የየመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ ያሲን ከዓረቢያ ኒውስ ቻናል ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰደ፡፡ የሑቲ ሚሊሻዎች አገሪቱን ከተቆጣጠሩ በኋላ በተነሳው ግጭት ምክንያት ጦርነት ውስጥ የገባችውን የመን መሠረተ ልማቶችና ሕዝቡን ከውድመት ለመከላከል፣ የዓረብ አገሮች በእግረኛ ጦር ጣልቃ መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡ በኢራን ይደገፋሉ የተባሉትን የሑቲ ሚሊሻዎች ለመደምሰስ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራ የአየር ጥቃት ከተከፈተ ሳምንት የሞላው ሲሆን፣ የመንን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከትቷል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ሑቲዎችን በአየር ማጥቃቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች፡፡ የመን እስክትረጋጋም ይቀጥላል ብላለች፡፡ ‹‹ጦርነትን እየቀሰቀስን አይደለም፡፡ ነገር ግን ለጦርነት ዝግጁ ነን፤›› ስትልም በአንድ ባለሥልጣን አማካይነት ሳዑዲ ዓረቢያ አስታውቃለች፡፡ የየመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሁኑ ጊዜ በሳዑዲ ዓረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በጊዜያዊነት ሥራውን እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሪያድ ያሲን ናቸው፡፡