Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሆቴሎች ደረጃ ለመስጠት የምዘና ሥራ ሊጀመር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በአገሪቱ ለሚገኙ ሆቴሎች በአዘጋጀው መሥፈርት በመለካት፣ የኮከብ ደረጃ ለመስጠት የግምገማና ምዘና ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቱሪዝም ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ እንዳይላሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱን ሆቴሎች የሚመጥናቸውን የኮከብ ደረጃ ለመለካት በተመድ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በቅርቡ በፀደቀው በመሥፈርት መሠረት ሚያዝያ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡

ለሆቴሎች ደረጃ የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ በተለያዩ ጊዜያት ደረጃ ለማውጣት እየሞከረ ከሽፎበታል፡፡ ባለፈው ዓመት ይህን ሥራ ለዓለም ቱሪዝም ድርጅት መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፣ አሰጣጡ የዘገየበት ምክንያት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጨረታዎች አፈጻጸም ምክንያት ነው፡፡ የጨረታ ሒደቱ ሁሉ አልቆ ደረጃ የማውጣቱ ሥራ ለዓለም ቱሪዝም ድርጅት መሰጠቱን ያስታወሱት አቶ ታደሰ፣ በዚህ ድርጅት መሥፈርት መሠረት አገር በቀሎቹም ሆነ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ይገዛሉ ብለዋል፡፡

በመላው አገሪቱ የሚገኙ 600 ሆቴሎች እንደሚያሟሏቸው መሥፈርቶችና እንደ አገልግሎት ብቃታቸው ተመዝነው በሚያገኙት ውጤት መሠረት፣ ደረጃዎቻቸውን እንደሚያገኙ ይጠበቃል ሲሉ አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት በአዲስ አበባ የሚገኙ 400 ሆቴሎችን እስከ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ባሉት 45 ቀናት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ታደሰ፣ በክልል ከተሞች የሚገኙት 200 ሆቴሎች ደግሞ በሚኒስቴሩና በክልል ቢሮዎች በጋራ እንደሚከናወን ጨምረው አስረድተዋል።

ለሆቴሎቹ የደረጃ ምደባ መሥፈርቶችን የመገምገም ሥራ ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ተገቢውን ሥልጠና በአሁን ወቅት እየተሰጠ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ታደሰ፣ የሁሉም ሆቴሎች የግምገማና  የምዘና ውጤት ሙሉ በሙሉ ተሰብስቦ  ሳያልቅ የየትኛውም ሆቴል ደረጃ ይፋ እንደማይደረግ አስታውቀዋል።

ከወራት በፊት  ሚኒስቴሩ ከሆቴል ባለቤቶችና ከመስተንግዶ ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሆቴሎች ደረጃ መለኪያና የመመዘኛ መሥፈርቶችን አስመልክቶ፣ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ፣ ለሆቴሎች ደረጃ መስጠት ያስፈለገው ለተጠቃሚዎች ሆቴሎች ያሟላቸውን አስፈላጊ ግብዓቶችና የሚሰጡትን አገልግሎት በተመለከተ ግልጽ ምሥል ለመስጠት ነው፡፡ በተጨማሪም በዘልማድ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሰጠውን ደረጃ በተሻለ መሥፈርት መዝኖ ለመስጠት ታስቦ መሆኑን ተናግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሆቴሎችን የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርት የሚያትተው መረጃ እንደሚገልጸው፣ እያንዳንዱ ሆቴል ለደረጃ ምደባው ብቁ መሆን የሚችለው ቢያንስ እስከ አሥር የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፣ የጤና ጥበቃ አስፈላጊ ሕጎችንና ደንቦችን ሲያከብር፣ ከእሳት አደጋ አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ ሲሆን፣ አካባቢያዊ መሥፈርቶችን፣ የቆሻሻ አወጋገድና ሌሎች አስፈላጊ ሰነዶች ማሟላት ሲችል እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሆቴሉ ያሉት የተማረ ሰው ኃይልና በሥልጠናና በክህሎት መሥፈርቱ ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች ናቸው።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሁሉም ሆቴሎች ለራሳቸው በሰጡት ደረጃ ሲተዳደሩ የቆዩ ሲሆን፣ ይህም የተለያዩ ችግሮችን ሲፈጥር መቆየቱን የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ሲገልጹ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በገጽታ ግንባታ በኩል የራሱ የሆነ እክል ሊፈጥር እንደሚችል መረዳት እንደሚገባ የሚገልጹም አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በብራንድ ሆቴልነት የሚተዳደሩት ሸራተን አዲስ፣ ሒልተንና ራዲሰን ብሉ ሆቴሎች ብቻ ናቸው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች