Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተሽከርካሪዎች እጥረት የሲሚንቶ ዋጋ አሻቀበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በጂቡቲ ወደብ የተከማቹ ዕቃዎችን እንዲያነሱ መንግሥት ግዳጅ በመስጠቱ፣ በአገር ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ ላይ ንረት ማስከተሉ ታወቀ፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሦስት ቀናት በሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ላይ ጉልህ ለውጥ ከመታየቱ በተጨማሪ፣ የሲሚንቶ እጥረት መከሰቱ እየተነገረ ነው፡፡ ከቀናት በፊት 250 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ደርባ ሲሚንቶ ባለፈው ሐሙስ 350 ብር፣ ዓርብ ደግሞ 400 ብር መድረሱን በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ መሰቦ ሲሚንቶም እንዲሁ ከቀናት በፊት ከ230 እስከ 240 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ሲሚንቶ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኩንታል 350 ብር መግባቱ ታውቋል፡፡ ይህ የዋጋ ንረት ሊከሰት የቻለው በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት መሆኑን፣ የደርባ ግሩፕና ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይሌ እንደገለጹት ደርባ ሲሚንቶ የምርት እጥረት ባይኖርበትም፣ ሲሚንቶ የሚያመላልሱ 50 ተሽከርካሪዎች ወደ ጂቡቲ ወደብ ተጉዘው ዕቃ እንዲያነሱ በመደረጉ ሲሚንቶ ወደ ገበያ ለማቅረብ የራሱን ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ አቶ ኃይሌ ጨምረው እንደገለጹት፣ በቀሩት ተሽከርካሪዎች ከመጋቢት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ክልል ከተሞች የሚደረግ ጉዞ በማስቀረት አዲስ አበባ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ከአንድ ሳምንት በፊት ለትራንስፖርት ባለንብረቶች ማኅበራት ባስተላለፈው ጥሪ በጂቡቲ ወደብ በርካታ ዕቃዎች በመከማቸታቸው፣ ዕቃዎቹን ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገቡ ለትራንስፖርት ባለቤቶች በማኅበራቸው በኩል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 በጂቡቲ ወደብ የተከማቹ ዕቃዎች ዘይትና ስንዴ ሲሆኑ፣ በአገሪቱ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች ዕቃዎቹን ለማስገባት መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡ ነገር ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ የሲሚንቶ አቅርቦት በመስተጓጎሉና አጋጣሚውን ለመጠቀም በሚፈልጉ ነጋዴዎች የሲሚንቶ ዋጋ መናሩ ተገልጿል፡፡ አቶ ኃይሌ በአንድ ኩንታል ሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ ላይ የ90 ብር ልዩነት መታየቱን አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ደርባ ሲሚንቶ የዋጋ ጭማሪ አለማድረጉን አስረድተዋል፡፡  

የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች የሲሚንቶ ዋጋ ጭማሪን በፍጥነት መቅረፍ ካልተቻለ፣ በኮንስትራክሽን ግንባታዎችና ሌሎች ዕቃዎች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ሊኖር እንደሚችል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበረውን የሲሚንቶ እጥረት ለመግታት ዘንድሮ በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 25 አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለማስገንባትና ከ27 ሚሊዮን ቶን በላይ ሲሚንቶ እንዲመረት ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡

ፋብሪካዎቹን ለማስገንባት መንግሥት የያዘው ዕቅድ ቢሳካም ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ባለመጀመራቸው ክፍተት መኖሩ እየተገለጸ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው ችግር መንስዔ ግን የትራንስፖርት ችግር መሆኑን የዘርፉ ተዋናዮች ይገልጻሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች