Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የአገርን የዕለት ሁኔታ በግልጽ ያስረዳ!

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ፣ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ የማስረዳት ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ በፓርላማ በዓመቱ የሥራ መጀመሪያ ወቅት፣ በዓመቱ አጋማሽና መጨረሻ የመንግሥትን የሥራ ዕቅድና አፈጻጸም የማስረዳት ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ በተወሰኑ ወቅቶች ደግሞ ከአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ጋር ተገናኝተው ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አለባቸው፡፡ ከዚያ በተረፈ ሕዝቡ የአገሪቱን የዕለት ሁኔታ በግልጽ ማወቅ ሲኖርበት፣ መንግሥትም የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡

በሕዝብ የተመረጥኩ መንግሥት ነኝ የሚል አካል ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ስላለበት ስለአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ለሕዝብ ማስረዳት አለበት፡፡ ይኼ በአገራችን በተግባር እየታየ ነው ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ አይደለም ነው፡፡ በተወሰኑ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም በየደረጃው ያሉ ሹማምንት መግለጫ ቢሰጡም፣ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡ በርካታ ጥያቄ የሚነሳባቸው ጉዳዮች ምላሽ ባለማግኘታቸው እንቆቅልሾች በዝተዋል፡፡ መንግሥት የአገርን የዕለት ሁኔታ በግልጽ ማስረዳት ሲያቅተው ምላሽ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ በቴሌቪዥን ታይተዋል፡፡ በዚያ መግለጫ ላይ የተገኙት ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡ የተነሱት ጥያቄዎች ደግሞ የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በጥንካሬ የሚዳስሱ አልነበሩም፡፡ በሌላ አባባል ጥንካሬ አልነበራቸውም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የግሉ ፕሬስ እንዳይገኝ በመደረጉ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄ ባክነው ቀርተዋል፡፡ የአገሪቱን ክራሞትና የዕለት ሁኔታ የማስረዳት ኃላፊነት ያለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩም መመለስ የነበረባቸውን ጥያቄዎች እንደ ዋዛ ሲያልፉዋቸው ታዝበናል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መነሳት ከነበረባቸው ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ቢነሱ ኖሮ የምንነጋገርበትን አጀንዳ ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል የተደረገው የሦስትዮሽ ስምምነት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ ስምምነት እ.ኤ.አ በ2010 በአብዛኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ከተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ጋር ይጣረሳል? ወይስ ስምምነቱን ያጠናክራል? ይህ ስምምነት በተጨባጭ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ጥቅም ምንድነው? የካርቱሙ ስምምነት ለኢትዮጵያ ወጥመድ እንዳይሆን ምን መላ ተበጅቷል? የአገሪቱ የመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተገባዶ ሁለተኛውን ዕቅድ ለማዘጋጀት ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡ የመጀመሪያው ዕቅድ ያጋጠሙት ፈተናዎች ምን ነበሩ? ስኬቱስ በምን ይለካል? በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ፈታኝ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንዴት ለመቋቋም ዝግጅት ተደርጓል? ከተገኘው ትምህርት ምን ተቀስሟል? በሰው ኃይል ሥምሪት፣ በበጀት አመዳደብና በተቋማት ደረጃስ ብክነት ነበር? ምን የተወሰደ ዕርምጃ አለ?

በሌላ በኩል ዜጎች በመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት አሁንም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በእርግጥ መንግሥት ብቻ ቤቶችን እየገነባ ይህንን ግዙፍ ችግር ለመፍታት ይችላል? ችግሩን በጥልቀት በማጤን ምን የተዘየደ መላ አለ? የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ ኃይልን በተመለከተ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የአጭርና የሩቅ ጊዜ ዕቅድ እንዳለ ሆኖ፣ በየቀኑ ለሚያነጋግሩ ችግሮች መፍትሔው የታለ? የመልካም አስተዳደር እጦት ተግዳሮቶች ከዲስኩር ባለፈ እንዴት ነው መፈታት ያለባቸው? ከችግሩ ፅናት የተነሳ ሕዝብ አቤት የሚልባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ መንግሥት በተጨባጭ ምን እያደረገ ነው? መንግሥት ከሚኩራራባቸው ስኬቶች በላይ በርካታ ችግሮች ስላሉ ምን እየተደረገ ነው?

ሕዝብ ከዕለት ተዕለት ኑሮው ጋር የሚገናኙ ወይም ተፅዕኖ የሚያሳድሩበት ጉዳዮችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ የትራንስፖርት እጥረት አንዱ ነው፡፡ ቀላል የባቡር አገልግሎቱን በፍጥነት ለማስጀመር የተያዘው ዕቅድ መቼ ነው ተግባራዊ የሚሆነው? ሕዝቡ በፀሐይና በውርጭ በየቀኑ እየተጉላላ ነው፡፡ በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት የሚባክነው ጊዜ ሥራ እየጎዳ ከመሆኑም በላይ፣ አገልግሎት ፈላጊዎችንም እያንገላታ ነው፡፡ መኖሪያ ቤት በዕጣ የደረሳቸው ሰዎች የአከፋፈሉ ሁኔታና የዋጋ ጭማሪው እያሳሰባቸው ነው፡፡ በመልሶ ማልማት ከነባር አካባቢዎች የሚነሱ ዜጎች በቂ ካሳ ካለማግኘታቸውም በላይ፣ በመልካም አስተዳደር ጉድለት መጉላላታቸው በየጊዜው ይነገራል፡፡ ሰሚ ግን የለም፡፡ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ምላሽ ሰጪ አካል ባለመኖሩ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡

እነዚህ ከላይ የተነሱት ጥያቄዎች በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚነሱ በመሆናቸው፣ መንግሥት የማብራራትና ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ የሕዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለሚመለከተው መንግሥት የማስተላለፍ ኃላፊነት ያለባቸው ሚዲያዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳይገኙ ሲደረግ፣ የመንግሥት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ምን ድረስ ነው ያስብላል? በየተገኘው መድረክ ሁሉ የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ጥያቄዎች መገፋት የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ጥያቄዎቹ ገፍተው በወጡ ቁጥር መፍትሔ መፈለጉ ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ከሚለካባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል፣ መረጃን በምልዓት የማግኘት መብት አንዱ ነው፡፡

መንግሥት የአገሪቱን የዕለት ሁኔታ ለሕዝቡ በግልጽ ማስረዳት አለበት ሲባል፣ በአገሪቱ ውስጥ እየሠሩ ያሉ ሚዲያዎች በሙሉ መገኘት አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ በአገሪቱ ድንገተኛ ክስተቶች ሲያጋጥሙ መረጃ ለማግኘት ጥረት ሲደረግ፣ ከአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ይልቅ የውጭ ሚዲያዎች ላይ ማብራሪያ ይሰጥና ከእነሱ ተጠቀሙ ይባላል፡፡ ይኼ አድሎአዊ ከመሆኑም በላይ ያሳፍራል፡፡ አስፈጻሚውን አካል የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግብፅ ፕሬዚዳንት አገሪቱን በጎበኙ ማግሥት፣ በኤርትራ ላይ በጦር አውሮፕላኖች ጥቃት ተፈጸመ በተባለ ሰሞን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የግል መገናኛ ብዙኃን ለምን ይገለላሉ? ለምሳሌ በሁለቱ ጉዳዮች ላይ ሞጋች ጥያቄዎች መቅረብ ሲገባቸው እንደ ዘበት ምላሽ ተሰጥቶባቸው ታልፏል፡፡ ለምን? ማንን እንዲጠቅም?

 እየተገባደደ ባለው ዓመት አገሪቱ ለአምስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ምርጫ ታካሂድበታለች፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይጠናቀቃል፡፡ በሌሎች አገራዊና የውጭ ጉዳይ ተግባራት ላይ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሕዝቡ የአገሪቱን ውሎና አዳር በተመለከተ ከመንግሥት ሪፖርት ይጠብቃል፡፡ ይህ ሪፖርት ደግሞ ተሟልቶ የሚቀርበው ሞጋች የሆነ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ ተጠሪነትና ኃላፊነት አለብኝ ብሎ አፉን መናገር የሚችለው፣ ለሕዝቡ የአገሪቱን የዕለት ሁኔታ በግልጽ ማስረዳት ሲችል ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...