እነሆ ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ዝንጥ ያሉ የደስ ደስ ያላቸው አዛውንት የጋቢናውን በር ይከፍታሉ። “እስኪ ና ወዲህ! ዓይንህን ልየው? እናቴ ዘንድሮ የአውሮፕላና የታክሲ መሪ የሚጭብጥ አላምንም። መንበሩን የጨበጡትን ረስተህ ማለቴ ነው! ነገር እንዳታመጣብኝ ደግሞ በዚህ ማለዳ፤” ሲቀልዱ ይቆጣሉ። የምር መስሎት ሾፌሩ ዓይኑን ሊያስመረምር ከአንገቱ ይሰጋል። “ወይድ! የዓይን ሐኪም አደረገኝ እንዴ በአንድ ጊዜ?” ፌስታል ይዛ የምትከተላቸው ኮረዳ ትስቃለች። “እኔ መቼ ይኼን ብሌንህን አልኩህ? ሰው ዓይኑ ያለው ልቡ ላይ ነው። የሳይንስ ልጅ ከሆንክ ደግሞ አዕምሮ በለው። ያው ነው ግን። የስም ለውጥ ነው። ከስም ለዋጭ፣ ከአውቆ አበድ፣ ከአታላይ ቀስቃሽና ተመራጭ አገራችንን ይጠብቃት!” እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ዘረጉ። በቆሙበት ጸሎታቸውን አጉተመተሙ። “የዚህን ሾፌር ልብ አንተ ምራ። የውስጡን ቁጭት በእኛ እንዳይወጣ ዛሬ ከሞት ጋር ቀጠሮ ቢኖረው ሐበሻ ነውና አስረፍደው። ሰው መቼም ሙት ብሎ ተብሎ ተቀጥሮ ሞት አይቀርለትም። መዘግየት ነው ጥበብ ማምለጥ አይቻል?” ብለው ሲያባሩ ተሳፈሩ። አፍታ ሳይቆይ ታክሲያችንም ሞላች። የጀመረውን መንገድ እንደሚጨርስ ስንቱ ይሆን እርግጠኛ?
“አያ ሞኛ ሞኝ ሰው ጥበብ የጎደለው፣ እህል ያከማቻል ስንቅ እየመሰለው፤” ይላል በገና ደርዳሪው። ወያላው፣ “ወይ ስምንተኛው ሺሕ! ሁዳዴ ሊያበቃ ሳምንት ሲቀረው ፆም ትጀምር? ምናለበት ማስመሰሉን ትተህ ዘፈን ብትከፍትልን?” እያለ ሾፌሩን ይለክፈዋል። ሾፌራችን፣ “ግድ የለም ፆም ይውጣና እኔና አንተ እንገናኛለን፤” ሲል ይዝታል። “ጉድ ነው የዘንድሮ ሰው የሰፈረበት ጋኔን እንኳን በሁለት ወር በዓመት ፆምና ፀሎትም የሚለቀው አይመስልም። እንዲያው ብቻ ለይምሰል ካጨበጨቡት ሲያጨበጭብ፣ ከሰከሩት ሲሳከር፣ ከካዱት ሲወዳጅ፣ ከክፉ እየተቃቀፈ መኖር ሲችልበት፤” ትላለች ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች ጥርሰ ፍንጭት። ደግሞ መልሳ አጠገቧ ወዳለሁት ዘወር ብላ፣ “ለምን ዝም ትላለህ? እምቢም አንድ ነው። እሺም አንድ ነው። ልክ ነሽ፣ ተሳሳተሻል ማለትም ያባት ነው። ዝም ምንድነው?” ስትለኝ ደንግጬ አያታለሁ። ጥያቄው አዕምሮዬ ውስጥ እየተጉላላ ጆሮዬ ላይ ንግግሯ ይደውላል። ‘ዝም ምንድነው?’
“እሱን አብረን የዝምታን አባት እንጠይቀዋለን። እስከዚያው ወንድማችንን ለቀቅ አድርጊው፤” ብሎ ከጀርባችን ሙሉ ልብስ የለበሰ ጎልማሳ ተሳፋሪ አጉረመረመ። ታክሲ ውስጥ ነው ፀብ ውስጥ ነው የገባሁት እያልኩ ስወዛገብ፣ “ማን ነው ደግሞ የዝምታ አባት?” ብላ ጎልማሳውን ጠየቀችው። “እሱ!” አላት ወደ ታክሲያችን ጣራ እየጠቆመ። መላው ተሳፋሪ ወደ ጥቆማው ሲያንጋጥጥ ብርሃን የሚተፋ የልብ ቅርፅ በእጁ የታቀፈ የፈጣሪ ምሥል ተለጥፏል። ከጎንና ጎኑ የሻኪራና የጄዚ ምሥሎች ያጅቡታል። “ወይ ዘንድሮ! መድኃኔዓለምን ነው የዝምታ አባት የሚለው? እውነት እሱ ዝም ቢል ኖሮ ድሆችና የዕውነት ተሟጋቾች ከምደረ ገጽ አንጠፋም ነበር?” ብላ ሦስተኛ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ትመፃደቃለች። አጠገቧ ወደ ተቀመጠው ወጣት ዞራ መልስ ስትሻ ጆሮው ላይ ‘ኢርፎን’ ሰክቶ ሲወዛወዝ አልሰማትም። “ኔትወርክ ሳይኖር ስለፈልፍ ዝም አላችሁ?” ብላ መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ዞራ ብትጠይቅ ሁሉም ፈገግ እያለ አንዴ እሷን አንዴ ልጁን አፈራርቆ አያቸው። በገና ልባችንን የሚያሸፍተን ደግሞ፣ “የቀድሞ ሰው ስህተት፣ በፆም ቀን አሳን መብላት፣ ያሁን ዘመን ሰው አያውቅ መላ፣ በጦም ሽሮ ነው ሚበላ፤” ሲል እየሰማን እንሰመጣለን።
ታክሲያችን ረጅሙን ጉዞ ተያይዛዋለች። “እንካ! እሱን ሒሳብ እንዳትቀበለው፤” መጨሻ ወንበር የተቀመጠ ፀጉረ ጨብራራ ከጎልማሳው አጠገብ ወደተሰየመው ይጠቁማል። የተጠቆመው ተሳፋሪ ዞሮ የምሥጋና አፀፋውን በጩኸት ሲመልስ ታክሲያችን የሚሳይል ማስወንጨፊያ ጣቢያ መሰለች። ጆሮውን በ ‘ኢርፎን’ ደፍኖ የተቀመጠው አውልቆ “ኧረ ፍሬንድ! ‘ታይታኒክ’ ላይ አልተሳፈርንም እኮ? ከዚህ ስትወርድ ሲኦል ደጃፍ ላይ እንድትገኝ መጥሪያ ተልኮልሃል እንዴ? ጆሮሯችንን እንፈልገዋለን፤” ብሎ መልሶ ጆሮውን ደፈነ። ከጮኸብን ተሳፋሪ ይልቅ በዚህኛው ተገርመን ጥቂት ስንተያይ እንደቆየን “የ ‘ዳያስፖራ’ ተቃዋሚዎች አባል ይሆናል ተውት። ዘንድሮ በሰው ቁስል እንጨት እየሰደዱ ሳይሰሙ ሳያዩ እንደ ጋጋሪ ቆስቋሽ ያልበላቸውን የሚያኩት ብሰውብናል፤” ብላ ሙንሙን ያለች ቀዘባ ስትናገር፣ “ሰው እስካሁን ከስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ አላለፈም ልበል? ምንድነው እሱ ምርጫ እያለ በአዛምድ የተለከፍነው?” አለ ጎልማሳው። “አዛምድ አይጭበረበርማ!” ሲል ታንቡራችንን የበሳው ተሳፋሪ፣ “እና ‘ኢቲቪ’ እንዳደረገው ምርጫ ቦርድም ‘ሎጎ’ ይቀይር ነው የምትለው?” ጎልማሳው መለሰ። “ጎበዝመንፈስ ቅዱስንና ምርጫ ቦርድን የሰደበ በምድርም በሰማይም ምሕረት እንደማይደረግለት እያስታወሳችሁ፤” አለች ወይዘሮዋ። ወዲያው እሷው ለሳቅ ቀደመች። እውነትም ሰው ከምርጫ ይልቅ በአዛምድ ተማርኳል ‘ባካችሁ!
መንገዳችን ገና እየተጋመሰ ነው። ሾፌራችን በበገና ቅኝት ተመስጦ በቅኔ ማሳ እየዳከረ ከራሱ ጋር ጥሞና ይዟል። “አንተ ሰውዬ በየት አገር ነው ሰው በገና እየደረደረ ትዝታ እየተጫወተ ወደፊት ሲጓዝ ያየኸው? በማሽት ግድ የለም በቀን እንዳታስገኘን እባክህ፤” አዛውንቷ ከምናቡ ዓለም ገሃድ ወደሆነው ጎዳና ሊመልሱት ያባብሉታል። ትንሽ ቆየት ይሉና ደግሞ፣ “ወይ አዲስ አበባ! ታጭታ ሳትዳር ጥሎሿ ደም ሆኖ ቀረ። ምን ይሆን ሳንካዋ? ምን ይሆን ሕመሟ ይኼ ቀለበት መንገድ እኮ ከጥቅሙ ጥፋቱ በዛ!” አሉ ሻሻቸውን እያስተካከሉ። መከለኛው የፍጥነት መንገድ ላይ አንድ ‘ሲኖትራክ’ እና ‘አይሱዙ’ ተጋጭተው ቆመዋል። የደቀቀ መስታወት በሐሴት እንደጎዘጎዙት ጠጅ ሳር ሿ ብትን ብሏል። “ምንድነው የሚሉት ሴትዮዋ? እና መንገድ ስጋጃ ነው? አልረባም ተብሎ ይጠቀለላል እንዴ? አሁን ገና በኢሕአዴግ ብቸኛ ታሪክ መጡ፤” ስትለኝ አጠገቤ ያለችው፣ “አይ ሰው! ይኼኔ ሰሞኑን ከወጣው የቤት ዕጣ ባለ ዕድል ሆና ቢሆን ኖሮ ምስክርነቷን አንችለውም ነበር። እንዲያው ግን የሃይማኖታችን፣ የፖለቲካችንና የልማዳችን ድምዳሜ ሁሉ ከጥቅማችን ውጪ ከሆነ ‘ኤክስ’ ነው ማለት ነው?” ወይዘሮዋ መጨረሻ ወንበር ወደተሰየሙት ዞራ በለሆሳስ ጠየቀች። “ቢሆን ነዋ! ባይሆንማ ዛሬ በአንብሮና ተቃርኖ መሀል ሦስተኛውን የመፍትሔ አስተፃምሮ መንገድ በመፈለግ መጠመድ በተገባን ነበር። ባለመታደል ከጽንፍ ጽንፍ ሆነን በደቦ ፉከራ፣ በጥቅም ተሳስረን በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ እየተሻኮትን ‘ኤክስና ራይት’ ለመለጣጠፍ እሽቅድምድም ጀምረናል፤” አለች ሞንሟኒት። ጨብራራው የሰው ታሪፍ ከፋይ (የታሪክችንን ዕዳ ለመክፈል ሲሆን ወደኋላ እንሸሻለን’ ያለው ወያላ የት መስመር ላይ አሳፍሮ እያወረደ ይሆን?) “እውነት ነው። በተለይ ይኼ ተቧድኖ መተራረምና መተራረብ ‘ፌስቡክ’ን ወደ መልመጃ ደብተርነት ሊቀይረው ምንም አልቀረው፤” ብሎ ተናገረ። ‘ኤክስ ራይት’ ከመጣ ‘ፌስቡክ’ ቅጡን አጣ እንበል መሰል!
ጉዟችን ተገባዷል። ሾፌራችን የነፍሱን ጥያቄ መልሶ መጨረስ ያቃተው ይመስላል። መንፈሳዊ ዝማሬውን አቋርጦ፣ “ሳስጠራው ከርሜ ስሜን በጀግንነት፣ ምን ሰበረው ቅስሜን አንቺን ያገኘሁ ዕለት፤” ወደሚለው ገብቷል። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ወጣቶች ‘ሙድ’ ይይዛሉ። “ሰሞነኛ ወሬ፣ ሰሞነኛ አቋም፣ ሰሞነኛ ቋንቋ አልሰለቻችሁም? ግን እስከ መቼ ነው በየቅፅበቱ እንደ እስስት የሚለዋወጥ ሰብዕና ይዘን አገር የምናለማው? ትውልድስ የምንቀርፀው?” ሲባባሉ ወያላው ጆሮውን አቅንቶ ያዳምጣል። “አንድ ሐረግ ሲመዙ ዛፍ ይወዛወዛል፣ ይኼ ሰው በሆዱ ለካ ነገር ይዟል፤” ሙዚቃው መሀል መሀል ላይ ድምፁ ይጎላል። ወጣቶቹ ሽሙጣቸውን ያሰፋሉ። “ቅስቀሳው ሰሞነኛ፣ እንክብካቤው ሰሞነኛ፣ የማርያም መንገዱ ሰሞነኛ፤” ስትል ሞንሟኒት፣ “በግልጽ በይው። ማንን ትፈሪያለሽ? ዴሞክራሲው ሰሞነኛ፣ ምርጫው የይስሙላ፣ ድህነታችን ብቻ ቋሚና ሀቀኛ። እሱ ነው የትም ጥሎን የማይሄድ፤” አላት ድምፁ እየሰለለ። ወያላው አንድ ደስ ያላለው ነገር ያለ ይመስላል። አረፍ ካለበት ተነስቶ “ይቅርታ እዚህ ጋ! ከታክሲያችን ‘የወግ ፖሊሲ’ ውጪ የሆነ ጨዋታ ባትጫወቱ! ከሾፌሩ ራስ ብትወርዱ ደስ ይለኛል። ለጊዜው በቢጫ አልፌያችኋለሁ፤” አላቸው።
ወጣቶቹ ‘ምን እንዳታመጣ?’ ሳይሉ፣ ሳይደነፉ ሳቃቸውን ሲለቁት የንዴት እንደሆነ ያስታውቃል። “እሺ ሳንሱር! ከስንት ዓመታት የውጭ አገር ዕረፍት በኋላ ወደ አባቶቿ አገር መጣች እባክህ? ወይኔ! ድል አድርገን ደግሰን እንቀበልልህ ነበር እኮ!” ሲሉት ወያላው ፊቱ በርበሬ መሰለ። ደነገጠ። “እኔ ሾፌሩን መተቸትም ሆነ መንቀፍ አትችሉም ነው ያልኩት፡፡ ሌላውን እንደፈለጋችሁ፤” ሊከራከር ቃጣው። “ኧረ እንወርድልሃለን! አውርደን እንዲያውም!” አንደኛው ደነፋ። “ዕልፍ ሲሉ ዕልፍ ይገኛል። ግፉን ግድ የለም!” ሞንሟኒት ትደረባለች። “ሳንናገርም ሳንበላም እንዴት ይሆናል?” ጎልማሳው ያግዛል። ጥቂት እንደሄድን “መጨረሻ” ብሎ ወያላው በሩን ከፈተው። እሱና እሱ ብቻ ከሚተቸው ከሚቀርበው ሾፌር ጋር የማንሰማውን እያወሩ ተፈተለኩ። “የእስትንፋስ ሳንሱር አይምጣብን እንጂ ሌላውስ ምድራዊ ነው ለምደነዋል፤” እያለች ወይዘሮዋ “ለእስትንፋስም ሳንሱር?” እያልን ሌሎቻችን ቀሪው መንገድ በእግር ተያያዝነው። መልካም ጉዞ!