Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያና የግብፅ ስምምነት አለመተማመንን ብቻ ሳይሆን ኢፍትሐዊ ስምምነቶችንም መቅበር አለበት!

ባለፈው ሰሞን አዲስ አበባ ለሦስት ቀናት የሰነበቱት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ከቀድሞዎቹ የግብፅ መሪዎች በተለየ ሁኔታ ‹‹ሥር ነቀል›› የሚመስል ለውጥ አሳይተዋል፡፡ እንደ ካሁን በፊቱ ሁለቱ አገሮች በዓባይ ወንዝ ምክንያት ፍጥጫ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸውና ለአለመተማመን ምክንያት ይሆናሉ የሚባሉ ችግሮችን መቅበር አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ይህንን ሰላማዊ አማራጭ ግብፅ ስትቀበል፣ እግረ መንገዱንም የቀድሞዋ ቅኝ ገዥ እንግሊዝና ግብፅ እ.ኤ.አ. በ1929 እንዲሁም በግብፅና በሱዳን መካከል እ.ኤ.አ. በ1959 የተደረጉ ስምምነቶችም መቀበር አለባቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች የውኃ መጠቀም መብት ላይ ኢፍትሐዊና ኢምክንያታዊ ጫና ሲያሳድሩ በመቆየታቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግንባር ቀደምትነት እ.ኤ.አ. በ2010 በኡጋንዳ ዋና ከተማ ኢንተቤ በአብዛኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የፀደቀው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA)፣ ለፍትሐዊና ለምክንያታዊ የውኃ ሀብት አጠቃቀም መርህ የቆመ በመሆኑ የዘመኑ ገዥ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ ሕግ አፈንግጦ መውጣት አይቻልም፡፡ ያስጠይቃል፡፡

ይልቁንም ለዘመናት በውኃው ላይ በሞኖፖል የመጠቀም መብት የነበራት ግትሯ ግብፅና አሁን በመለሳለስ ላይ ያለችው ሱዳን ይህንን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንዲፈርሙ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለ፡፡ ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ጉልህ የሆነ ጉዳት እንደማይደርስባት በተደጋጋሚ ቃል ሲገባላት፣ እሷ ደግሞ ከእነዚያ ያረጁና ያፈጁ ኢፍትሐዊ ስምምነቶች መላቀቅ ይኖርባታል፡፡ የግድ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ለወደፊቱ ትውልድ ጠቃሚ የሆነ መሠረት ማኖር እንደሚገባ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ሕፃናት የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች የኤሌክትሪክ ብርሃን ሲያገኙ የግብፅ ሕፃናትም እንደ አባቶቻቸውና አያቶቻቸው ከዓባይ ውኃ መጠጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰላማዊና ለትብብር የተዘረጋ እጅ ተቀባይነት ማግኘት ይኖርበታል፡፡

ነገር ግን ግብፅም ለምክንያታዊና ለፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ የሚረዳትን ያንን ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ፈርማ በፓርላማዋ እንድታፀድቀው ግፊቱ ይጠንክር፡፡ የትብብር ማዕቀፉ የተፋሰሱ አገሮች አንደኛቸው በሌላኛቸው ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ በፍትሐዊነት ውኃውን እንዲጠቀሙ ስለሚያስገድድ፣ ግብፅ ‹‹ታሪካዊ የመጠቀም›› መብቷን በመታከክ ዘመን ያለፈባቸውንና አቧራ የጠጡ ኢፍትሐዊ የስምምነት ሰነዶችን ግብዓተ መሬታቸውን ትፈጽም፡፡ ለፍትሐዊነትና ለምክንያታዊነት ትገዛ፡፡

ኢትዮጵያና ግብፅ በካርቱም በተደረገው ‹‹የስምምነት መርህ›› አማካይነት ለግንኙነታቸው ‹‹አዲስ ምዕራፍ›› ተከፈተ ሲባል፣ ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል የሚችለው ለፍትሐዊነትና ለምክንያታዊነት መርህ መገዛት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ግብፅ ለዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን አለመተማመን እንዲያበቃ እፈልጋለሁ ስትልና ውጥረት የሚያረግብ አቅጣጫ ስትከተል፣ በነካ እጇ ለመርህ እንድትገዛ ይደረግ፡፡ ያረጁ ዶሴዎችን ከየሥርቻው እያወጣች ስለ ‹‹ታሪካዊ የመጠቀም›› መብትና ‹‹ሥጋት›› አታነብንብ፡፡ ከተፋሰሱ አገሮችም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በዚህ መንገድ ትቃኝ፡፡ ይህም በየተገኘው አጋጣሚ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ይነገራት፡፡

በተለይ በኢትዮጵያና በግብፅ ግንኙነት በታሪክ ውስጥ የሠፈሩ አሳዛኝ ክስተቶች ይታወሳሉ፡፡ ግብፅ በቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ዘመንም ሆነ ከዚያም በፊት፣ እንዲሁም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ደባዎችን ፈጽማለች፡፡ ኢትዮጵያ ለታላቁ የዓባይ ወንዝ 87 በመቶ ውኃ የምታበረክት አገር ሆና እያለ በጠላትነት ስሜት በርካታ ደባዎችን ፈጽማባታለች፡፡ በጦር ኃይል ለመውረር በመሞከር፣ በማስፈራራት፣ በዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማትና አገሮች ዘንድ ብድር የማስከልከል ዘመቻ በማድረግ፣ ሽምቅ ተዋጊዎችን አሠልጥኖ በማስታጠቅና በማሰማራት፣ ወዘተ በርካታ ደባዎችን ፈጽማለች፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አንድም ቀን የዓባይ ወንዝ ውኃ አልተቋረጠባትም፡፡

ፕሬዚዳንት አልሲሲ አሁን ‹‹አዲስ ምዕራፍ›› ተከፍቷል ቢሉም፣ ኢትዮጵያ የመልማት መብት እንዳላት አገራቸው ብታምንም፣ አሁንም ‹‹ሥጋት›› እንዳለ በውስጠ ወይራ ተናግረዋል፡፡ አለመተማመንን እንቅበር እያሉ አሁንም ‹‹ታኮ›› ማስቀመጥ ሲፈልጉ፣ ከድሮው አስተሳሰብ በፍፁም ተላቀዋል ብሎ ማመን አይቻልም፡፡ ይህም ይታሰብበት፡፡

በካርቱም የተደረሰበት ስምምነት በጋራ የመጠቀም ፍትሐዊና ምክንያታዊ መርህን እንዲያስከብር የማድረግ ትልቁ ኃላፊነት አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ የላይኛውን የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ለ13 ዓመታት በማስተባበር የግንባር ቀደምትነት ሚናዋን የተወጣችው ኢትዮጵያ፣ አሁንም ከግብፅ ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶችና ድርድሮች ሁሌም ነቃና ጠንከር ማለት አለባት፡፡ ግብፅ በምንም ዓይነት ሁኔታ ‹‹ታሪካዊ የመጠቀም መብት›› የምትለውን ጫና በማቆም ለትብብር ራሷን በፈቃደኝነት እንድታቀርብ መወትወት አለባት፡፡ ኢትዮጵያም በምንም ዓይነት ሁኔታ እንደማትጎዳት ያለመሰልቸት ታረጋግጥላት፡፡ በዚህ መሠረትም ያረጁት ፋይሎች ተቀደው ይቀበሩ፡፡

ኢትዮጵያ በትብብር ማዕቀፉ ስምምነት መሠረት አካባቢውን የማስተባበር ሚናዋን ስትወጣ፣ ግብፅ ይህንን ሚና ለመቀማት ጥረት አታደርግም ማለትም የዋህነት ነው፡፡ የውስጥ ትርምሷና በመካከለኛው ምሥራቅ የተነሳው የጽንፈኛው አይኤስ ችግሮች አላላውስ ብለዋት ነው እንጂ፣ ግብፅ የኢትዮጵያን የተፋሰሱ አገሮች የመሪነት ሚና እንደማያስደስታት በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ የግብፅ አክራሪ ምሁራንና ፖለቲከኞች፣ እንዲሁም ጽንፈኛ ሚዲያዎች የሚያራግቡዋቸው ፕሮፓጋንዳዎች ይህንን ድብቅ አጀንዳ ያሳያሉ፡፡ ይህንን ድብቅ አጀንዳ ለማወቅ ደግሞ ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ መንግሥት በተፋሰሱ አገሮች ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ያስከብር፡፡

ግብፃውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከዓባይ ውኃ በፍትሐዊና በምክንያታዊ መርህ እንዲጠቀሙ ይደረግ፡፡ አለመተማመን ይወገድ፡፡ ውጥረት ይርገብ፡፡ አሻጥሮችና መሰሪ ተግባራት ከሥራቸው ይነቀሉ፡፡ በካርቱም የተፈረመው የሦስቱ አገሮች ስምምነት የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ያከበረ ይሁን፡፡ ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ዕድገት፣ ብልፅግናና ሰላም ሲባል ግን ዘመን ያለፈባቸው ኢፍትሐዊ ስምምነቶች ቀብራቸው ይፈጸም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...