‹‹ባሳየነው በጎ የፖለቲካ ፍላጎት ዛሬ እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የመርህ መገለጫዎችን (Declaration of Principles) በሱዳን ከተማ ካርቱም ላይ ለመፈራረም ችለናል፡፡ የቀረን ነገር ቢኖር በየአገሮቻችን ሕገ መንግሥታዊ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት አልፎ ወደ አፈጻጸም እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የስምምነታችን ፋይዳ ያለው በቃላቱ ላይ አይደለም፡፡ ፋይዳው ያለው ስምምነታችንን በቀናነትና በታማኝነት ወደ ተግባር ስንቀይር ነው፡፡›› ከላይ የተገለጸውን ንግግር ያደረጉት ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት በኢትዮጵያ ሕግ አውጪ አካል ለሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባዔ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በኢትዮጵያ ፓርላማ ያደረጉት ንግግር ማጠንጠኛ ከላይ የተቀጠው ሐሳብ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ቤተሰባዊ ግንኙነትና የጋራ ህልም ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦችና መጪ ትውልድ ሲባል አዲስ ታሪክ አሁን መጀመር እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ከመጣንበት አስቸጋሪ ሁኔታም እንድንማር እጠይቃችኋለሁ፡፡ የቀድሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቅረፍ የምናደርገው ስምምነት ዛሬያችንን ወይም የወደፊት ምኞታችንን እንዲያጨናግፍብን መፍቀድ የለብንም፡፡ አዎ መተማመንን መገንባት አለብን፡፡ የጥርጣሬ ክፍተቶች እንዳይሰፉና ሸለቆ ሆነው ጨርሶውኑ እንዳይለያየን መጠንቀቅ አለብን፤›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ የግብፅን አብዮት አረጋግተው በሕዝባዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ በአጀንዳቸው ካመጧቸው የግብፅ የውጭ ፖለቲካ አንኳር ጉዳዮች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ከተማ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጐን ለጐን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በህዳሴው ግድብና በዓባይ ወንዝ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ ተወያይተው የመግባቢያ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በዋናነት እየተጉበት ያለው ጉዳይ፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የግብፅን የውኃ ፍላጎት እንደማትጎዳ በተለያዩ ባለሥልጣናቷ የምታስነግረውን በሰነድ እንዲሰፍር ማድረግ ነው፡፡
በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. በማላቦ ከተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በኋላም የግብፅ ፕሬዚዳንትና የካቢኔ አባሎቻቸው ይህንኑ የግብፅን ታሪካዊ የውኃ መጠን ለማስከበር የሰነድ ዝግጅት ውስጥ እንደገቡ፣ ይህንኑ ሰነድም ኢትዮጵያና ሱዳን እንዲመለከቱትና እንዲመክሩበት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የዚህ የመርህ መግለጫ ሰነድ በግብፅ በኩል ተዘጋጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ፕሬዚዳንት አልሲሲና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በማላቦ በሰኔ ወር ከተገናኙ በኋላ በነሐሴ ወር መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው ረቂቅ በተለየ ፎርማት ማለትም በአዋጅ መልክ የተቀረፀ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በኩል ቅርፁንና ይዘቱን በማሻሻል የመርህ መገለጫ እንዲሆን መደረጉን ቃል አቀባዩ ያስረዳሉ፡፡
ሰነዱ ይህንን ቅርፅ ከያዘ በኋላ በየካቲት እና በመጋቢት 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በግብፅ እንዲሁም ሱዳንን ጨምሮ ጥልቅ ውይይት ተደርጎ፣ ‹‹የመርህ መግለጫ ወይም ዴክላሬሽን ኦፍ ፕረንሲፕልስ›› ሆኖ ስምምነት መደረሱን ያስረዳሉ፡፡
የመርህ መግለጫው ውስጣዊ ይዘት
የመርህ መግለጫው አሥር አንቀጾችን የያዘ ባለ አምስት ገጽ ሰነድ ነው፡፡ የሰነዱ መግቢያ እንደሚያስረዳው ሦስቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሦስቱም አገሮች እየጨመረ ያለውን የውኃ ፍላጎታቸውንና ለዚህም የዓባይ ወንዝ ፋይዳን ከግምት በማስገባት የደረሱበት መግባቢያ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡
የሰነዱ የመጀመሪያ አንቀጽ ስለ ትብብር መርህ የሚያትት ሲሆን፣ ሦስቱ አገሮች በጋራ መግባባት፣ የጋራ ተጠቃሚነትን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ባረጋገጠ መንገድ መተባበር፣ የላይኛው ተፋሰስና የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን የውኃ ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት መተባበርን ስለመፍጠር ያትታል፡፡
የመርህ መግለጫው አንቀጽ ሁለት ቀጣይነት ስላለው ልማትና አካባቢያዊ ትስስር ይመለከታል፡፡ በውስጡም ‹‹የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሠረታዊ ዓላማና ጥቅም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት፣ ለኢኮኖሚ ልማት አስተዋፅኦ ለማድረግ፣ ድንበር ዘለል ትብብርንና አስተማማኝ በሆነ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢው አገሮችን ማስተሳሰር›› መሆኑን አስቀምጧል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞችና ከህዳሴ ግድብ ፖለቲካ ጋር በተገናኘ በጥልቀት የሚያውቁ በስምምነቱ ከተጠቀሱት ዝርዝር ነጥቦች መካከል ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ባፀደቀው ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ልማዳዊ ሕጎች፣ እንዲሁም ከግብፅና ከሱዳን በስተቀር ሌሎቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የተፈራረሙበትና ሦስት አገሮች በፓርላማቸው ባፀደቁት የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ውስጥ የተገለጹ ናቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ሰሞኑን የተፈራረሙት የመርህ መግለጫ ሰነድ ባይኖርም በሰነዱ የተገለጹት አብዛኞቹ ነጥቦች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው አሠራሮች በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ የምትገዛባቸው መሆኑን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ የመርህ መግለጫው አንቀጽ ሁለት በቀጥታ የህዳሴውን ግድብ የሚመለከት ለሦስቱም አገሮች ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ኮሌጅ በማስተማር ላይ የሚገኙትና በዓባይ ወንዝ ፖለቲካ ተመራማሪ የሆኑትና እንዲሁም በዚሁ ዙሪያ “International Water Cources Law in the Nile Basin River: Three States at a Crossroads” የሚል መጽሐፍ እ.ኤ.አ. በ2013 ያሳተሙት ዶ/ር ታደሰ ካሳ፣ ኢትዮጵያ ሰሞኑን በፈረመችው ስምምነት 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ የተንጣለለ ውኃዋን የምግብ እህል ዋስትናዋን ለማረጋገጥ እንዳትጠቀምበት ሊያደርጋት ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ከ74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ላይ የመጠጥ ፍላጎታቸውን ለማርካት እንዳይችሉ፣ በህዳሴው ግድብ አካባቢ የሚቋቋሙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የውኃ ፍላጎታቸውን ከዚህ የውኃ ምንጭ እንዳያሟሉ በራሷ ፈቃድ በገባችው ስምምነት እያገደች ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
ግብፆች የታላቁ ህዳሴ ግድብ የደረሰበት ደረጃ የሚቀለበስ አለመሆኑን በመረዳት ላለፉት ጊዜያት በታታሪነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት፣ ከግድቡ መጠናቀቅ በኋላ የግድቡ ውጤት የሚያመጣውን ተፅዕኖ ከወዲሁ ለማስተካከል እንደሆነ ዶ/ር ታደሰ ይናገራሉ፡፡
ይህ ጥረታቸውም ሰሞኑን ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በተፈራረሙት ‹‹የመርህ መግለጫ›› ሰነድ አንቀጽ ሁለት ላይ መቀመጡን ያስረዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የህዳሴው ግድብ የሚያጠራቅመው ውኃ ወደፊት ምን ዓይነት ጥቅም ሊሰጥ ይችላል የሚለውን በአግባቡ ማስረዳት፣ እንዲሁም ውኃውን ለማንኛውም ጥቅም የማዋል ሉዓላዊ መብቷ መሆኑን አስረግጦ ማስገንዘብ ሲገባ ግድቡ የሚያጠራቅመው ውኃ የሚውለው ለኃይል ማመንጫ ብቻ ነው በማለት መስማማት የተደረገው ዘመቻ ውጤት መሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡
በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት የቀድሞ ዳይሬክተር፣ በአሁኑ ወቅት የምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ የቴክኒክ ቢሮ ዋና ዳይሬክተርና ኢትዮጵያን በመወከል በህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ የሆኑት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ግን ከላይ በተቀመጠው ሐሳብ አይስማሙም፡፡
‹‹እኔም ሆንኩ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች ግድቡ የሚያጠራቅመው ውኃ ለመስኖ አይውልም የምንለው፡፡ መብታችንን አሳልፈን ለመስጠት ሳይሆን በትክክልም ለግብርና አመቺ የሆነ መሬት ባለመኖሩ ነው፤›› ይላሉ፡፡
አቶ ፈቅአህመድ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ በቤንሻንጉል ክልል ለእርሻ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለአብነት ያህል በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ብቻ 345 ሺሕ ሔክታር ማለትም አዲስ አበባን ስድስት ጊዜ የሚበልጥ መሬት መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ለግብርና ምቹ የሆነ መሬት ከህዳሴ ግድብ ውኃ መጠቀም ሳያስፈልገው ከሌሎች የውኃ ምንጮች መጠቀም ቢቻል እንኳ፣ ሉዓላዊ መብትን አሳልፎ በመስጠት የወደፊት ትውልድን የመጠቀም መብት መገደብ አይገባም የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ አሉ፡፡
ዶ/ር ታደሰ በበኩላቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እንደሚሉት አካባቢው ለእርሻ ምቹ ባይሆን እንኳን፣ ግብፅ ብዙ ማይሎችን አቋርጣ በፓምፕ ለግብርና ልማት እንደምታውል ሁሉ ኢትዮጵያም ይህንኑ ማድረግ ትችላለች ይላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም ከባለሥልጣን ተሰምቶ የማይታወቀውን አሁን መናገር የቻሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ናቸው፡፡ ስምምነቱ ከተፈረመና ፕሬዚዳንት አልሲሲ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለፋና ብሮድካስቲንግ በሰጡት አስተያየት፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለግብርና ልማት እንዳታውል የሚከለክላት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደሳቸው አባባል ከሆነ ኢትዮጵያ ውኃውን መሳቢያ ቱቦዎችን በመጠቀም መለስተኛ የእርሻ ልማቶችን ማከናወን፣ እንዲሁም ለቱሪዝምና ለዓሣ ዕርባታ ማከናወን እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በድርድሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ፈቅአህመድ በበኩላቸው፣ በግብፅ በኩል ቀርቦ የነበረው ረቂቅ ሰነድ የህዳሴው ግድብ የሚይዘው ውኃ ለግብርና ልማት አይውልም ይል እንደነበር አስታውሰው፣ ይህ ግን በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ተገልጾ የኢኮኖሚ ልማት በሚል እንዲተካ መደረጉን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹በመሆኑም ኃይል ከማመንጨት ውጪ ለመረጥነው ዓላማ ለመጠቀም አንቀጹ የሚገድብ ነገር የለውም፤›› ብለዋል፡፡ የመርህ መግለጫ ሰነዱ በአንቀጽ ሁለት ካስቀመጠው አወዛጋቢ ሐሳብ ውጪ ያሉት ሌሎች ነጥቦች ይህንኑ ማዕከላዊ ሐሳብ ለመደገፍ የገቡ እንጂ፣ በአብዛኛው የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ፍላጎት የሚጋፉ አይደሉም በማለት ዶ/ር ታደሰ ይከራከራሉ፡፡
ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም ሌሎቹ አንቀጾች በመርህ መግለጫው ላይ ባይሰፍሩም፣ በሌሎች ዓለም አቀፍ ሕጎች፣ በዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ውስጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕጎች (International Customary Laws) ኢትዮጵያ የምትገደድባቸው ናቸው ይላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የመርህ መግለጫ ሰነዱ አንቀጽ አምስት ላይ የተቀመጠው ሐሳብ ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጠቅም ድንቅ አንቀጽ ነው ብለዋል፡፡ ይህ አንቀጽ በአሁኑ ወቅት ሦስቱ አገሮች የውጭ አማካሪ በመቅጠር ኩባንያው በጥናቱ የሚደርስበት ግኝት ተመልሶ ለሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቀርብና እነሱ ከተቀበሉት ብቻ ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚገልጽ ነው፡፡
በመጀመሪያ በግብፅ በኩል በዚህ አንቀጽ ላይ ሰፍሮ የነበረው ዓረፍተ ነገር የሚቀጠረው ኩባንያ የሚያደርገውን ጥናት ተንተርሶ የሚሰጠው ምክረ ሐሳብ በቀጥታ ተቀባይነት እንደሚኖረው የሚገልጽ እንደነበርና እንዲስተካከል መደረጉን አቶ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ፡፡
በመሆኑም በዚህ ረገድ ሊቀርብ የሚችልን የግድቡ የውኃ የመያዝ አቅምና ከፍታ የመሳሰሉትን የግብፅ ጥያቄዎችን በሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ኮሚቴ መመለስ እንደሚቻል አቶ ፈቅአህመድ ገልጸዋል፡፡
የመርህ መግለጫ ሰነዱ ሕጋዊነት
አገሮች በመረጧቸው ጉዳዮች ላይ የሚያደርጓቸው ስምምነቶች የተለያዩ የሕግ ደረጃዎችን እንደሚይዙ ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1996 የወጣው የቪየና ኮንቬንሽን አገሮች እርስ በርሳቸው የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች የሚገዛ ነው፡፡ በዚህ የቪዬና ኮንቬንሽን መሠረት የተለያዩ ሕጋዊ ተቀባይነት የሚኖራቸው ስምምነቶች መካከል ‹‹ትሪቲ፣ ፕሮቶኮል፣ አክት፣ ፓክት እንዲሁም ኮቬናንት›› ጥቂቶቹ መሆናቸውን ዶ/ር ታደሰ ያስረዳሉ፡፡
የመርህ መግለጫ ሰነዱ የሚሰጠው ትርጓሜ የፖሊሲ መልዕክት ለማስተላለፍ ቢመስልም፣ ሦስቱ አገሮች ይህንን ሰነድ ለማዘጋጀት ያለፉባቸው ድርድሮችና ይዘቶቻቸው የሦስቱ አገሮች ፍላጎት ከታከለበት አስገዳጅ ሕግ መሆን እንደሚችል ይከራከራሉ፡፡
አቶ ፈቅአህመድ በበኩላቸው፣ በመጀመሪያ በግብፅ በኩል የቀረበው ረቂቅ ሰነድ በሦስቱም አገሮች ሕግ አውጪ አካል እንዲፀድቅ ሐሳብ የሚያቀርብ ቢሆንም ይህ አንቀጽ እንዲሰረዝ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡
ይሁን እንጂ በግብፅ በኩል አሁንም ፍላጎት መኖሩን አቶ ፈቅአህመድ ይናገራሉ፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኝ በበኩላቸው፣ ስምምነት የተደረሰበት ሰነድ የፖለቲካ እንጂ ሕጋዊ ግዴታን የሚጥል አይደለም ሲሉ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሰነዱ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው በሦስቱ አገሮች ሕግ አውጪ አካል ሰነዱ እንዲፀድቅ የሚል አንቀጽ በስምምነቱ ባለመኖሩ፣ እንዲሁም በሰነዱ ላይ ከተገለጹት አንቀጾች መካከል አንቀጽ ዘጠኝ ‹‹ሦስቱ አገሮች የሚተባበሩት በእኩል የሉዓላዊነት መርህ ነው›› የሚል በመሆኑ አስገዳጅ ሊሆን አይችልም ብለዋል፡፡
በግብፅ በኩል ይህ የመርህ መገለጫ ሰነድ ሕጋዊ ግዴታን የሚጥል እንዲሆን ፅኑ ፍላጎት መኖሩን ፕሬዚዳንት አልሲሲ ለኢትዮጵያ ፓርላማ ካደረጉት ንግግር፣ ወይም ሰነዱ ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ያላቸውን ፍላጎት ለፓርላማው አባላት በመግለጻቸው ፍላጎታቸውን በግልጽ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በዓረብኛ ያደረጉትን ንግግር ብቁ ባልሆነ ትርጉም ያዳመጠው ፓርላማው በደመቀ ጭብጨባ ተቀብሎ ቢሸኛቸውም፣ ሰነዱን እንዲያፀድቅ ይቀርብለት ይሆን? ቢሆንስ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ የሚጠራቀመውን ውኃ ለፈለገችው ዓላማ የማዋል ሉዓላዊ መብቷን ያስከብራል? የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡ (ሚኪያስ ሰብስቤ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)