Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየድሮ ሙዚቃ አልበሞች

የድሮ ሙዚቃ አልበሞች

ቀን:

ቆየት ያሉ፣ አዳዲስ አልበሞችንም ተከታትሎ ይገዛል፡፡ የድሮ ሙዚቃዎችን ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ቢያውቅም፣ ገበያ ላይ ከዋለ አሥር ዓመት እንኳን ያልሞላው አልበም ማጣቱ ግን አስገርሞታል፡፡ ወንድወሰን ሀብቴ እንደሚለው፣ ከቀናት በፊት የጃሉድን አልበም ለመግዛት ፈልጎ ወደ ሙዚቃ ቤቶች ጎራ ቢልም አለማግኘቱን ይናገራል፡፡ አልበሙን ለቀናት ካፈላለገ በኋላ ማግኘቱን ከዚህ በመነሳትም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሙዚቃውን መስማት የሚሹ ሰዎች ምን ያህል ሊቸገሩ እንደሚችሉ ግምቱን ይገልጻል፡፡

በተለይ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን ስለሚወድ ባገኘው አጋጣሚ ያሰባስባል፡፡ አሁን ያለውን ሙዚቃ ለማሰባሰብ የወሰደበት ጊዜና ያደረገው ጥረት ቀላል አልነበረም፡፡ ፈልጎ ያላገኛቸው ሥራዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይሰማቸው የነበሩ እንዲሁም አሁን በሸገር ኤፍኤም 102.1 የሚያዳምጣቸው የጥንት ዘፈኖች ገበያ ላይ ለማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል፡፡ ‹‹የቆዩ ሙዚቃዎችን ለማግኘት አለመቻሉ አድማጩን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጡ ሥራዎች ብቻ ይወስነዋል፤›› የሚለው ወንድወሰን፣ የቀድሞ ሥራዎች በቀላሉ የሚገኙበት መንገድ እንዲኖር ይመኛል፡፡ ተመሳሳይ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች፣ በይበልጥ በሸክላ የተዘጋጁ አልበሞችና አንዳንዴም የካሴት ሥራዎችን ለማግኝት እንደተቸገሩ ያስረዳሉ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች መንስኤው የቀደሙትን የሙዚቃ አልበሞች ለገበያ ያቀረቡ አሳታሚዎች ዛሬ ላይ ከገበያው መውጣታቸው ነው ይላሉ፡፡ ወንድወሰን እንደ ሙዚቃ አፍቃሪነቱ እነዚህን ሥራዎች መገኘት ፈላጊውን ከማስደሰቱ ባሻገር፣ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻግረው እንዲደመጡ ያስችላሉ ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ ቀደምት ሥራዎችን በተለያየ መንገድ ማግኘት ቢቻልም የጥራት ደረጃቸው የወረደ ነው ይላሉ፡፡ ዘመን አመጣሽ መሣሪያዎችን በመጠቀም ሥራዎቹ መስተካከል እንዳለባቸው፤ ይህ መሆን የሚችለው የሙዚቃው ባለቤቶች ሕጋዊ ፈቃድ ሰጥተው ሥራዎቹ በድጋሚ ሲታተሙ በመሆኑ፣ የባለቤቶቹ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኃላፊነቱን ወስዶ በድጋሚ የሚያሳትም አካል በማጣት ተረስተው የቀሩ ሥራዎች አሉ፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ማኅበሩ በአንድ ወቅት የቆዩ ሙዚቃዎችን የማሰባሰብ ጥረት ቢጀምርም የባለቤትነት መብት ስለሌለው እንዳልገፉበት ያስረዳሉ፡፡ ቀደምት ሥራዎች በብዛት የሚገኝባቸው እንደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የመሰሉ ድርጅቶች ስብስቦችን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ አዳዲስ ሥራዎች ብቻ መድረኩን እየተቆጣጠሩ እንዳሉ በማስገንዘብ፣ የክብር ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊትና ሌሎችም ሥራዎች ለዓይነት መቅረብ አለባቸው ይላሉ፡፡ ከተቋሞች በተጨማሪ አንዳንድ ሰፊ ስብስብ ያላቸው ግለሰቦች ሥራዎቹ የሚጋሩበት ሕጋዊ መዋቅር መኖር እንዳለበት ያምናሉ፡፡ በቆዩ ሙዚቃዎች ስብስቡ ተጠቃሽ የነበረው ማራቶን ሙዚቃ ቤት በኮፒ ራይት ችግር ሳቢያ መዘጋቱን እንደምሳሌ የሚጠቅሱት ሙዚቀኛው ዳዊት፣ አንጋፋ ሙዚቃ ቤቶች ከገበያ ሲወጡ ስብስባቸው በሥራ ላይ ላለ ሰው ቢተላለፍ መልካም ነው ይላሉ፡፡ በጥንት ሥራዎች ሽያጭ ታዋቂ የሆኑ አምባሳል፣ ኤሌክትራ፣ ሱፐር ሶኒክ፣ ዋልያ፣ ኢትዮ ሳውንድና ሌሎችም ሙዚቃ ቤቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ሙዚቃ ቤቶች አዳዲስ የሙዚቃ አልበሞች የሚያስገኙትን ትርፍ ከግምት በማስገባት በነሱ ላይ ቢያተኩሩም፣ ‹‹በአገሪቱ የሙዚቃ ታሪክ ተጠቃሽና የብዙዎችን ትዝታ የሚጠቃቅሱ ሥራዎችም ታሳቢ መሆን አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡ ብዙዎች የሚጠቅሱት የኢትዮጲክስ ተከታታይ ስብስብ ሥራዎችን ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቆየት ያሉ ሥራዎች መቅረብ እንዳለባቸው የሚናገሩ አሉ፡፡ ዘመን በዘመን ሲተካ በየወቅቱ ያለውን ቴክኖሎጂ በመከተል ሙዚቃዎች መቅረብ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ጉዳዩ ከቅጂና ተዛማጅ መብቶች አንፃር መታየት እንዳለበት የሚናገሩት የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ኃይላይ ታደሰ ናቸው፡፡

ሙዚቃዎች ሕጋዊ አካሄዱን ጠብቆ በድረ ገጽ ቢገኙ የተሻለ አማራጭ ይሆናል ይላሉ፡፡ አልበሞች ለገበያ የሚቀርቡበት ባዛርና ዐውደ ርዕይ ማዘጋጀት ሌላው መፍትሔ ነው፡ በቅርቡ የፀደቀው የቅጂና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ 872 የጋራ አስተዳደር ማኅበር በሚል፣ የሙዚቃ ባለቤቶችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ቀደምት ሥራዎች እንዲታተሙ ይፈቅዳል፡፡ አዋጁ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸው፣ ‹‹ባለሙያዎች ተገቢውን ጥቅም እያገኙ ሥራዎቻቸው ለሕዝብ መድረስ አለባቸው፤ ሥራዎቻቸው ቅርስ ስለሆኑ መረሳት የለባቸውም፤ ሕዝቡም ሙዚቃዎቹን የማግኘት መብቱ መጠበቅ አለበት፤›› ይላሉ፡፡

በሙዚቃ ሽያጭ የተሰማሩ ግለሰቦች አስፈላጊው ማበረታቻ ተደርጎላቸው በገበያው እንዲቆዩ ማገዝ ይቻላል፡፡ ከእግዛ ባሻገር አልበሞች በየክፍለ አገሩ በስፋት የሚዳረሱበት መንገድ መስተካከል አለበት ይላሉ ሥራ አስኪያጁ፡፡ ዛሬ ዛሬ አዳዲስ አልበሞች ከተለቀቁ ከጥቂት ወራት በኋላ ገበያ ላይ አለመገኘታቸው አሳሳቢ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የቀደሙት ሥራዎችም ይሁን የአሁኑ እንደልብ አለመኖራቸው ሙዚቃው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች በሸክላ ያሉ የሙዚቃ አልበሞችን ያሰባስባሉ፡፡ በጋዜጣ፣ በታክሲ እንዲሁም በማስታወቂያ መለጠፊያ ቦርዶች ስልክ ቁጥራቸውን በማስፈር የሸክላ ሙዚቃዎችን እንደሚገዙ ያስታውቃሉ፡፡ የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ፈቃዱ ዋሪ እንደሚሉት፣ በሸክላ ያሉ ሙዚቃዎችን ዘመናዊ በሚል መንገድ ለገበያ ማቅረብ በሙዚቃ ቤት ደረጃ አይቻልም፡፡ ሙዚቃ ቤቶች እነዚህን ሥራዎች የማከፋፈል መብት ባይኖራቸውም፣ ቢያንስ የካሴት ሥራዎች መቅረብ ይችላሉ፡፡

በአምባሰል ሙዚቃ ቤት ከ1970ዎቹ ወዲህ የታተሙ አልበሞች እንደሚገኙ ይናገራለ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በካሴትና ከዛ በኋላም በሲዲ የታተሙ አልበሞችን ለማግኘት አያዳግትም፡፡ አልበሞቹ አከፋፋዮች ጋር ባይኖሩ አሳታሚዎች ጋር በቀላሉ እንደሚገኙ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ፈቃዱ አንዳንድ አሳታሚዎች ዘርፉን ጥለው በሚወጡበት ወቅት በሙያው ላሉ ሌሎች ግለሰቦች ስብስባቸውን የሰጡበት አጋጣሚ እንዳለ ያስታውሳሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርነው ድምፃዊ አረጋኸኝ ወራሽ ያወጣቸው 11 አልበሞቹ በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ይገኛሉ፡፡ የአልበሞቹ አሳታሚ በሆነው ሙዚቃ ቤቱ ሥራዎቹ ቢገኙም፣ የበርካታ አሳታሚዎች ከዘርፉ መውጣት ብዙ ሥራዎቹን ከገበያ አጥፍቷል ይላል፡፡ ድምፃዊው እንደ መፍትሔ የሚያቀርበው ሐሳብ በሕይወት ያሉ ዘፋኞች ሥራዎቻቸውን ዳግም እንዲያቀርቡ ነው፡፡ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ነዋይ ደበበ፣ ፀጋዬ እሸቱና ሌሎችም ድምፃውያንን በመጥቀስ ከቀደሙ ሥራዎች ተወዳጅ የነበሩት በድጋሚ ቢቀርቡ መልካም ነው ይላል፡፡ እሱ ከድሮ ሥራዎቹ መካከል መርጦ በድጋሚ በሁለት ሲዲ አሳትሞ ለገበያ የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡ ድምፃውያን ከማለፋቸው ወይም ዕድሜያቸው ከመግፋቱ በፊት ሥራዎቻቸውን ዘመን ባመጣው ቴክኖሎጂ እንዲያቀርቡ የሚያሳስበው አረጋኸኝ ‹‹በሕይወት እያለን ካልሠራነው ነገ ከየትም አይመጣም፤›› በማለት አሻራቸውን የማኖር ኃላፊነት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ በተለይ ወጣቶች ባለሙያዎች የሚያደንቋቸው አንጋፋ ድምፃውያንን ሥራዎችን የሚያገኙበትን መንገድ እንደሚያሰፋው ያምናል፡፡

የንጋቷ ከልካይ፣ የሽሽግ ቸኮል፣ ፈረደ ጎላና ዘለቀ ጌታሁን የሸክላ ሥራዎች ዶ/ር ተስፋዬ አበበ ለማግኘት ከማይቻሉ የሙዚቃ አልበሞች መካከል ይጠቅሷቸዋል፡፡ እሳቸው በፖሊስ ሠራዊት ሙዚቃ የድርሰትና ዝግጅት ኃላፊ በነበሩበት ወቅት በካሴት የታተሙ የዓለማየሁ እሸቴ፣ ሒሩት በቀለ፣ ሙሉቀን መለሰና ሌሎችም በርካታ ድምፃውያን ሥራዎች በቀላሉ የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ካለባቸው ተቋሞች ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው ይላሉ፡፡

‹‹ያለፈው ዘመን ሥራዎች በዚህ ትውልድ በኪነ ጥበብ ላሉ ወጣቶች መማሪያ ናቸው፤›› በማለት የአልበሞች አቅርቦትና ሥርጭት ያለውን አስተዋጽኦ ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንያንዳንዳቸው የግል ሥራዎቻቸውን ቢያስቀምጡም በትዝታ ወደኋላ የሚመልሷቸውን የሌሎች አርቲስቶች ሥራዎችም በቀላሉ ማግኘት ይሻሉ፡፡ ለረዥም ዓመታት የሠሩ መገናኛ ብዙኃን በሙዚቃ ክምችታቸው ይታወቃሉ፡፡ የሙዚቃዎቹ ተደራሽነት ላይ ጥያቄ ያላቸው ግለሰቦች ቢኖሩም፣ የጣቢያው ክምችት የእሱን ለመሰሉ መርሐ ግብሮች አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር የሚናገረው ይናገር ጌታቸው ነው፡፡ በኤፍኤም አዲስ 97.1 ላይ የሚደመጠው የትዝታን በዜማ አዘጋጅ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ከ1970ዎቹ በፊት ያሉ ሙዚቃዎች ላይ ያተኩራል፡፡ እሱ በጣቢያው የድምፅ ክምችት ክፍል አግኝቷቸው የሚያስደምጣቸው ሙዚቃዎች ሌላ ቦታ ለማግኘት እንደሚከብድ ይገልጻል፡፡

ቀደምት ሥራዎች ያሏቸው ተቋሞች የባለቤቶቹን መብት በማይጋፋ መልኩ የሚያቀርቡበት መንገድ ቢመቻች ያለውን ጠቀሜታ ያስረዳል፡፡ ሙዚቃዎቹ የአገሪቱን የሙዚቃ ታሪክ የሚያንፀባርቁና በየተሠሩበት ዘመን የነበረውን የአገሪቱን ገጽታም የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ተደራሽነታቸው ሲሰፋ በትውልዶች መካከል ቅርርብ ይፈጥራሉ ይላል፡፡ የየዘመኑ ሙዚቀኞች የነበራቸው አስተዋጽኦ እንዲታወቅ ከማድረግ በተጨማሪ ለጥናትና ምርምር አጋዥም ይሆናል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ አንዳንድ ድጎማ የሚያስፈልጋቸው ድምፃውያን የቀደሙት ሥራዎቸው ለገበያ ቢቀርቡ ገንዘብ ማግኛም ይሆናቸዋል፡፡ የሙዚቃዎቹ አለመገኘት የአንዳንድ ድምፃውያን የልጅ ልጆች እንኳን ቤተሰቦቻቸው በሙዚቃው ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዳይገነዘቡ ያደረገበት አጋጣሚ ማስተዋሉን ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዥዋል አሳታሚ ማኅበር እንዲሁም ቴአትር ቤቶች ተረባርበው አንዳች መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል የሚል ሐሳቡን አካፍሎናል፡፡

ወንድወሰን በማንኛውም ዘመን የተሠሩ ሥራዎች ከክምችት ባለፈ ለፍጆታ የሚውሉበት የሙዚቃ መሸጫ ወይም ተቋም ቢኖር ጥሩ ነው ይላል፡፡ የጥላሁን ገሠሠ፣ መሀሙድ አሕመድ፣ የአስናቀች ወርቁ፣ ግርማ በየነና አያሌው መስፍን ሥራዎችን ከስብስቦቹ መካከል ይጠቅሳል፡፡ እሱ ሊያገኛቸው ያልቻሉና ሌሎች አልበሞችን ብዙዎች ስለሚፈልጓቸው በቀላሉ ቢያገኙ ይመኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...