Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አጐዋ ስለመራዘሙ ማረጋገጫ አላገኘም

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት አሥራ ዓምስት ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑበት ታስቦ በአሜሪካ ለአፍሪካውያን የተሰጠው ከታሪፍና ከቀረጥ ነፃ የገበያ ዕድልን (አፍሪካ ግሮውዝ ኦፖርቹኒቲ አክት-አጎዋ) ዘንድሮ መጠናቀቂያው ቢሆንም፣ ለተጨማሪ ዓመታት እንዲራዘም ከአፍሪካውያኑ ወገን ውትወታ ሲደረግበት ከቆየ ሰነባብቷል፡፡

በአምባሳደር ግርማ ብሩና በሌሎች የአፍሪካ ዲፕሎማቶች የሚመራ የዲፕሎማቶች ስብስብ አጎዋ ይራዘም የሚለውን ጥያቄ ለአሜሪካ ኮንግረስ ማቅረቡም ይታወሳል፡፡ ጥናት እንደሚደረግበትና ምላሹም ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ከመግለጽ ውጪ አጎዋ ለተጨማሪ ዓመታት ሊቀጥል ስለመቻሉ አሜሪካ መተማመኛ ከመስጠት ተቶጥባ ቆይታለች፡፡ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አጎዋ ሊቀጥል እንደሚችል ፍንጭ ከመስጠት ባሻገር አጎዋ መቀጠል እንዳለበት የሚያስታውቁ የአሜሪካ ባለሥልጣናትም ብቅ እያሉ ነው፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የደቡብና ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ በመገኘት ንግግር ካደረጉት ባለሥልጣናት መካከል ፍሎሪዝ ሊዘር አንዷ ናቸው፡፡ ሊዘር በአፍሪካ ጉዳዮች የአሜሪካ የንግድ ቢሮ ረዳት ወኪል ሲሆኑ፣ በንግግራቸውም በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሚመራው የአሜሪካ አስተዳደር ከኮንግሬሱ ጋር በመሆን በአጎዋ ጉዳይ ላይ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮች አሜሪካ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ላላት ግንኙነት አጎዋ የመሠረት ድንጋይ ነው ያሉት ሊዘር፣ አጎዋ ምናልባትም ለመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት በተቻለ አቅም እንዲራዘም ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአጎዋ መራዘም አፍሪካውያንን አምራቾችን ከመጥቀሙ ባሻገር ለአሜሪካ ሸማቾችና ኢንቨስተሮችም መልካም የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ባለሥልጣኗ አስታውሰዋል፡፡

አሜሪካ ምንም እንኳ አጎዋ ወደፊት ስለመቀጠሉ ተስፋ እየሰጠች ብትገኝም፣ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት በተጓዘበት መንገድ እንደማይቀጥል በማሳሰብ ላይ ትገኛለች፡፡ የንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊዋም ይህንኑ ጠቆም አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለአፍሪካውያኑ መጪው ጊዜ እንዳለፉት ዓመታት በቸልተኝነት የሚያሳልፏቸው እንደማይሆኑም ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገሮች በአጎዋ ገበያ የሚገባቸውን ያህል አለመጠቀማቸውን ልብ ይሏል፡፡ ይህንን ተከትሎ ይመስላል ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ታንዛንያ ያሉ አገሮች ብሔራዊ የአጎዋ ስትራቴጂ ለመቀየስ ደፋ ቀና ማለት የጀመሩት፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ብሔራዊ የአጎዋ ስትራቴጂ ዝግጅት መጀመሩ የተገለጸው ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ በተስተናገደው 12ኛው የአጎዋ ፎረም ላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነትን በሚመለከት በአጎዋ ድረ ገጽ ላይ የሰፈሩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ እ.ኤ.አ. በ2014 ወደ አሜሪካ የተላኩ የግብርና ውጤቶች 96.7 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል፡፡ በአንፃሩ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለተላኩ ተመሳሳይ ምርቶች ኢትዮጵያ የ39.7 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ፈጽማለች፡፡ ሆኖም በአጎዋ በኩል ከኢትዮጵያ የተላኩ የግብርና ምርቶች ግን ከ4.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኙ እንዳልሆኑ መረጃው ይጠቁማል፡፡ በአጎዋ አማካይነት የተላኩ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ውጤቶች 11.7 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገኙ በአጎዋ አማካይነት የተላኩት ምርቶችም 11.5 ሚሊዮን ዶላር በማስመዝገብ ትልቁን ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካስገኙ የጫማ ምርቶች ውስጥ በአጎዋ በኩል የተገኘው 14.9 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በጠቅላላው በአጎዋ ዕድል አማካይነት ከተላኩ ምርቶች የተገኘው ገቢ 31.2 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 በአጎዋ በኩል የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 27 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዓምናና ካቻምና የተገኘው ጠቅላላ ገቢ ከካቻምናው ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የተመዘገበው ገቢ 35.3 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ከአጎዋ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካ ከ6,400 በላይ ምርቶች ወደ አገሯ ያለቀረጥና ታሪፍ እንዲገቡ በአጎዋ ዕድል አማካይነት ብትፈቅድም፣ ሙሉ ለሙሉ ግን ነፃ ገበያ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ቀረጥና ታሪፍ ነክ ያልሆኑ እንቅፋቶች፣ ለድሆቹ የአፍሪካ ደካማ የግል ዘርፎች የማይቻሉ መጠይቆች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የተሰጣቸውን የነፃ ገበያ ዕድል ባላቸው አቅም ሳይጠቀሙ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚያበቃውን ዕድል እንዲራዘም መማፀናቸው አፍሪካውያኑን ሲያስተቻቸው ይታያል፡፡

እንዲህ ባለ ሁኔታ የቀጠለው አጎዋ በአብዛኞቹ አገሮች ዘንድም ዝቅተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡ እየታየ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ይመስላል የአሜሪካ ኮንግረስ አጎዋ ወደፊት በሚራዘምበት አኳኋን ላይ ፍንጭ ከመስጠት ባሻገር ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ያልሰጠ ሲሆን፣ አጎዋ ይቀጥል ቢባል እንኳ እስካሁን ከነበረው አተገባበር ጠበቅ ሊል እንደሚችል፣ እስካሁን የነበሩት ቅድመ ሁኔታዎችም ጠጣር ሊሆኑ እንደሚችሉ እየጠነከረ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም አሜሪካ አጎዋን ከአፍሪካ አገሮች ጋር ላላት የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ወሳኝ ድልድይ አድርጋ እንደምትመለከተው ባለሥልጣኖቿ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

ማርክ ሊንስኮር በአሜሪካ ረዳት የንግድ ልዑክ፣ የዓለም ንግድ ድርጅትና የብዙ አካላት ጉዳዮች ቢሮ ወኪል እንደገለጹት፣ አሜሪካ ለአፍሪካ ከምትሰጠው ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የገበያ ዕድል በተጨማሪ የንግድ ፋሲሊቲ ድጋፍ በማድረግ የአፍሪካ አገሮችን የመደገፍ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ የንግድ ፋሲሊቲ ድጋፍ የአፍሪካ አገሮችን የንግድ ተወዳዳሪነት ከማጎልበት ባሻገር የግሉ ዘርፍን የኢንቨስትመንት ለመሳብም እገዛ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

በዓለም ንግድ ድርጅት አማካይነት አባል አገሮች የንግድ ፋሲሊቲ ስምምነት ያፀደቁ ሲሆን፣ ስምምነቱም በጉምሩክና በድንበር አካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ስለተገኙ ለውጦች ሊንስኮር ሲጠቅሱ ዋቢ ያደረጓቸው ኬንያና ሩዋንዳን ነው፡፡ ለምሳሌ ከሞምባሳ ወደ ኪጋሊ አንድ ኮንቴይነር ለማሸጋገር ይወስድ የነበረው ጊዜ 21 ቀናት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ስድስት ቀናት እንዲቀንስ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በአንድ ኮንቴይነር ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረው ከፍተኛ ወጪም ወደ 1,700 ዶላር መውረዱንም በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ተስፋ ሰጭ ንግግሮች የተደመጡበት የኮሜሳው ጉባዔ ለአሥር ቀናት በአዲስ አበባ እየመከረ ይገኛል፡፡ የአጎዋ ቀጣይነት ተስፋም፣ በተስፋ እንደቀጠለ ሲሆን፣ አሜሪካ እስካሁን የታሪፍ ነፃ ገበያ ዕድሉ ሊራዘም የመቻሉን ፍንጭ ስትሰጥ ከሁለት ዓመት በላይ ቢሆናትም አሁንም ድረስ ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥባለች፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች