የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ባለፈው ሳምንት ለይፋዊ ሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ላይ የሚገኘው ኤልስዌዲ ኤሌክትሪክ፣ በድጋሚ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት ጥያቄ አቀረበ፡፡ በኤልስዌዲ አስተባባሪነት በቀረበው የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ጥያቄ በርካታ የግብፅ ኩባንያዎች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ አዳማ በሚያመራው ነባሩ መንገድ ላይ በምትገኘው ዱከም ከተማ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ማምረቻ የገነባው ኤልስዌዲ፣ ከአራት ዓመት በፊት የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡
ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የኩባንያው ዕቅድ ተግባራዊ ባለመሆኑ፣ ባለፈው ረቡዕ ይህንን የቆየ ፍላጎቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ጥያቄ ማቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ዶ/ር አርከበ ለኩባንያው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ሰሎሞን፣ ኩባንያው ለኮርፖሬሽኑ ይፋዊ ጥያቄ እንዳላቀረበ ገልጸው፣ ኩባንያው የኢንዱስትሪ ዞን ጥያቄውን በቅድሚያ ወደ በላይ አካል መውሰዱን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሦስት ዓይነት መንገድ የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ይካሄዳል ያሉት አቶ ሽፈራው፣ የኢንዱስትሪ ዞን ልማቱ በመንግሥት፣ በግል ኩባንያዎችና የግል አልሚዎች ከመንግሥት ጋር በሽርክና የሚያካሂዷቸው ናቸው ብለዋል፡፡
የግብፅ የሚዲያ አውታሮች ፕሬዚዳንት አልሲሲ ለግብፃውያን ባለሀብቶች ባቀረቡት ጥሪ ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንዱስትሪ ዞን እንዲገነቡ መጠየቃቸውን ዘግበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚዲያ ተቋማቱ ለኢንዱስትሪ ዞን ግንባታው ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ መሰጠቱን ቢገልጹም፣ በዚህ መግለጫ ላይ ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠም፡፡
መንግሥት በአምስት ከተሞች ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የክልል መንግሥታትም በራሳቸው አቅም በበርካታ ከተሞች የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማቋቋም ላይ ናቸው፡፡
በውጭ ድርጅቶች ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት በርካታ ፋብሪካዎችን ወደ ምርት አስገብተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቱርክና የህንድ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ ለማካሄድ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ሲሆኑ ግብፅ ከእነዚህ ኩባንያዎች ጎራ ተቀላቅላለች፡፡
አገር በቀል ኩባንያዎች በተለይ በዘመናዊ ቄራ በመታገዝ ሥጋ ወደ ግብፅ ሲልኩ ቆይተዋል፡፡ የግብፅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በጥልቀት በመግባት በተለይ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ፡፡ 40 የሚጠጉ የግብፅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡