ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተገኙት የደቡብ ኮሪያው የመንግሥት አስተዳደርና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቾንግ ዮንግ-ሱ ‹‹የአፍሪካ – ኮሪያ ሪፐብሊክ የሚኒስትሮች የሕዝብ አስተዳደር ስብሰባ›› በሚል ርዕስ ሲካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሚኒስትሮችም ተሳትፈውበት ነበር፡፡ ኮሪያ በአፍሪካ የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓትና የመንግሥት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው እንዲሰጡ ዲጂታል የሕዝብ አገልግሎት በመንግሥት መሥርያ ቤቶች ውስጥ ይስፋፋ ዘንድ ድጋፍ ለማድረግ አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ ሥራ ኃላፊነት ያለባቸውን የአምስቱን አገሮች ሚኒስትሮችና ዴኤታዎቻቸው ሥልጠና እንዲወስዱ፣ ከሹማምቱ በታች ያሉ ኃላፈዎችም ሥልጠና እንዲወስዱ ዕድሉ መመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በደም የተሳሰረች የኮሪያ ወዳጅ አገር መሆኗንና ለዚህም የኮሪያውን ጦርነት ወቅት የሚያስታውሱት ሚኒስትር ቾንግ ዮንግ-ሱ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው የኢትዮጵያን፣ የኬንያን፣ የታንዛንያን፣ የሩዋንዳንና የኡጋንዳን መንግሥታት ከመደገፍ ባሻገር ለየአገሩ ተጨባጭ ፍላጎት የሚያገለግል የፖሊሲ እገዛ እስከ ማድረግ የዘለቀ ፍላጎት እንዳላት፣ በአንዳንዶቹ አገሮችም ይህ እየተተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የመንግሥት አገልግሎቶችንና የሲቪል ሰርቪስ ሙያተኞችን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ‹‹ኢ-ገቨርናንስ›› የተሰኘውን ሥርዓት በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለማስፋፋት ፍላጎት እንዳላት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ብርሃኑ ፈቃደ ሚኒስትር ቾንግ ዮንግ-ሱን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ከአምስቱ የአፍሪካ አገሮች ጋር በኢ-ገቨርናንስ መስክ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ይልቅ እነዚህ አምስት አገሮች የተመረጡበት የተለየ ምክንያት አለ?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- አምስቱ አገሮች በሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የተገኙት በኢኮኖሚ እያደጉ ያሉ አገሮች በመሆናቸው ነው፡፡ ለማደግ ከፍተኛ አቅም አላቸው፡፡ ከአገሮቹ አንዷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ናት፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና የተቀሩት አራቱ አገሮች አብረናቸው ለመሥራት በጣም ጠቃሚ አገሮች ናቸው፡፡ እንደ ኮሪያ ሪፐብሊክ ሚኒስትር ለገጠር የልማት ሞዴሎች ትልቅ ዋጋ እሰጣለሁ፡፡ ሲማኡንዶ ብለን የምንጠራው የኮሪያ የገጠር ልማት ሞዴል አለን፤ ይህም አዲስ የማኅበረሰብ እንቅስቃሴ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ይህ ሞዴል በኢትዮጵያና በተቀሩት አገሮች ውስጥ ሊተገበር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ወደፊት በኮሪያና በአፍሪካ አገሮች መካከል ለሚኖረው ትብብርም እነዚህ አምስት አገሮች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለን እናምናለን፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ አምስት አገሮች ድህነትን ከማጥፋት ዘመቻ ባሻገር ሰፋፊ የልማት ሥራዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ገቨርናንስ፣ የመንግሥት አስተዳደርና የመንግሥት አገልግሎቶች መሻሻል ላይ እየሠሩ ነው፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን አገሮች በመምረጥ ከሚኒስትሮቻቸው ጋር የተነጋገርኩት፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህ አገሮች በኢ-ገቨርናንስ መስክ እንደ ኮሪያ ዓይነት ሥርዓት መዘርጋት እንዲችሉ ያስቀመጣችሁት የቅድሚያ ተግባር ይኖር ይሆን?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- የተባበሩት መንግሥታት በየሁለት ዓመቱ የሚያደርገውን የኢ-ገቨርናንስ ጥናት መሠረት በማድረግ ባወጣው ደረጃ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2010፣ በ2012 እና በ2014 የኮሪያ ሪፐብሊክ በተከታታይ የመጀመሪያውን ደረጃ በማግኘት አሸንፋለች፡፡ ስለዚህ ኮሪያ ይህንን የልማት ተሞክሮ ለማካፈል ፍላጎት አላት፡፡ እንደምታውቀው ኢትዮጵያና ኮሪያ በደም የተሳሰሩ ወንድማማች አገሮች ናቸው፡፡ ኮሪያ ከባድ መከራ ውስጥ በነበረች ጊዜ ኢትዮጵያ ደርሳላታለች፡፡ ብሔራዊ ወይም አገር አቀፍ ልማት ከሚያካትታቸው መካከል የሕዝብ አስተዳደር፣ የሰው ሀብት ልማትና ተቋማዊ አወቃቀርና ሥርዓት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኢ-ገቨርናንስ በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ የታጠረ መስክ አይደለም፡፡ የሰው ሀብትን በማጎልበት፣ ኢ-ገቨርናንስን በብቃትና በቅልጥፍና ለመጠቀም ብሎም ለመተግበር እንዲችል ማድረግንም ያካትታል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያና ቀሪዎቹን አራት አገሮች በመምረጥ የኢ-ገቨርናንስ የልማት ተሞክሯችንን ለማካፈል ፍላጎት አለኝ፡፡ ሌላው ብሔራዊ ልማት ሊያጎለብተው የሚገባው ነገር፣ የሲቪል ሰርቪስ አገልጋዮችን ክህሎትና ዕውቀት ነው፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሙያተኞች በክህሎትና በዕውቀታቸው በጣም የተካኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ኮሪያ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ የበቃችው ምሥጋና ይግባቸውና ብልህ ወጣት የሲቪል ሰርቪስ ሙያተኞቿ ለአገራቸው ብሔራዊ ልማት ቁርጠኛ ሆነው በማገልገላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የሲቪል ሰርቪስ ብቃታችንን ለኢትዮጵያ በማጋራት ለአገሪቱ ብሔራዊ ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ አምስቱ አገሮች መልካም አመራር የሚሰጡ መሪዎች እንዳሏቸው እገነዘባለሁ፡፡ መሪዎቹ ልክ እኛ እንዳደረግነው በገጠር ልማት ሞዴል ላይ በመሥራት በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦቻቸውን ለማልማት እየሠሩ ነው፡፡ የገጠር ልማት ሞዴላችንን በመውሰድ አሻሽለውና ከአገራቸው ተጨባጭ ፍላጎት አኳያ እያስማሙ ተግባራዊ ለማድረግ አምስቱ አገሮች እየሠሩ ነው፡፡ ሆኖም የገጠር ልማት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የሰው ሀብትን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማካተትና ማጎልበት አለብን፡፡ የኮሪያ መንግሥት አምስቱ አገሮች የሕዝብ አስተዳደርና ኢ-ገቨርናንስ ብሔራዊ የልማት መስመሮቻቸውን እንዲመሩት ለማድረግ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ የአገራችሁ የአምስት ዓመቱ የኢኮኖሚ ዕቅድ [የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ] አንደኛው ምዕራፍ ተገባዶ ሁለተኛውና በኢንዱስትሪ የሚመራ ኢኮኖሚ ለማድረግ የሚታሰበውን ዕቅድ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን ኮሪያን ጨምሮ በውጭ አገር እየተማሩ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ልማት ፍላጎት እንዳላቸውም አውቃለሁ፡፡ በኮሪያ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ባሻገር የኮሪያን የሕዝብ አስተዳደርና የሕግ ሥርዓቶች እያጠኑ ነው፡፡ ተማሪዎችን ካነሳን አይቀር አንድ ከፍተኛ ነጥብ ያመጣ የሕክምና ተማሪ የነበረን ወጣት ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ከፍተኛ ነጥብ አምጥቶ ሕክምና ማጥናት ቢችልም ይህንን በመተው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለማጥናት ወስኗል፡፡ በሕክምና ጥሩ ደመወዝ ሊያገኝ እንደሚችል ቢታወቅም፣ የሕክምና ትምህርቱን ቀይሮ ከእሱ ይልቅ አገሩን የበለጠ ሊጠቅማት በሚችል ሙያ ላይ ለመሰማራት መርጦ እያጠና ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የአምስቱን አገሮች የሕዝብ አስተዳደር ወይም ሕዝባዊ አገልግሎት እንዴት ይገመግሙታል? በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- በእኔ አስተሳሰብ በአፍሪካ ያለው የሕዝብ አስተዳደር ልማት ገና ጅምር ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ኮሪያ በዚህ መስክ ላይ ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለች ብዬ አምናለሁ፡፡ ዋናው የሕዝብ አገልግሎት ወሳኝ ነጥብ ተፈላጊውን አገልግሎት ለሕዝብ በተገቢው ጊዜ ማድረስ መቻል ነው፡፡ ይህንን ለማከናወን ግን ብቃት ያለው የሲቪል ሰርቪስ ባለሙያ እንዲኖርና አገልግሎቱን እንዲሰጥ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የትምህርት ተቋማትም ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ልንተባበር የምንችልባቸው መስኮች አሉ፡፡ በተጨማሪም የአምስቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኮሪያ የሥልጠና ፕሮግራሞች ላይ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡፡ ሆኖም ሥልጠናዎቹ በሠራተኛ ደረጃ ያሉትን ቅጥር ባለሙያዎችም እንዲያካትቱ በማድረግ በሕዝብ አስተዳደር መስኮች ላይ የሁለትዮሽ ትብብራችንን ማስረጽ እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሚኒስትሮችንና ሚኒስትር ዴኤታዎችን በዋነኛነት የሚያሳትፈው ሥልጠና ዝርዝር ይዘቶች ምንድን ናቸው?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሥልጠናው በአብዛኛው የኮሪያን ስኬታማ ገድሎች ከማካፈል ባሻገር በኢ-ገቨርናንስ በኩል የመንግሥት በጀት እንዴት እንደምናዘጋጅ ያሳያል፡፡ ሆኖም መንግሥታዊ አወቃቀር ላይ በአምስቱ አገሮች ዘንድ ችግር ሳይገጥመን አይቀርም፡፡ በመነጋገር ወደ አንድ ግብ ሊያደርሰን በሚችል ሐሳብ ላይ እንስማማለን ብለን እናስባለን፡፡ የትኛውም ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በሥልጠናው ላይ መወከል እንደሚገባው እንወያያለን፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ካነጋገሯቸው ሚኒስትሮች አንዳንዶቹ በየአገሮቻቸው መሠረተ ልማት ገና እየገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ፋይበር ኦፕቲክ ኬብሎችን እየዘረጉ እንደሚገኙ አውስተዋል፡፡ ሌሎች እንደ ሞባይል ባንኪንግ ያሉትን ሥርዓቶች መመሥረታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ባለው የተዘበራረቀ ሒደት ውስጥ በምን መልኩ ነው በአምስቱ አገሮች ውስጥ ኢ-ገቨርናንስ እንዲዘረጋ ድጋፍና ትብብር የምታደርጉት?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- በአሁኑ ወቅት በኮሪያ እንደ ክላውድ ኮምፒውተር ‹‹ቢግ ዳታ›› ሥርዓት ዓይነት የመጠቁ ቴክኖሎጂዎችን አጣምረን በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ ውስጥ እየተጠቀምን እንገኛለን፡፡ ቴክኖሎጂው በዚህ መንገድ ሲጎለብት የመንግሥትም ሚና በዚያው መጠን እየተለወጠ ይመጣል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው መስተጋብርም እየተለወጠ መሄዱን ይቀጥላል፡፡ በርካታ ሰዎች በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ተሳታፊነታቸው እየጨመረ፣ ስለመንግሥት ፖሊሲዎችም ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የየራሱ የልማት ምዕራፍ እንዳለው በሚገባ እገነዘባለሁ፡፡ ለመልማትም ፈርጀ ብዙ ስትራቴጂዎች አሏቸው፡፡ ሆኖም የጎደለውን መሙላት ጠቃሚው ነጥብ ይሆናል፡፡ የኮሪያን የልማት ሞዴል እንደተዋሰ ታዳጊ አገር፣ በሁለት አማራጮች መጓዝ እንደሚቻል ሐሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛው አማራጭ የኮሪያን ውድቀቶች በመዝለል በጣም የመጠቀው የልማት ደረጃ ላይ ለመድረስ መነሳት ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ኮሪያ ያለፈችበትንና ደረጃ በደረጃ የሚተገበረውን የልማት መንገድ መከተል ነው፡፡ የትኛውን ሞዴል መተግበር እንዳለባችሁ የምትመርጡት እናንተ ናችሁ፡፡ በትብብራችን መሠረትም የሚወሰን ይሆናል፡፡ የኬንያ ሚኒስትር እንደጠቀሱት አዲሱ የኬንያ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ቀድሞ የነበረው የኮሙዩኒኬሽን፣ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን እንደገና አዋቅሮታል፡፡ የኮሪያው የቀድሞ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙዩኒኬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን አፍርሶ የነበሩትን ኃላፊነቶችም ለተለያዩ ሚኒስቴሮች ደልድሏል፡፡ በኬንያ የትኛው መሥሪያ ቤት ኢ-ገቨርናንስ ይተግብር በሚለው ላይ እየመከሩ ነው፡፡ እኛም እንዲህ ያለው ነገር አጋጥሞን ስለነበር ከኬንያውያኑ ጋር እንመክርበታለን፡፡ የኬንያ ባለሥልጣናት ደረጃ በደረጃ የሚኬድበትን አማራጭ በመተው የመጠቁ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት እንደሚቀዱ እያሰቡ ነው፡፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያስ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ የአገሪቱ ድንበር ክልል ከደቡብ ኮሪያ አኳያ በአሥራ ሁለት እጥፍ ይበልጣል፡፡ የሕዝቡ ብዛትም ከኮሪያ በሁለት እጥፍ ይበልጣል፡፡ በርካታ የክልል መንግሥታት እንዳሏችሁ አውቃለሁ፡፡ የኢ-ገቨርናንስ ስትራቴጂውን ለመምረጥ የእያንዳንዱ ክልላዊ መንግሥት አካሄድ ይወስነዋል፡፡ የፋይበር ኦፕቲክ ኔትወርክ አልያም ክላውድ ኮምፒውቲንግ ቴክኖሎጂን ለመተግበር የክልሎች ጉዳይ ይሆናል፡፡ ለአገራችሁ እንዲስማማ ተደርጎ ለሚዘጋጀው ሞዴል ኮሪያ ፍላጎቶቻችሁን ማወቅ ትፈልጋለች፡፡ ለልማት የሚስማማውን፣ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞና ተለክቶ የሚዘጋጀውን ሞዴል ለማምጣት የሁለታችን ትብብር ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ በዚህ መስክ ለመሥራት እንድንችልም የሁለትዮሽ ግንኙነታችንን ማስፋት እንችላለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአምስቱ አገሮች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማችኋል፡፡ የተፈራረማችኋቸው ሰነዶች ይዘት ምን እንደሆነ ቢገልጹልን?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- የመግባቢያ ሰነዶቹ ይዘቶች ፈጣን ለውጦች ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ እስካሁን ስናጎለብታቸው በነበሩት የሁለትዮሽ ትብብሮች ላይ ለመጨመርና ለማጠናከር እየሞከርን ነው፡፡ በመግባቢያ ሰነዶቹ አማካይነት ትብብራችንን ወደ ፊት በማራመድ በጋራ በመነጋገር ለየአገሮቹ ፍላጎት የሚስማማ ሞዴል መቅረጹ ላይ ለመሥራት እየጣርን ነው፡፡ በዚህ አኳኋን የኮሪያ መንግሥት ለአፍሪካ አገሮች የሚስማሙ የልማት ሞዴሎችን ለመፍጠርና ለአገሮቹ ለማቅረብ ይቻለዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አገርዎ ዲጂታል ከመሆን አልፋ በፈጠራና በውስብስብ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ማማ ላይ ትገኛለች፡፡ በኢ-ገቨርናንስ አማካይነት መንግሥት በርካታ አገልግሎቶችን ያቀርባል፡፡ ለኢኮኖሚውም ሥርዓት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ በመንግሥት ግዥ፣ በገቢና ወጪ ንግድ፣ በጉምሩክ ሥነ ሥርዓትና በመሳሰሉት አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የወጪ ቅነሳ አምጥቷል፡፡ የኮሪያ ዜጎች የኢ-ገቨርናንስ አገልግሎት ባስገኘው በዚህ ሁሉ ለውጥ ምን ያህል ደስተኞች ናቸው?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- ኮሪያውያን ዲጂታል ሕዝቦች መባላቸው እንደሚያኮራቸው መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ከመነሻው የኮሪያውያን ባህርይ ለዲጂታል ዓለም የሚስማማ ነው፡፡ ፍጥነት ላይ የተመሠረተ ፀባይ ስላላቸው መንግሥት ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ለፍላጎታቸው መሟላት ምላሽ ካልሰጠም በጣም ይከፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በጣም ግልጽ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሲሆን የመንግሥት መረጃዎችንና ሰነዶችን በቀላሉ ማግኘትም ይቻላቸዋል፡፡ ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው የመንግሥት መረጃዎችን በማግኘት ሕይወታቸውን ማሻሻል ይፈልጋሉ፡፡ የኮሪያ መንግሥትም አዲስ ምዕራፍ በመከተል ‹‹መንግሥት 3.0›› ብለን የሰየምነውን ለውጥ መተግበር ጀምረናል፡፡ ይህ በመሆኑም በተቻለን አቅም ግልጽ ለመሆን እየጣርን ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በፖሊሲ አወጣጥ ሒደቶች ላይ ከፖሊሲ ቀረፃ ጀምሮ ባለው እርከን ሁሉ እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ ኮሪያ ዴሞክራሲያዊት አገር ለመሆን ሁለት አሥርት ብቻ ወስዶባታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1987 ጀምሮ የተጠነሰሰውን ዴሞክራሲ ማሳካት ተችሏል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም መንግሥትና ሕዝቡ ግልጽነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጥረዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ አገልግሎት ሰጪ በመሆን ለማገልገል ይሞክራል፡፡ ኮሪያውያን ግን የመንግሥትን መረጃና ሰነዶች ለማግኘት ከዚህም በላይ ዕድል እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሲሆን የመንግሥት ሙስናን ለማስቀረትና የኑሮ ጫናዎችን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ በጥቅሉ ኮሪያውያን በመንግሥት አገልግሎት ደስተኞች ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ ሆኖም ኮሪያውያንን ማስደሰት ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ ልናሻሽላቸው የሚገቡ ነገሮች አሁንም አሉ፡፡ ስለ ወጣት ኮሪያውያንም ማለት የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ለአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ አዲስ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ እንደ ዲጂታል ማኅበረሰብ ይኼ አኳኋን በአዎንታዊነት የሚታይ ነው፡፡ ጊዜ ያለፈባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወዲያውኑ ያስወግዳሉ፡፡ ይህ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ወጣት ኮሪያውያኑ አዲስ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ስማርት ስልኮች ቢኖሯቸው እንኳ ሌላ የተሻለ ከመጣ የነበራቸውን ትተው አዲሱን ሥሪት ይገዛሉ፡፡ በዚህ ዓመት ጥቅምት ላይ ሳምሰንግ አዲስ ሥሪት የስማርት ፎን ስልኮችን ለገበያ አብቅቶ ነበር፡፡ እንደማምነው የቱንም ያህል አዲስ ሥሪት ቢኖራቸው፣ በርካታ ኮሪያውያን በአሁኑ ወቅት አዲሱን ስልክ በእጃቸው ማስገባታቸውን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ካነሱ አይቀር ሌሎችም እንደ ኤልጂ ያሉ በዓለምና በአፍሪካ ጭምር ትልቅ ቦታ የያዙ ናቸው፡፡ በአፍሪካ እየታሰበ ላለው የኢ-ገቨርናንስ ሥርዓት የሚኖራቸው ተሳትፎ ወይም ሚና ምንድነው?
ቾንግ ዮንግ-ሱ፡- እንደ መንግሥት ኃላፊ የሳምሰንግ ወይም የኤልጂ አስተዋጽኦን በሚመለከት መናገር ይከብደኛል፡፡ ሆኖም ግን መሠረተ ልማቶችና ተያያዥ ሥርዓቶች በኮሪያ መንግሥት እንደተዘረጉ መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ሳምሰንግና ኤልጂ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች የመንግሥትን እግር ተከትለው በተዘረጉ ሥርዓቶችና ተቋማት መነሻነት በኮሪያ ዲጂታል ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አስችለዋል፡፡ በግሌ እንደማምነው በመንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደሩ ኩባንያዎች ይህንን ተግባር ይወጡ ነበር ብሎ ማሰብ ያቸግራል፡፡ ለግሉ ዘርፍ ምስጋና ይሁንና በኮሪያ ዲጂታል ማኅበረሰብ ለመፍጠር ችለናል፡፡ በመሆኑም የግሉ ዘርፍ በዲጂታል ማኅበሰረብ መፈጠርና ዕውን መሆን ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለ አፍሪካ ሲታሰብም ዲጂታል ማኅበረሰብ በመፍጠሩ ላይ የግሉ ዘርፍ ሚና ይሆንና ባለቤትነትና አስተዳደሩን አፍሪካውያን ራሳቸው ሊያከናውኑት ይችላሉ፡፡ ትልልቅ የኮሪያ ኩባንያዎችን ማምጣቱ ላይ ግን የየአገሮቹ ውሳኔ ይሆናል፡፡ የኮሪያ ኩባንያዎች አስተዋጽኦ በማድረግ በአፍሪካ የዲጂታል ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ማገዙ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው ተሳትፎ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡