ድርጅቱ የተቋቋመው በተለይ ሴት ሕፃናት ጎዳና ተዳዳሪዎችን ካሉበት ሕይወት ለማላቀቅ ነው፡፡ ዓላማውን ለማስፈጸም በአራት ሥፍራዎች መጠለያ ያለው ቢሆንም ሥራውን በሚፈለገው ደረጃ ለመሥራት እክሎች አሉበት፡፡ ወ/ሮ ዝናሽ በዛብህ የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ሕፃናት መከላከያ፣ ተራድኦና ማቋቋሚያ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ሕፃናት መከላከያ ተራድኦ እና ማቋቋሚያ ማዕከል የተቋቋመበትን ዓላማ ቢያብራሩልን?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- ድርጅቱ እ.ኤ.አ. በ2000 የተቋቋመ ሲሆን፣ ከሕፃናት አድን ድርጅት ፕሮጀክቶች አንዱም ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ በጥናቶቹም ሴት ሕፃናት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ድርጅት ያስፈልጋል የሚልም ምክረ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ምክረ ሐሳቡን መሠረት አድርጎ ድርጅታችን ተቋቋመ፡፡ ከተቋቋመም በኋላ ብዙ ጊዜ ለምን ሴት ላይ ብቻ ትሠራላችሁ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በእርግጥም ድርጅቱ በተቋቋመበት ወቅት ያለው አስተሳሰብ የጥቃት ሰለባ ሴቶች ብቻ እንደሆኑ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ በሕፃን ወንዶች ላይም ተመሳሳይ ጥቃት እንደሚደርስ እያየን ነው፡፡ ይህንንም ከግምት በማስገባት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ፣ ራዕይና ተልዕኮ በምናሻሽልበት ጊዜ የወንድ ሕፃናትን ጉዳይ ለማካተት ሞክረን ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ መጀመሪያ በያዘው ዓላማ እንዲፀናና የጀመራቸውን ሥራዎች ቢቀጥል ይሻላል የሚል ሐሳብ በመነሳቱ እስካሁን በሴቶች ላይ ብቻ ለመሥራት ተገደናል፡፡ ይሁን እንጂ ወንዶች ልጆችን የማናገለግለው በመጠለያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከመጠለያ ውጪ የተለያዩ እገዛ የሚደረግላቸው ወንዶች አሉ፡፡ ከመከላከል እና ከልጆች እንክብካቤ ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞች አሉ፡፡ እነዚህም፣ በቤተሰብ ተኮር የሕፃናት እንክብካቤ፣ በትምህርት ቤት ተኮር ሕፃናት እንክብካቤ ጥበቃና በማኅበረሰብ ተኮር ሕፃናት እንክብካቤና ጥበቃ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ ዋና ዓላማቸውም ልጆች ጥቃት ደርሶባቸው ከመጡ ወዲያ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ ኅብረተሰቡን በማስተማር ልጆችም ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል ነው፡፡ በዚህ የመማሪያ መድረክ ላይም ሁሉም የኅብረተሰብ አካል ይካተታል፡፡ ይህም ከሴቶች ልጆች በተጨማሪ ወንዶችን ለመድረስ ይረዳል፡፡ የመማሪያ ቁሳቁሶችን የምናሟላላቸው ወንዶች ተማሪዎችም አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ሲቋቋም ምን ያህል ተረጂዎችን ይዞ ነበር? ዛሬ ላይ ያለውስ የተረጂዎች ቁጥር ምን ያህል ነው?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- በወቅቱ ሥራ ስንጀምር ሙሉ ለሙሉ መጠለያ ቦታ አልነበረም፡፡ ማቆያ ማዕከል ነበር ያለን፡፡ ልጆች ገብተው የተወሰነ አገልግሎት አግኝተው ይወጡ ነበር፡፡ በመጀመሪያም በአንድ ጊዜ 50 ልጆች የሚገለገሉበት ማቆያ ሥፍራ ፍልውኃ አካባቢ ነበረን፡፡ በማቆያ ሥፍራ ላይ መሥራት ግን ልጆቹ ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጉዳት እንዲያገግሙ አይረዳቸውም፡፡ 150 ለሚሆኑ ልጆች ባሉበት ሆነው ትምህርት እንዲማሩ የተለያየ ዕርዳታ እናደርግላቸውም ነበር፡፡ ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁስ እናቀርባለን፡፡ አሁን ላይ አገልግሎታችንን ሰፋ አድርገናል፡፡ በአራት አካባቢዎች ማለትም በሻሸመኔና ባህርዳር አንድ፣ አንድ፤ በአዲስ አበባ ሁለት የመጠለያ ጣቢያዎች በድምሩ አራት መጠለያ ጣቢያዎች አሉን፡፡ በአዲስ አበባ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጎዳና 22 ማዞሪያ ድንበሯ አካባቢ መጠለያዎቻችን ይገኛሉ፡፡ በአንድ ጊዜም እስከ 180 ልጆችን ይቀበላል፡፡ መጠለያ፣ ምግብ፣ የንፅህና አገልግሎት፣ አልባሳት ያገኛሉ፡፡ በዋናነትም ልጆቹ በሥነ ልቦና ታንፀው እንዲወጡ ትምህርትና ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ልጆቹ በመጠለያችሁ ውስጥ የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- ልጆቹ እኛ ጋር የሚቆዩት ከሦስት እስከ ስድስት ወር ነው፡፡ ሁሉም ሕፃናት የሕግ ጉዳያቸው ካለቀ በኋላ ወደ ቤተሰቦቻቸው ወይም ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል፡፡ በዚህም ጊዜ ከትምህርት እንዳይርቁ በሠለጠኑ መምህራን ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ማንበብ መፃፍ የማይችሉ ማንበብና ማፃፍ እንዲችሉ፣ በትምህርት ዓለም የነበሩ ደግሞ ከትምህርታቸው እንዳይርቁ ለማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም ዕድሜአቸው ተለቅ ያለና በተለያዩ ምክንያቶች መማር የማይችሉ ሲሆኑ፣ ሙያዊ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን የመቀጠል ከፍተኛ ጉጉት ሲያድርባቸው ሙያዊ ሥልጠና ያገኙትም እንዲሁ ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ፍላጎቱ ያድርባቸዋል፡፡ ሌላው ልጆቹን የሚያንፃቸው ደግሞ እርስ በርስ በሚኖራቸው መስተጋብር ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሮችን የሚፈቱበት፣ ችሎታቸውን የሚያጎለብቱበት አሠራር አለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራ ላይ የሚገጥሟችሁ አስቸጋሪ ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- መጠለያው ጊዜያዊ መጠለያ ነው፡፡ ማሳደጊያ ቦታ አይደለም፡፡ ልጆች የተወሰኑ ወራቶች ቆይተው ወደ ቤተሰብ አልያም ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል አለባቸው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ልጆች ከመጡበት ጉዳይ የተነሳ ቤተሰብ ጋር ላይቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርብ የቤተሰብ አባላት ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች ተመልሰው ወደ ቤተሰብ ለመቀላቀል ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ስለዚህም ሌሎች አማራጮች ይፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ አማራጮች አንዱ ፈቃደኛ የሆነ ሌላ የሥጋ ዘመድ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በቤተሰብ መካከል ቅራኔ ሊፈጠር ይችላል ብለው በመስጋት ዘመዶች ልጆቹን ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ እንደዚህ በሚሆንበት ጊዜ አማራጭ ቤተሰብ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እኛ አገር ብዙ አልተለመደም፡፡ አንዳንድ ፈቃደኛ ግለሰቦች ብናገኝም የልጆቹን ባህሪ ካለመረዳት አንፃር ከወሰዷቸው በኋላ መልሰው ያመጧቸዋል፡፡ ሌላው ልጆቹ የመጡበትን አካባቢም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ስም ይዘነጋሉ፡፡ ከቤተሰብ ለመቀላቀል በሚደረገው ሒደት በቅድሚያ ስለመጡበት አካባቢና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ጥናት የሚደረግ ቢሆንም፣ አካባቢውን ካላወቁት ሒደቱን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ አንዳንዴም ልጆቹ ከተማ ሲገቡ ስማቸውን ይቀይራሉ፡፡ እንዲህ በሚሆን ጊዜ እኛ የያዝነው ስም እና ከመጡበት አካባቢ የሚታወቁበት ስም ተመሳሳይ ስለማይሆን ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ይከብደናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከጥቂት ልጆች በስተቀር ብዙዎቹን ልጆች ከቤተሰብ ለማቀላቀል ችለናል፡፡ የሕግ ጉዳያቸው በቶሎ ያላለቀላቸው ልጆችም ራሳቸውን የመጥላት፣ የመፀፀትና የመደበት ባህሪ ያሳያሉ፡፡ ይህም ትልቅ ችግር ይፈጥርብናል፡፡ የቤት ኪራይም ትልቁ ችግራችን ነው፡፡ ስማችን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ገንዘብ አላቸው በሚል እሳቤ ቤት አከራዮች በአንዴ ከ5,000 ብር በላይ ይጨምሩብናል፡፡ ይህ አንዴ ብቻ የሆነ ሳይሆን በየጊዜው በሚገጥመን ችግር ነው፡፡ በዚህም ከአከራዮች ጋር ሙግት እንደገጥማለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? የገቢ ማሰባሰቢያ ታደርጋላችሁ?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- በሕፃናት ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ የጋራ ፕሮጀክቶችም አሉን፡፡ በተጨማሪም እኛ አባል የሆንባቸው ኮንሰርቲየሞች አሉ፡፡ ‹‹ዩካን›› ሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ኅብረት አንዱ ነው፡፡ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅትና ልማት ጥምረት (ሲሲአርዲኤ) የመሳሰሉት ድርጅቶች ውስጥም አባል ነን፡፡ ገቢ ማሰባሰቢያ፣ ማድረግን በተመለከት አገር ውስጥ የገቢ ማሰባሰቢያ ሙከራ አድርገን አናውቅም ማለት ይቻላል፡፡ አገር ውስጥ ገቢ ማሰባሰብ ራሱን የቻለ ሥራ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ባለሙያ ሊመደብለት ይገባል፡፡ በትናንሽ ደረጃ የምንጀምራቸው፣ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ነገር ግን ያልተጠቀምንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ አገር ውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ ጉዳዩን በደንብ የሚያስረዳ ሰው ያስፈልጋል፡፡ የለጋሶችን እጅ ለማስዘርጋት ልባቸውን በርግዶ መግባት ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ላይ ግን አልሠራንም፡፡ ያለው ሰው መስጠት ይፈልጋል፡፡ ለመስጠት ግን በቂ ምክንያት ይፈልጋል፡፡ ድርጅቱ ስለሚሠራው ሥራ ማመን አለበት፡፡ ይህን ለመሥራት ቀጣይነት ያላቸው ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ እስካሁን የምንንቀሳቀሰው ከውጭ በሚመጣ እርዳታ ነው፡፡ ከ95 በመቶ በላይ ገቢያችንን ከውጭ እናገኛለን፡፡ እንደ ወርልድ ኪንድረን ኤም፣ በአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራትን የሚደግፉ ፕሮጀክቶች ይደግፉናል፡፡ ሌላው ኢሳፕቱ የሚባል ከዓለም ባንክና ከመንግሥት ጋር የሚሠራ የመንግሥት ፕሮጀክት በራሱ የሚያደርግልን እገዛ አለ፡፡ በአገልግሎት ሰጪው እና ተጠቃሚው መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ተጠቃሚው የተሻለ ግልጋሎት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡ ሌላው ቴሬዶዞም ኔዘርላንድስ ከሚባል በባህርዳር ከሚሠራ ድርጅት ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ እነሱ በተለይ በሴቶች ትምህርት ላይ ነው የሚሠሩት፡፡ ከእኛ ጋርም በፓርትነርሺፕ ይሠራሉ፡፡ እነሱ የወንዶች መጠለያ አላቸው እኛ የሴቶች መጠለያ አለን፡፡ እነሱ ሴቶችን ሲያገኙ ይልኩልናል፡፡ እኛ ደግሞ ወንዶችን ስናገኝ እንልክላቸዋለን፡፡ በገንዘብም በቴክኒክም ይረዱናል፡፡ ኦክፋውንዴሽንም ፌዝ አውት ከማድረጉ በፊት አብረን እንሠራ ነበር፡፡ እና ሌሎችም የሚረዱን ድርጅቶች አሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ የሚጠበቅብንን ያህል መሥራት አልቻልንም፡፡ ፍላጎቱ ቢበዛም አቅማችን ስለማይፈቅድ የተወሰኑ ልጆች ብቻ ለመቀበል እንገደዳለን፡፡ አገልግሎቱን ፈላጊዎች በብዛት አሉ፡፡ አቅማችን ስለማይፈቅድ ሁሉንም ጥያቄ አንቀበልም፡፡ ይኼ ድርጅት ፌዝ አውት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ማኅበረሰቡ የእኛን ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ በጉዳዩም ቀደም ብለን አስበን ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ የእኛን ሥራ ወደ ማኅበረሰቡ አውርደናል፡፡ ምንም ወጪ በሌለበት ሁኔታ የበጎ ፈቃደኛ እናቶችን አሠልጥነን አብረውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በአቅም ማነስ ምክንያት መጠለያችን መዋል ያልቻሉ ልጆች ሥልጠና ወዳገኙት እናቶች እንልካቸዋለን፡፡ ወደ ቤተሰቦቻቸው እስኪመለሱ ድረስም እዚያው ይቆያሉ፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ምን ዓይነት እገዛ ያደርግላችኋል?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- የፕሮጀክት ስምምነቶችን በማቀላጠፍ፣ ከውጭ የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት እንዲሁም ባህርዳር ላይ 1,385 ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥቶን ሞዴል የሆነ የመጠለያና የተሐድሶ ማዕከል እየገነባን ነው፡፡ መሬቱን ያገኘነው በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ በሚከፈል 160,000 ብር በሚሆን የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡ ይህንን አንደ ነፃ ስጦታ ነው የምንቆጥረው፡፡ በአዲስ አበባም እንደዚሁ ቢያደርጉልን ቤት ኪራይ ላይ ያለውን ችግር ይቀርፉልናል፡፡ በዋነኛነት ግን መንግሥት ለሥራችን ዕውቅና ይሰጠናል፣ ይተባበረናል አስፈላጊውን ባለሙያም ይሰጠናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለወደፊት ምን አቅዳችኋል?
ወ/ሮ ዝናሽ፡- የማኅበረሰቡን የአገልግሎት ክንፍ ለማጠናከር አስበናል፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ገቢ ለማሰባሰብ በበጎ ፈቃደኞች መሥራት አስበናል፡፡ በመከላከሉ ረገድም የማኅበረሰብ አገልግሎት ክንፉን በማጠናከር የሴት ጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግሮች ለመቅረፍ ተዘጋጅተናል፡፡