Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብርቅዬ ፍራፍሬዎች

በግሩም አብርሃም

በአንድ ወቅት መንገዱን ሞልተው ይታዩ ከነበሩ ቁሳቁሶችና ሸቀጣቀጦች መካከል አስጎምጅ ፍራፍሬዎች ዛሬ የገቡበትን አፈላልጎ ለማግኘት አዳኝ ኃይል ወይም አነፍናፊ ውሾችን ማሰማራት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ እነብርቱካንና መንደሪን፣ አናናስና ፓፓዬ፣ ዘይቱንና ማንጎ፣ ወዘተ. ከሰው አልፈው የእንስሳት ቀለብ እንደነበሩ ስናስብ አሁን ላይ ከየመንገዱ ገበያና ከየፍራፍሬ መሸጫ መደብሩ ምን እንደሰወራቸው መመርመር ግድ ያሰኛል፡፡

ከሁሉ በላይ የብርቱካን ከአዲስ አበባ ፍራፍሬ ቤቶችና የጎዳና ገበያዎች መሰወሩ ማጠያየቅ የጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ ብርቱካን ለሽታ እንኳ መጥፋቱ አስተዛዛቢ የሚያደርገው ደግሞ አምራች ኩባንያዎች፣ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ የሼክ መሐመድ አላሙዲ ኩባንያዎች ከሆኑት አንዱ ለሆነው ሆራይዘን እርሻ ልማት ተሸጦም ቢሆን ብርቱካን እየተመረተ ከአገር ባሻገር ለውጭ ገበያ እየቀረበ ስለመሆኑ የንግድ ሚኒስቴር ምስክር መሆኑ ነው፡፡

ከፍራፍሬዎች ይልቅ ብርቱካንን የማንሳታችን ምክንያቱ፣ ከዓመት በፊት የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ልማት እርሻ ለሆራይዘን መሸጡን ተከትሎ ለአዲስ አበባ ፍራፍሬ ቸርቻሪ ነጋዴዎችና ጅምላ አከፋፋዮች መመርያ ተላልፎ እንደነበር ስለምናስታውስ ነው፡፡ መመርያው ከፍራፍሬዎች ሁሉ ለይቶ ብርቱካንን የተመለከተ ነበር፡፡ በወቅቱ የብርቱካን ዋጋ ሰማይ ነካ ተብሎ ነበር ንግድ ሚኒስቴር ቸርቻሪዎችንና አከፋፋዮችን እስከማስጠንቀቅና ማስፈራራት የደረሰ ተግሳጽ ለማሰማት ምክንያት ያደረገው፡፡ በወቅቱ የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ በአማካይ 30 ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴሩ ባለሥልጣናት ዓምና በሚኒስቴሩ አዳራሽ የሰበሰቧቸውን ፍራፍሬ ነጋዴዎች ያስጠነቀቁት ዋጋው መናር እንደሌለበት በመግለጽ ብቻ አልነበረም፡፡ የአንድ ኪሎ ብርቱካን የመሸጫ ዋጋን ከግማሽ በላይ ቀንሶ ገበያ ላይ ባይሸጥ እያንዳንዱን መደብር እስከማሸግ ሊደርስ የሚችል ዕርምጃ ሁሉ እንደሚወሰድ ዝተውም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከማስፈራራትና ከማስጠንቀቂያ ዛቻ የዘለለ አልነበርም፡፡ የሚገርመው የብርቱካን ዋጋ ብቻም ሳይሆን የጥራት ደረጃውም ሳይቀር እየተጠቀሰ የትኛውም በምን ያህል ዋጋ መሸጥ እንደሚገባው ሁሉ ሲዘረዘር ነበር፡፡

ዋሽንግተን፣ ቫሌንሺያ ወዘተ. ስያሜ ያላቸው የብርቱካን ዝርያ ዓይነቶች እንዳሉ፣ የጥራት ደረጃቸውም በዝርያቸው ልክ እንደሚለያይ ዋጋቸውም በዚያው መጠን እንደሚለያይ የሚኒስቴሩ ሰዎች አስገራሚ ገለጻ ሰጥተውበት እንደነበርም እናስታውሳለን፡፡ የትኛውም ዓይነት ዝርያና ጥራት ይኑረው ብርቱካኑ በችርቻሮ ገበያ ላይ ከአሥራ አምስት ብር በላይ እንዳይሸጥ ማሳሰቢያ የሰጠው ንግድ ሚኒስቴር፣ ይህንን በማይከተሉት ላይ ቁጥጥሩን እንደሚያጠብቅ ማስጠንቀቁም አይዘነጋም፡፡ ማስጠንቀቂያውም ቁጥጥሩም በተግባር ሳይታዩ፣ ዋጋውም ጥራቱም ብሶባቸው ቀጠሉ፡፡

እነሆ ከዓመት በኋላ ብርቱካን ልክ እንደመድኃኒት ተፈልጎ የማይገኝ፣ ከተገኘም ወይ በዋጋው ወይ በጥራቱ፣ በተለይ በጣዕሙ እያማረረን ይገኛል፡፡ አንድ ኪሎ ብርቱካን ከ60 ብር በላይ በሚሸጥበት ከተማ ውስጥ ለመኖር ተገደናል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ይሰማ የነበረው እሮሮማ ከመቶ ብር በላይ እንደነበርም የሚያሳብቅ ነበር፡፡ ዓምና ዋጋ ቀንሱ እየተባለ ነጋዴዎች ሲወተወቱ የነበረው ምርቱ ተትረፍርፏል በሚል ምክንያት ነበር፡፡ በተለይ በክረምቱ ወራት አብዛኛው የብርቱካን ምርት ጥራት የሚቀንስ በመሆኑና ለውጭ ገበያም የሚቀርብበት መጠን የሚቀንስ በመሆኑ፣ በአገር ውስጥ እንደልብ እንደሚገኝ ንግድ ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ እንደውም የሚገዛ ጠፍቶ እየተበላሸ የሚጣለው ብርቱካንና ሌላው ፍራፍሬ ጭምር ከፍተኛ መጠን እንደሆነ የሚኒስቴሩ ሰዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

በወቅቱ ለወቀሳ የተጠሩት ነጋዴዎች ያሰሙት ቅሬታና አቤቱታም መጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ግብይት ላይ አድልዎ እንደሚፈጸምባቸው፣ ከአሁኑ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ባለቤት ሆራይዘን እርሻ በጅምላ እየተረከበ ለቸርቻሪዎች የሚያሰራጨው ኢትፍሩት ወቀሳ የበረታበት ድርጅት ነበር፡፡ ነጋዴዎቹ በሚዛን ልኬት ማጉደልና በሌሎችም አሠራሮች ተገቢነት የጎደለው መስተንግዶ እንደሚገጥማቸው አምርረው ገልጸው ነበር፡፡ የነጋዴዎቹን እሮሮ ያዳመጠው ሚኒስቴሩ በተለይ በሚዛን ማጉደል ኢትፍሩት ስሙ የሚነሳ የመንግሥት ድርጅት መሆኑን መስማቱ ክፉኛ አስቆጥቶት ነበር፡፡ እያዳንዱን የኢትፍሩት መደብር እስከመመርመር የሚደርስ ዕርምጃ ከመውሰድ ባሻገር፣ የሚዛን ማጉደል ተግባር ተፈጽሞ ባገኝም አይማረኝ ብምራችሁ ያሉት ሚኒስትር ዲኤታም አይዘነጉም፡፡

ምንም እንኳ ብርቱካንን ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላከው የፍራፍሬ መጠን አነስተኛ ነው እየተባለ በመንግሥት ቢገለጽም፣ እውነታው ግን ሌላ እንደሆነ ነው በገበያው በሰፊው የሚነገረው፡፡ ይህም ቢባል ግን ዘንድሮ የብርቱካን ምርት ላይ ችግር እንዳለ ዳር ዳሩን እየሰማን ነው፡፡ በሆራይዘን እርሻ አካባቢ ምርቱ እንደዓምናው ሊሆን ቀርቶ ከመኖሩም እያወዛገበ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

ስለብርቱካን ይህንን ያህል ማለታችን መንግሥት ያገባኛል ብሎ ከሌሎች ምርቶች ነጥሎ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ ሰጥቶበት ስለነበር ነው፡፡ ሕሙማን የሚጠየቁባቸው፣ ሕፃናት የሚያድጉባቸው፣ በዓላት፣ አጽዋማት በመጡ ቁጥር፣ የበጋ፣ የበልግ፣ የክረምት፣ የፀደይና የመፀው ወራት በመጡ ቁጥር ልዩ ልዩ የፍራፍሬ ዓይነቶችን፣ የአትክልት ምርቶችን እንደልብ በየገበያው፣ በየመንገዱ ማየት የተለመደ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የማይቀመሱ፣ የማይሞከሩ የቅንጦት ምርቶች እስኪመስሉን ድረስ እየናፈቁን ነው፡፡ በዚህ ዓብይ ጾም እንኳ የቲማቲም፣ የሰላጣ፣ የቃርያና የሽንኩርት የሌሎችም አትክልት ዓይነቶች በዋጋ የሚቀመሱ አይመስሉም፡፡ በቅርብ ጊዜ የነበረው ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነ አንድ ኪሎ ቲማቲም እስከ 20 ብር ሲሸጥ ከርሟል፡፡ ሽንኩርትም ከዚያ የራቀ አልነበርም፡፡ እርግጥ የዋጋው ጉዳይ በዋና ዋና የገበያ አካባቢዎች ማለትም በአትክልት ተራ የሚታየው ዋጋና በየሰፈሩና በየመንደሩ ጉልቶች የሚታየው ዋጋ መለያየት ይታይበት እንጂ፣ ጭማሪው ግን የባሳ አያምጣ የሚያሰኝ ለመሆኑ አይታበልም፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት