Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የመርህ መገለጫ ስምምነቱ የግብፅን በዓባይ ላይ የቆየ የበላይነት ያስቀረ ነው›› ዶ/ር...

‹‹የመርህ መገለጫ ስምምነቱ የግብፅን በዓባይ ላይ የቆየ የበላይነት ያስቀረ ነው›› ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

ቀን:

ኢትዮጵያ እስከ ሳዑዲ ዓረቢያ ድረስ ኃይል ለማቅረብ እየሠራች ነው

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተፈራረሙት የመርህ መገለጫ ስምምነት ግብፅ በዓባይ ላይ የነበራትን የቆየ የበላይነት የቀየረ መሆኑን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምና  ሌሎች የፖለቲካ ምሁራን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ግድቡ የተጀመረበትን አራተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብና የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን የምሁራን ሲምፖዚየም››ን መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ ሲምፖዚየሙ የተዘጋጀው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሚኒስትሩ 40 ደቂቃ በፈጀ ንግግራቸው ሦስቱ አገሮች እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ የቻሉበትን ሒደት አብራርተዋል፡፡

ግብፆች በተደጋጋሚ የግድቡ ግንባታ እንዲቆም፣ ርዝማኔው እንዲቀንስ፣ የሚያከማቸው የውኃ መጠን ከ74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ እንዲቀንስና ሌሎችንም መከራከሪያ ነጥቦቻቸውን እያነሱ፣ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴውንና የቴክኒክ ድርድሩን እየረበሹ በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህንን ለማስቀረት ለየት ወዳለ ድርድር መግባት እንዳለባት መታመኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በየካቲት ወር 2007 ዓ.ም. ውስጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብዣ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በሒልተን ሆቴል አዋሽ አዳራሽ በዝግ ድርድር መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት ግን ውጤት ማግኘት ከተፈለገ ቀድሞ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በዚህኛው ድርድር እንዳይነሱ፣ ጋዜጠኞች እንዳይገቡ፣ በአጠቃላይ ድርድሩ ከዜሮ እንዲጀመር በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ድርድሩ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹በመሆኑም በዓለም አቀፍ መርህ ላይ ተመሥርተን እንደ አዲስ እንነጋገር በሚል ሐሳብ ላይ ተስማምተን ሦስቱም አገሮች የየራሳቸውን መደራደሪያ እንዲያመጡ በተስማማነው መሠረት የቀረቡት መደራደሪያ ነጥቦች በአብዛኛው ተመሳሳይ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ድርድር 65 በመቶውን በመግባባት፣ ቀሪውን ደግሞ  ከባድ የሚባለውን ሱዳን ውስጥ መጨረሳቸውን ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡

በስምምነቱ የተሸነፈ አካል እንዳልነበርና ሁሉም አሸናፊ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ግብፆች ድሮ ከሚያንፀባርቁት አቋም ብዙ ርቀው በመምጣታቸው ተሸንፈዋል ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የመርህ መገለጫ ስምምነቱ የህዳሴው ግድብ በዋናነት ለኃይል ማመንጫ፣  ለኢኮኖሚ ልማትና ለአካባቢያዊ የኃይል አቅርቦት ትስስር እንደሚውል በሚገልጸው አንቀጽ ሁለት ውስጥ ለግብርና የሚል ባለመኖሩ፣ ኢትዮጵያ ግድቡ የሚይዘውን ውኃ ለመስኖ ልማት ላለመጠቀም ተስማማች በሚል የሚቀርበው ሐሳብ የተሳሳተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ግድቡ በዋናነት የሚውለው ለኃይል ማመንጫ ቢሆንም፣ ሌሎች አገልግሎቶችንም ይጨምራል ያሉት ሚኒስትሩ ግድቡ በዋናነት በኢትዮጵያ በኩል የተገነባው ለኃይል ማመንጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ነገር ግን በስምምነቱ ላይ ኢትዮጵያ ለመስኖ አታውለውም የሚል እንደሌለ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹በማያነታርክ ነገር ላይ ከመነታረክ [አሁን ባለበት ሁኔታ] ብንቀበለው ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ለግብርና አንጠቀምም ብለን አልፈረምንም፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ስምምነቱ ግብፅ በዓባይ ፖለቲካ ላይ ለማስጠበቅ የምትፈልገውን የበላይነት የቀየረ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹አሁን መንገዱን አውቀዋል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የመነጋገር ጥቅም የገባቸው ግብፃውያን ጥቂት ቢሆኑም ይህንን አመለካከት በማንፀባረቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂው የውኃ ፖለቲካ (ኃይድሮ ፖለቲክስ) ምሁርና በድርድሩ ተሳታፊ በመሆን ሙያዊ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ፣ ‹‹ታላቁ ህዳሴ ግድብ ናይልን በፍትሐዊነትና በዘላቂነት ለመጠቀም ያበረከተው አስተዋጽኦ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ የግብፅ የበላይነት እየተቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ምሁርና ተመራማሪ በዓባይ ፖለቲካ ላይ መጽሐፍ ያሳተሙት ዶ/ር ተስፋዬ ታፈሠ  ‹‹በዓባይ ተፋሰስ የፖለቲካ ተለዋጭነት›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ ለረዥም ዘመናት የቆየው የሌሎች አገሮች ‹‹የበይ ተመልካችነት›› እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል የህዳሴው ግድብ መጀመር፣ የሱዳን አቋም መቀየር፣ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች አንድ መሆን የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ ጥናት ያቀረቡት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚና በአሁኑ ወቅት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ምሕረት ደበበ፣ ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከኃይል ፍላጐትና ልማት አንፃር›› በሚል ባቀረቡት ጽሑፍ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል አቅርቦት ኔትወርክ ትስስር ውስጥ የህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጫ ተቀባይነት ያለው ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቷን እስከ ሊቢያ ድረስ መሸጥ የሚያስችላት ዕድል የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲና በየመን መንግሥታት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ደግሞ ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቷን እስከ ሳዑዲ ዓረቢያ ድረስ ለመሸጥ እንደሚያስችላት አቶ ምሕረት አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱን መስመር ለማስያዝ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት በየመን ቀውስ መፈጠሩን ገልጸው፣ ፕሮጀክቱ ግን ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...