- በአፋር ፖታሽ ላይ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደርጋል
በዓለም በማዳበሪያ ምርት የሚታወቀው እስራኤል ኬሚካልስ (አይሲኤል) የተሰኘው የእስራኤል ኩባንያ፣ በአፋር ክልል በፖታሽ ማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማራውን አላና ፖታሽ ኩባንያን ገዛው፡፡
ባለፈው ዓመት አይሲኤል ከአላና ፖታሽ ላይ 16 በመቶ አክሲዮን መግዛቱ የሚታወስ ነው፡፡ የተቀረውን የአላና ፖታሽ 84 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ለአይሲኤል ለመሸጥ ከስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የአላና ፖታሽና የአይሲኤል ኃላፊዎች ስምምነቱን መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የአላና ፖታሽ ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት በቶሮንቶ ካናዳ ተፈራርመዋል፡፡
ከአላና ፖታሽ አፋር መሥራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ነጂብ አባቢያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስምምነቱ በአላና ዳይሬክተሮች ቦርድ የፀደቀ ቢሆንም የኩባንያው ሁለት ሦስተኛ ባለአክሲዮኖችን ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
አይሲኤል የአላናን 300 ሚሊዮን አክሲዮን እያንዳንዱን 0.50 የካናዳ ዶላር እንደሚገዛ አቶ ነጂብ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ አይሲኤል 150 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በመክፈል የአላና ኩባንያን በመጠቅለል በአፋር ክልል ዳሎል የሚገኘውን የኩባንያውን ፖታሽ ማዕድን ክምችት ባለቤት ይሆናል፡፡ አላና ፖታሽ ላለፉት ስድስት ዓመታት በዳሎል የፖታሽ ፍለጋና የአዋጭነት ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በፍለጋ ሥራው ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጉን አቶ ነጂብ ተናግረዋል፡፡
የአላና የፖታሽ ማዕድን ይዞታ 300 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆነው ቦታ በፖታሽ ማዕድን የተሸፈነ ነው፡፡ አላና ባካሄደው ጥናት 3.2 ቢሊዮን ቶን የሚሆን የፖታሽ ክምችት መኖሩን አረጋግጧል፡፡
የአላና ማኔጅመንት ኩባንያውን ለመሸጥ ውሳኔ ላይ የደረሰው የፖታሽ ማዕድን በዓለም ገበያ ላይ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት 570 ዶላር የነበረው የአንድ ቶን ፖታሽ ዋጋ እያሽቆለቆለ መጥቶ 280 ዶላር ደርሷል፡፡ ለዚህም በዋነኝነት የሚጠቀሰው ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው አጠቃላይ የፖታሽ ምርት 40 በመቶውን የሚያመርቱት ሩሲያና ቤላሩስ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የፖታሽ ምርት በማምረት የዓለም ገበያን በጋራ ሲቆጣጠሩ ኖረዋል፡፡
የዓለም የፖታሽ ዋጋ በመመካከር ይወስኑ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት ዓመት በፊት በሁለቱ አገሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት አገሮቹ በየፊናቸው እንደልባቸው በማምረት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በገፍ ማስገባት ጀምረዋል፡፡ በተለይ ቤላሩስ የምታቀርበውን ፖታሽ በከፍተኛ መጠን በመጨመር በዝቅተኛ ዋጋ በመሸጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም በዓለም የፖታሽ ኢንዱስትሪ ላይ ከፍተኛ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን በርካታ ኩባንያዎችን ለኪሳራ ዳርጓል፡፡
የፖታሽ ኩባንያዎች በስቶክ ገበያ ላይ ያላቸው ዋጋ አሽቆልቁሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 2.8 የካናዳ ዶላር የነበረው የአላና ፖታሽ አክሲዮን ዋጋ ወደ 0.34 ካናዳ ዶላር ወርዷል፡፡
የተፈጠረው የገበያ ቀውስ በአፋር ክልል ዳሎል የሚገኘውን የፖታሽ ክምችት ለማልማት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ‹‹ይህ የተከሰተው በእኛ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና ባለሀብቶች በፖታሽ ማዕድን ላይ በአሁኑ ወቅት ኢንቨስት ማድረግ አይፈልጉም፡፡ ጊዜው ለጀማሪ አልሚ ጥሩ አይደለም፤›› ብለዋል አቶ ነጂብ፡፡
አላና ፖታሽ በዳሎል የፖታሽ ማዕድን ማውጫና የፖታሽ ማዳበሪያ ፋብሪካ በ750 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ምርቱንም እ.ኤ.አ. በ2015 ለመጀመር አቅዶ ነበር፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ የማዕድን ልማት ፈቃድ ለኩባንያው ሰጥቶ ነበር፡፡
የአላና የስቶክ ዋጋ በመውረዱ አቶ ነጂብን ጨምሮ በርካታ ባለአክሲዮኖችን ከፍተኛ ገንዘብ አሳጥቷቸዋል፡፡ ‹‹እኔ አገሬን በጣም የምወድ ሰው ነኝ፡፡ ለእኔ ትልቁ ነገር የፖታሽ ማዕድኑ ጥቅም ላይ ውሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሥራ አግኝተው መመልከት ነው፡፡ ይህን ደግሞ አይሲኤል እንደሚያሳካው እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡
አላና በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ላይ የሚሠሩ 200 ያህል ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን፣ የፍለጋ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ 80 ያህሉን ቀንሷል፡፡ የተቀሩትን 120 ሠራተኞች አይሲኤል ይዞ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከአቶ ነጂብ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ አይሲኤል በአፋር ፖታሽ ልማት ፕሮጀክት ላይ አንድ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ 3,000 ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ኩባንያው ከፖታሽ ኤክስፖርት በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማስገባት አቅዷል፡፡
አይሲኤል ከዓለም ስድስተኛ ግዙፍ የፖታሽ ማዕድን አምራች ሲሆን ጠቅላላ ሀብቱ 12 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ኩባንያው ኢዳን ኦፈር በተባሉ ቀዳሚ የእስራኤል ባለሀብት የተቋቋመ በእስራኤል ስቶክ ማርኬት የተመዘገበ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በቅርቡ በኒውዮርክ ስቶክ ገበያ ተመዝግቧል፡፡ የ59 ዓመቱ ኢዳን ኦፈር ጠቅላላ ሀብት 4.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የፎርብስ መጽሔት የቱጃሮች ዝርዝር ያሳያል፡፡
አይሲኤል በእስራኤልና እንግሊዝ የፖታሽ ማዕድን ማውጫ ያለው ሲሆን፣ በእንግሊዝ የሚገኘው ፖታሽ እየተሟጠጠ ነው፡፡ በመሆኑም በእንግሊዝ ፕሮጀክት ላይ ሲሠሩ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያመጣና ሥራውን በፍጥነት እንደሚጀምር የተናገሩት አቶ ነጂብ፣ ‹‹የዳሎልን ፕሮጀክት ለጥሩ ኩባንያ በመስጠታችን ደስተኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ኩባንያው የቴክኒክ ብቃትና ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያለው በመሆኑ የማንንም በር ሳያንኳኳ ፕሮጀክቱን ዕውን የማድረግ አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአፍሪካ የመጀመሪያውን የፖታሽ ማዕድን ማውጫ በመክፈቴና የኢትዮጵያን ንብረት ለመጀመሪያ ጊዜ በስቶክ ገበያ ላይ በማስመዝገቤ ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህም የምታወስበትን ታሪክ ሠርቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡