Monday, June 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያና ግብፅ ከመስማማት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም

በልዑል ዘሩ

ኢትዮጵያና ግብፅ በታሪክ፣ በሃይማኖትም ሆነ በጦርነት የነበራቸው ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ ነው፡፡ አጥቂውም ሆነ ተጠቂው የትኛውም አገር ቢሆን የሁለቱ አገሮች ለዘመናት የተሻገረው የበጎና የክፉ መፈላለግ መነሻው ዓባይ (ናይል) መሆኑም ነጋሪ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡

ጥንትም ቢሆን የግብፅ ነገሥታትና መሪዎች አቅም ባይኖራቸው ተፈጥሮ እደጃቸው ድረስ ያመጣውን የዓባይ ወንዝ ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡ የወንዙ ምንጭ ከኢትዮጵያ ተራራማ ሥፍራ መሆኑን ባይስቱትም፣ ኢትዮጵያዊያን እየተራቡና እየተቸገሩ ግብፅ ስለመድረሱ አይጨነቁም፡፡ የውኃውና የጎርፉ መጠንከር ግብፃዊያኑን የሚያጥለቀልቅበት ጊዜም እጅግ ይበዛ ነበር፡፡

በዘመናዊው የግብፅ ታሪክ (ቢያንስ ከ100 ዓመታት ወዲህ) ያለው ጊዜም ሲታይ ግብፃዊያን በቅኝ ገዥዎቻቸው እየተደገፉ ጭምር ውኃውን በበላይነትና በኢፍትሐዊነት ለመጠቀም የተጉበት ነበር፡፡ ከዚያም ብሶ በዋናነት ግብፃዊያን፣ በመቀጠል ሱዳናዊያን በተናጠልና በጋራ የሚጠቅማቸውን፣ ነገር ግን ኢትዮጵያንና ሌሎቹን የተፋሰስ አገሮች እንደ ባለድርሻ እንኳን የማይቆጠር ስምምነትና ውል እያዘጋጁ፣ ‹‹ሥራ ላይ ውሏል›› በማለት ለበርካታ አሥርት ዓመታት ተጠቅመውበታል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ገዥዎችም አንድም ዕውቀት፣ ገንዘብም ሆነ ቁርጠኝነት በማጣት በሌላ በኩል ከጦርነትና ከድርቅ አጀንዳ ለመውጣት ባለመቻል ዓባይን ሲረግሙ ብቻ ኖረዋል፡፡ ሕዝቡም በወንዙ ከመተረት ውጪ ግብፃዊያኑም ሆኑ ሌሎች የሚጠቀሙበት በኢፍትሐዊነት መሆኑን ቢረዳም፣ ምንም ሊያደርግ ባለመቻሉ እግርና እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ኖሯል፡፡

በዚህ ላይ የግብፅ የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ መሪዎች ግልጽና የእጅ አዙር ጫና ሊካድ የሚቻል አልነበረም፡፡ ዜጎች ያላቸውን አቅም አሟጠው ትርፍ አምራች መሆን ወደሚችሉበት ሥራ እንዳይገቡ ከማዳከም አንስቶ በዘር፣ በብሔርና በሃይማኖት እንዲባሉ ትውልድ የተሻገረ ጫና ደርሶባቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ግብፃዊያኑ በአውሮፓ ገዥዎች (በተለይ በእንግሊዝና በጣሊያን) አለፍ ሲልም በቱርክ በመታገዝ በሰሜንና በምሥራቅ በርካታ ጦርነቶችና ጥቃቶችን እስከመሰንዘር ደርሰዋል፡፡ ያ ሁሉ ያለፈ ታሪክ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ አቅም መፍጠርና ቀና ማለት የቻለችባቸው ያለፉት ሃያ ዓመታት እንደመሆኑ፣ በዓባይ ጉዳይ ላይ ዓይናችን መገለጥ የቻለውም በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ የውኃ አጠቃቀም አቅሙን በማሳደግ፣ በውስጥ አቅም የመፈጸም ብቃትና የካፒታል ጉልበትን በማጠናከር ሲዘጋጅ፣ በሌላ በኩል ይህ ለዘመናት ያለፍትሐዊነት ሲፈስ የኖረው የአሥር አገሮች የውኃ ሀብት እንዴት የጋራ ጥቅም እንደሚሰጥ ሲያስብና ሲመክር ኖሯል፡፡

የናይል የተፋሰስ አገሮች የምክክር መድረክ የሚባለው የውኃ ማኅበር ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያን ጨምሮ እነ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያን ጨምሮ አሥር አገሮች የሚገኙበት ነው፡፡ ግብፃውኑም ሆኑ አንዳንዶቹ አገሮች ገባ ወጣ እያሉም ቢሆን በውኃ አጠቃቀሙ ፍትሐዊነት ላይ ሲመክሩ መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ የብዙዎች ግምት ላይሆን የሚችለው እ.ኤ.አ. ከ2010 በፊት አገሮቹ የሚስማሙበት የትግበራ ማዕቀፍ መፅደቁ ላይ ነበር፡፡ ነገሩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የምሥራቅ አፍሪካ ደሃ ሕዝቦች (እስካሁን የዓለም ደሃ ቀጠና እንደሚባል ልብ ይሏል) ጉዳይ በመሆኑ፣ በፍጥነት መቀራረብ የታዩበት የውኃ ስምምነት በአብላጫ ድምፅ መፅደቁና አንዳንዶቹ አገሮችም ይህን ተከትለው በየአገራቸው በማፅደቅ ሕግ ማድረጋቸው የዘርፉን ምሁራን አድናቆት አስገኝቷል፡፡

የአገሪቱን ስምምነት ተከትላ ኢትዮጵያ የወሰደችው በፍትሐዊና በምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ደግሞ አስደናቂ ነበር፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ታሪካዊ ንግግር የታጀበ የስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጫ ግድብ መሠረት ድንጋይ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ውስጥ ተቀመጠ፡፡ የማይነካውና የማይደፈረው ዓባይም ዕድሜውን ሙሉ አድርጎ ለማያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ግልጋሎት የሚሰጥበት ዕቅድ እውን ሆነ፡፡

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ ደብረ ማርቆስና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ 750 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምድር ጉባ ላይ ነው የሚገነባው፡፡ ለሱዳን ድንበርም ከ30 ኪ.ሜ ባነሰ ርቀት ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን የግድቡን ፋይዳ ሲያብራሩ፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልና በአማካይ 15,692  ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በዓመት ማመንጨቱን ብቻ አይገልጹትም፡፡

የኃይል ማመንጨቱ ጉዳይ ኤሌክትሪክ ያልተዳረሰባቸውን የገጠር መንደሮችና ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግና አቅርቦቱን አሁን ካለበት 46 በመቶ ወደ 75 በመቶ፣ ይልቁንም ሌሎች ፋይዳዎች ብዙም እየተነገረላቸው ባለመሆኑ ነው፡፡ በ1,680 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት፣ በ145 ሜትር ጥልቀት፣ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር  ውኃ ማቆር የሚችለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ሲፈጠር በአገሪቱ ብቻ ሳይሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካም አዲስ የውኃ ሀብት (ሰው ሠራሽ ሐይቅ) ይፈጠራል ነው የሚሉት፡፡

የሚፈጠረው ሐይቅና ደሴቶች ለብዙ የሐይቅ ዳር አዕዋፍና መስህብ መዳረሻ ይሆናል፡፡ በዚህም በአካባቢው ነዋሪ ለሆኑትም ሆነ ከሌላ ቦታ ፈልሰው ለሚመጡ አዕዋፋት ተመራጭ ቦታ ይሆንላቸዋል፡፡ የውኃ ኃይል ማመንጫ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ነፃ በመሆኑ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአካባቢ ሥነ ምኅዳርንም በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተደጋግሞ ተረጋግጧል፡፡ አሁን በተጨባጭ እያየነው እንዳለው በግንባታ ወቅት በአሥር ሺሕዎች ለሚቆጠሩ ለአገሪቱ ዜጎች (መሐንዲሶች፣ ኦፕሬተሮች ፎርማኖችና የቀን ሠራተኞች…) የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ በፕሮጀክቱ አካባቢ የሚፈጠረው ከተማ፣ መሠረተ ልማትና የቱሪዝም መዳረሻ ሁሉ የአገር ሁለንተናዊ ጉዞን የሚያሳድግ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ ከራሳቸው አልፎ ለጎረቤትም ይተርፋል ያሉትን ጥቅም እያሰቡ በስፋት ወደ ሥራ በገቡበት በዚህ ወቅት በግብፃዊያኑ በኩል ግን ምቾት አልነበረም፡፡

በተለይ የግድቡ ግንባታ መጀመርና በግብፅ ለ30 ዓመታት ሥር የሰደደውን ፀረ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የገረሰሰው ሕዝባዊ አብዮት መፈንዳት ሆን ተብሎ እንደተገናኘ የሚገምቱ ነበሩ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የግብፅ ሕዝብን ጥቅም ሆን ብላ ለመንጠቅ ‹‹ባላጣችው የውኃ ሀብት›› በዓባይ (ናይል) ላይ ግድብ መገንባት ጀመረች ተብሏል፡፡ በተለይ አብዮቱ ወደ መሪነት ያመጣችው የሙስሊም ወንድማማቾች መሪዎች፣ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገሪቱ ታዋቂ መገናኛ ብዙኃን ይህንን አስተሳሰብ አራግበውት ቅሬታውን ለማክረር ሞክረዋል፡፡

ወትሮም የግብፅ ሕዝብን ስሜታዊነት በዓረብ ፖለቲካና በዋነኛ ጥቅሙ ናይል ላይ የሚያዘምቱት የግብፅ መሪዎች የውኃ ድርድሩን በማቋረጥ፣ በሦስትዮሽ (ሱዳን ግብፅና ኢትዮጵያ) ውይይት ገባ ወጣ በማለት አልፎ አልፎ በሥነ ልቦናና በዛቻ ግድቡን ለማስቆም ሞክረዋል፡፡ ቀድሞውኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የግንባታውን ጉዳይ አስቦበት መነሳቱ እንጂ፣ ብድር የማስከልከልና ድጋፍ የማሳጠት ዘመቻውም ከፍተኛ ነበር፡፡ ያ ሁሉ የማያስኬድ ተግባር አለፈና ዛሬ የሁለቱ አገሮች መቀራረብና መተማመን አንድ ደረጃ የተሻሻለ መስሏል፡፡

በወዲያኛው ሳምንት በግብፅ ፖርትሳይድ በተካሄደው የግብፅ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጻ ይህንኑ አባባል ያጠናክራል፡፡ ‹‹እና የዓባይ (ናይል) ወንዝ ያስተሳሰረን የቀጣናው ሕዝቦች በውኃ አጠቃቀምም ሆነ በሌሎች መስኮች ተባብረንና ተደጋግፈን የሕዝባችንን ጥቅም ልናስከብር ይገባል፡፡ የናይል ወንዝም ቢሆን የጋራ ትብብር ፍሬ የሚታይበት እንጂ የቅሬታና ያለመግባባት መነሻ ሊሆንም አይችልም፡፡ ስለሆነም ያለን ዕድል በሁሉም መስክ ተደጋግፎ ማደግ አልያም ተይይዞ መስጠም መሆኑን ተረድተን ልንሠራ ይገባል፤›› ነበር ያሉት፡፡

በፎረሙ ተሳታፊ የሆኑ ከሁለት ሺሕ በላይ የንግድና የኢንቨስትመንት ተወካዮች እንዲሁም የአገሮች መሪዎች በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰነዘሩት ጠቃሚ ንግግር. መተማመንን ይበልጥ የሚያዳብር መሆኑን ተንታኞች አብራርተዋል፡፡ በእርግጥ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ካለፉት የግብፅ መሪዎች በተሻለና በተለየ ሁኔታ የናይል ውኃን የጋራ ሀብትነት የተቀበሉ መስለዋል፡፡

‹‹የናይል ውኃን በቁጠባና በውጤታማነት ከተጠቀምንበት ለሁላችንም ይበቃል፤›› ሲሉ በቀዳሚነት ያስቀመጡትን የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሐሳብ ፕሬዚዳንት አልሲሲ አሁን የተናገሩት ነው፡፡ ግብፃዊያን ‹‹ዓባይ የህልውናችን ጉዳይ እንደመሆኑ ነባሩ ጥቅማችን ሊነካ አይገባም፡፡ ይህን የተረዳ አካሄድን ግን አቁሙ ልንል አንችልም፤›› ማለታቸው ለውይይትም ሆነ ለስምምነት አንድ ዕርምጃ ተደርጎ መወሰድ አለበት ሊበረታታም ይገባዋል፡፡

ይህ ማለት ግን የግብፅ የውኃ ባለሥልጣናትና ተደራዳሪ ሙያተኞች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተለያዩ ጥርጣሬ ያላቸውም ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ወረቀት ላይ አርፎ ወደ ሙሉ መተማመን የተገባበት ስምምነት እስከሌለም ድረስ አልቆለታል ማለት ያስቸግራል፡፡ ከሰኔ 2005 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2007 ዓ.ም. በሱዳን፣ በግብፅና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገው ውይይት እልህ አስጨራሽ ሒደት መታለፉን የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ግብፃዊያኑ ግድቡን በጋራ እንገንባ ከማለት አንስቶ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማስቀመጥ ሞክረዋል፡፡ በኤሌክትሪካልና በመካኒካል ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት የሚሰጡ አስተያየቶችም ነበሩ፡፡ የግድቡን ፋይዳና ገጽታ በጋራ እናጥና በማለትና የጥናት ውጤቱን ለመቀበል የተስተዋለው ማንገራገር፣ እስካሁንም ድረስ ጥናቱንም ሆነ ውይይቱን በሙሉ ልብ ለመቀጠል ያለመቻሉ ድምር ውጤት ነበር የታየው፡፡ ይህ ግን ግንባታውን ለሰከንድ ያለቆመና የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙሉ ድጋፍ ያልተለየው ቢሆንም የግብፃዊያኑ ይፋዊ ይሁንታ አልቸረውም፡፡

ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ንግግርና ጉብኝት ወይም ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ተመሳሳይ አስተያየት በጎ እውነታዎች ባሻገር ሌሎች መልካም ሁኔታዎችም ታይተዋል፡፡ በቅርቡ ሱዳን ካርቱም የተገናኙት የሦስት አገሮች የውኃ ባለሙያዎች የጋራ ጥናቱን ለማካሄድ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን መሠረት በማድረግ የውሳኔ ሐሳቡን ለየመንግሥታቸው በማቅረብ በተደረሰው መግባባት መሠረት ሦስቱ አገሮች የመርህ ስምምነት ማድረጋቸውን ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያና የግብፅ መንግሥታት ለሕዝቦቻቸው ጥቅም የሚበጀውን የድርድርና ውይይት መንገድ መምረጣቸውና ከግጭትና ንትርክ መውጣታቸው የሚበረታታ ነው፡፡ ለዚህም ነው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ታላቁ አብርሃም ሊንከን እንደተናገሩት የሚታመንበትን የጽሑፌ መነሻ ርዕስ ያደረግኩት፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በየትኛውም ዓለም ያሉ መንግሥታት የሕዝቦቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ከመወያየትና ከመስማማት ውጪ ሌላ መልካም መንገድ የለም፡፡ እልህ፣ ማናለብኝነት፣ ግጭትና አለመግባባት የትኛውንም ወገን ዋጋ  የሚያስከፍሉ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት የፓርላማ ንግግራቸው፣ የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት ገልጸው የሁለቱን አገሮች አስተሳሰብ አንድ ለማድረግ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ መናገራቸው ጥሩ ነው፡፡ የመተማመን ድልድይ በመገንባትና የጥርጣሬ ክፍተቶችን በማጥበብ ሁለቱን ሕዝቦች ለጋራ ብልፅግና ማነሳሳት አስፈላጊነትን በማውሳታቸው አዎንታዊ አቀባበል ተችሮአቸዋል፡፡ ካርቱም ላይ የተፈረመውን ስምምነት አገራቸው በማክበር ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች ጋር በጋራ ለመሥራት መነሳቷን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ የካርቱሙ ስምምነትም ለመጪው ትውልድ ውጤታማ ግንኙነት መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል፡፡ ከትብብር ውጪ ምንም መፍትሔ እንደሌለ መቀበላቸው ድጋፍ ይቸረዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የግብፅና የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድኖች በተለያየ መንገድ ትስስር ይፈጥሩ ዘንድ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የግብፅ ኢንዱስትሪ ልምድ ሊቀስምበት ይገባል፡፡ እንዳለፈው ዓመት የግብፅ ኢኮኖሚ መረጃ በኤክስፖርት (ወጪ ንግድ) 25.6 ቢሊዮን ዶላር ስታገኝ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባችው (ኢምፖርት) ደግሞ 59.3 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ከዚህ ሰፊ ከፒታል አገራችን ልትጠቀም የምትችልበት ዕድል አለ፡፡ አንደኛው ግብፃዊያኑ በስፋት የሚፈልጓቸውን የግብርና ምርቶች፣ የእንስሳት ሀብትና ቆዳን በመላክ ሲሆን ሌላኛው ግብፅ በስፋት ከምታመርታቸው የምግብ ዘይት፣ አልባሳት፣ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል ማስፋት ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ ጉርብትና በሌላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል ሊያቃልል የሚችለውን የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በረጅም ጊዜ ማሰብ ይገባል፡፡ እንደ ውኃ ትራንስፖርት ያሉ አማራጮችንም ማየት እንዲሁ፡፡ በተጨማሪ የግብፅ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የጀመሩት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴም ዘርፉን ማስፋት ብቻ ሳይሆን፣ በተጨባጭ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ የሚጠቀሙበት ሊሆን ይገባል፡፡

ግብፃዊያኑ ከነጭ ዓባይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ጋር የጀመሩት አዲስ ግንኙነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ በኡጋንዳ፣ በብሩንዲና በደቡብ ሱዳን ግድቦችንና የመስኖ ሥራዎችን በጋራ እስከ መሥራት ይደርሳል፡፡ ይህን ተግባር ለመከልከል የማይቻል ቢሆንም፣ ግብፅ ለረጅም ጊዜ በአገሯ ይዛቸው የነበሩ የመስኖ ዕቅዶች ላይ መነጋገር ግን ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የዓባይ (ናይል) ውኃን ለከፍተኛ ብክነት ያጋልጣል የሚባል አዲሱ የሲናይ በረሃ የመስኖ ልማት ለመጪው ጊዜ የውኃ እጥረት ጭቅጭቅን የሚጋብዝ ስለሆነ ሊጤን የሚገባው ነው፡፡

በአጠቃላይ ግን በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው መስተጋብርና መቀራረብ ዓባይ ሊያጨቃጭቅ የማይችል ጉዳይ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ጥቅም የሚበጀውን መንገድ የተከተለም ነው፡፡ ይጠናከር ይስፋፋ እንላለን፡፡ አሁንም ከመስማማት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው   [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles