስት ወራት ዕገዳ ቢደረግም ወራትን ወራት እያስቆጠሩ 18 ወራት ኮበለሉ፡፡ በእነዚህም 18 ወራት ጉዳዩ የሚመለከታቸው በተለይም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  ኃላፊዎች አንዳንዴ በተለያዩ የመገኛኛ ብዙኃን ብቅ እያሉ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየቀረቡ አዋጁን እያሻሻልን ነው አሉ፡፡ በተጨማሪም በቅርብ ቀን ተመልሶ ይከፈታል ከማለት ውጪ አንድም ተግባራዊ ዕምርጃ ሳያሳዩን 540 ቀናት ነጎዱ፡፡ ከላይ ጓደኛዬ ያጫወተኝን ቀልድ እዚህ ላይ ተመልሶ ማስታወስ ከዚህ የመነሳቴን ምክንያት በደንብ ሳያስረዳልኝ አይቀርም፡፡ ሚኒስቴሩ 18 ወራት የፈጁበትን ጉዳዮች ሳስባቸው ምንም ዓይነት ትኩረት አለመስጠቱን ነው፡፡ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ ከቶ የራሱን የአደረጃጀትና የማስፈጸም ብቃት ጥያቄዎች ውስጥ የከተቱኝን ጥቂት ነጥቦችን ላነሳ ወደድኩ፡፡

 ለሕገወጦች የተመቸ የሀብት ምንጭ

የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች የዕገዳው ሰሞን ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ የአዋጅ 632/2001  ዕገዳ ምንጭ በአግባቡ ለሥራ የሚሄዱ ሴት እህቶቻችንን ክብር፣ ደኅንነትና መብት ለማስጠበቅ ታስቦ መሆኑን ሲነግሩን የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ የሁላችንም ትዝታዎች ናቸው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በየብስም ሆነ በአየር የሚደረጉ በረራዎችና ተጓዦች ላይ ልዩና ጥንቃቄ የተሞላው ሥራን እንደሚከናውኑ ጨምረው ሲያስረዱን ሰንብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ  በአሁኑ ጊዜ በጥቅም ከተሳሰሩ የተወሰኑ ሕገወጥ ደላሎች፣ የኤጀንሲ ባለቤቶችና የሚኒስቴሩ  ሠራተኞች በመተባበር ዕገዳውና አቅም የሌለው ተቋማዊ አደረጃጀት  ያመጣለቸውን በረከት ተጠቅመዋል፡፡ ዜጎቻችንን ወደ ስደት ቀጥታ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕገወጥ መንገድ እየላኩ በክብሩ የሰው ሰውነት ላይ ንግድ ማካሄዱን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንዲጎን አድርገውታል፡፡

በቅርቡ ከጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ወደተከለከሉት የዓረብ አገሮች ለመሄድ በደላላ፣ በኤጀንሲና በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ የመንግሥት ሠራተኞች አማካይነት ሒደቱን የጀመረችው የአክስቴ ልጅ በየጊዜው የምወስድሽ እኮ በሕጋዊና በድብቅ መንገድ ስለሆነ፣ ብር ጨምሪ እያሉ ያለ የሌለ የቤተሰቦቿን ንብረት መጨረሷን  በመጨረሻው የበረራዋ   ዕለት ለማረፍ እኛ ቤት መጥታ አጫውታኛለች፡፡

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወደ የሚገኘው ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን ጎራ ማለትም ሌላኛው የሕገወጥ ስደት መበራከትን ዓይን አውጥቶ ከሚነግረን ማስረጃ ውስጥ መክተት ይቻላል፡፡ ዘወትር ከቤቴ ጀሞ ወደ ሜክሲኮ ስመጣ በሱዳን ኤምባሲ አካባቢ የሚገኙ ሴት እህቶቻችንን መመልከት ምናልባትም ሌላኛው ማሳያ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በርካታ ምሳሌዎች ማንሳት ቢቻልም እንደማሳረጊያ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅትን (አይኦኤም) ሪፖርቶች ማየት በቂ ይመስለኛል፡፡ ሚንስቴሩ ታዲያ ይዞት የተነሳው የጉዞ ዕገዳ ዕውን በአግባቡ የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና መብት ለማስጠበቅ ከመርዳት ይልቅ ሕገወጥነትን ማባባሱ የአደባባይ ሚስጥር የሆነ ይመስለኛል፡፡

ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የጣሰ ዕግድ

በ1987 ዓ.ም. በዜጎች መልካም ፈቃድና ሙሉ ስምምነት ከፍፁም አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገራችንን ያበሰረው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት፣ የዜጎችን የመንቀሳቀስና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ሕጋዊ ዕውቅና አስገኝቷል፡፡ እነዚህ መብቶች ዕውቅና ካገኙ በኋላ ዜጎች በፈለጉት የሥራ መስክ በመሰማራት የአገሪቱን ሕግ፣ ደንብና መመርያዎች በማክበር አገራቸውን በኢኮኖሚ ዕድገት እንዲረዱ ዕድሉን ሰጥቷል፡፡ የውጭ ሥራ ሥምሪት ዘርፍም እንደ አንድ ዘርፍ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ለዚህም ለመጀመርያ ጊዜ ዘርፉን የሚቆጣጠር አዋጅ በ1990 ዓ.ም. ታውጆ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በቆየበት ጊዜ የታዩትን ክፍተቶች ለመሙላትና ዘርፉን በተጠናከረ ሁኔታ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 ተተክቷል፡፡ ይህም አዋጅ በዕግድ ይቆይ እንጂ ለድፈን አምስት ዓመታት በሥራ ላይ ቆይታ አድርጓል፡፡

ይህንንም አዋጅ መሠረት በማድረግ በርካታ ኤጀንሲዎች ከፍተኛ ገንዘብ በዝግ ሒሳብ አካውንት አስቀምጠው ወደ ሥራ ተሠማርተዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ያሉት የአደረጃጀትና ሌሎች እየተነሱ የሚገኙ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ባለሀብቶቹ በተለይም ደግሞ ሕግና ሕጋዊነትን ብቻ አክብረው የሚንቀሳቀሱት በራሳቸውም ላይ የሞራል ክስረት፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ ደግሞ ከባድ የሆነ የኢኮኖሚ ውድቀትን እየተጋፈጡ ይገኛሉ፡፡ ኤጀንሲዎቹ በአዋጅ ቁጥር 632/2001 በተጣለባቸው መሠረት የላኳቸውን ዜጎች ደኅንነት የመከታተል፣ አቤቱታዎችን የማስተናገድና ተገቢውንና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት መሠረት ላለፉት 18 ወራት ያለምንም ገቢ ከፍተኛ የሆነ የቢሮ ክራይና የሠራተኛ ወርኃዊ ደሞዝ እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱና ሌሎች ሕጎች በሰጡን መብቶች ተጠቅመው ዜጎችን አገልግለውና ጠቅመው ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም በኢኮኖሚ እንጠቅማለን ብለው የተጀመረው ሥራ በደረሰበት ዕገዳና የዕገዳው ጊዜ ያለምንም ተጨባጭ ምክንያቶች መራዘም ለተለያዩ የጤና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ለዕለት ኑሯቸው ሀብትና ንብረታቸውን ሸጠው የሀብታም ችግረኛ ሆነዋል፡፡ ወይ ባንክ የተዘጋበት ገንዘባቸው ተለቆ አልሠሩበት ወይም ሴክተሩ የተባለው ማሻሻያ መጥቶለት ሥራ አልተጀመረም፡፡ በነገራችን ላይ ኤጀንሲዎቹ በአብዛኛው ሠራተኞቻቸውን ያሰናበቱ ሲሆን፣ ይህ በራሱ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ መገመት አያዳግትም፡፡ የዜጎችን ነፃነት፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት ያረጋገጠ ሕገ መንግሥት በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በአንዲት ቀጭን ትዕዛዝ እንዲህ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡

አገራዊ ኢኮኖሚ ጥቅም ያሳጣ ዕግድ

አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭ ሥራ ሥምሪት ዘርፍ ምን ያህል እያገኘች እንደሆነ ያገኘሁት ምንም ዓይነት ጥናት ባይኖርም፣ የሌሎች አገሮች በተለይም ደግሞ እንደኛው የቤት ሠራተኛ ወደ ዓረብ አገሮች የሚልኩ እንደ ኔፓል፣ ባንግላዴሽ፣ ህንድና  ፊሊፒንስ የመሳሰሉ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያስረዳው የየአገራቸውን ኢኮኖሚ በተለይም የውጭ ምንዛሪ በማሳደግ ረገድ ዘርፉ እየተጫወተ የሚገኘው ሚና ቀላል አለመሆኑን፣ የዓለም ባንክና የተለያዩ ድርጅቶች ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ዛሬ ግን ይህ ሕጋዊ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያትና በጥቂት ኪራይ ሰብሳቢዎች እጅ ሥር በመውደቁ አገሪቱ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል፡፡ ከተለያዩ አገሮች ልምዶች በመነሳት የውጭ ሥራ ሥምሪት በአግባቡ የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና መብት ማስጠበቅ ከተቻለ በርካታ አገሮች የውጭ ምንዛሪ (ሬሚታንስ) በማግኘት ለአገራቸው ልማትና ዕድገት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚቻል መሆኑን፣ የዓለም ባንክ ሪፖርቶችን ማገላበጥ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡

ማጠቃለያ

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዘርፉ ከሌሎች አገሮች ልምዶች በመነሳት ስንመለከተተው የአመራር፣ የአደረጃጀትና የብቃት ችግር ውስጥ እንዳለ ለመረዳት ያለፉትን 18 ወራት ሥራ መመልከት ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡ መንግሥት በተለይም የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸው ሴክተሮች በማጥራት ሕዝቡም ሆነ ባለሀብቱ ሕጋዊና ሕጋዊ አሠራርን ብቻ ተከትለው ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ፣ ኃላፊነቱን ብቃትና አቅም ላላቸው ሰዎች መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ከእምዬ ወደ አብዬ ሆነ የምክንያትን፣ በቅርብ አስተሳሰብና በዜጎች ላይ የመቀለድ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን የማጣት አስተሳሰብ ሃይ ሊባል ይገባል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜል አድራሻቸው [email protected]   ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...