በእስክንድር መርሐጽድቅ
‹‹የሚያደምጥህ የለ … ወይ የሚሰማህ፣
እያለህ ካልሆነ … ከሌለህ የለህም›› አይደል ያለው፤ ታዋቂው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ? እውነቱን ነው፤ ምክንያቱም፤ ይህን የሚያጠናክር ነገር አይቻለሁና!
አራት ኪሎ አካባቢ ቀጠሮ ይዤ ወይም ሌላ ጉዳይ ኖሮኝ ጊዜው ካልደረሰ ወይም ከተረፈኝ እየዞርኩም ሆነ ቁጭ ብዬ ከምቆምባቸው ቦታዎች ዋነኛው ከፓርላማ አጠገብ የሚገኘው መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነው፡፡ ካቴድራሉ ከምቀመጥበት ይልቅ እየተዟዟርኩ የምጎበኝበት ጊዜ ይበልጣል፡፡
ቅድስት ሥላሴ ገብተው ከተዘዋወሩ ከምዕራብ መግቢያ በቤይሩት አውሮኘላን መከስከስ ካለቁት በርካታ ተጓዥ እህቶቻችንና የበረራ አስተናጋጆች እንዲሁም አብራሪዎች ሐውልት ይጀምሩና በስተደቡብ እስካለው ደርግ በግፍ እስከገደላቸው 68ቱ የአፄ ኃይለ ሥለሌ ሹማምንት መታሰቢያ ይደርሳሉ፡፡ ትንሽ እልፍ ብለው በስተጓሮም የቅዱስ በዐለ ወልድ ግቢንም ሆነ ባሻገር የፉካ መካነ መቃብሮችን ቃኝተው ሲመለሱ የበርካታ ሊቃነ ጳጳሳት ዕረፍት ቦታን ከሐውልታቸው ይረዳሉ፡፡ ዘወር ብለው ወደ ሰሜን የካቴድራሉ መውጫ ሲያቀኑ የታዋቂውን ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤን ከወገብ በላይ ቅርጽ ከሐውልቱ ላይ ተለጥፎ ይመለከታሉ፡፡
ብዙም ሳይርቁ ደግሞ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መለስ ዜናዊ አጽም ያረፈበት ሐውልት ዘንድ ይደርሳሉ፡፡ ለሁሉም ከንፈርዎን መጠው የምዕመናን ማረፊያ ክልል (ፓርክ) ውስጥ አረፍ እንዳሉ ከሁሉም ጎልቶ የሚታይ ሐውልት ያዩና አላስችል ብሎዎት ተነስተው ይሄዳሉ፡፡ እዚያ ጉልህ ሐውልት ዘንድ ከመድረስዎ በፊት ደግሞ በ1980 ዓ.ም. ያረፉት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት መታሰቢያ ቅርጽ ይጎበኛሉ፡፡ ከእርሳቸው ቀጥሎ ያለው ግርማ ሞገሳማው ሐውልት ደግሞ ከሩቅ ጠርቶዎታልና ሲጠጉ ከሦስት ዓመት በፊት ያረፉት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ግዙፍ ምስል መሆኑን ይረዳሉ፡፡
እኔ ከአንድም ሁለቴ እንዳጋጠመኝ እርስዎም ካጋጠመዎት በዙሪያው ካሉት ዛፎች የረገፉትን ቅጠሎች የሚጠርግ ሰው ላያጡ ይችላሉ፡፡ ደፈር ብዬ እንደጠየቅሁት ከደፈሩ ደግሞ፣ ‹‹ምናለ በነካ እጅህ የዚያኛውንም ሐውልት አቧራና የሸረሪት ድረ ብታነሳ?›› ሊሉት ይችላሉ፤ እንደ’ኔ በግልምጫ ከመነሳት ግን እንዲሰውራችሁ እመኝላችኋለሁ፡፡ ዕድለኛ ሆነው ከተሰሙ ደግሞ፣ ‹ተመስገን!› እልዎታለሁ፡፡
እንዲህ አሽከርክሬ የምመልሳችሁ አንድ መካነ መቃብር ዘንድ ላሳርፋችሁና ትዝብቴን ላካፍላችሁ ፈልጌ ነው፡፡ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳወሎስ ቀጥሎ በ1952 ዓ.ም. ያረፉት የጎንደሩ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል እና በ1958 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የሌተናል ጄነራል መርዕድ መንገሻ ሐውልቶች ያጋጥዎታል፡፡ አልፈው መንገዱን ሲሻገሩ ደግሞ በፀረ ሙስና ትግሉ ስማቸው በክብር የሚነሳው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቀድሞው ርእሰ መስተዳድር አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ ግሩም ተደርጎ የታነፀው ከአንገት በላይ ምስል ቀልብዎትን ይገዛል፡፡ ስለርሳቸው በተባለውም፣ ባልተባለውም ነገር እየተከዙ ወደቀኝ በኩል ራመድ ሲሉ የአንድ በሙያው አንጋፋ የሆነ ሰው ቅርጽ መላ አካሉን በሚያሳይ ሁኔታ በግቢው ውስጥ ካሉት ሁሉ በብቸኝነቱ ቆሞ ያጋጥሞዎታል፤ የታዋቂው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት፡፡
ሥራዎቹን የሚወዱለት ከሆነ (መቼም ሕዝብ ሁሉ ይወድለታል ባልልም አብዛኛው ወዳጁ ይመስለኛል) ‹‹ይገባሃል!›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ ግን ግን ምነው ተንከባካቢ አጣሳ? በአቧራና በወዳደቁ ነገሮች ጽዳት ጎድሎታል እኮ! የሕይወት ታሪኩ ከተጻፈባቸው የእብነበረድ ድንጋዮች አንደኛው ከወገቡ በላይ ድር እስኪያደራ ተለያይቷል፡፡ ደግሞስ ለምንድን ነው አጥር ያልተሠራለት? ‹‹ወገን አለኝ›› ላለ ታላቅ ሰው ይህ አይመጥነውም፡፡ ከባለቤቱ ጀምሮ የሚመለከተው የሚገባውን እድሳትና ክትትል ቢያደርጉለት መልካም ነው፡፡ በበኩሌ እርሱ ላይ የወደቁ ነገሮችን አንስቼና የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ይማኖትን ሐውልት ሸረሪት ድር ጠርጌ በማለፌ ትንሽ እፎይታ ተሰምቶኛል፡፡ ነገር ግን የነገሬ ሁሉ መነሻ የሆነው የአንድ ሰው መካነ መቃብር ከማስቆጨትም በላይ አሳሰበኝ፡፡
እስከ አሁን በምናብ ካስቃኘኋችሁ ሐውልቶች የታነፀላቸው ሰዎች አብዛኞቹ ዕውቅናቸው ወይም የተሰጣቸው ማዕረግ አገር አቀፍ ነው፡፡ ቀጥሎ የማስቃኛችሁ ሰው ግን ከአገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥራቸው የታወቁ ባለማዕረግ፣ ከምድራችን አልፎ ደግሞ ሥራቸው በጨረቃ ላይ እንዲያርፍ የተደረገ ናቸው፤ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፡፡ እኒህን ሰው የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ከአመዛኙ ያነሰ እንጂ የሚበልጥ አይደለም፡፡ የርሳቸው ብሩሽ ያረፈባቸው ሥዕሎች በየሕትመት ውጤቶች፣ በየሥዕል ኤግዚቢሽኖች (ጋለሪዎች)፣ በየእምነት ተቋማት እና በታላላቅ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን፤ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በ2004 ዓ.ም አጽማቸው ባረፈበት ላይ ከተራና ጥቁር ቀለም ከተቀባው አጥር እና በመስቀል ቅርጽ ከተተከለው የቆርቆሮ ምልክት በቀር የሚታይ ነገር አለመኖሩ ለሥራቸውና ለክብራቸው የሚመጥን አይደለም፡፡
አርቲስቱ በሕይወት ሳሉ በዙሪያቸው በርካታ አድናቂዎቻቸው የሚከቧቸውን ያህል የቀብራቸው ዕለት ከመገኘት ውጪ አሁን የት እንዳሉ እንደረሷቸው ይህ ብቻ በቂ ምስክር ነው፡፡ ሌለው ቢቀር ከሥራዎቻቸው የአንዱን ሥዕል ቅጂ (ኮፒ) በመስታወት ማድረግ ወይም መጠነኛ ቅርጽ ማቆም ማንን ገደለ? የቀብራቸው ዕለት ያ ሁሉ አጀብ ለታይታ ወይም ለካሜራ ብቻ ነበር እንዴ?
በበኩሌ ሦስት አካላትን ታዝቤአለሁ፡፡ በመጀመሪያ መንግሥትን እናንሳ፡፡ አርቲስቱ በሕይወት ዘመናቸው ያፈሯቸውን ሀብቶች፣ የሣሏቸውን ሥዕሎችና ‹‹አልፋ ቪላ›› የተሰኘ መኖሪያ ቤታቸውና ጋለሪያቸውን በኑዛዜ ያወረሱት ለመንግሥት ነው፡፡ ይህ ወደ ገንዘብ ቢለወጥ በርካታ ሚሊዮን ብር ይሆናል፡፡ ታዲያ… ይህ የተሰጠው መንግሥት ለሰጪው እጁ ማጠር አለበት? ለእኔ፣ ‹‹ወርቅ ላበደረ ጠጠር›› እንደተባለው ነው የሆነብኝ፡፡ ሌላው ተወቃሽ የኢትዮጵያ ሠዓልያን ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ ለአርቲስቱ የሚመጥነውን የማድረግ አቅም ቢያጣ እንኳ መንግሥት ላይ ግፊት ማድረግ አይችልም? ‹‹ወዳጅ›› የሚባሉት ደግሞ በሦስተኛ ደረጃ የሚወቀሱ ናቸው፡፡ የአርቲስቱ ወዳጅነት እስከ ዕረፍታቸው ድረብ ብቻ ነው እንዴ? ብዙ ባልላችሁም አንባቢ ይፍረድ! አራተኛ ብዬ ያላስቀመጥኳቸው ዘመዶችን ነው፤ ስለዛ ብዙ ነገር ስለሚወራና እርግጠኛ ባልሆንኩበት መፍረድ ስለማልችል!
ለማንኛውም፣ ‹‹የሚያደምጥህ የለ … ወይ የሚሰማህ፣ እያለህ ካልሆነ … ከሌለህ የለህም!›› የተባለው ነገር ከዚህ በኋላ በኒህ አርቲስት መካነ መቃብር ላይ መታሰብ የለበትምና የሚያስብ ያስብበት! ምናልባት እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ትዕዛዝ መቃብራቸውን የማስዋቡን ነገር፣ ‹‹ይቅርብኝ›› ብለው ከተናዘዙ ሐሳቤ ባለማወቅ እንደተሰነዘረ ተደርጎ ይያዝልኝ፡፡ ካላሉ ግን ትዝብት ነው መንግሥት! ትዝብት ነው የሠዓልያን ማኅበር! ትዝብት ነው ‹‹ወዳጅ››!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ፀሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡