Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከአሥር ዓመት በፊት ዛሬ የፕሬስ ረቂቅ ሕጉ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ የመጨረሻ...

ከአሥር ዓመት በፊት ዛሬ የፕሬስ ረቂቅ ሕጉ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ የመጨረሻ ትዕይንት

ቀን:

ከአሥር ዓመት በፊት ዛሬ

የፕሬስ ረቂቅ ሕጉ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ የመጨረሻ ትዕይንት

በሰሙ ንጉሥ ዳርጌ

‹‹በቅርቡ የተረቀቀውን የፕሬስ ሕግ ገና በእንግሊዝኛ ሳይተረጐም ለውይይት በመቅረቡ አንዳንድ ጋዜጠኞች አፋኝ ነው ብለው ረግጠው መውጣታቸውን ተከትሎም፣ አንድ አማርኛ የማይችል ፈረንጅ አንድ ግለሰብ የነገረውን ተንተርሶ የሰጠውን መግለጫ ለማውገዝ የተጣደፉበትን ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሳሌነት አንስተዋል፡፡››

ይህ በ1995 ዓ.ም. የካቲት 19 ቀን በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተፈሪ ለገሰ ከለንደን የዘገበው ዜና ዋና ፍሬ ቃል ነው፡፡

ሳንሱርን የቅድሚያ ምርመራንና ማናቸውንም ሌላ ተመሳሳይ ገደብ በሕግ ያስቀረውን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዛሬም ድረስ ብዙ ሰዎች ኢንዱስትሪውን ጭምር የማያውቁትን የፕሬስ ውጤቶችን ይዘት ሕጋዊነት የማረጋገጥ ግዴታን ዳር ድንበር አሳምሮና አሻሽሎ የወሰነውን የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ ለማሻሻል፣ መንግሥት በሕግ ማውጣቱ ጎራና ግንባር ዕርምጃዎችን ማስታወቅና መውሰድ የጀመረው በ1995 ዓ.ም. ነው፡፡

ኅዳር 1995 ዓ.ም. ድንገትና ሳይታሰብ በማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካይነት ይፋ የተደረገው የመጀመሪያው የፕሬሱ ረቂቅ ሕግ ግን እንደ ሌሎች የአገሪቱ ረቂቅ ሕጎች ማን አባቱ ያዘኛል ምን የጎበረበት እያለ ኮርቶና ተንቀባሮ የፀደቀ ሕግ አይደለም፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረቂቅ ይፋ ሲሆንና በአንድ በኩል እዚህ አገር ቤት ሕጋዊና ሰላማዊ እሳት ሲጭርና አቧራ ሲያስነሳ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የውጭ አገር ጉብኝት ጉዞ ሲያደርጉ አንድ ሆነ፡፡

በዚህ ምክንያት ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል (በውጭ አገር) አንዱ ግንባር ቀደሙ የፕሬስ ነፃነትና የፕሬስ ሕግ ረቂቁ ጉዳይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በአቶ መለስ ጉብኝትና ጉዞ አብሯቸው የተጓዘው የተፈሪ ለገሰ የለንደን ዘገባ ትርጉምና ሚስጥርም ይኼው ነው፡፡ የረቂቅ ሕጉን ለመከላከልና ለመከራከር ረቂቁ ገና ወደ እንግሊዝኛ አልተተረጐመም፣ አማርኛ የማይችል ፈረንጅ አንድ ሌላ ሰው ያለውን ሰምቶ ነው መግለጫ ለመስጠት የተጣደፈው ማለት ድረስ የተኬደው ገና ከጅምሩ ነው፡፡

እንዲህ በሚያሳዝን ሁኔታ ሳያምርበት ጀምሮ፣ አላማረብህም ቢባል እምቢ ብሎ ሳያምርበትና ከዚያም በላይ ብዙ ነገር አበላሽቶ ያለቀበት፣ የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ ለመሻርና ለመተካት የተዘጋጀው የዚህ የፕሬስ ሕግ ረቂቅ ታሪክ ገና ተተርኮ አለዚያም ተሰምቶ ያበቃ አይመስለኝም፡፡

በወቅቱ ሥራ ላይ ያለውን ረቂቅ ሕግ ወይም የሕግ ሐሳብ አንቅቶ (አመንጭቶ) የማቅረብ የአገር ሕግ ሳይከተል፣ በመደበኛውና በደንበኛው የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ውሰጥ ሳይገባ፣ የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ ለመሻርና ለመተካት ረቂቅ ሆኖ የቀረበው ይህ ‹‹ፕሮጀክት›› በመጨረሻ 2000 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ ሕግ ሆኖ የወጣው የለመደበትን እያስመዘገበ ነው፡፡

በመጨረሻ ሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ረቂቁ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ኮሚቴ የተመራውና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ ሆኖ የፀደቀው ሰኔ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ብቻ ከወንጀል ሕጉ ከተደነገገው በተቃራኒ በባለሥልጣናት ላይ የሚፈጸሙ የስም ማጥፋትና የሐሰት ወንጀል ድርጊቶች ላይ የወንጀል ክስ ለመመሠረት የግል ተበዳይ አቤቱታን አስፈላጊነት ቀሪ አድርጓል፡፡ የአገርን የህሊና ጉዳት ካሳ ወደ 100 ሺሕ ብር ከፍ አድርጓል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ የሚገርመው የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን ልክ የዛሬ አሥር ዓመት በዚህ ቀን በሕግ ማውጣት ስም የተወሰደው የሕግ ማውጣት ዕርምጃ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት፣ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው በመንግሥት በኩል ‹‹በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሳይተረጐም›› ማለትን ከመሰለ ማፈሪያ መከራከሪያ ጀምሮ፣ አስፈላጊው ሁሉ ዕርምጃ የተደገሰለት ረቂቅ የፕሬስ ሕግ የፀደቀው ‹‹የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ›› በ2000 ሲወጣ አይደለም፡፡ የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ የፀደቀው ወይም በግልባጩ የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ የተሻረው ልክ የዛሬ አሥር ዓመት መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጨረሻው የሥራ ዘመኑ በወንጀል ሕጉ ውስጥ የረቂቁ ሕግ ዋነኛ አከርካሪዎች ተጭነው እንዲያልፉ ሲደረግ ነው፡፡

ይህንን ሪፖርተር ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 1997 ‹‹የረቂቁ የፕሬስ ሕግ ድንጋጌዎች የወንጀል ሕግ ሆነው ፀደቁ›› ብሎ ዘገቦታል፡፡ የመጋቢት 25 ቀን 1997 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ርዕሰ አንቀጽም ‹‹ደፈጣም ቆረጣም በፕሬስ ነፃነትና በዴሞክራሲ ላይ›› ብሎ ጽፎበታል፡፡ እኔም በዚያው ዕለት በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በተሟገት ዓምድ ላይ በቅርብ የተከታተልኩትን የፕሬስ ሕግ ረቂቅ የመጋቢት 20 ቀን 1997 ‹‹አሸናፊነት›› እና የፕሬስ ነፃነትን ግብዓተ መሬት በምሬት ጭምር ጽፌያለሁ፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ታሪክ ሲወሳ የ1985 ዓ.ም የፕሬስ ነፃነት አዋጅን ለመሻርና በሌላ ለመተካት የተደረገው ትግል በተነሳ ቁጥር፣ የወንጀል ሕጉ የተሠራበት፣ ደግሞ እንደገና የተሠራበት፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የተጠናወተው ችግር ሲጠቀስ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያስተዋወቀው አዲስና አብዮታዊ የፕሬስ ውጤቶችን ይዘት ሕጋዊነት የመጠበቅ ግዴታ በተዘከረ ቁጥር፣ ሁልጊዜም የመጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአጀንዳ ቁጥር 2 ውሳኔን አስታውሳለሁ፡፡

ይህን ታላቅ ጉዳይ ለማስታወስ ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ይበልጥ ለማጠናከርና ለማጥራት የዛሬ አሥር ዓመቱን ጽሑፍ መልሼ ሳነብ፣ በየትኛውም መለኪያና በየትኛውም ዘርፍ በፕሬስ ነፃነት ስፋትና ጥልቀት ጭምር፣ ከዛሬ ትናንት እንደምንሻል፣ ዛሬ ከትናንት እየከፋ እንደመጣ ያለጥርጥር አረጋገጠኩ፡፡ በዚህ ምክንያት የሪፖርተርን ኤዲቶሪያል ፈቃድ ከማግኘት ጋር ጭምር የትናንቱን ጽሑፍ እንዳለ መድገም ፈለግሁ፡፡

ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 20ኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሄደበት ዕለት እንደተለመደው ሁሉም የምክር ቤት አባላት አልተገኙም፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር በራሱ በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገው፣ ‹‹የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ ከ550 የማይበልጥ ቢሆንም፣ ፓርላማው ውስጥ ግን በየትኛውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (አንደኛውም ሆነ ሁለተኛው) በየትኛውም የሥራ ዘመን በየትኛውም መደበኛ ስብሰባ ሁሉም የፓርላማ አባላት፣ ሁሉም የሕዝብ ተወካዮቻችን በነቂስ ወጥተውና ተገኝተው አያውቁም፡፡

ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. በ‹‹መጀመሪያው›› ምርጫ የተመሠረተው አንደኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 491 መቀመጫዎች የኢሕአዴግ፣ ‹‹ሌሎች 14 የፖለቲካ ድርጅቶች በአጠቃላይ 49 ተወካዮች ስድስት መቀመጫዎችን…›› የያዙበት ምክር ቤት ነበር፡፡ በሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹481 መቀመጫዎች በኢሕአዴግ … 14 የፖለቲካ ድርጀቶች በአጠቃላይ 53 መቀመጫዎች፣ በግል ተወዳድረው ባሸነፉ ተወካዮች ደግሞ 13 መቀመጫዎች ተይዘው ይገኛሉ›› ይህ በምክር ቤት ይፋ መረጃ መሠረት ነው፡፡

መጋቢት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የ17ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተገኙት 262 ወይም 262+2 ከግማሽ በላይ (ምልዓተ ጉባዔ) ስለመሆናቸው አጨቃጭቆ ከምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በተሰጠው መግለጫ መሠረት 23ቱ ሞተዋል፣ ከ30 በላይ የሆኑት ለተለያየ ስብሰባ ወደ ውጭ አገር ሄደው ቀርተዋል፣ ከ10 በላይ ዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ውስጥ ተመድበዋል፡፡ ‹‹ሃምሳ አምስት አባላት በቋሚነት የማይገኙ ናቸው፤›› ተብሏል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርና የሥነ ሥርዓት ደንብ ‹‹ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወይም በአፈ ጉባዔው ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር›› ማንኛውም የምክር ቤት አባል በማናቸውም የምክር ቤት ስብሰባዎች መገኘት እንዳለበት፣ ይህንንና ሌሎች የሥነ ምግባርና የሥራ ግዴታዎችን አለማክበር ከምክር ቤት እስከማገድና እስከማስወገድ በሚደርስ የዲሲፕሊን ዕርምጃ እንደሚያስጠይቅ ይደነግጋል፡፡ ይህንን ደንብ ያወጣው ራሱ ምክር ቤቱ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ባወጀው የ1989 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 88 (አንቀጽ 7 እንደተመለከተው) የሕዝብ የውክልና ሥልጣኑን ባጣ፣ እንዲያጣ በተደረገ ማንኛውም እንደራሴ ምትክ ሌላ ሰው መተካት ይቻል ዘንድ የሟሟያ ምርጫ መካሄድ ያለበት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡

በመጋቢት 20 ቀን 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የተገኙት እንደራሴዎች ቁጥር 325 እንደነበር የዕለቱ የምክር ቤቱ ስብሰባ መዝግቧል፡፡ የአጠቃላይ ተመራጮች 59 በመቶ መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም የኢሕአዴግ አባላት ናቸው ቢባሉ እንኳን የገዥው ፓርቲ የራሱ 32 በመቶ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ግንቦት 6 ቀን 1992 ዓ.ም. በተካሄደው ሁለተኛ ምርጫ ከተመረጡት 547 እንደራሴዎች መካከል 23ቱ በሞት፣ ከ30 በላይ የሆኑት በ‹‹ክዳት›› አሥሩ በሹመት በድምሩ ከ63 አባላት በላይ ከመካከሉ የተለዩበት ፓርላማ ሕዝብ ምትክ እንደራሴዎቹን እንዲልክ ማሳወቅ፣ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የማሟያ ምርጫ እንዲካሄድ ወይም መካሄዱን ማረጋገጥ ያለበት ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት›› ሌላም ጉድ አለው፡፡

የመጋቢት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. 17ኛ መደበኛ ስብሰባ እንዳጋለጠው ከ48 በመቶ ያነሰ ቁጥር ያላቸው እንደራሴዎች የተገኙበት ምክር ቤትና አመራር፣ እንዲሁም ከእነሱ ሰማይ በላይ እንደ ሰማያዊ ንጉሥ የትምና ሁሉም ቦታ የሚገኘው ‹‹የሕይወታቸውን ንጉሥ›› የነፍሳቸው ባለአደራ፣ የዕለት እንጀራቸው ለጋሽ በሰጠው ፈቃድ መሠረት ተጨማሪ 55 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በቋሚነት አይገኙም፡፡

52ቱ የመጫወቻ ካርታዎች የማይበቋቸውን የእነዚህን ‹‹በቋሚነት የማይገኙ››፣ ይህ ነፃ ፈቃድና ዕርምጃ የተሰጣቸው ሰዎች ማንነትና ምሥል ማወቅ የሚፈልግ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገኙበትን የፓርላማ ስብሰባ ቢታዘብ ይበቃዋል፡፡

‹‹የኢፌዴሪ ሁለተኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 20ኛው መደበኛ›› እና የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የፕሬስ ነፃነት ታሪክ በመዘገበው ስብሰባ ካልተገኙት፣ መገኘት ከማያስፈልጋቸው፣ የራሱ የምክር ቤቱ የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ (አንቀጽ 21 በምክር ቤቱ ስብሰባዎች የመገኘት) ግዴታ ከማይመለከታቸውና ይልቁንም ‹‹በቋሚነት ከማይገኙት›› መካከል አንዱ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ እኚህን ‹‹በማይቀርበት ጉዳይ›› ላይ ያልተገኙት፣ አሁን አሁን ከሆነ በኋላ ብቻ ሳይሆን ድሮምና ሲጀመር ጭምር እንደምናውቀው ደግሞ የመገኘት ግዴታም አስፈላጊነት የሌለባቸውን እንደራሴ ማንነት መግለጽ ያስፈለገው፣ ጉዳዩ የዕለቱ ውሉ የእሳቸውና የእሳቸው ስለሆነ ነው፡፡

የተከበሩ እንደራሴና ክቡር ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን በዕለቱና በሰዓቱ ሌላ ቦታ፣ ሌላ ሥራ ነበራቸው፡፡ ፓርቲያቸውን ኢሕአዴግን ወክለው፣ በሁለመናቸው በአጠቃላይ ኢሕአዴግን አክለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዳራሽ ውስጥ ስለፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ ይነጋገራሉ፡፡

ቢያንስ ቢያንስ ከተወካዮች ምክር ቤት ከፓርላማው አኳያ ሲታይ የምርጫ ቦርዱ የዚህ ዕለት ስብሰባና ሰብሳቢ፣ ተሰብሳቢም ጭምር ሌላ ቦታ፣ ሌላ ጊዜ እንደተለመደው ‹‹ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት›› የሚል ወይም ‹‹እንደጠሩህ ስማ፣ እንዳሸተቱህ…›› ተብሎ የተረገመ አይደለም፡፡

የተከበሩ የቡግና ሕዝብ እንደራሴው፣ ክቡር የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ወክለው ምርጫ ቦርድ ውስጥ የማይናቅ እሰጥ አገባ ክርክር ባሉበት ወቅት፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 20ኛ መደበኛ ስብሰባ ‹‹የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግን አስመልክቶ የሕግና አስተዳደር፣ የሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አዘጋጅተው ባቀረቡት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠት›› በሚል አጀንዳ ላይ ‹‹ይመክር›› ነበር፡፡ ከምክር ቤቱ 12 ቋሚ ኮሚቴዎች መካከል እነዚህ ሦስቱ ብቻ ያገባቸዋል በተባለበት (ከሌሎች መካከል) ሌላው ቀርቶ የማስታወቂያና የባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንኳን ለስሙ ያገባዋል ባልተባለበት በዚህ አጀንዳ ውስጥ ከተካተቱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው፣ ‹‹በፕሬስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ከሽግግር አዋጁ 34/85 ጋር በተጣጣመ እንዲስተካከል ተደርጓል (አንቀጽ 43-45)›› የተባለው የወንጀል ሕግ ይገኝበታል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 20ኛ መደበኛ ስብሰባ መጋቢት 20 ቀን ‹‹የተመለከተው›› እና ያፀደቀው ጉዳይ ሕግ በማውጣት አጠቃላይ የምክር ቤቱ ተግባር ሥር የሚወድቅ ነው፡፡ ‹‹ይወድቃል›› ወይስ አይወድቅም? (የታቀደ ቅኔ ወይም ሚስጥር አዘል ንግግር አይደለም) ወደፊት፣ ከዚህ በኋላ አብረን የምናየው ጉዳይ ነው፡፡

ሕግ የማውጣት የምክር ቤቱ ተግባር የሚያካትታቸውን ነገሮች ጓዝና ተጓዥ አድርጐ የሚያስከትላቸውን ጉዳዮች የሚያውቅ፣ ሕግ አድርጐ ያፀደቀ፣ ምክር ቤት ቀርቶ አራት ኪሎ የማይጠፋው፤ ከአራት ኪሎ የሚመጣው ዕለታዊ ስብከት ያሰለቸው ሰው የሚያቀርበው ጥያቄ አለ፡፡

ምክር ቤቱ ምን አደረገ? አዲስ ሕግ አወጣ? ነባር ሕግ አሻሻለ? ወይስ ሻረ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ይህንን ጥያቄ ከሁሉ አስቀድሞ፣ ከማንም በፊት፣ ማንም ሳይጠይቀው መመለስ ያለበት ራሱ ምክር ቤቱ ነው፡፡ ፓርላማው ከሕግና አስተዳደር፣ ከሴቶችና ከማኅበራዊ ጉዳዮች (ሦስት) ቋሚ ኮሚቴዎች መጋቢት 12 ቀን 1997 ዓ.ም. የቀረበለትን ‹‹ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ›› መጋቢት 20 ቀን 1997 እንዳለና ‹‹በሙሉ ድምፅ›› ያፀደቀው አዋጅ ቁጥር 414/1996ን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ሕግን ነው፡፡ ‹‹… ልዩ መጽሐፍ ሆኖ በአዋጅ ቁጥር 414/1996 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣ በኋላ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና›› ይሆን ዘንድ የተወሰነውን ሕግ ነው፡፡

ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የሚፀናው፣ የ1949 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግንና የ1974 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት የተሻሻለው ልዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥር 214/1974ን የሚሽረው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የፀደቀው ግን ሰኔ 24 እና 25 ቀን 1996 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 40ኛ መደበኛ ስብሰባ ነው፡፡ መጋቢት 20 ቀን 1997 አይደለም፡፡

ሰኔ 1996 ዓ.ም. የፀደቀና ‹‹የታወጀ›› ሕግ ከግንቦት 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የፀና ይሆናል መባሉ ነውርም ሕገወጥነትም የለበትም፡፡ ሐምሌ 16 ቀን 1949 ዓ.ም. የታወጀው የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የፀናው ከሚያዝያ 27 ቀን 1950 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ የ1952 ዓ.ም. የፍትሐ ብሔር ሕግ ሚያዝያ 27 ቀን 1952 ዓ.ም. ታውጆ እንዲፀና (በሥራ ላይ እንዲውል) የተደረገው ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ የማስረጃ ወይም የተሞክሮ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ሕግ በኢትዮጵያ የነጋሪት ጋዜጣ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ወይም በወጣበት የነጋሪት ጋዜጣ በተወሰነው ወደፊት ከሚመጣ ቀን በኋላ የፀና ይሆናል፡፡ ሥራ ላይ ይውላል ቢባል ነውር አይደለም፣ የተለመደ ነው፡፡ አግባብም ሕጋዊም ነው፡፡

የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አሁንም መጋቢት 97 በነጋሪት ጋዜጣ አልወጣም፡፡ ‹‹የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አዋጅ ቁጥር 414/96 ሆኖ እንዲወጣ መፅደቁ የሚታወስ›› ቢሆንም አሁንም ‹‹አልወጣም›› ‹‹አዋጅ››ም አልሆነም፡፡ የሚፀናበት ጊዜ ከሞላ ጐደል ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣበት ጊዜ የሚዘገይ፣ ቆይ ገና ነው፣ ይደርሳል የሚያሰኝ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ ከፀደቀበት ሴኔ 24 እና 25 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ድረስ ያለው ጊዜም የአሥር ወር ጊዜ የተሰጠው ለሕትመትና ለትርጉም አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ አሁን እንደተደረገው ለሕግ አመንጪው ወይም ለሕግ አውጪው የማሰቢያ፣ የማሰላሰያ፣ የቀረ፣ የተረሳ ነገር ቢኖር የማሰባሰቢያ ጊዜ ለመስጠት፣ ‹‹አንዳንድ መስተካከልና መካተት የሚገባቸው ጉዳዮች በጥንቃቄ ተመርምረው እንዲስተካከሉ…›› ለመፍቀድ አይደለም፡፡ ይህ ‹‹ድሮ›› 40ኛው የ1996 መደበኛ ጉባዔ ላይ ቀረ፡፡ ‹‹የሚመከረው ነገር ሁሉ በዝግታና በጥልቅ ታስቦ፣ በለዘብታ ክርክር ተጣርቶ በትዕግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ የተቆረጠ ነገር እንዲሆን›› እና እንዲወጣ የሚደረገው ከመፅደቁ፣ ፀደቀ ከመባሉ በፊት ነው፡፡ ፀደቀ ከተባለ ተቆረጠ ማለት ነው፡፡ እያረፉ ማማጥ ቀስ እያሉ፣ ትንሽ በትንሽ ምዕራፍ በምዕራፍ መውለድ፣ መገላገል የሚባል በቀጠሮ የሚያድር ነገር የለም፡፡

ምክር ቤቱ በሦስቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት መጋቢት 12 ቀን 1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕጉ ከታወጀ ከዘጠኝና ከአሥር ወር በኋላ የሚለው እውነትም ‹‹በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረገው ውይይት አንዳንድ መስተካከልና መካተት የሚገባቸው ጉዳዮች በጥንቃቄ ተመርምረው እንዲስተካከሉ…›› ተብሎ ከሆነ ውይይቱ ገና አላበቃም፣ የፀደቀ አዋጅም የለም፣ ‹‹በሽልም የወጣ››

ቀጠሮ ያደረ ጉዳይ አልነበረም፡፡ አዋጅ ቁጥር 414/96 ሆኖ እንዲወጣ የፀደቀ ሕግ ነው፡፡ ምክር ቤቱንና የምክር ቤቱን የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት የተጠናወተው የዚህና የዚህ ሕግ ብቻ ያልሆነ ችግር ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ ሳይወጣ ይህን ያህል ጊዜ እንዲቆይ አድርጐታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 57 እና በአገሪቷ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 271/1994 እንዲሁም በምክር ቤቱ አሠራር ደንብ አንቀጽ 41 መሠረት ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ለፊርማ የተላከ፣ የተዘጋጀና ያለቀለት ሕግ ስለመኖሩም ማንም እርግጠኛ አይደለም፡፡ ከተወካዮች ምክር ቤትና ከፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ የሚበርሩ ወፎች የሚያረጋግጡትም ተቃራኒውን ነው፡፡

አሁን መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. የተወሰደው ዕርምጃ ያስከተለው ተጨማሪና እጅና እግር የሌለው ጣጣ ደግሞ ከግንቦት በፊት፣ ግንቦት 1 ቀን ቀርቶ ከዚያም በኋላ ቢሆን በነጋሪት ጋዜጣ ሊወጣ የሚችል ወጥነት ያለው ሕግ አዘጋጅቶ ማቅረብ የሚቻል ስለመሆኑ በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ‹‹ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውሏል›› ከተባለ በኋላ በእሱ ደረጃ እንኳን የወሰደውን ከመንፈቅ በላይ የሆነ ጊዜ በሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ የሚችለው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ብቻ ነው፡፡ የቤተሰብ ሕጉም፣ ወዘተ እንደዚሁ ነው፡፡ ይህ ማተሚያ ቤት ደግሞ የቀይ መስቀል ዓለም አቀፋዊ ኮሚቴ ቢጤ ቢሞት የማይናገር ነው፡፡

‹‹ሁለት›› ጊዜ የፀደቀው በ1996 ዓ.ም. ሰኔና በ1997 ዓ.ም. መጋቢት ሕግ ሆኖ የታወጀው የአዋጅ ቁጥር 414/96 ችግር ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ሰኔ 96 የፀደቀ፣ ከግንቦት 1 ቀን 1997 ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውል ሕግ (የወንጀለኛ መቅጫ የሚያህል ሕግ) እስካሁን እስከ ግንቦት 97 ድረስ በነጋሪት ጋዜጣ አለመውጣቱ፣ በእርግጥ ታላቅ የሕዝብ ችግር የመንግሥትም ማፈሪያ ችግር ነው፡፡ እዚህ ውስጥ የማናካትተው የይዘቱ ችግር ሌላ ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይና በዚህ አሁን በያዝነው ጉዳይ ላይ የምናነሳው ችግር ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ መንግሥት የወንጀል ሕጉን አሻሻልኩ፣ ግማሽ ምዕተ ዓመት የተጠጋውን የ1949 ዓ.ም. ሕግ ሽሬ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተጣጣመ አዲስ ሕግ አወጣሁ ያላለውን ያህል፣ ያንንም ያህል ሌሎችን ሕጐች (ለምሳሌ የሙስና ሕጉን) ከወንጀል ሕጉ ጋር ለማጣጣም እያለ ማሻሻል ውስጥ ያልገባ ይመስል፣ አሁን ደግሞ ይህንኑ የወንጀል ሕግ ከሌሎች ሕጐች ጋር ‹‹ለማጣጣም›› ማሻሻል ውስጥ ገባ፡፡ እስከ 1996 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የወጡትን 419 አዋጆች ዝርዝር ለሚያይና ለሚያውቅ፣ ከዚህ መካከል ዓለም አቀፋዊ ወይም የጋርዮሽ ስምምነቶች ማፅደቂያዎችን ከቁጥር አስወጥቶ፣ ዓይነተኛ ሕጐችን ለሚታዘብ ማንኛውም ሰው፣ ኢሕአዴግን የሚመስል ‹‹የማሻሻያ›› ሕግ በማውጣት ክብረ ወሰን የያዘ፣ ወደፊትም የሚይዝ መንግሥት የትም የሚያገኝ አይመስለኝም፡፡

የዚህ ችግር ግን ‹‹ማሻሻል›› አይደለም፡፡ በግልጽና በይፋ ተሻሻለ አልተባለም፡፡ ‹‹ቀደም ሲል የፀደቀውን የወንጀል ሕግ የተሻለ ከማድረግ አንፃር ….ሌሎች ጠቀሜታ ያላቸውን ሐሳቦች በማሻሻያነት እንዲካተቱ …›› ያደረገው የፀደቀውም ሰነድ የአዋጁ ማሻሻያ አዋጅ አልተባለም፡፡ ቁጥር እንኳን አልተሰጠውም፡፡

ጉዳዩ የቁጥርና የስያሜ ብቻም አይደለም፡፡ ማንም ውሳኔ ሰጪ አካል፣ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ የተማሪዎች ካውንስል፣ ወይም የመንደር ዕቁብና ዕድር፣ ወይም የአንድ አገር ሕግ አውጪ፣ ውሳኔ የሰጠባቸውን ጉዳዮች እንደገና የሚያየው እንዳሻውና እንደፈቀደው አይደለም፡፡ ሥርዓት አለው፡፡ ይህ ሥርዓት በራሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የሥነ ሥርዓት ደንብ አንቀጽ 36 ተደንግጓል፡፡

እንኳንስ አሁን ‹‹እንዲካተቱ›› የተደረጉትን የመሰሉ ማሻሻያዎች ይቅርና በአንድ የፀደቀ ሕግ ላይ የቴክኒክ እርምት (ማለትም በማናቸውም ረገድ የሕጉን ይዘት የማይለውጥ የቋንቋና የሌላም ዓይነት ግድፈት ማሻሻያ) ለማድረግ በ88 ዓ.ም. ሕግ መሠረት ጉዳዩ ለምክር ቤቱ ቀርቦ እርምቱ ይደረጋል፡፡ ይህም ሲደረግ ፕሬዚዳንቱ በአፈ ጉባዔው አማካይነት እንዲያውቁት ይሆናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ተቃውሞ ያላቸው እንደሆነ የተደረገው የቴክኒክ እርምት ቀርቶ በጉዳዩ ላይ አዲስ የሕግ ረቂቅ ለምክር ቤቱ ይቀርባል፡፡ በ1994 ዓ.ም. የወጣው ሕግ ይህንን ያሻሻለው የቴክኒክ እርምቱን ፕሬዚዳንቱ እንዲያውቀው የማድረግ ግዴታ ብቻ የአፈ ጉባዔው ሥልጣን በማድረግ ነው፡፡

ከ1988 ወደ 94 እንዴት እያደረግን እንዳማረብን፣ እያማረብን እንመጣለን ሌላ ነገር ሆኖ ይህ ሁሉ ግን የሚመለከተው የቴክኒክ እምርትን ብቻ ነው፡፡ በ1994 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 271 መሠረት የቴክኒክ እርምት ‹‹የቋንቋና መሰል ግድፈት ማስተካከያ ሲሆን፣ በማናቸውም ረገድ ይዘት የማይለውጥ ማሻሻያ ነው፡፡››

አዋጅ ቁጥር 414/96 ውስጥ መጋቢት 20 ቀን 1997 ‹‹እንዲካተቱ›› ቀርበው የፀደቁት ጉዳዮች ‹‹የቋንቋና መሰል ግድፈት ማስተካከያዎች›› በጭራሽ አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የሕዝብ ተወካች ምክር ቤት ሕግ የማመንጨት፣ አዲስ ሕግ የማውጣት፣ ነባሮችን የማሻሻልና የመሻር የሕገ መንግሥቱን፣ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ሕጉን፣ የገዛ ራሱን የአሠራር ደንብ እየረመረመና እየጣሰ፣ በሕግ የተደነገገ የሥርዓት ዋስትናችንን እያበራየና ለንፋስ እየሰጠ መሥራቱ በገዛ ራሱ ምክንያት ሕገወጥ አካሄድና ይቅርታ የማያሰጥ ጉዳይ ነው፡፡

የተሻሻለው፣ እርምት የተደረገበት፣ አዲስ ‹‹እንዲካተት›› የተደረገው ጉዳይ ይዘት ተገቢና ፍትሐዊ ቢሆን እንኳን ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› በማይሠራበት፣ ሕገወጥ በሆነበት አሠራር ነገሩ፣ በ‹‹እንዳይደገምህ›› የሚታለፍ አይደለም፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. ሕግ በማውጣት ወይም በማሻሻል ስም የወሰደው ዕርምጃና አፀደቅሁት ያለው ከዚህ የከፋ አንድምታ ብቻ ሳይሆን፣ አደገኛና መሰሪም ጭምር ነው፡፡ ምክር ቤቱ ራሱና መንግሥት የፈጠሩትን ድቅድቅ ጨለማ ተገን አድርጐ፣ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በገዢው ፓርቲ የፖሊሲ ሰነድ፣ ከ1995 ወዲህ ደግሞ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረቂቅ የፕሬስ ሕግ አማካይነት በንግግር፣ ሐሳብን በመግለጽና በፕሬስ ነፃነት ላይ በአደባባይ ተደጋግሞ እየተቃጣ፣ እየተሰነዘረና እየተወረወረ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ የከሸፈውን ሴራና ሙከራ በስውርና በሚስጥር ‹‹እውን›› ያደረገ ነው፡፡ የፕሬስና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት የሞት ፍርድ ቅጣት የማዘዣ ዋራንት የቆረጠ ነው፡፡

ኅዳር 25 ቀን 1995 ዓ.ም. መጀመሪያ ይፋ የተደረገው፣ ‹‹በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚጣሉ ገደቦች›› ማለት የሚቀናውና መነሻውና መድረሻው ይኸው የሆነው፣ ከዚያ ወዲህ በአማርኛ ሦስት ጊዜ በእንግሊዝኛ ደግሞ ትርጉሙን ሳይጨምር ሁለት ጊዜ የተሻሻለውና እነሆ እስካሁን መጋቢት 1997 ዓ.ም. ድረስ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ረቂቅ ሆኖ ሲያወዛግብ የቆየው የፕሬስ ሕግ ሐሳብ እንደ ደራሲዎቹ አያያዝና ‹‹ክፋት›› ቢሆን ኖሮ እሽረዋለሁ፣ እተካዋለሁ ብሎ ቆርጦ የተነሳው አዋጅ ቁጥር 34/85 (ስለ ፕሬስ ነፃነት የወጣ አዋጅን) ነበር፡፡

ከጥቅምት 11 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናውና አሁንም ድረስ እስከ ኅዳር 2001 ዓ.ም. ሥራ ላይ ያለው የፕሬስ ነፃነት አዋጅ ያኔ በወቅቱ ከዚህ ከአሁኑ ሁኔታው የተሻለ፣ የላቀ ሊሆን ይችል እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ አሁንም መሻሻል የሚገባው ስለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ኢሕአዴግና ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አዋጅ ቁጥር 34/85 ለምን መሻሻል እንዳለበት የሚገልጹትና ከዚህም ተነስተው የሚወስዱት፣ እየወሰዱትም ያለው ዕርምጃ ከሌላው ሁሉና ከመላው የውስጥና የውጭው ዓለም የተለየና የብቻው ነው፡፡ በወዳጅም በ‹‹ጠላት››ም እንደተገለጸው፣ የ1994 ዓ.ም. የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የፖሊሲ ሰነድ፣ በራሱ የረቂቅ ሕጉ፣ የመንግሥት ሚዲያዎች አዋጆች፣ የብሮድካስቲንግ ሕጉ አተገባበሮች፣ የማስታወቂያ ሚኒስቴርና የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ የሚያወጧቸው ‹‹መመርያዎች›› ይዘት እንደሚያሳየው መንግሥት ለፕሬስ ነፃነት መስፋፋት ኃይል አይደለም፡፡ ነባር ሕጐችን የማሻሻልና የመሻር አዳዲስ ሕጐችን የማውጣት ሥራውና ተግባሩ በዕለት ተዕለት የሕጎቹ ይዘት እንደሚመሰክረው አቅጣጫው ሌላ ነው፡፡ ከሕዝብና ከፕሬስ ነፃነት ጐን የሚቆም አይደለም፡፡

የ1985 ዓ.ም. የፕሬስ ሕግ ለመሻር፣ በአዲስ ሕግ ለመተካት፣ በዚህም መሣሪያነት ‹‹መጥፎ›› እና ‹‹እኩይ›› የፕሬስ ውጤቶችን ‹‹ልክ ለማስገባት›› ጥሩ ጥሩና ሰናይ ሰናዮችን በአዋጅና በሕግ አስገዳጅነት ዘርቶ ለማብቀል፣ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ጥረት ሁለት ዓመት ተኩልና ከዚያም በላይ በፈጀው የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ በ1991 ዓ.ም. የብሮድካስት ሕጉ ላይ የተጣለው እስራት እነሆ ለስድስተኛ ዓመት ቀጥሏል፡፡ ስድስት ዓመት ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ፣ የአንድ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሥልጣን ዘመን ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾችና በኢትዮጵያ በራሷና በመላው ዓለም የታወቁ ስመጥር ግለሰቦች ኢትዮጵያና ዓለም በአጠቃላይ ረቂቅ የፕሬስ ሕጉን አጥብቀው ኮንነውታል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነው፣ ወደ ኢትዮጵያም እየመጡ፣ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ውጭ አገር በአጋጣሚው የሚገኙ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከፍተኛ ባለሥልጣናት እግር እየጠበቁና እየተከተሉ ይህን የሕዝብ ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው የሚያቀርቡ፣ የሚጽፉ በርካታ ናቸው፡፡ በርካታ ብቻም አይደሉም ኃይልና ጥንካሬም ናቸው፡፡

አልታደል ያለው የዚህ የባለጉዳይነት ገጽታና ታሪካችን ሌላው አለመታደል ሆኖ ስለአገር ውስጥ ሕዝብ አድራጊ ፈጣሪነት አምናለሁ የሚለው፣ ስለዚህም ኤምባሲ እየሄዱ፤ የውጭ አገር ከፍተኛ የመንግሥት ልዑክ እየጠበቁ፣ ኮንግረስ ድረስ እየቀረቡ የአገር የውስጥ ኃይል የማያምኑ ጥገኞች እያለ የዕለት ተዕለት ክሱን ከመደርደር ቦዝኖ የማያውቀው መንግሥታችን፣ የፕሬሱ ረቂቅ ሕግ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ የወሰደበት የያዘውና ወደፊትም የሚይዘው ስለያዘው ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር በግል የደረሰውና ያረቀቀው ሌላው ቢቀር የአገሪቷ መንግሥት የሕግ አማካሪ (የፍትሕ ሚኒስቴር)፣ የፌዴራሉ መንግሥት ጠቅላይ ፈቃድ ሰጪና መዝጋቢ አካል (የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር) እንኳን ‹‹እወቁልኝ›› ተብለው ያልተጠሩበት ረቂቅ የፕሬስ ሕግ የአገርና የዓለም መነጋገሪያ መሆኑ ለአንድ አፍታም ሳያባራ ቀጠለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን፣ ይህ የፕሬስ ሕግ ረቂቅ አሁንም ሠልፍ ይዞ፣ መስመር ገብቶ፣ የአገር ሕግ ማውጣት ሥነ ሥርዓት በሚደነግገው መንገድ መጓዝ ሳይጀምር ባለበት ሆኖ ማስፈራራቱን ተያያዘው፡፡ በዚህ መካከል የ1997 ዓ.ም. ሁለተኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ መስከረም ላይ ሲከፈት፣ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ባሰሙት ንግግርና ባቀረቡት የፌዴራል መንግሥቱ የሕግ ማውጣት ፕሮግራም ዘንድሮ ለምክር ቤቱ ቀርበው ተመክሮባቸው ይፀድቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሕጐች መካከል አንደኛው የፕሬስ ሕግ መሆኑን ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ስለ ሕዝብ ተሳትፎ፣ ስለውይይትና ክርክር ይበልጥ የሰፋና ያካበተ ልምድ ቢናገሩም ኢትዮጵያችንን፣ መንግሥታችንን፣ ፓርላማችንን እናውቃለንና ለከፋውና ለሚመጣው ሁሉ ተዘጋጅተን በምንጠባበቅበት ወቅት መጋቢት 20 ቀን 1997 ዓ.ም. መጣና ያልተጠበቀውንና ያልታሰበውን አረዳን፡፡ በዕለቱ የምክር ቤቱ አጀንዳዎች ሆነው ከቀረቡት ጉዳዮች መካከል፡-

‹‹የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግን አስመልክቶ የሕግና አስተዳደር፣ ሴቶችና የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች አዘጋጅተው ባቀረቡት ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መስጠት›› የሚለው አንዱ ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ የተሻሻለው፣ የፕሬስ ሕጉ ረቂቅ አንቀጾች እዚህ ወንጀል ሕግ ውስጥ እንዲገቡና እንዲፀድቁ የተደረገው በዚህ አጀንዳ መሠረት ነው፡፡

አጀንዳው እንደሚለው ሪፖርቱና የውሳኔ ሐሳብ የቀረበለት ምክር ቤት ከዚህ ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በተጨማሪ የኢፌዴሪ ‹‹የወንጀል ሕግ 1997›› (መግቢያና 71 አንቀጾች የያዘ) ሕግ ቢጤ ነገር ጭምር ተያይዞ ቀርቦለታል፡፡

ለምክር ቤቱ የቀረበው የኮሚቴዎቹ ‹‹የውሳኔ ሐሳብ›› እና ሪፖርት በተራ ቁጥር 21 ‹‹በፕሬስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ በሽግግር ወቅት አዋጅ ቁጥር 34/85 ጋር በተጣጣመ እንዲስተካከል ተደርጓል (43 – 45)›› ይላል፡፡ ከ43 – 45 የሚባሉት ደግሞ ‹‹የ1997 የወንጀል ሕግ›› በተባለው 71 አንቀጾችን እያለፈና እየዘለለ በሚጠቅሰው ከ43 ጀምሮ በአንቀጽ 839 የሚያበቃው ‹‹የተሻሻለው›› ሕግ የተካተቱት አንቀጾች የመጀመሪያዎቹ ሦስት አንቀጾች ናቸው፡፡

ግራ የተጋባው ነገር ስለመኖሩ ሁለመናው የሚያጋልጥና የሚያረጋግጥ ቢሆንም፣ ይህም ከአጀንዳው አቀራረብ ከራሱ ቢጀመርም፣ ከያዝነው ጉዳይ ጋር የተያያዘው ዋነኛው ጉዳይ ያለው እዚህ ተራ ቁጥር 21 የኮሚቴው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ ላይ ነው፡፡

‹‹በፕሬስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ…›› ብሎ ይጀምራል፡፡ አንቀጽ 43 – 45 በፕሬስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎች አይደሉም፡፡ ‹‹በፕሬስ ዙሪያ›› ብሎ ነገር የለም፡፡ እነዚህ አንቀጾች በፕሬስ ወይም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ተካፋይ መሆንን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የእነዚህ ድንጋጌዎች ዋነኛ ማጠንጠኛ ሌላ የትኛውም ዓይነት ወንጀል ቢፈጸም (መግደል፣ መዝረፍ፣ መድፈር፣ ከፍተኛ ክዳት ራሱ) በእነዚህ ውስጥ ተሳታፊ መሆንን የሚገዛ ሕግ ለብቻ አለ፡፡ የፕሬስ ደግሞ የብቻው ነው፤ ሌላ ነው የሚል ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የዚህ ‹‹ማሻሻያ›› ሕግ ዓላማ ‹‹ከሽግግሩ ወቅት አዋጅ 34/85 ጋር በተጣጣመ እንዲስተካከል ተደርጓል›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ጨርሶ ውሸት ነው፤ አለዚያም ስለማያውቁት ነገር መናገር ነው፡፡ የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ይህንን ጉዳይ የደነገገው የአገሪቷ የመጀመሪያ ሕግ ነው፡፡ በወንጀል ሥራ ተካፋይ ስለመሆን የሚል ለሁሉም ዓይነት ወንጀሎች በእኩልነት ተፈጻሚ የሚሆን አንድ ራሱን የቻለ ምዕራፍ አለው፡፡ ከተካፋይነት አኳያ ብቻውን የቆመ፣ ለብቻው ሌላ ሕግ ያለው ‹‹ታትመው በሚወጡ ጽሑፎች በሚሠራ ወንጀል ተካፋይ ስለመሆን›› የሚል ሌላ የተካፋይነት ዓይነት አለ፡፡

የወቅቱ ሕግ አንዱ ጉልህ ድክመት ይኸው ነበር፡፡ ይህ ለዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአሁኗም ኢትዮጵያ ከጥቂት ማሻሻያዎች ጋር አሳምሮ የሚሠራ፣ የአሁኖቹን አርቃቂዎች ከምንቸት ያነሱ ኢምንትና ምስኪን መፃጉዎች የሚያደርግ ሕግ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በፕሬስ አማካይነት የሚሠራ ወንጀል አደገኛ ነው፤ ስለዚህም በአፋጣኝና በብርቱ መቀጣት አለበት፡፡ እናም ልዩ ‹‹የተካፋይነት ሕግ›› ያስፈልገዋል ይላል፡፡ የዚህን ሕግ ውስንነት፣ ገዳቢነት አድሏዊነት ራሳቸው አርቃቂዎች ያውቁታል፤ አምነውም ይቀበሉታል፡፡ ስለዚህ ከዘመናዊ የወንጀል ሕግ ጋር አብሮ አይሄድም ብለው መዝግበው ምስክርነታቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡

በ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተደነገጉት በፕሬስ አማካይነት ስለሚሠሩ ወንጀሎች ተካፋይ ስለመሆን ድንጋጌዎች መርሁን፣ ዋና ኃላፊ የሚሆነው ምክትል ኃላፊ የሚሆነውን፣ የጽሑፉን ሚስጥር ማክበርን በጽሑፍ ጉዳይ የማይደፈር መብትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የዚህ የ1949 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች (የጽሑፍ ሚስጥር ስለማክበርና በጽሑፍ ጉዳይ የማይደፈር መብትን ከሚመለከቱት ድንጋጌዎች በስተቀር) በፕሬስ አዋጁ ቁጥር 34/85 አንቀጽ 22 እና በአንቀጽ 14 መሠረት ተሽረዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እንዳለ ቀጠለ፡፡

በዚህ መካከል 1996 ዓ.ም. ሰኔ መጨረሻ ላይ አዋጅ ቁጥር 414/96 ሆኖ የታወጀውና ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጀምሮ የሚፀናው የወንጀል ሕግ ፀደቀ፡፡ እሱም እንደዚሁ ችግሩና ድንቁርናው ከሚገባው በላይ ከብዶት ‹‹በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ተካፋይ ስለመሆን›› የሚል ከሞላ ጐደል የ1949 ዓ.ምቱን ሕግ ድንጋጌዎች እንዳለ ይዞ እንዲቆይ ተደረገ፡፡ የፕሬስ አዋጁ ከጥቅምት 12 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የቀጠለው ፍርድ ቤት ሳያግዘው ባለሙያ ሳያፍታታው፣ የመብትና የነፃነት የሕዝብ ትግል ዳር ድንበሩን እንዲያሰፋ ሳያደርገው መሆኑ አንሶ ሕግ አውጪው ይበልጥ ሌላ ችግር ፈጠረበት፡፡ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ወይም የ1949 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ እንደሚለው ታትመው በሚወጡ ጽሑፎች በሚሠራ ወንጀል ተካፋይ ስለመሆን የሚል፣ ይህን የወንጀል ዓይነት ከሌሎች ሁሉም የወንጀል ዓይነቶች ነጥሎ የሚፈርጅ፣ የሚያስተናግድ፣ የሚቀጣ ሕግ ለምን መኖር አለበት የሚል ድምፅ በሌላ ከዚህ በባሰ የውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ ትግል ተዋጠ፡፡ የ1949 ዓ.ም. ሕግ አርቃቂዎች አውቀውና መርጠው፣ ግራ ቀኙን አገላብጠው፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን ዘርዝረው፣ ስለ ሥራቸው ተናዝዘው እንዳልተናገሩ ሁሉ አዲሶቹ ሐጋጊያንና ሊቃውንቶቻችን ተራ ‹‹ኮመንሴንስ›› እንኳን ገድዷቸው፣ የፕሬስ አዋጁ በግልጽ ሳይናገር የሻረውን የቀድሞ ችግር እንዳለ በውርስ ተረክበው መልሰው ሕግ አደረጉት፡፡

ይህ ወቅት በረቂቅ የፕሬስ አዋጁ በኩል ባለው የጦር ግንባር ‹‹መዋደቁ›› የበዛበት ፍልሚያው የተፋፋመበት ሁሉም ነገር ወደዚህ ግንባር የተባለበት ጊዜ ነበር፡፡ እንዲያውም በዚህ ጋዜጣ በራሱ ሲጻፍ እንደነበረው የ1949 የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በዚህ ክፍል የተደነገጉት የጽሑፍን ሚስጥር ስለማክበርና በጽሑፍ ጉዳይ የማይደፈር መብት እየጠቀሱ መዋጊያ መሣሪያ ሆነው ነበር፡፡ የ1996 የወንጀል ሕግ ከፀደቀ በኋላም እነዚሁ ድንጋጌዎች እንዳሉ መቀጠላቸው ድርብ ድርብርብ መሣሪያ ሆነው ማገልገላቸው ተፋፋመ፡፡

የረቂቅ የፕሬስ አዋጁ የእስካሁን 1996 ዓ.ም. የመጨረሻ የአማርኛ ቅጅ ለውይይት የቀረበውና የወንጀል ሕጉ ለምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀው በአንድ ወቅት ነው፡፡ ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመሪያ 96 ዓ.ም. የፕሬስ ሕጉ እንደ ረቂቅ ቀረ፤ የወንጀል ሕግ ፀደቀ፡፡ 1997 ዓ.ም. በገባ በሰባተኛ ወር ‹‹በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በሚፈጸሙ ወንጀሎች ያለው ኃላፊነትን››፣ ‹‹የደራሲ፣ የአመንጭና የአሳታሚ ልዩ የወንጀል ኃላፊነት›› ‹‹የመረጃ ምንጭን በሚስጥር ስለመጠበቅ›› የሚሉ የፕሬስ ግዴታዎች በሚል ክፍል አምስት ሥር ከተካተቱት አምስት አንቀጾች መካከል ሦስቱ (የፍትሐ ብሔር ኃላፊነትንና የዕገዳ ዕርምጃን ከሚመለከተው በስተቀር) እንዳለ ቃል በቃል ከፕሬስ ረቂቅ ሕጉ ተጭነው ወደ ወንጀል ሕጉ ተራግፈው በቋሚነት እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡

ይህ የተደረገው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችና ራሱ ምክር ቤቱና የምክር ቤቱ አመራሮች እንደሚነገሩን ‹‹በፕሬስ ዙሪያ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከሽግግሩ ወቅት አዋጅ ቁጥር 34/85 (የፕሬስ ነፃነት አዋጅ) ጋር በተጣጣመ እንዲስተካከል›› ለማድረግ ነው፡፡ ‹‹እንዲስተካከልም ተደርጓል››፡፡

የ1985 የፕሬስ ነፃነት ከወጣ ማግሥሰት ጀምሮ በዚህ አዋጅ ተፈጻሚነት ምክንያት አታሚ የሚባል ተከስሶ እንደማይታወቅ፣ መከሰሱ የቀረ መሆኑ እየታወቀ፣ ከዚህ በላይ ደግሞ የፕሬስ አዋጁ የሕግና የፍትሕ ሥርዓት ድጋፍና አቅም እያነሰው እንጂ፣ ከሞላ ጎደል ምትክና ተለዋጭ ኃላፊ የሚባል ወንጀል ተሠራ በተባለ ቁጥር እንደ ጦስ ዶሮ ጭዳ የሚሆን ሰው አፈላልጎ መቅጣትን አስቀረ፣ ያስቀራል እየተባለ ተስፋ ሲደረግ ረቂቁ የፕሬስ ሕግ መጣ፡፡ ይህን ረቂቅ ያፀደቀ የወንጀል ሕግ ወጣ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች የሚያቀርቡትና መመለስ ያለበት አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ይህም የወንጀል ሕጉ ከፀደቀ በኋላ እንደተለመደው ማሻሻያ አዋጅ ሳይወጣ እንዲሻሻል መደረጉ፣ ተሻሻለ መባሉ ይገባናል፣ ይገርማልም፡፡ ነገር ግን ከረቂቅ የፕሬስ ሕጉ መካከል የወንጀል ሕጉ ድንጋጌ ሆነው የፀደቁት ሦስት አንቀጾች ናቸው፡፡ ይህ ልዩነት ያመጣል? የፕሬስ ሕጉ የወንጀል ሕግ ሆኖ ፀደቀ ያሰኛል የሚል ነው፡፡

ተገቢ ጥያቄ፣ የሚገባ ጥንቃቄ ነው፡፡ ጉዳዩ የብዛት ጉዳይ አይደለም እንጂ ከብዛት አኳያም የወንጀሉ ሕግ ያፀደቃቸው አንቀጾች ስድስት ክፍሎች ካሉት የፕሬስ ሕጉ መካከል አንደኛው ክፍል (የክፍል አምስት) አንቀጾች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱና ዋነኛው የፕሬስ ጥፋት ተጠያቂነትን የሚያቋቁመው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 43 ሲሆን፣ (በፕሬስ ረቂቁ ሕግ አንቀጽ 41 የነበረ) አምስት ንዑስ አንቀጾችና 14 ንዑስ አንቀጾች ያሉት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ብዛቱ አይደለም፡፡ የረቂቁ የፕሬስ ሕግ ሰረገላ፣ የዚህ ሕግ መላ አካል ተሸካሚ እነዚህ የወንጀል ሕጉ አካል ሆነው የፀደቁት ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

                       

       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...