Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበተቋማዊ ለውጥ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ

በተቋማዊ ለውጥ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ

ቀን:

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀ ታሪክ አለው፡፡ በኦሊምፒክ መድረኮች የኢትዮጵያን ስም የናኙ አትሌቶችና በዓለም መድረክ የነበራቸው ውጤት የተቋሙን ተቀባይነት እንዳቀጣጠለ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ እንደጀመረ የሚነገረው በ1948 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ተቋማዊ ዕውቅና የተላበሰው ግን በ1960 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑ መዛግብት ያሳያሉ፡፡

ተቋማዊ አደረጃጀቱን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቢያመጣም፣ አሁንም ድረስ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረው ይነገራል፡፡ ይህንና በኦሊምፒክ አደባባዮች የታፈሩ አትሌቶች በምታፈራ አገር ውስጥ ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ለመሆን እየታተረ ለመሆኑ እያካሄዳቸው የሚገኙ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን ዋቢ ያደርጋል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው ሕልውናውን ካገኘበት ጀምሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችንና ስፖርቱን ከማስፋፋት አልፎ ተርፎም ዘመናዊ ተቋም ለመሆን የሚያስችለውን መሠረትም እየጣለ ይገኛል፡፡ ሁለት የስፖርት አካዴሚዎችን ጨምሮ የራሱን ዋና መሥሪያ ቤትና ሌሎችንም ግንባታዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ ይናገራሉ፡፡ ተቋሙ በመጪው ነሐሴ መጨረሻ በኮንጎ ብራዛቪል ለሚካሄደው 11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችና ለሪዮ ዲጄኔሮ ኢሊምፒክ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ የለንደን ኦሊምፒክ ተሳትፎን፣ አምና በቦትስዋና አስተናጋጅነት የተከናወነውን የመላ አፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮናና በዚያኑ ዓመት በቻይና ናይጂ በተካሄደው የዓለም ወጣቶች የክረምት ኦሊምፒክ ተሳትፎውን በመመልከት በውድድሩ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎን በመገምገም ለኮንጎ ብራዛቪልና ለሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ዝግጅት መጀመሩንም ይናገራሉ፡፡

ከነዚህ ዝግጅቶች በ2007 የውድድር ዓመት መጨረሻ በኮንጎ ብራዛቪል በሚካሄደው 11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ በ13 የስፖርት ዓይነቶች ለመሳተፍና ካለፈው ጨዋታ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተያዘው ዕቅድ አንዱና የመጀመርያው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ለ31ኛው የሪዮ ዲጂኔሮ ኦሊምፒክ አገሪቱ ‹‹ትወከልባቸዋለች›› ተብሎ በሚታመኑ ስፖርቶች ሚኒማ (የኦሊምፒክ መግቢያ ውጤት) የሚያሟሉበት መድረክ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ጭምር አቶ ታምራት ይገልጻሉ፡፡

እንደ ኃላፊው፣ ሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በውኃ ዋና፣ በቦክስ፣ በብስክሌትና በወርልድ ቴኳንዶ ከተሳትፎም በላይ ውጤት ለማምጣት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም ያስረዳሉ፡፡ በአትሌቲክሱ ደግሞ ከ400 ሜትር ጀምሮ ተፎካካሪ መሆን የሚቻልበት ዕቅድ  ተነድፎ በተለይም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

ለአሠልጣኞች፣ ለስፖርት ሐኪሞችና ወጌሻዎች፣ እንዲሁም ለሥነ ልቦናና ሥነ ምግብ ባለሙያዎች ተገቢው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መሰጠቱን የሚናገሩት አቶ ታምራት፣ በሥነ ምግብና ሥነ ልቦና የባለሙያዎች እጥረት እንዳይኖር እንዳስፈላጊነቱም ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት በሚደርስ ኮንትራት የባለሙያዎች ቅጥር እንደሚፈጸምም ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቹ የአገሪቱ አትሌቶች በሥነ ምግብና ሥነ ልቦና ረገድ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀደም ሲል ባደረገው ግምገማ እንደ ክፍተት ብሎ ከወሰዳቸው ነጥቦች በዋናነት የተቀመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዝግጅቱ ጎን ለጎን ለሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ ለአገሪቱ የወደፊት ተተኪ ተብለው ለሚታሰቡ አምስት ወንድና አምስት ሴቶች በድምሩ አሥር አትሌቶች የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠ መሆኑንና ይህም ወደ ገንዘብ ሲለወጥ እንያንዳንዱ አትሌት 5,000 ዶላር የሚደርስ እገዛ እንደተደረገለት ይወሰዳል፡፡ ነፃ የትምህርት ዕድሉ ለሪዮ ዲጄኒሮ ኦሊምፒክ የሚያበቁ ሚኒማዎችን (መግቢያ ሰዓት) ለማግኘት የሚያስችሉ ማጣሪያ ውድድሮችን እንደሚያካትትም ኃላፊው ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎችንም በየስፖርት ዓይነቱ በርካታ ተወዳዳሪዎች በመላው አፍሪካና በሌሎችም ዓለም አቀፍ መድረኮች የውድድር ዕድል እንዲያገኙ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታምራት፣ እንደ አስፈላጊነቱም በአህጉራዊም ይሁን ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች እየተወዳደሩ ውጤታማ የሚሆኑ፣ ነገር ግን ደግሞ ዕድሉ እንዳይፈጠር የፋይናንስ አቅም ለሌላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ማኅበራት ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ስኬትና ተከታታይነት ላለው እንቅስቃሴ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል ኦሊምፒክ ኮሚቴው የማርኬቲንግ እንቅስቃሴው እንዴት መቀጠል እንዳለበት በስትራቴጂክ ዕቅዱ ተካቷል፡፡ ዝርዝሩን በሚመለከት በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ ነው ያስረዱት፡፡

ስፖርቱን እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት የተጣለባቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የፋይናንስ አማራጮችን ከማስፋት ይልቅ ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ የመንግሥትን ቋት የሚጠብቁ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ይኼው ሥርዓት በአገሪቱ የስፖርት ተቋማት ሥር ሰዶ መቆየቱ ደግሞ ለስፖርቱ ዕድገት ማነቆ መሆኑም ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም በዚሁ የአሠራር ሥርዓት መቸገሩን ያመላከቱት ዋና ጸሐፊው፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በፋይናንስም ሆነ ተያያዥ ነገሮች ራሳቸውን ማጠናከር ቢገባቸውም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግን የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ እገዛ የሚያደርገው ውጤትን መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በማያያዝም ከዚህ በኋላ አትሌቲክስን ጨምሮ ውጤት ይመጣባቸዋል ተብሎ የሚታመኑ የስፖርት ዓይነቶች ድጋፍና እገዛ ይደረግላቸዋል ሲባል ዝም ተብሎ እንዳልሆነ የሚናገሩት አቶ ታምራት፣ ቦክስና ውኃ ዋናን እንደምሳሌ በማንሳት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ስፖርቱ አገር ወክሎ በሚቀርብበት ወቅት የሚያስመዘግበውን ውጤት በዕቅዱ እንዲያካትት የሚያስገድድ ደንብ የተዘጋጀ መሆኑም ገልጸዋል፡፡  ለተሳትፎ ከሆነ ግን አገሪቱ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የተሳትፎ ችግር እንደሌለባት፣ የአሁኑ ዝግጅቱ የግድ ውጤት ለማግኘት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ተብሎ በስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በአቶ አምበሳው እንየው የሚመራ ብሔራዊ ዓብይ ኮሚቴ መቋቋሙን ጭምር ኃላፊው አክለዋል፡፡ በኮንጎ ብራዛቪል አስተናጋጅነት በሚካሄደው 11ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ ከ140 እስከ 170 ብሔራዊ አትሌቶችን ለማሳተፍ ዕቅድ እንዳላትም ተናግረዋል፡፡

ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀጥሎ ጽሕፈት ቤቱን በራሱ አቅም አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በአሁኑ ወቅት እየተገለገለበት የሚገኘው ቢሮ በ2002 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ በ25 ሚሊዮን ብር በገዛው ሕንፃ ነው፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከዚህም በላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ላይ በተረከበው 86,000 ካሬ ሜትር መሬት ቦታ ላይ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የሚያዘወትሩበት አካዴሚ ግንባታውን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ይነገራል፡፡ አካዴሚው በአሁኑ ወቅት በአትሌቲክስና በእግር ኳስ ለታዳጊዎች የሥልጠና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ይናገራሉ፡፡

የቢሾፍቱው አካዳሚ በአካባቢው ከሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ታዳጊዎች በዓመት ሦስት ጊዜ በተለያዩ ስፖርቶች ስፖርታዊ ውድድሮችን እንደሚያከናውኑበትም ይነገራል፡፡ በዚህ ዓመት በግንቦት ወር መጨረሻ በሱዳን ካርቱም የዞን አምስት አገሮች በሁለቱም ጾታ ታዳጊ ወጣቶች የሚሳተፉበት የእግር ኳስ ሻምፒዮና ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ በዚሁ ሻምፒዮና የሚሳተፋ የሁለቱም ጾታ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በአካዴሚ እያዘጋጀች እንደምትገኝም አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡

ሌላው በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ አስተዳደር በተረከበው 120,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የዋናውን አካዴሚ ግንባታ ለመጀመር የሚያስችል የአጥር ሥራና የካሳ ክፍያ እንደተጠናቀቀ የሚናገሩት አቶ ታምራት፣ ተቋሙ ፈጥኖ ወደ ግንባታ ለመግባት ያልቻለው፣ የአካዴሚውን መሬት ከአዳማ የሚመጣው የፍጥነት መንገድ የተወሰነ ክፍል በመውሰዱ እንደሆነና በምትኩ ማግኘት ያለባቸውን መሬት ለመረከብ ጥያቄው መልስ ባለማግኘቱ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ከግንባታ ጋር በተያያዘ በተለምዶ ስሙ ደብረዘይት መንገድ (እምቧይ መስክ) ተብሎ የሚጠራውን መዝናኛ ማዕከል በአዲስ መልክ ግንባታውን ለመጀመር ያልቻሉት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በገጠማቸው ችግር እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...