በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ብሔሮች አንዱ የሆነው ኦሮሞ በረዥም ማኅበራዊ ታሪኩ የፈጠራቸው ያዳበራቸው ልዩ ልዩ ባህላዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ ከአኗኗር ዘዴ ውስጥ የሚተዳደርበት የገዳ ሥርዓት ተጠቃሽ ሲሆን በውስጡ ካሉት ተቋማት መካከል የሞጋሳ ተቋም አንደኛው ነው፡፡
የኦሮሞን ሕዝብ ባህልና ወግ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችለውን የባህል ማዕከልና ሙዚየም በአዲስ አበባ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. መመረቁን ተከትሎ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ ጥናትና የታሪክ ጥናት ቡድኖች በጋራ ባዘጋጁት መጣጥፍ ላይ ስለሞጋሳ ተቋም እንዲህ ተጽፏል፡፡
ሞጋሳ ማለት በአንድ ማኅበረሰብ ወይም ግለሰብ ላይ የተፈጥሮ ወይም የሰው ሠራሽ ልዩ ልዩ ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ከነበሩበት ቦታ በመፈናቀል ወደ ኦሮሞ ማኅበረሰብ በጥገኝነት ለማሳለፍ በሚመጡበት ወቅት፤ የኦሮሞ ማኅበረሰብም እንደ ወገናቸው የተቸገረውን ጥገኝነት ጠያቂውን ከራሱ ማኅበረሰብ በመቀላቀል የሚያስተሳስር ተቋም ነው፡፡
በዚህ ተቋም ውስጥ ጥገኝነት ጠያቂው ማኅበረሰብ ወይም ግለሰብ ለአንድ የኦሮሞ ቤተሰብ ወይም ጎሣ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት የጎሳው መሪ ወይም ኦዳ መልካ (ባለ ይዞታ) የዘመኑን አባገዳዎችና የጎሣ መሪዎች በተወሰነ ቦታ በማሰባሰብ ቀደም ሲል የወጣውን የገዳ ሕግና ደንብ በመጥቀስ ሥርዓቱ እንዲካሄድ ጠያቂውንና እሱ የመረጠውን ቤተሰብ የሚወክል ሕግ አዋቂዎችን በጉልበታቸው በመንበርከክ ‹‹ኮቱ ዱፌ›› ስማ አሰማ በማለት የነበረውን የሞጋሳ ሕግና ደንብ እንዲናገሩ ያመለክታቸዋል፡፡ ይህንንም በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፡-
ይህ ሰው ወይም ማኅበረሰብ ሞጋሳ ጠይቋል!
ሞጋሳ የገዳ ሕግ ነው!
አዎ የገዳ ሕግ ነው!
ለሞጋሳ የመረጠው ቤተሰብ ከኛ ጎሣ ነው!
አዎ ነው!
የሞጋሳው ሕግ የኛው ኦዳ ወይም ጨፌ ሕግ ነው!
አዎ የኛው ጨፌ ሕግ ነው!
በሞጋሳ ሂደት ስም መስጠት ሕግ ነው!
አዎ ሕግ ነው!
ስሙን የሚያወጣለት የሞጋሳው አባት ነው!
አዎ አባት ነው!
ይህ ሕግ የኦዳ ሕግ ነው!
አዎ የኦዳ ሕግ ነው!
የጨፌ ሕግ ነው!
አዎ የጨፌ ሕግ ነው!
በሞጋሳ መሠረት ልጄ ወገኔ ሆናል!
አዎ ልጄ (ወገኔ) ሆናል!
ይህ ሕግ አይፈርስም!
አዎ አይፈርስም!
በማለት አባገዳው ጦሩን መሬት ላይ ወግቶ በማቆም ሕጉ የጸና መሆኑን ያውጃል፡፡ በዚህ ጊዜም የሁለቱም ወገኖች በእማኝነት ቁመው ያዳምጣሉ፡፡ በተደነገገውም ደንብ በፈቃዳቸው ሞጋሳውን ማከናወናቸውን አለንጋቸውን በማንጣጣት ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚያችም ደቂቃ ጀምሮ የማኅበረሰቡ አካል ስለሆነ የሀብት መዋጮ ይደረግለትና ከመረጠው ቤተሰብ ጋር ይደባለቃል፡፡ ቤተሰብ እንዲያፈራና በጋዳ አባልነትም በሞጋሳ ከተደባለቀው ጋር የገዳ አባል በመሆን ይቀላቀላል፡፡ የሞጋሳ ሂደት በሚከናወንበት ጊዜ የገዳ ሕጉ ተጠቅሶ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ይህም የሁለቱም ክፍል መብቶች እንዲከበሩ የሚነገር ሲሆን ይህም አባ ገዳው ሽማግሌዎች አሮጊቶችና ሌሎችም የማኅበረሰቡ ተወካዮችና የሁለቱ ወገኖች እንዲገኙና ያለተቃውሞ በስምምነት መደረጉን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ለዚህም አባ ገዳው ይህንን ሞጋሳ በአምስቱ የገዳ ፓርቲዎች ስምና ሕግ መሠረት ማወጃቸውን የሚያመላክት በሁለት ዳኞች መካከል የሚደረግ፡-
አምስት አለንጋና አምስት ጦር እንዲጋደም ከተደረገ በኋላ ‹‹ኮቱ! ዱፌ! ና እሺ መጥቻለሁ›› በማለት ሕጉን ይዘረዝራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ሞጋሳ የሚገባውን ወገን ከሞጋሳ አድራጊው ጋር ኦሮሞ መሆኑን ያሳውቃሉ፡፡ ልጅነትም ካልፈለገ ሞጋሳው ከጎሳው ቤተሰብነት እንዲቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ጥቃቅን ጎሣዎች ከኦሮሞ ጋር በሞጋሳ ተቀላቅለው ከኦሮሞ ጋር በጥሩ ዝምድና እንዲኖሩ ሆነዋል፡፡
በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሲቄ አገልግሎት
ሲቄ በኦሮሞ ባህል ሴቶች ለሰላምና እርቅ የሚጫወቱትን ሚና የሚያሳይ ጠንካራ የባህል እሴት ነው፡፡
ሲቄ በኦሮሞ ባህል አንዲት ልጅ ስታገባ ወላጆቿ የሚሰጧት በትር ነች፡፡ አንዲት ሴት ልጅ በጋብቻዋ ወቅት የሰርጓለት እናቷ የምታስይዛት በትር ስትሆን በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ታገለግላታለች፡፡ ሕይወቷ ስታልፍና ስትቀበር ሰብረው አብረው ይቀብሯታል፡፡ በአንድ ቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ሲቄ መልካም ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አላት፡፡ የሴቷ መብት እንዳይደፈር፣ አለመግባባት እንዳይከሰት፣ ችግር እንዳይደርስባትና መብቷ እንዲከበር የምታደርግ ናት፡፡
ሲቄ ሴቶች በኅብረት ተደራጅተው በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖት በፖለቲካ ከወንዶች እኩል መብት እንዲጎናጸፉ ታደርጋለች፡፡ ሲቄ ግጭት ባለበትና አስጊ ሁኔታ ባለበት ቦታ እንደ ቦኩ ያላንዳች ስጋት ውጊያ መሀከል በመግባት የክፋት ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ድንበር በመሆን ግጭት እንዳይፈጠር የምታደርግ ናት፡፡ ለቦኩ የሚሰጠው ክብርና ሃይልም ሁሉ አላት፡፡ ከዚህ ሌላ ሲቄ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሴቶችን በማደራጀት ትሰራለች፡፡ ደም የተቃቡ አልያም የተጋደሉ ሰዎች ካሉ ሴቶች እታወቀ አደባባይ በመውጣት ሕግና ወግ ያለው ሲቄ (በትር) በመያዝ ልመናቸውን ያካሂዳሉ፡፡ ‹‹አባት ሆይ ለኛ ስትል ታረቅ›› ብለው ይማልዳሉ፣ የሚለመኑት ሰዎችም እሽ እስከሚሉ ድረስ ወደ ቤት መመለስ አይኖርም፡፡
ሴቶች ሲቄ ይዘው ከቤት ከሄዱ ቤተሰብ በሙሉ ይራባል፡፡ ጥጆች አይገናኙም፤ ለሕጻናት ምግብ የሚያዘጋጅ አይኖርም፡፡ ማንም ሰው ወደሥራና ምግብ ዝግጅት አይሰማራም፡፡ ማንኛውም የቤት ውስጥ እንቅስቃሴ ሁሉ ይቆማል፡፡ በመሆኑም ሽማግሌዎች አዋቂዎች ቦኩችና አባገዳችም በአደባባዩ በመገኘት ከሴቶች ጎን በመቆም ድጋፋቸውን ይሰጧቸዋል፡፡ ያለውን ችግር በማጥናትም ሁለቱም በክፋት የሚፈላለጉ ቡድኖች ወደ እርቅ እንዲመጡ ያስገድዷቸዋል፡፡ የሰው ሕይወት እንዳያልፍ በዘመቻ ወይም በግጭት ሳቢያ በጎሳና በሕዝብ መካከል አስከፊ ነገር እንዳይፈጠር በማድረግ ለእርቅ እንዲቀመጡ ያደርጋሉ፡፡ ያጠፋ እንዲክስና የተበደለም ካሳውን እንዲወስድ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ አኳኋን ሲንቄ በኅብረተሰቡ መካከል የእርቅ ተቋም በመሆን ስታገለግል እንደቆየች ያሳያል፡፡ በኦሮሞ ባህል ትልቅ ግጭት ከተፈጠረ ትልቅ ዘመቻ ከተደረገ ይህን ግጭት ለማቆም ትልቅ መብትና ብቃት አላት፣ ይህም ያለ አንዳች ፍርሃትና ማቅማማት ሴቶች ሲቄ ይዘው ‹‹ዲልቴንዲልና›› በማለት እልል እያሉ እርስ በእርስ እየተጨራረሱ ባሉት ጦረኞች መካከል ሲገቡ በውጊያ ላይ ያሉት ጦረኞች አዝማቾችም በእጃቸው የያዙትን የጦር መሣሪያ ወደታች በመዘቅዘቅ ‹‹አበኢ›› በማለት ጦርነቱን ያቆማሉ፡፡ ከዚያም በኋላ ቆስሎ በሕይወት ያለውን ያነሳሉ፡፡
ያላንዳች ፍርሃት የሞቱትንም ያነሳሉ ከዚህ በኋላም አዋቂዎች መሀል በመግባት የተፈጠረው ችግር መፍትሔ እንዲያገኝ ያደርጋሉ፡፡ ይህም በኅብረተሰቡ ለሲንቄ ያለውን ከበሬታ ያሳያል፡፡
በመሆኑም ሲቄ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ባህላዊ ሀብት ነው፡፡ እንዲሁም የሰላምና መረጋጋት መገኛ ምንጭ በመሆኑ ለወደፊቱም ከተሞክሮው በመማር እንዲቀጥል ማድረግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡