Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየባሌ ተራራዎች ሲፈተኑ

የባሌ ተራራዎች ሲፈተኑ

ቀን:

ባለጎፈሬ ዝንጀሮዎች መኪና ከርቀት ሲመለከቱ ወደሚመጣበት አቅጣጫ ይሮጣሉ፡፡ ወደ አካባቢው የሚሄዱ አንዳንድ ጎብኚዎች በመኪናቸው መስኮት ምግብ መስጠት ስላስለመዷቸው ተሽከርካሪ ሲያልፍ ይጓጓሉ፡፡ የዝንጀሮዎች መንገድ ላይ መገኘት አዲስ ባይሆንም፣ ወደ አካባቢው ለሚሄድ ጎብኚ ግር ሊል የሚችለው በዱር ነዋሪ የሆኑ ከርከሮዎች ወደ ሜዳ ወጥተው ከፈረስና አህያ ጋር እየተጋፉ ሳር ሲግጡ   መመልከት ነው፡፡  

ይህን ያስተዋልነበት በዓለም ላይ በብዝኃ ሕይወት ሀብት ከበለፀጉ 34 አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ተካቷል፡፡ በ1962 ዓ.ም. የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ያሉ አምስት ወረዳዎችና 26 ቀበሌዎች ያዋስኑታል፡፡ ፓርኩ 2,200 ስኲየር ካሬ ሜትር ስፋት የሳር ምድርና የደን መሬት (ከአደባ እስከ ዲንሾ ተራራ)፣ የፓርኩ ማዕከላዊ ክፍል (ሳነቴ ተራራና በዙሪያው ያለው የአሰጣ ቁጥቋጦ ደን) እና ሐረና ደንን ይሸፍናል፡፡

በፓርኩ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳት አሉ፡፡ ከነዚህ መሃከል 20ው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው ከእንስሳቱ ኒያላ፣ ቀይ ቀበሮና የደጋ አጋዘን ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የደጋ አጋዘን በሕጋዊ መንገድ ታድኖ ወደ 300,000 ብር ገደማ (ከየትኛውም የዱር እንስሳ በላይ) ይሸጣል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 200 የሚጠጉ አዕዋፋት በባሌ ተራሮች የሚኖሩ ሲሆን፣ ስድስቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አሥራ አንዱ ደግሞ በኢትዮጵያና ኤርትራ የሚገኙ ናቸው፡፡ በክረምት ወቅት ከተለያየ የዓለም ክፍል አእዋፋት ለመጠለል ወደ ፓርኩ ይሄዳሉ፡፡ ፓርኩ በወፍ ቱሪዝም ከአፍሪካ አራተኛ ነው፡፡  

በጫካ ቡና፣ መድኃኒትነት ባላቸው ዕፀዋትና ተራሮች የተከበበው ፓርኩ፣ ከኢትዮጵያ በከፍታ ሁለተኛው ቱሉ ዲምቱ (4377 ሜትር) ይገኝበታል፡፡ ከፓርኩ 1600 የዕፀዋት ዝርያዎች 32ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡ ፓርኩ የጎብኚዎች መዳረሻ ከመሆኑ ባሻገር ጥናትና ምርምር ይካሄድበታል፡፡ በቅርቡ የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ወደ 22 የሚሆኑ የቢራቢሮ ዝርያዎች አግኝተዋል፡፡ የተዘረዘሩትና የሌሎችም በርካታ ብዝኃ ሕይወት መገኛ የሆነው ፓርክ አጣብቂኝ ውስጥ ከገባ ሰነባብቷል፡፡

የፓርኩን ተፈጥሯዊ ባህሪ በሚፃረር መልኩ የሰዎች መኖሪያ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የሰፋሪዎች ቁጥር ወደ 40,000 ደርሷል፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎች አርሶ አደር ስለሆኑ ደኖች በመጨፍጨፍ እርሻቸውን እያስፋፉ ነው፡፡ የቤት እንስሳዎቻቸውም በፓርኩ እየኖሩ የዱር እንስሳቱን ሕልውና አደጋ ውስጥ ከተዋል፡፡ ሰዎቹም ይሁን እንስሳቱ በፓርኩ መከተማቸው ለብዝኃ ሕይወቱ እንደሚያሰጋ የዘርፉ ተመራማሪዎች በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ ሰሚ ያገኙ አይመስልም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ ጎጆ ወጪዎች በፓርኩ መኖር መብታቸው እስከሚመስል ድረስ ይዞታቸውን እያስፋፉ ነው፡፡

የአገሪቱን ስም የሚያስጠራው ይኸው ፓርክ ይባስ ብሎ ነዋሪዎች ሆነ ብለው አደጋ እያደረሱበት ነው፡፡ ባለፈው ወር አጋማሽ የተከሰተውን የእሳት አደጋ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አደጋው የደረሰው የሳንቴ ተራራ ሥር በሚገኘው የአስጣ ቁጥቋጦ ላይ ነው፡፡ እሳቱን ማጥፋት ስላልተቻለ ለሳምንታት መዝለቁና ከደቡብ አፍሪካ በመጡ ባለሙያዎች እገዛ መደረጉ ይታወሳል፡፡ እሳቱ አገር በቀል በሆኑ ዕፀዋትና እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳላደረሰና ከፓርኩ 90 በመቶ ጉዳት እንዳልደረሰበት ተገልጿል፡፡

ቢሆንም አደጋው ወጣት የተፈጥሮ ተቆርቋሪ ቢንያም አድማሱን ሕይወት የቀጠፈ መሆኑ በርካቶችን አሳዝኗል፡፡ አብረውት የነበሩ ሁለት ግለሰቦችም የቃጠሎ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ከፓርኩ አመራሮች ባገኘነው መረጃ መሠረት እሳቱን በማስነሳት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በአዳባ፣ ዲንሾና ጎባ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች የታሰሩት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ሲሆን፣ በፓርኩ 160 ኪሎ ሜትር የሚሆን የአሰጣ ቁጥቋጦ ተቃጥሏል፡፡

የፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ የኢትዮጵያ ተወካይና የብዝኃ ሕይወትና የዱር እንስሳት አጠባበቅ ባለሙያው ዶ/ር ዘላለም ተፈራ፣ በፓርኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ባለው ነዋሪዎች ሳቢያ እየደረሰ ያለው ጉዳት አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ይላሉ፡፡ ‹‹ፓርክ ውስጥ ሰው መኖር የለበትም፤ መንግሥት ያወጣው ሕግም ፓርክ ውስጥ ከሚሠሩ ባለሙያዎች በስተቀር ማንም ሰው እንዲኖር አይፈቅድም፤›› በማለት ነዋሪዎቹ በአፋጣኝ እንዲወጡ ያሳስባሉ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በተሠራ ጥናት ነዋሪዎቹ ወደ 60,000 እንደደረሱ ጠቁመው፣ የነዋሪዎቹ ቁጥር ሲጨምር ለከብቶቻቸው ግጦሽና ለእርሻ የሚያውሉት መሬት እንደሚሰፋ ያክላሉ፡፡

ደሪራ፣ ሐዋቦና ዋጌ በሚባሉ የሠፈራ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎችና እንስሳት ቁጥር ማንሰራራቱ አገሪቱ በዓለም ብቸኛ የሆነችባቸው ብዝኃ ሕይወቶች ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ይላሉ፡፡ በዋነኛነት የጠቀሱት ቀይ ቀበሮ ቁጥሩ ተመናምኖ የመጥፋት አደጋ አንዣቦበታል፡፡ ኢንተርናሽናል ዩኒየን ፎር ኮንሰርቬሽን ኦፍ ኔቸር ባወጣው መሥፈርት ቀይ ቀበሮ በከፍተኛ ደረጃ ለመጥፋት በደረሱ ዝርዝር ተካቷል፡፡ በዓለም ለመጥፋት ከተቃረቡ የውሻ ዝርያዎች መሃከልም ተቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡

ዶ/ር ዘለዓለም እንደሚናገሩት፣ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ነዋሪዎቹ ከሚያሳድጓቸው ውሾች ወደ ቀይ ቀበሮዎቹ የሚዛመቱ በሽታዎች ናቸው፡፡ ነዋሪዎቹ ራሳቸውንና የቤት እንስሳዎቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያሳድጓቸው ውሾች የእብድ ውሻ (ሬቢስ) ፣ አዲኖ ቫይረስ፣ ኢንፍሉዌንዛና ሌሎችም በሽታዎችን ወደ ቀይ ቀበሮዎቹ ያጋባሉ፡፡ ቀይ ቀበሮዎችን ለመታደግ በፓርኩ በዓመት ከ5,000 እስከ 10,000 ውሾች ቢከተቡም በሽታውን ፈጽሞ ማቆም አልተቻለም፡፡ በዋናነት ከአሩሲ፣ ሸካ፣ ጭላሎና ከሌሎች አካባቢዎች የሚመጡ ነዋሪዎችን ተከትለው የሚመጡ ውሾች ያልተከተቡ ስለሆኑ የተከተቡትን ይበክላሉ፡፡ ባለሙያው ከአንድ ወር በፊት በሽታው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ 50 ቀይ ቀበሮዎች ተይዘው መከተባቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

ከነዚህ ችግሮች በተጓዳኝ ነዋሪዎቹ ጫካውን ይመነጥሩታል፡፡ ባለሙያው ከሚጠቅሷቸው አንዱ በሐረና ጫካ ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ ነው፡፡ በአካባቢው የጫካ ቡና ቢገኝም፣ የቡና ምርትን ለማስፋፋት ጫካው እየተመነጠረ ቡና ይተከላል፡፡ ‹‹በዓለም በብዝኃ ሕይወቱ የሚታወቀው የታደለው ፓርክ ዓይናችን እያየው እየጠፋ ነው፤ የፓርኩ ሕልውና አሳሳቢነት አሁን የመጨረሻው ጥግ ደርሷል፤›› በማለት አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ ከአምስትና አሥር ዓመታት በኋላ ብዝኃ ሕይወቱ ሊጠፋ እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡

ስለ ፓርኩ የተሠሩ ጥናቶች የተጋረጠበትን አደጋ ቢያመላክቱም ይህ ነው የሚባል እርምጃ ሲወሰድ አልታየም፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የባሌ ተራሮች ለ40 የኢትዮጵያ ወንዞች መነሻና በሶድየም፣ ፖታሺየም፣ ማግኒዥየም፣ ዚንክና ካልሽየም የበለፀገ የሚኒራል (የከርሰምድር) ውኃ መገኛ ናቸው፡፡ በአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹ሖራ›› ተብሎ የሚጠራው ውኃ፣ የእንስሳትን ጤና እንደሚጠብቅና የወተት ምርታቸውን እንደሚጨምር ስለሚታመን ሰፋሪዎቹ እንስሳዎቻቸውን ከፓርኩ ማስወጣት አይፈልጉም፡፡ ውኃው ለአጎራባች አገሮች ተደራሽ በመሆኑ የሚደርስበት አደጋ ከኢትዮጵያ አልፎ ሶማሊያና ኬንያ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡

ዶ/ር ዘለዓለም እንደ መፍትሔ የሚያቀርቡት የአካባቢው አስተዳደርና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ድርጅቶች እጅና ጓንት ሆነው እንዲሠሩ ነው፡፡ በፓርኩ ዙሪያ ያሉ የአስተዳደር አካላት ኃላፊነት ተሰምቷቸው በቶሎ መፍትሔ እንዲፈልጉ የሚያሳስቡት ዶክተሩ፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ንብረትነቱ የመላው ኢትዮጵያውያንና የዓለምም ጭምር እንደመሆኑ የሁሉም ሰው ግዴታ መሆኑን በማስገንዘብ ነው፡፡

በባሌ አካባቢ በተፈጥሮ ጥበቃና እንክብካቤ ከሚንቀሳቀሱ ወጣቶች አንዱ አሰግድ ደጀኔ ‹‹ባሌ ውበት የተፈጥሮ ጥበቃ›› የተባለ ክለብ ኃላፊ ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም. በባሌ ተራሮች ተነስቶ የነበረውን እሳት ለማጥፋት የተረባረቡ የአካባቢው ተወላጆች አንዳች ለውጥ ለማምጣት ክለቡን እንደመሠረቱ ይናገራል፡፡ በዓመት ሁለቴ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ችግኝ ይተክላሉ፤ የአካባቢ ጥበቃ ትምህርትም ይሰጣሉ፡፡

በቅርቡ የደረሰውን የእሳት አደጋ በማጥፋት ሥራ ተሳትፈዋል፡፡ ደጀኔ እንደሚለው፣ እስካነጋገርነው ወቅት (መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም.)  ድረስ እሳቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም፡፡ የፓርኩና የከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አመራሮች እሳቱ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ቢናገሩም፣ እሳቱ እንዳልተዳፈነ የገለጹልን ሌሎችም ግለሰቦች ነበሩ፡፡ እሳቱ ለሳምንታት ያልጠፋው ባለሙያዎች በአንድ ወገን እሳቱን ሲያጠፉ በሌላ  በኩል ነዋሪዎቹ እሳት ይለኩሱበት ስለነበር ነው ይላል፡፡

አሰግድ ከዶ/ር ዘለዓለም ሐሳቦች በአብዛኛው ይስማማል፡፡ የተፈጥሮ ተቆርቋሪውን ሕይወት እስከማጥፋት የደረሰው እሳት ማንቂያ ደወል እንዲሆን ያሳስባል፡፡ ‹‹ሰዎች ወደ ተፈጥሯዊ መኖሪያ ሥፍራቸው ተመልሰው የዱር እንስሳት ከአደጋ ተጠብቀው በነፃነት ሊኖሩ ይገባል፤›› ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የአካባቢው ብዝኃ ሕይወት በኅብረተሰቡ ቦታ የሚሰጠው አይመስልም፡፡ በባሌ ጎባ መገበያያ ቦታዎች ተገኝተው በሠሩት ጥናት መሠረት በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት አገር በቀል እንጨት ጭነው ለገበያ ለማቅረብ ከየወረዳው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አገር በቀል በሆኑ ዕፀዋት እየደረሰ ያለው ጭፍጨፋ ከሌላው የከፋ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችና በዞኑ የሚሠሩ ድርጅቶች አማራጭ ኃይል ማመንጫ እንዲጠቀሙ ቢወተወትም አመርቂ ለውጥ አልመጣም፡፡ ወደ 12 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት መሠረት የሆኑት ከተራራ የሚፈልቁት ምንጮች ሌላው የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል የዱር እንስሳቱ ከመኖሪያቸው ወጥተው በየሜዳው ይታያሉ፡፡ አሰግድ እንስሳቱ በበሽታ ከመጠቃታቸው በተጨማሪ በመዳቀል የዘር መከለስ ሊገጥማቸው እንደሚችል ይናገራል፡፡

አሰግድ ‹‹ባለሙያዎች የተቻላቸውን ያህል ድምፃቸውን ቢያሰሙም ፓርኩ አልዳነም፤›› የሚለው በሐዘኔታ ተሞልቶ ነው፡፡ ነዋሪዎች ሆነ ብለው እሳት መለኮሰ ደረጃ የደረሱት ዕርምጃ ባለመወሰዱ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች አቅም በላይ የሆነ ችግር በመሆኑ መንግሥት በአፋጣኝ እጁን እንዲያስገባ ያሳስባል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊው አቶ አስቻለው ጋሻው በፓርኩ በሰፈሩ ሰዎች ላይ ለምን እርምጃ አይወስድም የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር፡፡ እንደእሳቸው ገለጻ፣ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ሦስት የፓርኩ አካባቢዎች በሪራ ወደ 500 አባወራዎች ይኖራሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ለዓመታት በቦታው ስለኖሩ ያለ ቅድመ ውይይት ማስነሳት አይቻልም ይላሉ፡፡ ነዋሪዎቹ ከፓርኩ ወጥተው በሌላ አካባቢ ኑሮ የሚመሠርቱበት ካሳ ክፍያ ከፓርኩ አቅም በላይ ስለሆነ የመንግሥትን ውሳኔ እየተጠባበቅን ነው ይላሉ፡፡

ዶ/ር ዘለዓለም በበኩላቸው ፓርኩ ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች አብዛኞቹ ከፓርኩ ውጭ ሌላ መኖሪያ ቤት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች እንስሳዎቻቸውን ለመመገብ ፓርኩ ውስጥ ጊዜያዊ ቤት አዘጋጅተው የሚኖሩ ቢሆንም፣ ከፓርኩ ውጭ መኖሪያ የሌላቸው ሰዎች መኖራቸውም መዘንጋት እንደሌለበት ይገልጻሉ፡፡ መኖሪያ ቤት ያላቸውን ነዋሪዎች ግን ከፓርኩ እንዲወጡ ለማድረግ እንደማይቸግር ያምናሉ፡፡

 ፓርኩ ሰፊ ስለሆነ በየቦታው ጠባቂ አቁሞ መከላከል ያዳግታል፡፡ አስተያየት የሰጡትን ዘላቂ መፍትሔ የማይሆኑ ቀላል ዕርምጃዎች ለውጥ እንደማያመጡ ይስማሙበታል፡፡ እንደምሳሌ የጠቀሱት ለእሳት አደጋው ተጠያቂ ተብለው የታሰሩ ግለሰቦችን ነው፡፡ ግለሰቦቹ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ለዓመታት በእስራት ቢቀጡም ዘለቄታ ያለው መፍትሔ አይሆንም፡፡

በባሌ ተራሮች ‹‹ጎድ አንቱ›› (ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ለግጦሽ በሚመች አካባቢ ከብቶችን መመገብ) ለዓመታት የዘለቀ ልማድ ነው፡፡ ከድሮ ጀምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች እንስሳዎቻቸውን ወደ ፓርኩ ወስደው ሳር አስግጠው ሚኒራል ውኃ አጠጥተው ይመለሳሉ፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አሁን የከብቶች ቁጥር ስለጨመረ እንቅስቃሴው ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡

በተለያዩ ድረ ገጾች ላይ የጉዞ ማስታወሻ የሚያስቀምጡ ቱሪስቶች ስለ ፓርኩ በጎ ነገር ያሰፍራሉ፡፡ ጉብኝት የሚያሰናክለው ችግሩ ካልተፈታ ግን ቀጣይነቱ ያጠራጥራል፡፡ ባገኘነው መረጃ መሠረት ፓርኩ አምና 6,000 ጎብኝዎችን አስተናግዷል፡፡  የባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ አባድር ጀኢላን እንደሚሉት፣ የፓርኩ መጎዳት ከዞኑ  አልፎ የአገሪቱን ቱሪዝም ይጎደዋል፡፡ ሰዎቹ በአግባቡ ቦታ ተዘጋድቶላቸው የማስፈር ሥራው መጓተቱን ይናገራሉ፡፡

አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ ፓርኩ በዩኔስኮ የመመዝገብ ዕድሉ እንደሚጠብ ያክላሉ፡፡ ሐሳቡን የሚጋሩት የዲንሾ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘይላን መሐመድ ጎብኚዎችን የሚስቡ ዕፀዋትና እንስሳት ቁጥራቸው ሲመናመን የቱሪዝም ፍሰቱ መቀነሱ አይቀርም ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የመረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ነዋሪዎች ከፓርኩ እንዲወጡ  የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት በራሳቸው ፍላጎት ከፓርኩ ወጥተው ሌላ ቦታ እንዲሠፍሩ ማድረግ በቀጣይ ጂቲፒ (የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ) ውስጥ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ፓርኩ ውስጥ እያረሱ መኖሪያቸውን ከፓርኩ ውጪ ያደረጉ ግለሰቦችና መሥሪያቸውም መኖሪያቸውም ፓርኩ ውስጥ የሆኑ አሉ፡፡ አቶ ዘሪሁን እንደሚገልጹት፣ ነዋሪዎቹ ከፓርክ ከወጡ በኋላ የሚኖሩበትን ቦታ ከማመቻቸት ጎን ለጎን ገቢ የሚያገኙበት መንገድም ታሳቢ መሆን አለበት፡፡ በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተሠራውን እንደተሞክሮ በመውሰድ በባሌ የመተግበር እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በእሳት ቃጠሎው ሕይወቱን ያጣውን ቢንያም ቢሮው እንደ ጀግና እንደሚያየውና ክብር ለመስጠት በትውልድ ቀዬው ዶዶላና በአዲስ አበባም የመታሰቢያ ዝግጅት በያዝነው ወር መጨረሻ ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሆነ ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...