በአሰፋ እንደሻው
ከሁሉ አስቀድሞ ስለ ስም አወጣጥ ላንሳ፡፡ በቻይናውያን አሰያየም መጀመሪያ የሚቀመጠው የአባት ወይም የቤተሰብ ስም ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚገባው የልጅ ስም ነው፡፡ አሁን አሁን ሁለት ተቀጣጣይ ስሞች ከማበጀት አንድ ይበቃል ማለት ተጀምሯል፡፡ ስሞቹ እንደ ኢትዮጵያውያን ትርጉም ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቻይናውያን ወደ ምዕራብ አገሮች ሲሄዱ በጋባዦቻቸው ወይም ተቀባዮቻቸው ዘንድ ስማቸው ቀለል ብሎ እንዲታይ ብለው ይመስላል የአካባቢ ስም ይወስዳሉ፡፡ ይህንንም እንዳሳፋሪ ጉዳይ አይቆጥሩትም፡፡ ብዙዎች እንደተዋወቃችኋቸው የቻይና ስማቸውን ከነገሩዋችሁ በኋላ “ፒተር” ወይም “ማርጋሬት” ልትለኝ ትችላለህ ብለው ወዲያው ያከታትላሉ፡፡ (አትቸገር ስማችን ሊረዝም ወይም ላይያዝልህ ቢችል ይገባናልና ይህንን በተለዋጭ ተጠቀም የሚል ዓይነት)፡፡ ሊ ኩዋን ዩ ከትንሽነቱ ጀምሮ ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሕግ እስከተማረ ድረስና ከዚያም በኋላ “ሃሪ” የሚል ተጨማሪ ስም ስለሚጠቀም የምዕራብ ዕውቂያዎቹ በዚያ ስም ይጠሩት ነበር፡፡ ማርጋሬት ታቸር የሕይወት ታሪኩን አዘጋጅቶ ሲያወጣ በጻፈችለት ማስታወሻ ላይ “ሃሪ” ብላ ነው የጠራችው፡፡ ሲንጋፖር ውስጥ ግን በጋዜጣም ሆነ በቃል ይህንን ተቀጥላ ስያሜውን ሲያነሱ ሰምቼ አላውቅም፡፡
ኩዋን ዩ በትውልዱ ሲንጋፖር ውስጥ በጣም አናሳ (ህዳጣን) ከሚባል ከሃካ ነው፡፡ ነገር ግን የእናት የአባት ቁንቋውን አለመናገሩ በውል የተመዘገበ ነው፡፡ ከትንሽነቱ አንስቶ ወደ እንግሊዝኛ ስላጋደለ ሌሎች ቋንቋዎችን ወደጎን ትቶ ነው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እስከጨረሰና ወደ ፖለቲካ እስኪገባ ድረስ የኖረው፡፡ ሲንጋፖር ውስጥ አብዛኛው ሕዝብ (ሆኪየን) የሚናገረውን ሆነ የደሴቲቱና የአካባቢው አገሮች የጥንት ነዋሪዎች መሌዎች የሚገለገሉበትን ቁንቋ ምናልባት ትንሽ ትንሽ ካልሆነ በስተቀር አያውቃቸውም ነበር፡፡ ማን እንደሆነ አሁን ለጊዜው የማላስታውሰው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኩዋን ዩን ከስዊዝ ወዲያ ያለው ብቸኛ እንግሊዛዊ ማለቱ፣ ምንኛ በባህሉና በቋንቋው ከአካባቢው የወጣ እንደነበር አመልካች ነው፡፡
ኩዋን ዩ እንግሊዝ አገር ለትምህርት እንደሄደ ስለነፃነት ጉዳይ የሚከራከሩ የመሌና የሲንጋፖር ልጆች ጋር በመደባለቁ እሱ ውስጥ የአገር ስሜት ማደሩ አልቀረም፡፡ እያደር እሱም የእንቅስቃሴው ተካፋይ እየሆነ ሲሄድ የአካባቢ ቋንቋዎች ያለማወቁ ጉዳይ አሳስቦት ይመስላል የመሌን፣ የሆኪንን እንዲሁም የማንደሪንን ቋንቋዎች (በተለይ ማንደሪንን) በእጅጉ ለማወቅ በ32 ዓመቱ ጀምሮ ተራውጦ ነበር፡፡ የቋንቋዎቹ ዕውቀት በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የበላይነት ለመጨበጥ አስፈላጊ መሣሪያዎች በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የነፃነት ተጋድሎው ላይ ብልጫ ለመቀዳጀት ቀርቶ አብሮ ለመሠለፍ መቻል አስገዳጅ ስለነበር ይመስላል፡፡ በሕዝቡ ቋንቋ መናገር ካልተቻለ የትም እንደማይደረስ ስለተረዳው በፍጥነት ይህንን ጉድለቱን ለማስተካከል ተራውጧል፡፡ የፖለቲካ ትንቅንቁን በድል ተወጥቶ የደሴቲቱ “ቀዳሚ መኰንን” ከሆነ በኋላ አልፎ አልፎ ለፓርላማ ሲናገር ማንደሪንን ወይም መሌን መጠቀም እንደሚችል አስመስክሮዋል፡፡
ኩ ዋን ዩ ኋላ ኋላ ላይ ሲንጋፖርን እንደ ብረት ቀጥቅጦ የሠራት፣ የአገሪቱ አባት ይባል እንጂ ለፖለቲካ ወይም ለሕዝብ መሪነት የተወለደ ሰው አልነበረም፡፡ አንደበቱ ርቱዕ፣ ፈጣን አሳቢና በምላሱ የሚኖር ቢሆንም እንኳን እንደ ብዙዎቹ ቻይናዊ ዘመዶቹ ወደ ንግድና ወደ ገንዘብ ሥራ ያዘነበለ ነበር፡፡ በ19 ዓመቱ ጃፓኖች አካባቢውን ወረው ይዘው ወዲያና ወዲህ ባሉበት ወቅት እሱም የሚታሰሩ፣ የሚደበደቡና የሚረሸኑትን ለመመልከት ችሎ ሲንቀሳቀስ በሐሳቡ ውስጥ የነበረው ንግድ ነበር፡፡ በጻፈው የሕይወት ታሪኩ የመጀመሪያ ቅጽ ላይ ጃፓኖች ሲዘርፍ ተገኘ ብለው ጭንቅላቱን ቆርጠው በእንጨት ያንጠለጠሉትን ቻይናዊ መንገድ ላይ ተመልክቶ፣ “ጃፓኖቹን የመፍራት ስሜት ይዞኝ ተመለስኩ፡፡ ወዲያውኑም ላይፍ ለሚባለው የአሜሪካ መጽሔት ምንኛ የሚያስደንቅ ፎቶ ይሆንላቸው እንደነበር አሰብኩ፡፡ ያ የአሜሪካ ሳምንታዊ ኅትመት የደረሰውን ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ የሚያስረዳ ሥዕል ቢያገኝ ጥሩ ክፍያ ይሰጥ ነበር፤” ብሎ ተርኳል፡፡ ጭንቅላቱ የተቀላው የወገኑ ክብር ሕይወት ሳያሳስበው (እንዲያውም ሳያስቆጨው) ፎቶውን አንስቶ ሊገኝ የሚችለውን ገቢ ያሰላስል ነበር! ይባስ ብሎ ጃፓንኛ አጥንቶ ለወራሪው ኃይል በአስተርጓሚነት ሲሠራ እንደቆየ ከዚያ በኋላ ወደ ንግድ እንደገባ ተተርኳል፡፡
ይህ በጉልምስናው የተገለጠው ዕይታው አብሮት ያደገና አስተሳሰቡን፣ አኗኗሩንና በገዥነት የተከተለውን መስመር የቀየሰለት ይመስለኛል፡፡ ኩዋን ዩ እንደ ሌሎች አብሮ አደግ የፖለቲካ አቀንቃኞች ማርክሲስት (ኮሙዩኒስት) አልነበረም፡፡ የወጣለት የምዕራብ አስተሳሰብ አራጋቢ ማለትም ሊበራል ዲሞክራት ወይም ወግ አጥባቂም አልነበረም፡፡ በመሀሉ ላይ ሆኖ ግራ ዘመም የሚመስል የአገር ነፃነት ከተገኘ በኋላ ከምዕራባውን ጋር በአብዛኛው ተቀራርቦ በብልጥነት ከእነሱ የሚገኘውን እየወሰዱ ራስን ማሳደግ የሚል አስተሳሰብ ነበረው፡፡ በዚህም ምክንያት ሊበራል ዴሞክራሲ ላለበት አካባቢ እንደማይሠራ፣ ምርጫን ማካሄድ ከተቻለ ሜዳው የተለቀቀ የሁሉም ፖለቲከኞች መጫወቻ ማድረግ ጎጂነት አለው ባይ ነበር፡፡ አደባባይ ላይ ወጥቶ ይህ የፖለቲካ መስመር ፀንቶ እንዲቆይ አይከራከር እንጂ፣ በተግባሩ ከሌሎች ፖለቲከኞች ጋር ባደረገው መፋለም ይህን አሳይቷል፡፡ በተለይ ግራ ክንፍ ከነበረው ሰፊ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ዕውቅ መሪ ከሊም ቺን ሲዮንግ ጋር በብሪትን ቅኝ ገዥ አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች ረዳትነት አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላ፣ በሥሩ የተደራጀውን የሕዝብ አድራጎት ፓርቲ የተባለውን አጠናክሮ የአገር መሪነቱን ከጨበጠ አንስቶ ሌሎች ተቀናቃኞች መፈናፈኛ እንዳያገኙ በማድረግ ይህንን አስተሳሰቡን በተግባር ላይ አውሏል፡፡ ሊም ቺን ሲዮንግ በግዞትና በእስራት ሲሰቃይ ኖሮ በመጨረሻ ለንደን ተሰዶ አትክልትና ፍራፍሬ እየቸረቸረ ሕይወቱን እንዲገፋ አብቅቶታል፡፡ ከእሱ ጋር ተጓዳኝ የነበረውን የፖለቲካ አቀንቃኝና የፓርላማ አባል ቺያ ታይ ፖህ ደግሞ ከኔልሰን ማንዴላ የበለጠ ለ23 ዓመታት ለፍርድ ሳይቀርብ በውስጣዊ እስራት፣ ለዘጠኝ ዓመት ደግሞ በግዞት አቆይቶት አስረጅቶ ከ32 ዓመታት በኋላ እንደፈታው ሁሉም ዜጋ የሚያውቀው ነው፡፡
የሲንጋፖርን ፖለቲካ በቅርቡ ለሚያውቀው፣ እዚያው ውስጥ ተቀምጦ ለተከታተለው በመንግሥቱ በኩል የሚሰነዘር ጉልህ ሕገወጥ አፈናና ብተና አያገኝም፡፡ በተለይ ኩዋን ዩ የሕግ ሰውም ስለሆነ ይሆናል የሁሉ ነገር አቀራረፅ ሕግን የተከተለ ነው፡፡ የሕጉን ቃል አስተካክሎ ከማውጣት ጀምሮ የአስፈጻሚው አካል (ፖሊሱ፣ ቢሮክራሲው) አንድም ነገር ሳያዛንፍ ሕጉን ስለሚከተል በፓርላማው ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የበላይነት (በአብዛኛው ከ60 በመቶ የሕዝብ ድምፅ ይዞ) እየተመረኮዘ ያሻውን ለማድረግ አስችሎታል፡፡ በዚህም ሕጉን የመጣስ ሥራ በመንግሥት በኩል አይከናወንም፡፡ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ከሚደረገው በተቃራኒ! ይልቅ ተመልካቹና ጉዳዩን ያጠኑ ሁሉ ኩዋን ዩ ሕጉን እየተጠቀመ አምባገነንነትን ገንብቷል የሚል ክስ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ታዲያ በሕግ መዳኘቱ አንድ ትልቅ ነገር ስለሆነና እንዲያውም አንድ ዕርምጃ ወደፊት በመሄዱ ኅብረተሰቡ በራሱ መንግሥት ከመንገላታት በመጠኑ እንደዳነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሲንጋፖር አሥር ብር በጉቦ የተቀበለን ፖሊስና አሥር ሚሊዮን ወደ ኪሱ ያገባን ሹመኛ በእኩልነት ወደ ወህኒ ቤት የመስደድ ተግባር ስለምታሳይ፣ የኩዋን ዩ መንግሥት አድልዎ የማይፈጸምበት ቢባል ሐሰት አይመስልም፡፡ በተለይ ለተራው ዜጋ “ሠርቶ መብላትን” በሰፊው ስላስቻለ ይህ ሕግን አክብሮ፣ “የሚያስቸግረውን” ወገን ግን በሕግ ሸብቦ የማስቀመጥ ተግባር የአመራሩን “ብልህነት”፣ “ዘዴኛነት”፣ አልፎ አልፎም “ጭካኔ” ስለሚፈነጥቅ ኅብረተሰቡ ሰጥ ለጥ ብሎ ለዕድገትና ለሰላም እንዲሠለፍ አድርጎታል፡፡
የኩዋን ዩ መንግሥት እንደተባለው በሕግ የተዋቀረና ሰባራ ስንጥሩን ሁሉ በሕግ ሥር የሚያስገባ ስለሆነ በሌላ መሥፈርት ጩኸት የሚያስነሳ ይሁን እንጂ፣ ፊት ለፊት ዝርፊያንና በደልን አያስፈጽምም፡፡ የጉቦ ማጥፊያና መቆጣጠሪያው ሕግ እንደተባለው በአፈጻጸሙ ምንም የሚዛነፍ ነገር የለውም፡፡ ይልቅ ጉቦ ከመሠረቱ በሥልጣን እርከን ላይ ያሉ የመንግሥታዊና የግል ተቋማት ሠራተኞች የሚያገኙት የወር ገቢ ከሚያገላብጡት ገንዘብ ብዛት እጅግ ያነሰ በመሆኑ ነው የሚለውን አስተሳሰብ መነሻ በማድረግ፣ ለእነዚህ ሠራተኞች የሚሰጠው ደመወዝና አበል ከፍ እንዲል ተደርጎ የሚኒስትር ደመወዝ ራሱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንዲሆን፣ ሌሎችም በተዋረድ እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡ የደመወዝ እርከን ወደ ላይ ከፍ ሲባል ጭራሽ የመኖሪያና መተዳደሪያ ሳይሆን፣ የማድለቢያና ሀብት ማጎናፀፊያ በሚመስል መንገድ ተዋቅሯል፡፡ ኩዋን ዩ በዙሪያው ያሰባሰባቸው የቢሮና የግል ድርጅቶች ኃላፊዎች የአንድ ትልቅ ኩባንያ የቦርድ አባል ይመስላሉ፡፡ ይህንንም በመመርኮዝ አንዳንዴ ሲንጋፖርን እንደ ኩባንያ የመቁጠርና በኃላፊነት አገልግሎት የሚሠለፉት ራሳቸውን እንደ ባለቤት (ባለድርሻ) እንዲቆጥሩ፣ ከሥራቸው ቢወገዱ ሀብታቸው የሚያድግበትን ምንጭ እንደሚያጡ በማድረግ በጥንቃቄ ሥራቸውን እንዲፈጽሙ፣ ለገዢው ፓርቲም ተገዥና ታማኝ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ላይ ከየትምህርት ቤቶች ብልጫ ያላቸውን ተመራቂዎች ወደ ውጭ አገር ከፍተኛ ስም ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ልኮ አሠልጥኖ ሲመለሱ በከፍተኛ ሥራ ላይ ማሰማራት ለዚህ ሥርዓት ከፍተኛ እገዛ ያጎናፅፈዋል፡፡ ሄዶ ሄዶ ያው ከላይ የተጠቀሰው የሚሠራውን አስተሳሰብ (ፕራግማቲዝምን) ይዞ የሚንቀሳቀሰው የኩዋን ዩ መንግሥት ትርፍ የሚያስገኘውን ሁሉ በመከተል፣ የማይሠራውን በመተው የተዋቀረ ስለሆነ ውጤቱ ፊት ለፊት ሲገኝ ለሕዝቡ ማባበያና ማስማሚያ ሆኗል፡፡
ከሕዝቡ መካከል አልፎ አልፎ ተቃውሞዎችና ሮሮዎች ሲሰነዘሩ፣ በተለይ ከተማረው ወገን ትችት ሲቀርብና በመደራጀት የፖለቲካ ፍጥጫ ሲፈጠር፣ የሊ ኩዋን ዩ መንግሥትና ፓርቲ ወዲያውኑ ጥይትና የመርዝ ጢስ አይተኩስም፡፡ መሪ የተባሉት ላይ በማተኮር ከእነሱው ውስጥ የሕግ ጥሰት አለባቸው የሚባሉትን ከሕግ ጋር እንዲነጋገሩ በማድረግ ይጨርሰዋል፡፡ በትችቶቻቸው ስም አንስተው “ኩዋን ዩ በለፀገ ወይም ይህን ፈጸመ” ቢሉ በስም ማጥፋት ተከሰው እንዲሸነፉና ያለ የሌለ ሀብታቸውን በካሳ ክፍያ አንጠፍጥፈው እንዲደኸዩ ይደረጋሉ፡፡ አንዳንዶች ከመደህየት ብለው አገር ለቀው ሲጠፉም ያ ዓላማቸው አፈር ይበላል፡፡ ኩዋን ዩ የፈለገውን ቢባል መልስ የማያጣ፣ ሕጉን ተመርኩዞ ተቀናቃኞቹን የመደበቂያ ቦታ የሚያሳጣ ስለሆነ የውጭ አገር ተችዎች እንኳን ቢነሱበት ወይ በፍርድ ቤት ያስበይንባቸዋል፡፡ አሊያም በሲንጋፖር አድርገው ወደ ሌላ አገር ለመብረር ቢሞክሩ ከአየር ጣቢያ እልፍ እንዳይሉ ያስደርጋቸዋል፡፡ አንድ የሲንጋፖር የቀድሞ ባለሥልጣን የነበረ አገር ለቆ ከሄደ በኋላ አውስትራሊያ ገብቶ በመጽሐፍ መልክ እንዳተተው “የነብር ጅራት…” የሚሉት ብጤ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና በተባለው ዘዴ ሥራውንና ሀብቱን ያጣው አንዱ የሲንጋፖር ዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪም መተዳደሪያ እንዲሆነው መጽሐፍ እያዞረ መሸጥ ውስጥ ገብቶ እንደነበር በዓይኔ አይቻለሁ፡፡
በዚያውም ሁኔታ ሥልጣኑ ሰማይ ደርሶ ምንም ሥጋት ከየትም አቅጣጫ ሊደቀንበት በማይችልበት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ማብቂያ አካባቢ የማርክሲስቶች ሴራ ጠንሳሾች የተባሉትን ወጣቶች አስሮና መቀጣጫ አድርጎ በፓርላማው አጣሪ ኮሚቴ ሳይቀር ዋና መርማሪያቸው ሆኖ ከአፉ የሚወጣውን በፓርላማው ዘገባ ላይ ላነበበ፣ ምን ያህል የሚሰቀጥጥ የአፈና ሥርዓት እንዳቋቋመ ይገነዘባል፡፡ በእርግጥም የኩዋን ዩ ዘመን በፖለቲካው ዘርፍ ምን ይመስል እንደነበር ያንን ይፋ የሆነ የፓርላማ ዘገባ ማንበብ ብቻውን ቁልጭ አድርጎ ያስረዳል፡፡
ኩዋን ዩ የአገር ውስጡን የፖለቲካ አየር በዚህ መልክ ሲቃኝ ከውጭ አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ግን ለማስተካከል ሳይቻለው ቀርቷል፡፡ የመጀመሪያው ፈተናው ሲንጋፖር ከማሌዥያ ጋር በፌዴሬሽን መልክ እንድትተዳደር እንግሊዞች በቀየሱት መሠረት፣ በፌዴሬሽኑ ውስጥ የተሰባሰበውን የቻይና ተወላጅ በሙሉ አስተባብሮ መሪነቱን ለመውሰድ ያደረገው ጥረት ከሽፎበታል፡፡
መሌዎች ከእንግሊዝ እጅ ወጥተው በቻይናውያን ሥር መግባቱን ፈጽሞ ስለተቃወሙ ምንም እንኳን በዴሞክራሲያዊ አሠራር አብላጫ ያለው መንግሥት መመሥረት እንዲቻል ስምምነት ቢኖርም፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የመሌዎች የበላይነት እንዲሰፍር በመደረጉ ለኩዋን ዩ መርዝ ሆነበት፡፡ በተነሳው ክርክርና ውዝግብ ደም መፋሰስ ከመድረሱ በፊት ብለው መሌዎች ሲንጋፖርን ከፌዴሬሽኑ አስወጧት፡፡ ኩዋን ዩም ለቅሶ ቀረሽ በነበረ ምላሹ ወደ ደሴቲቱ ገብቶ ተቀመጠ፡፡
ሲንጋፖር የማሌዥያ ፌዴሬሽን አባል መሆኗ ከከሸፈ በኋላ ሙጭጭ አድርጋ የያዘችው መመርያ ከአሜሪካኖችና ከእንግሊዞች ጋር በማኅበር ህልውናዋን የሚያሰጋት ነገር እንዳይፈጸም መከላከል ነበር፡፡ ማሌዥያም ሆነች ኢንዶኔዥያ ሁለቱም መሌ ስለሆኑ ተቀራምተው ወደ ራሳቸው ለማስገባት የቆየ ዛቻና ሐሳብ ስለነበር፣ ያንን አደጋ ለመቋቋም የሁለቱን ኃያላን የጦር ሠፈር ሲንጋፖር ላይ ተተክሎ እንዲቆይ ኩዋን ዩ አደረገ፡፡ ያው የሚሠራ ሐሳብ እንጂ የነፃነት ፍላጎት ገዥነት አልነበረውም ማለት ነው፡፡ ከሁለቱ ኃያላን ጋር የነበረው ስምምነትና ትብብር ሲንጋፖር ወደ ንግድ ሥራና ወደ ኢኮኖሚ ዕድገት እንድትዞር ያግዛታል በሚል ነበር፡፡ በእርግጥም ለጦር ኃይል ግንባታና ለመከላከያ የሚያስፈልገውን ወጪ ሁሉ ከማውጣት ድነው ሲንጋፖር ከድሮ ጀምሮ የነበራት የንግድ መተላለፊያ በርነቷ እንዲጠናከር፣ ከዚያም ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ መበርታት ያዙ፡፡ የኩዋን ዩ መንግሥት ዋናው የወቅቱ ሥራ በየአገሩ እየዞሩ ፋብሪካ እንዲከፍቱላቸው ሀብታሞችንና ትልልቅ ኩባንያዎችን መለማመጥ ነበር፡፡ አንድ ፋብሪካ እንደምንም ለመክፈት ሲቻል ደግሞ በታላቅ በዓልና በዕልልታ ራሱ ኩዋን ዩ መጀመሪያ ላይ፣ ከዚያም ፋብሪካዎቹ እየበዙ ሲሄዱ ሚኒስትሮች እየመረቁ ይከፍቱ ነበር፡፡ ዋናው ዓላማ መገጣጠሚያዎችና አዳዲስ ዕቃዎች ማምረቻዎችን አብዝቶ ለአካባቢው ማሰራጨት ነበር፡፡
ይህም ተሳክቶ ሲንጋፖር ከወደብ አበል መሰብሰን ብቻ ሳይሆን፣ የምርት ዕቃዎችን ማከፋፈልና ማሰራጨት ተያያዘች፡፡ “ሲንጋፖር የተሠራ” የሚል ምልክትም መውጣት ጀመረ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የነዳጅ ዘይት ሳይኖራት ከአካባቢው አስመጥታ ማጣሪያ ማበጀትና የፕላስቲክ ዕቃዎችንና ከነዳጅ የሚገኙትን ነገሮች ማምረትና ማሰራጭት ተቻላት፡፡
የማሌዥያ መሪዎች በፊት በፊት በፌዴሬሽኑ ዘመን ሲንጋፖርን “ኒውዮርክ” እናደርጋታለን ይሉት የነበረውን ትተው ብቻዋን ከሆነች በኋላ “ምድረ በዳ ትሆናለች” ያሰኙ ነበር፡፡ ነገር ግን በኩዋን ዩ መሐንዲስነት የንግድና የኢንዱስትሪው መንገድ እየቀና ከዓለም በውጭ ዕቃ መላክ አሥረኛ አገር ለመሆን በቃች፡፡ ከዚህም በላይ ከአገራቸው ከቻይና እየለቀቁ በዓለም ዙሪያ የተበተኑት በተለይ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የየአገሮችን ኢኮኖሚዎች እየተቆጣጠሩ ያሉትን ቻይናውያን ባንክ ለመሆን ቻለች፡፡ ገንዘባቸውን ከየአካባቢው ገዥዎች ለማራቅ የፈለገ ሁሉ በሲንጋፖር ንግድ መክፈት ብቻ ሳይሆን ባንክ ውስጥ ለማስቀመጥ ቻለ፡፡ ያም በስፋት ያልታወቀ ለሲንጋፖር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ክስተት ነው፡፡ ዋናው ነገር የሚያበላና በተግባር የሚጠቅም ከሆነ ሲንጋፖር (ኩዋን ዩ) ያንን ነገር ለማስገባትና ለማሠራት ወደኋላ ማለት ታይቶበት አያውቅም፡፡
ሲንጋፖር ሌላው በጣም የጠቀማት ነገር በዓለም ዙሪያ እንደ መረብ የተዘረጋው የአሜሪካ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች መናኸሪያ መሆኗ ነው፡፡ በማንኛውም ዘርፍ የተሠለፉ ኩባንያዎች ሲንጋፖርን እንቅ አድርገው የያዙት በመረማመጃነት ለአካባቢው ዕቃቸውን እንድታሰራጭላቸው እንጂ የሲንጋፖር ሕዝብ ከአራት ሚሊዮን አያልፍም፡፡ ያውም ከውጭ ለሥራ የገባው አንድ ሚሊዮን የህንድ፣ የኢንዶኔዥያና የፊሊፒንስ ዜጋ ተጨምሮ፡፡ የአሜሪካ ኩባንያዎችን ለመሳብ ሲንጋፖር ትልቅ የአውሮፕላን ጣቢያና ዓለምን የሚያካልል የአየር መንገድ አቋቁማለች፡፡ በዚህ ላይ ለመሪዎች ተስማሚ የሆነ የቤትና የሆቴል ግንባታ ተያይዛለች፡፡ መጨረሻም ከዓለም በቆዳ ስፋት በጣም ትንሽ ሆና ነገር ግን በገና (ጐልፍ) መጫወቻ ሥፍራ ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች፡፡ በሥራ ብዛት ተወጥረው ለሚውሉ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ “ሻምበሎች” ሁሉ መናፈሻና መዝናኛ ሆናለች፡፡
ኩዋን ዩ የገነባው የኢኮኖሚ መሠረት በላይ በላዩ እንዲንሰራራ ሲንጋፖርን የምርምርና የጥበብ ማዕከል ለማድረግ በተለይ በመረጃ ጥበብና በሕይወት ጥበብ አቅጣጫ ለማደግ የገንዘብና የሰው ኃይል መድባ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በመድኃኒት ቅመማ፣ በሕይወት ሳይንስ ዕድገት በመጨበጥ ከአሜሪካና ከጃፓን ቀድማ የተነሳች ናት፡፡ ሰዎች የደሴትነቷን ማነስ በማየትና በዴሞክራሲ ሥርዓት አለማበብ ኩዋን ዩ አፋኝና አምባገነን ነው በሚለው ፍረጃ ሲንጋፖርን ፊት ቢነሱም፣ በገንዘብና በኢኮኖሚ ጡንቻዋ በጣም የምትንጠራራ ሆናለች፡፡ በምድቧም ከአንደኛው ዓለም እንጂ ከታዳጊና ተመንዳጊ (ብሪክ) መሀል እንዳልሆነች ልብ ይሏል፡፡ ይሁንና ኩዋን ዩን በየትኛውም ቤተ መንግሥት ለመቀበልና ለማስተናገድ የሚፈቅድ ሰው አልነበረም፡፡ ሰሞኑን ኦባማ እንኳን የዓለማችን ታላቅ ሰው ይበለው እንጂ በኋይት ሐውስ እንዲገባ ማንም ጋብዞት አያውቅም፡፡
ኩዋን ዩ ለሲንጋፖር ያደረገው ሁሉ በበጎ ሊታይለት ቢችልም፣ ለተቀናቃኞቹ ያሳየው ጭካኔና አለመበገር ሁሌም የማይፋቅ ጠባሳ ሆኖበት ኖሯል፡፡ ከአገር የተሰደዱት፣ በድህነት የተቆራመዱት፣ መፈናፈኛ አሳጥቷቸው በአገር ውስጥ የኖሩት ተቀናቃኞች ምንም ያህል ከእሱ የማይተናነስ በጎ አስተሳሰብ የነበራቸው ሆነው ሳለ፣ አንዳችም አዘኔታ በሌለው ሁኔታ መቅጣቱ ያለርኅራኄ የሚተቹትን አፍርቶበታል፡፡ እንዲያውም ይባስ ብሎ የራሱን ቤተሰብ በፖለቲካው አናት ላይ ለማስቀመጥ የወሰደው ዕርምጃና በኋላ ላይ ልጁን የዙፋኑ ወራሽ ማድረጉ ክፉኛ አስወቅሶታል፡፡ ኅብረተሰቡ በሚበላና በሚጠጣ ተራራ ውስጥ እየኖረ፣ መተዳደሪያና መኖሪያ ቤት ተጎናጽፎ እያለ ነገር ግን አገሬ ብሎ የልቡን ተንፍሶ እፎይታ ስለማያገኝ እንደተቆለፈበት ፈንጂ ሆኗል፡፡ ሀብት ያበጀው ወገን ልጆቹንም ራሱንም እየጫነ ወደ አውስትራሊያና ካናዳ ስለሚጎርፍ ይህ ምልክት አልሆን ብሎ የፖለቲካ ምኅዳር መሻሻል አልተገኘም፡፡ በኅብረተሰቡ አዕምሮ ውስጥ አንድም የመሌዎች ቋሚ የደሴቲቱ ባለቤትነት ጥያቄ ስላለና የመብት እጦት ስለሚያንገሸግሸው ለቆ የመሰደድ አስተሳሰብ ስላለ፣ ያንን ለማጥፋት “እኛ ሲንጋፖራውያን ነን” የሚል መዝሙር እስከሚሰለች ድረስ በመገናኛ ብዙኃን ይሰማል፡፡
የሊ ኩዋን ዩ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ከሥልጣን ቦታ በለቀቀ በስንት ዓመቱ ስለሆነ ወዲያውኑ ለውጥ ይመጣል የሚል ግምት መኖር አይችልም፡፡ አንድም ሥልጣንን ለቆ በአማካሪነት፣ በ”ክብር” ሚኒስትርነት፣ ወዘተ ስለቆየ ከሥፍራው ብዙም ዞር ብሎ አያውቅም፡፡ ሁለተኛም ኅብረተሰቡን እንደ መረብ ተተብትቦ እንዲቆይ ያደረገው ባህል አሁንም ከሥሩ አልተነቀለም፡፡ ቻይናውያን አባታዊነትና “የእስያ ሥልተ ምርት” የሚባለው ዘይቤ የተጣወራቸው ስለሆነ ሲንጋፖርን በቀላሉ ወደ አዲስ ነገር የሚገፋ አይገኝም፡፡ የኅብረተሰቡ 90 በመቶ ያህሉ ቻይናውያን በመሆናቸውና ከውጭ የሚመጣው ሠራተኛ ሕዝብ የውስጡን ማኅበረተሰብ እንዳያናጋ በዘዴና በቀመር የተያዘ ስለሆነ፣ በማንም ዘንድ አንዳችም ቀቢጸ ተስፋ ሊበጅ አይችልም፡፡ የቀድሞው የሲንጋፖር አባትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ዩ ባለፈው ሳምንት ከሃያ ሦስት አገሮች የተውጣ የአገር መሪዎችና ተወካዮች በተገኙበት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡ የዘመናዊቷ ሲንጋፖር መሥራች አባት ኩዋን ዩ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው እ.ኤ.አ. ማርች 25 ቀን 2015 በ95 ዓመቱ ነው፡፡ ለሲንጋፖር ግንባታ አሥር ዓመት አስተዋጽኦ ያደረግሁ በመሆኔ ግን መልካሙን ሁሉ ለሕዝቧ እመኛለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ዶ/ር አሰፋ እንደሻው ቦረና ትምህርት ቤት፣ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት፣ ቀኃሥና ለንደን ዩኒቨርሲቲ ተምረው ሲንጋፖርና ኢንግላንድ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮፌሰርነት ሕግ አስተምረዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡